የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዘንድሮ መካሄድ የነበረበትን አጠቃላይ ምርጫ ለማከናወን የሚያስችሉ ዝግጅቶን እያከናወነ ሳለ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃና በኢትዮጵያ የተከሰተውን የኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከል መንግሥት በጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት፣ ምርጫውን በዕቅዱ መሠረት ማከናወን እንደማይችል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቆ ነበር።
ይህንን ተከትሎም ምክር ቤቱ ቦርዱ የደረሰበትን ውሳኔ የተቀበለ ሲሆን፣ ምርጫውን በወቅቱ ማካሄድ ካልተቻለ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ለአምስት ዓመት የሥራ ዘመን በሕዝብ የተመረጡት የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤቶች፣ እንዲሁም የሥራ አስፈጻሚ መንግሥት አካላት የሥልጣን ዘመን ምን ሊሆን እንደሚችል የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥበት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል።
ሕወሓት ከጅምሩ አንስቶ ይኼንን የምክር ቤቱ ውሳኔና የሕገ መንግሥት ትርጉም ውሳኔ ሕጋዊነት ሲጠይቅ የነበረ ሲሆን፣ የኮሮና ወረርሽኝ ሥርጭትን ለመከላለከል የሚያስችሉ ጥንቃቄዎችን በማድረግ ምርጫውን ማካሄድ እንደሚቻል ሲገልጽ መቆየቱ አይዘነጋም።
በሕገ መንግሥቱ የአንድ የተመረጠ ምክር ቤትና መንግሥት የሥልጣን ዘመን አምስት ዓመት ስለመሆኑ በግልጽ በመቀመጡ፣ የሥልጣን ዘመንን ለማራዘም ሕገ መንግሥቱ እንዲተረጎም ጥቀያቄ መቅረቡም ሕጋዊ አለመሆኑን ሕወሓት ሲሞግት ነበር።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከጥቂት ሳምንት በፊት ባካሄደው ስብሰባ ከሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በቀረበለት የሕገ መንግሥት ትርጉም የውሳኔ ሐሳብ ላይ ተወያይቶ፣ ምርጫው እስኪካሄድ ድረስ በሥልጣን ላይ ያሉ የፌዴራልና የክልል ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን እንዲራዘም ወስኗል። ይሁን እንጂ ቀድሞውንም በሒደቱ ላይ ጥያቄ ሲያነሳ የነበረው ሕወሓት በሚያስተዳድረው የትግራይ ክልል ምክር ቤት በኩል ምርጫው በትግራይ ክልል እንዲካሄድ ወስኗል።
በውሳኔው መሠረትም ምርጫ ቦርድ በክልሉ እንዲካሄድ የተወሰነውን ምርጫ እንዲያስፈጽምለትና ውሳኔውንም ካለው የጊዜ እጥረት አኳያ በአስቸኳይ እንዲያሳውቀው በደብዳቤ መጠየቁን፣ የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ ለሪፖርተር ገልጸዋል።
ደብዳቤው የደረሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ረቡዕ ሰኔ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ያሳለፈውን ውሳኔ የተመለከተ ዝርዝር መረጃ በድረገጹ አውጥቷል። ‹‹የትግራይ ክልል ምክር ቤት ኮቪድ 19ን እየተከላከለ ስድስተኛውን ዙር ምርጫ ለማካሄድ የወሰነ በመሆኑ፣ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በሚያዘው መሠረት ቦርዱ ውሳኔውን ተቀብሎ ምርጫውን እንዲያስፈጽም፣ ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስፈልግ የሰው ኃይልና የሎጂስቲክስ ዝግጅት እንዲያደርግና ውሳኔውን ለምክር ቤቱ እንዲያሳውቀን፤›› ሲል ጥያቄ እንዳቀረበለት የሚገልጸው የምርጫ ቦርድ መግለጫ፣ የትግራይ ክልል ጥያቄን እንዳልተቀበለውና ለዚህም ምክንያቶቹን በዝርዝር አቅርቧል፡፡
በመላ አገሪቱ በፌዴራልም ሆነ በክልሎች የሚደረጉ ምርጫዎችን የማስፈጸም ሥልጣን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደሆነ በሕገ መንግሥት አንቀጽ 102 (1) ላይ መደንገጉን የሚገልጸው መግለጫው፣ ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ የወጡ ሕጎችም የቦርዱን ሥልጣን ከዚሁ አኳያ በማጠናከር መደንገጋቸውን አመልክቷል።
የቦርዱን ሥልጣንና ኃላፊነት ለመወሰን የወጣው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1133/2011 በአንቀጽ 7(1) ላይ በአገሪቱ ውስጥ የሚፈጸሙ ምርጫዎችና ሕዝበ ውሳኔዎችን በሙሉ የቦርዱ ሥልጣን እንደሚሸፈኑ፣ የሚፈጸሙትም በዚሁ ቦርድ አማካይነት እንደሆነ በተብራራ ሁኔታ መደንገጉን መግለጫው ያስረዳል።
በተጨማሪም የቦርዱን የሥራ ኃላፊነቶች በተለያየ ሁኔታ በዝርዝር በሚደነግጉት ሕጎች፣ ማለትም በአዋጅ ቁጥር 1133/2011 እና በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 ላይ በማንኛውም የምርጫ ዑደት የሚፈጸሙ ዋና ዋና ክንዋኔዎች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብቻ እንደሚፈጸሙ መደንገጉን አመልክቷል።
ከእነዚህ የምርጫ ዑደት ተግባራት መካከልም ዋና ዋናዎቹ ማለትም የምርጫ ጊዜ ሰሌዳን ማውጣት፣ ለምርጫ የሚወዳደሩ የፓለቲካ ፓርቲዎችን መመዝገብ፣ መቆጣጠርና ማስተዳደር፣ የምርጫ አስፈጻሚዎችን መልምሎ ማሰማራት፣ ጣቢያዎችን ማቋቋም፣ ምርጫውን ከተፅዕኖ ነፃና ፍትሕዊ በሆነ መንገድ ማስፈጸም፣ በመጨረሻም የውድድሩን ውጤት አረጋግጦ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ መሆናቸውን ገልጿል።
እነዚህ ተግባራት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውጪ ለሌላ ማንኛውም የመንግሥት አካል ወይም ተቋም አለመሰጠቱንና ኃላፊነቶቹ በሙሉ ለምርጫ ቦርድ የተሰጡ መሆናቸውን ገልጿል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫን ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ እንቅስቃሴዎችን በማከናወን ላይ እያለ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵያ በመከሰቱ ምርጫውን ለማስፈጸም ሲያካሂዳቸው የነበሩት ሥራዎች እንደተስተጓጎሉ ማሳወቁን፣ ስድስተኛውን አገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ቀደም ሲል ባወጣው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ማካናወን እንደማይችል ወስኖ ይህንኑም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ማፅደቁን አስታውሷል።
ምክር ቤቱም የቀረበለትን የቦርዱን ውሳኔ ተቀብሎ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ እንዲሰጥበት መወሰኑን፣ በዚህም መሠረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. የትርጉም ውሳኔ ማሳለፉን ገልጿል።
በተሰጠው የሕገ መንግሥት ትርጉም ውሳኔም የዘንድሮውን ምርጫ የኮሮና ወረርሽኝ የሕዝብ ጤና ሥጋት ሆኖ ባለበት ሁኔታ ማካሄድ የማይቻል በመሆኑ፣ የፌደራልና ክልል ምክር ቤቶች የሥልጣን ዘመን እንዲቀጥል፣ እንዲሁም አጠቃላይ ምርጫው ሥልጣን ያላቸው አካላት ወረርሽኙ የሕዝብ ጤና ሥጋት አለመሆኑን ካረጋገጡበት ጀምሮ ከዘጠኝ ወር እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ እንዲካሄድ ማለቱን የቦርዱ መግለጫ ያስታውሳል።
