Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሸገር ዳቦ በሥራው በምርቱ ትኩስ!

በአዲስ አበባ ሸገር የተባለው የዳቦ ማምረቻ ፋብሪካ ሥራ መጀመሩ እሰየሁ ያስብላል፡፡ ለዘመናት የነዋሪዎች ችግር ከሆኑት አንዱና በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ወገኖች ሲፈታተን የከረመው የዳቦ ዋጋና የአቅርቦት ችግር ጉዳይ የአዲሱ የዳቦ ማምረቻ ሥራ መጀመር ትልቅ ተስፋ ይሰጣል፡፡

በተመጣጠነ ዋጋ ዳቦ ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ እንዲችል ታስቦበት ሥራ የጀመረው ይህ ፋብሪካ፣ ከተመን በላይ ያላግባብ ዋጋ የሚጫንበትን የዳቦ ገበያ አደብ እንደሚያስገዛው ይጠበቃል፡፡ በተጠና መንገድ ለብዙኃኑ በቀላሉ ተደራሽ መሆን የሚችሉ ፕሮጀክቶች የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ የዕለት ጉርስ፣ የሥራ ዕድል በማስፋፋት ረገድ ፕሮጀክቶቹ ጠቃሚ ናቸው፡፡

እንዲህ ያሉ ፕሮጀክቶችን ዘመናዊ ግብይትን ለማስፋፋት ይረዳሉ፡፡ ዋናውን የምርት ችግር በመቅረፍ ረገድ አስተዋጽኦዋቸው ትልቅ ነው፡፡ ለዝብርቅርቁ ገበያም ልጓም ለማበጀት አጋዥነታቸው ይጎላል፡፡ ተመሳሳይ መጠን ያላቸው ምርቶች በሁሉም አካባቢ በተመሳሳይ ዋጋ እንዲገበይ ያስችላሉ፡፡ በገፍ ማምረት የመቻልና የማሠራጨትን ዋነኛ ችግር ለመፍታት መንገድ አመላካች ይሆናሉ፡፡

ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ዳቦ እንዲያቀርቡ መንግሥት በድጎማ የሚያቀርብላቸውን ዱቄት አየር በአየር ቸብችበው በሰው ሠራሽ እጥረት ሲደልቡ የኖሩትም አደብ መግዛት ይጀምራሉ፡፡ ሌሎችንም ጠቀሜታዎች መዘርዘር ይቻላል፡፡

የሸገር ዳቦ ፋብሪካ የማምረት አቅም የአዲስ አበባን ፍላጎት በቀላሉ ለማሟላት የሚያስችል ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት ቁርጠኛ ውሳኔ ተሰጥቶበት እንደተጀመረ፣ ከየትኛውም ፕሮጀክት ይልቅ በጥብቅ ቁጥጥር እየተመራ እስከ ግንባታ መጠናቀቂያው ድረስ በስኬት ተከናውኖ በወራት ውስጥ ግንባታው አልቆ ሥራ መጀመሩ የተለየ ያደርገዋል፡፡

በምረቃው ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በግንባታ ሥራ ማጓተት ስሙ የጎላውን ሚድሮክ ኢትዮጵያ ሸንቆጥ ያደረጉት ያለምክንያት አይደለም፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ቦታቸውን ከወረሰባቸው አንዱ ይኸው ተቋም ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ለውዳሴና ለሙገሳ የበቃበትን ሥራ በአጭር ጊዜ በመጨረስ መሥራቱ ከልብ ከታሰበበት የትኛውንም ሥራ በሚፈለግበት ወቅት አጠናቆ ለሕዝብ ማድረስ የሚቻልበትን ትጋት ያሳየ በመሆኑ ከበሬታን አትርፎለታል፡፡

የሸገር ፋብሪካ፣ ዳቦ ፍለጋ ለሚንገላታውና በየሱቁ ደጃፍ በወረፋ እግሩ የሚርደውን ወገን አፍ ያስታግሳል፡፡ ከአንድ ጉርሻ ለማታልፍ ጥቢኛ ዳቦ ብር በሚቆጠርባት ከተማ፣ ለዋጋ ብዝበዛ የተጋለጠውን ነዋሪ የሚደግፍ ብቻ ሳይሆን፣ እንዲህ በፍጥነት በመሥራት ለሕዝቡ የጭንቅ ጉዳዮች የሚደርስ አካል እንዳለ፣ ሥራዬ ከተባለ አጀንት አርስ በሆነ ፍፃሜ ከግብ እንደሚደርስ ያስተማረ ወሳኝ ሥራ ተከናውኗል፡፡ እጅግ የተንቀራፈፈና ለግንባታ ከሚሰጠው ጊዜ በላይ ለሚያንጓትቱ ግንባታን እንዲህ ባለው መልኩ ሊሄድ ይችል ዘንድ የዘርፉ ተዋንያኖች የማንቂያ ደወል  ነው ማለት ይቻላል፡፡

ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ የፈጀውን የዳቦ ፋብሪካ ለመገንባት ከአሥር ወራት ያጠረ ጊዜ ተይዞለት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለሥራ መብቃቱ ከአገራችን የግንባታ ችግር አንፃር ይህ ሥራ ሙገሳ ይገባዋል፡፡

ፋብሪካው በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለሥራ መብቃት የቻለበት ሌላው ዓበይት ምክንያት፣ በደንብ ሊጤን የሚገባውና መሠረታዊ ሊባል የሚችል ነው፡፡ አንድ ፕሮጀክት ግንባታው ከተጀመረበት ዕለት ጀምሮ ባለቤቱ ወይም ተቆጣጣሪው አካል ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ ሥራውን ከሥር ሥር መከታተሉና መቆጣጠሩ ያስገኘው ውጤት እንደሆነም ጭምር ማሰብ አለብን፡፡

በተለይ የከተማዋ ከንቲባ የዳቦ ፋብሪካውን ጉዳይ እግር በእግር እየተከታተሉ የኮንስትራክሽን ሥራው ለተሰጠው ድርጅት ሥራ እንዳያጓትት ፋታ መንሳታቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአንዴም ሁለቴ ሥራውን በአካል ሄደው መመልከታቸው ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የሥራውን ሒደት በተደጋጋሚ በአካል እየሄዱ መመልከትና ችግር ሲኖርም ዕርምት መውሰድ መቻል ሥራው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ አግዟል፡፡

የግንባታውን ሁኔታ ከሁለተኛና ከሦስተኛ አካል በሚቀርብ ሪፖርት ከመከታተል ይልቅ በአካል ሒደቱን ሥራዬ ብሎ መከታተል የግንባታውን ሒደት በቶሎ ለማጠናቀቅ አስችሏል፡፡ እርግጥ ነው ብዙ ገንዘብና ሀብት ፈሶበታል፡፡ በውጤቱ ስኬትን ማጎናጸፍ በማስቻሉ ሁሉንም አስደስቷል፡፡

ሌላው ሊማርበት የሚገባ ፕሮጀክት መሆኑ የተነገረለትን በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች የሚሠራውን ሥራ በአካል እየጎበኙ ጭምር በአግባቡ በመቆጣጠራቸው ውጤታማ ሊሆን ችሏል፡፡ እርግጥ ነው ይህ ሁልጊዜ አዋጭ አካሄድ ነው ማለትም አይደለም፡፡ ሁልጊዜ ከንቲባና ጠቅላይ ሚኒስትር በየፕሮጀክቱ ይቆጣጠሩ ማለት አግባብ አይሆንም፡፡ በዚህ መንገድ የሚጠናቀቅ ፕሮጀክትም በልምጭ እንደገነባ ያህል ሊያስቆጥረው ይችላል፡፡ ይህም ሆኖ መሠረታዊ የቁጥጥር ምርኅ ግን እንዲህ ያለውን አካሄድም ይደግፋልና ትኩረት የሚያሻቸው ላይ ክትትል ማድረጉ እሰየሁ ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ሜድሮክ ግንባታውን በትኩረት አጠናቆ ቀድሞ ሲተችበት የቆየውን ስም ማደስ የቻለበት አዲስ ምዕራፍ ሆኖለታል፡፡

የሸገር ዳቦ ፕሮጀክት በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ያስቻለው ሌለው ምክንያት ፕሮጀክቱን በቅርብ ተከታትሎና ተገቢውን ቁጥጥር ማድረግ በመቻሉ ነው ካልን፣ እንዲህ ያለውን ልምድ በሌሎች ፕሮጀክቶችም መተግበር የማይቻልበት ምንም ምክንያት እንደማይኖር ያሳየናል፡፡ በግንባታው ዘርፍ የሚታየውን አመለኛ የሥራ መጓተት ለመቀልበስ ሸገር ላይ እንደታየው ዓይነት የቅርብ ክትትል ጠቃሚ መሆኑ ነጋሪ አያሻውም፡፡ ፕሮጀክቶች እንዲህ ባለው ሁኔታ ቢቃኙ ይበጃል፡፡

ስለሸገር ዳቦ ፕሮጀክት ዕውን መሆን ስናስብ በኅብረተሰቡ ዘንድ በብዛት የሚፈለጉ ሌሎች ምርቶች ላይም ተመሳሳይ ዕርምጃ በመውሰድ ገበያን ከማረጋጋት በላይ ዘመናዊ ግብይትን ማቀላጠፍ የሚቻል መሆኑ ነው፡፡

በተለይ በቀላሉ በአገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉ እንደ ዘይት፣ ዱቄት፣ ሳሙና፣ ፓስታና መኮሮኒ የመሳሰሉ ምርቶችን እንዲህ ባለው ደረጃ በማቀድ ሸማቹን መደገፍ ገበያን ማረገጋትና የውጭ ምንዛሪ በማዳን አገርን መታደግ ይቻላል፡፡ አሁን በዘይት ላይ የተጀመረውን እንቅስቃሴ በማስፋት ለሌሎችም እንተርፍ ዘንድ ይሁን፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት