Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና​​​​​​​የሻለቃ ኃይለ ገብረ ሥላሴ ሁለት ሆቴሎች ወደሙ

​​​​​​​የሻለቃ ኃይለ ገብረ ሥላሴ ሁለት ሆቴሎች ወደሙ

ቀን:

በዝዋይ (ባቱ) እና በሻሸመኔ ከተሞች የሚገኙት የሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ንብረት የሆኑ ኃይሌ ሪዞርት ሆቴሎች ወደሙ፡፡ ማክሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ከንጋቱ አሥር ሰዓት እስከ ቀኑ አሥር ሰዓት በሁለቱ ሆቴሎች ላይ በተፈጸመው ቃጠሎ ሙሉ በሙሉና በከፈል መውደማቸው ተረጋግጧል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን ሻሸመኔ ከተማ የሚገኘው ኃይሌ ሪዞርት ሆቴል ባለ አራት ፎቅ ሕንፃ ሲሆን፣ 52 የመኝታ ክፍሎችና የተለያዩ የሆቴል አገልግሎት መስጫዎች ነበሩት፡፡ ሆቴሉ ሙሉ በሙሉ ሲወድም አንድም ዓይነት ንብረት እንዳልተረፈ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አልጋዎች፣ ቴሌቪዥኖች፣ ፍሪጆች፣ የወጥ ቤትና የጅምናዚየም ዕቃዎችና ሌሎች ቁሳቁሶች ወድመዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ዝዋይ (ባቱ) ከተማ የሚገኘው ባለ ሁለት ፎቅ ሆቴል በከፊል የወደመ ሲሆን፣ የሆቴሉ ቁሳቁሶች ግን በሙሉ መጋየታቸው ታውቋል፡፡ ሆቴሉ 53 መኝታዎች ነበሩት፡፡

በአካባቢው የነበሩ የዓይን ምስክሮች ለሪፖርተር እንደገለጹት ከቃጠሎ የተረፉት የሆቴሉ ዕቃዎች ጥቃቱን በፈጸሙ ግለሰቦች ነው የተሰባበሩት፡፡ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የወጣባቸው የሁለቱ ሆቴሎች ዕቃዎች ከመውደማቸውም በላይ፣ በሆቴሎቹ ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በሁለቱ ሆቴሎች ውድመት ምክንያት ከ400 በላይ ሠራተኞች ከሥራ ውጪ እንደሚሆኑ የታወቀ ሲሆን፣ የሆቴሎቹን ውድመት በተመለከተ ሻለቃ ኃይሌን ለማነጋገር ጥረት ቢደረግም አልተሳካም፡፡

ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ሰኞ ሰኔ 22 ቀን ከምሽቱ 3፡30 ሰዓት ላይ ማንነታቸው ባልታወቀ ሰዎች መገደሉ ይፋ ከተደረገ በኋላ፣ በአዲስ አበባ ከተማና በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች በርካታ ሰዎች ሲገደሉ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ የፌዴራል ፖሊስና የኦሮሚያ ፖሊስ በሰጡት መግለጫ የግድያው ተጠርጣሪዎችና ተሳትፎ ነበራቸው የተባሉ ግሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው ፍርድ ቤት መቅረባቸው ይታወሳል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የድምፃዊ ሃጫሉን ግድያ በመቃወም በወጡ ከተለያዩ አካባቢዎች በመጡ ግለሰቦች የንግድ መደብሮች፣ ሕንፃዎችና ተሽከርካሪዎች ወድመት ደርሶባቸዋል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ 250 ተሽከርካሪዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በአዳማ፣ በአሰላ፣ በዝዋይ፣ በአርሲ ነገሌ፣ በሻሸመኔ፣ በአሰበ ተፈሪ፣ በሐረር፣ በአምቦና በሌሎች ከተሞች በመንግሥትና በግለሰቦች ንብረቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱ ታውቋል፡፡ በሐረር ከተማ የራስ መኮንን ሐውልት ፈርሷል፡፡ በአዳማ ከተማ ማዘጋጃ ቤቱ በቃጠሎ ወድሟል፡፡ በሻሸመኔ ከተማ የደረሰው ውድመት በጣም ከፍተኛ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ዋና ዋና የሚባሉ ሕንፃዎች ወድመዋል፡፡ የንግድ መደብሮች፣ ሕንፃዎች፣ ተሽከርካሪዎችና የተለያዩ ንብረቶች ላይ የደረሰው ውድመት ከፍተኛ መሆኑን ከአካባቢዎቹ ምንጮች ለመረዳት ተችሏል፡፡

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በክልሉ 87 ሰዎች መሞታቸውንና በ76 ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ስምንት ሰዎች መሞታቸው ተሰምቷል፡፡ በኦሮሚያ ክልል አራት የፖሊስ ባልደረቦች መሞታቸው ሲገለጽ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ሁለት የፖሊስ ባልደረቦች ሞተዋል ተብሏል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የደረሰው ጉዳት የተጠቀሰውን ቁጥር ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ታምኗል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ንብረቶቻቸው ከወደሙባቸው መካከል አንዱ አቶ ነፃነት ሰለሞን ራሱን ጨምሮ ስድስት ቤተሰቦቹን የሚያስተዳድርበት ሚኒ ባስ ታክሲው የፊት፣ የጎንና የኋላ መስተዋቶቹ መሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ እንደተደረጉበት ለሪፖርተር  ገልጿል፡፡ መስተዋቶቹን መልሶ ለመተካት 32 ሺሕ ብር ግምት ስለተነገረው በገንዘብ ችግር ምክንያት ወደ ሥራው በቶሎ መመለስ እንደማይችል በከፍተኛ ሐዘን ውስጥ ሆኖ ተናግሯል፡፡

ዶልፊን በመባል የሚታወቀው የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ተሽከርካሪ ባለቤት የሆነው አቶ መስፍን ነገደ፣ ከመስታዎቶቹ በተጨማሪ የተሽከርካሪው አካል በድንጋይና በብረት ዱላ በመቀጥቀጡ ከፍተኛ ጉዳት እንደ ደረሰበት ለሪፖርተር አስረድቷል፡፡ ተሽከርካሪውን በቅርቡ በዕቁብና ከወዳጆቹ ባገኘው ብድር የገዛው ስለሆነና ዕዳም ስላለበት፣ ብድር ወይም ድጋፍ ካላገኘ በስተቀር አሁን ባለው ሁኔታ መልሶ ማንቀሳቀስ እንደማይችል ገልጿል፡፡ ይህንን ዓይነት ውድመት ኢንሹራንስ ስለሌለውም ከባድ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለሁት ያለው አቶ መስፍን፣ ባለቤቱ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየቷ ምክንያት ሦስት ሕፃናትን የማሳደግ ኃላፊነት የእሱ ብቻ እንደሆነ ተናግሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...