ከላይ የተገለጹትን መንደርደሪያ የሆኑ መሠረታዊ የሕግ ምክንያቶችን ከገለጸ በኋላ፣ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ያቀረበውን ምርጫ ይፈጸምልኝ ጥያቄ በተመለከተ ሦስት የቦርዱን አቋም የሚገልጹና ለትግራይ ክልል ጥያቄ ምላሽ የሚሆኑ ነጥቦችን በመግለጫው አስታውቋል።
የቦርዱን አቋምና ምላሽ ከሚገልጹት ነጥቦች መካከል አንዱ፣ ‹‹ስድስተኛው አገራዊ ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄድበት ጊዜ እንዲራዘም ምክንያት የሆነው የኮሮና ወረርሽኝ ሁኔታ እንደገና ተገምግሞ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩ እስኪረጋገጥ ድረስ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በየትኛውም የአገሪቱ ክልል ምርጫ አያካሂድም፤›› የሚል ነው፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መመዝገብ፣ መቆጣጠርና ማስተዳደር፣ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣት፣ የምርጫውን ከተፅዕኖ ነፃና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ማስፈጸም ሥልጣን ያለው ብቸኛ ተቋም ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳን፣ አፈጻጸምንም ሆነ ተያያዥ ሁኔታን የሚወስነውም ቦርዱ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም የትግራይ ክልል ምክር ቤት በክልሉ ውስጥ ስድስተኛውን ዙር የክልል ምክር ቤት ምርጫ እንዲካሄድ ውሳኔ ለመስጠት፣ እንዲሁም ቦርዱ ይህንን ውሳኔውን ተቀብሎ ሊያስፈጽም ይገባል የሚልበት ሕጋዊ መሠረት የለውም፤›› የሚለው ሁለተኛው ነጥብ ነው።
በመጨረሻም፣ ‹‹ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች የትግራይ ክልል ምክር ቤት ምርጫን አስመልክቶ የሰጠውን ውሳኔ እንዲያውቅለትና ምርጫ እንዲፈጸምለት ለቦርዱ ያቀረበውን ጥያቄ ቦርዱ የማይቀበለው ሲሆን፣ የተጠየቀውን የሰው ኃይል፣ የሎጂስቲክስና የቁሳቁስ አቅርቦት የሚሰጥበት የሕግ አግባብ አለመኖሩን ያሳውቃል፤›› የሚል የመደምደሚያ ነጥብ ነው።
የትግራይ ክልል አቋም
የቦርዱ ምላሽ አዎንታዊ ባይሆን ቀጣዩ የትግራይ አቋም ምን ሊሆን እንደሚችል የተጠየቁት የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ‹‹የክልሉ ምክር ቤት በወሰነው በራሱ ክልል ምርጫው ይካሄዳል፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል።
የትግራይ ክልል ምክር ቤት በክልሉ ምርጫ እንዲካሄድ ከመወሰኑ አስቀድሞ ክልሉን የሚመራው ሕወሓት በዚህ ጉዳይ ላይ በፓርቲ ደረጃ የፖለቲካ ውሳኔ ማሳለፉን የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ የፓርቲውን ፖለቲካዊ ውሳኔ መሠረት በማድረግም የክልሉ መንግሥት ካቢኔ ቀደም ብሎ ውሳኔዎችን እንዳሳለፈ ጠቁመዋል። እነዚህ የፓርቲና የካቢኔ ውሳኔዎች ከመተላለፋቸው በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የትግራይ ክልል የሚያቀርበውን የምርጫ ይፈጸምልኝ ጥያቄ አስመልክቶ ሊሰጣቸው የሚችሉ የቢሆን ምላሾችን ከግምት በማስገባት የትግራይ ክልል ቀጣይ ውሳኔዎች ምን ሊሆን እንደሚገባ፣ በፓርቲ ደረጃ ምክክር ተካሂዶበት ውሳኔ መተላለፉንና ይህንንም የክልሉ መንግሥት ካቢኔ በድጋሚ ተወያይቶበት ማፅደቁን ገልጸዋል።
በመሆኑም ቀድሞ በካቢኔ በፀደቀው መሠረት የትግራይ ክልል የራሱን ምርጫ አስፈጻሚ ተቋም በማደረጃት ምርጫውን እንደሚያካሂድ የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ በክልሉ ምርጫ የሚያስፈጽም ተቋም እንዲመሠረትም ለክልሉ ምክር ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ እንደሚቀርብ አስታውቀዋል።
ይህ የሚሆንበት ምክንያትም ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መሠረታዊ የሉዓላዊነት መገለጫ መብት በመሆኑ ሊገሰስ ስለማይገባውና ክልሎችም በራሳቸው የአስተዳደር ወሰን ውስጥ በፌዴራል መንግሥት የማይገሰስ ሉዓላዊነት ያለቸው በመሆኑ እንደሆነ አመልክተዋል።
ጥቂት የማይባሉ የሕግና የሕገ መንግሥት ባለሙያዎች፣ እንዲሁም የፖለቲካ ተንታኞች የትግራይ ክልል በራሱ መዋቅር ውስጥ የሚሆን የክልል ምርጫ አስፈጻሚ ለማቋቋምና ምርጫ ለማካሄድ እየተከተለው ያለውን ፖለቲካዊ መንገድ እየተቹ ሲሆን፣ የትችታቸው መሠረትም ሕገ መንግሥታዊ መብትን ለማስከበር ሕገ መንግሥቱን የመጣስ አካሄድ መከተል አይገባም የሚል ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከትግራይ ክልል ለቀረበለት ጥያቄ የሰጠውን ምላሽ አስመልክቶ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ ላይ፣ የትግራይ ክልል በቀጣይ ሊይዝ የሚችለውን አቋም ወይም ሊወስድ የሚችለውን ዕርምጃ የተገነዘበ የሚመስል ምላሽ ተካቷል።
ይኸውም፣ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መመዝገብ፣ መቆጣጠርና ማስተዳደር፣ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳን ማውጣት፣ የምርጫውን ከተፅዕኖ ነፃና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ማስፈጸም ሥልጣን ያለው ብቸኛ ተቋም ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳን፣ አፈጻጸምንም ሆነ ተያያዥ ሁኔታን የሚወስነውም ቦርዱ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም የትግራይ ክልል ምክር ቤት በክልሉ ውስጥ ስድስተኛውን ዙር የክልል ምክር ቤት ምርጫ እንዲካሄድ ውሳኔ ለመስጠት፣ እንዲሁም ቦርዱ ይህንን ውሳኔውን ተቀብሎ ሊያስፈጽም ይገባል የሚልበት ሕጋዊ መሠረት የለውም፤›› የሚል ነው።
ምርጫ ቦርድ ለሰጠው ውሳኔ የሰጠውን አመክንዮ በተመለከተ አቶ ጌታቸው ለሚዲያዎች በሰጡት አሰተያየት፣ ‹‹ምርጫ ቦርድ በሆነ ምክንያት ምርጫ ማካሄድ አልፈለገም ተብሎ፣ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠ የክልሎች ወይም የብሔር ብሔረሰቦችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ይታጠፋል ማለት አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ ምርጫ ቦርድ በአገሪቱ ብቸኛ የምርጫ አስፈጻሚነት መብት የሚኖረው ምርጫ እንዲያስፈጽም ለቀረበለት ጥያቄ ፈቃደኛ እስከሆነ ድረስ ብቻ እንደሆነም አመልክተዋል።
‹‹የመምረጥ መብት ከምርጫ ቦርድ ህልውና በላይ ነው፤›› የሚሉት አቶ ጌታቸው፣ ‹‹ራስን በራስ የማስተዳደርና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ከምርጫ ቦርድም ሆነ ከማንም በላይ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም ምርጫ ቦርድ ለቀረበለት ጥያቄ ፈቃደኛ አልሆነም ተብሎ የትግራይ ክልል ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ተሽቀንጥሮ መጣል እንደሌለበትና እንደማይችልም ገልጸዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሰጠው የሕገ መንግሥት ትርጉም የክልል ምክር ቤቶችን ሥልጣን ለማራዘም የዘረዘረው የሕግ አመክንዮ የተሟላ እንዳልሆነ የሚገልጹት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕገ መንግሥት ባለሙያዎች፣ ከዚህ እኩል የትግራይ ክልልም ሆነ ሌላ አካል የተሰጠውን ትርጓሜ መቃወሙ ተገቢ ሆኖ ሳለ ራስን በራስ የማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ መብትን በመጥቀስ፣ የክልል ምርጫን በራስ የምርጫ አስፈጻሚ ለማካሄድ የሚያራምዱት አቋም ሕጋዊ እንዳልሆነ ይገልጻሉ።
ባለሙያዎቹ እንደሚሉት በፌዴራል መንግሥት የሕዝብ ጤና ደኅንነትን ለማረጋገጥ ባለው ኃላፊነት መሠረት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሕገ መንግሥቱን የተከተለ እንደሆነ ገልጸዋል። ይህ አከራካሪ አለመሆኑን የሚጠቅሱት እነዚህ ባለሙያዎች፣ በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሕገ መንግሥቱ ከተጠቀሱት አምስት አንቀጾች ውጪ ሌሎች መብቶች መገደባቸውን ገልጸዋል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መገደብ ከማይችሉት አምስት ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች አንዱ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 (1) እና (2) ላይ የተገለጹት ራስን በራስ የማስተዳደርና የመገንጠል መብቶች እንደሆኑ ገልጸው፣ ይህንን መብት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችለው ቀጣዩ አንቀጽ 39 (3) ግን በአስቸኳይ አዋጁ ገደብ የተጣለበት መሆኑን ያስረዳሉ።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ገደብ እንደተጣለበት ባለሙያዎቹ የሚገልጹት አንቀጽ 39(3) ‹‹ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ብሔሩ፣ ብሔረሰቡና ሕዝቡ በሰፈረበት መልክ ዓምድር ራሱን የሚያስተዳድርበት መንግሥታዊ ተቋማት የማቋቋም፣ እንዲሁም በክልልና በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብትን ያጠቃልላል፤›› የሚል ሲሆን፣ ይህ ደግሞ በምርጫ አማካይነት የሚፈጸም እንደሆነና ምርጫው ደግሞ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት መራዘሙን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከወራት በፊት በሰጡት አስተያየት ምርጫ ማካሄድ ባለመቻሉ መራዘሙን በመቃወም፣ ከሕግ ውጪ የጨረባ ምርጫ እናካሂዳለን የሚል አካልን መንግሥታቸው እንደማይታገስና ለዚህም በቂ ዝግጅት ማድረጉን መግለጻቸው ይታወሳል።
የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) በበኩላቸው ቀደም ሲል በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹ምርጫ መሠረታዊና ትልቅ ነገር ነው፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ነው። በሌላ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር እንችላለን፣ በዚህ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብታችንን በተመለከተ ግን መደራደር በፍፁም አንችልም። ይህ ቀይ መስመር ነው፤›› ማለታቸው ይታወሳል።
በሁለቱ ወገኖች የሚታየው እሰጥ አገባና መካረር አሁንም እንደቀጠለ የሚገኝ ሲሆን፣ ይህንን መካረር ለማርገብ ያሰቡ የአገር ሽማግሌዎች በቅርቡ ጥረት መጀመራቸው ይታወሳል።