Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየታላቁ የህዳሴ ግድብ የዲፕሎማሲና የኃይል አሠላለፍ

የታላቁ የህዳሴ ግድብ የዲፕሎማሲና የኃይል አሠላለፍ

ቀን:

በአሰፋ ኢያሱ

ለቀደምት ዓለም ሥልጣኔ መሠረት ከሆኑት ወንዞች መካከል ናይል፣ ኤፍራጥስ፣  ጤግሮሰ፣ ጋንጀስ፣ አማዞን፣ የሎው ሪቭር፣ ሜኮንግና የመሳሰሉት በመጀመርያ ረድፍ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እነዚህ ወንዞች ቀደምት ሥልጣኔዎች ተነስተው የገነኑባቸው ቢሆኑም፣ በጊዜ ሒደት ሥልጣኔዎች መሠረታቸውን ወደ ቴክኖሎጂ ፈጠራና አጠቃቀም እያጋደሉ በመምጣታቸው፣ የእነዚያ ቀደምት ሥልጣኔ ባለቤት ሕዝቦች የውኃ አጠቃቀማቸው በተለያዩ ምክንያቶች በአብዛኛው የተለየ ገጽታ ይዞ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ናይል ተፋሰስ የጥንቱ አጠቃቀምና አስተሳሰብ ገኖ የሚታይበት አካባቢ የለም፡፡

ግብፅ የ5‚000 ዓመታት ሥልጣኔ ባለቤት አገር ስትሆን የሥልጣኔ መሠረቷም ናይል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዓለም ካሉ ትልልቅ ወንዞች ውስጥ ከስፋቱና ከርዝመቱ (6‚700 ኪሎ ሜትር) አንፃር አነስተኛ ዓመታዊ የዝናብ መጠን (220 ሚ.ሜ.) ከሚያገኙትና ከፍተኛ ትነት ካላቸው ወንዞች መካከል ናይል ዋነኛው ነው፡፡ በተጨማሪም ተፋሰሱ ከሚያገኘው የዝናብ መጠን አነስተኛ ፍሰት (14 በመቶ) ያለው ወንዝ ነው፡፡ የተፋሰሱ ስፋት ወደ 2.8 ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር ሲሆን፣ አብዛኛው (1.9 ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር) ተፋሰስ በሁለቱ ሱዳኖች ውስጥ ይገኛል፡፡ ቀሪውን ሌሎች ዘጠኝ የተፋሰሱ አገሮች ይጋሩታል፡፡ በተለይ 95 በመቶ የሚሆነው የግብፅ ሕዝብ በወንዙ ግራና ቀኝ በአማካይ እስከ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ከጥንት ጀምሮ የውኃው መጠን በተለያዩ ምክንያቶች መቀነሱን ትከትሎ ግብፆች የወንዝ ከፍታ መለኪያ (ናይሎ ሜትር) ከመገንባት በተጨማሪ፣ የላኛው ተፋሰስ አገሮችን የውኃ አጠቃቀም ይከታተሉ ነበር፡፡ በተለይ ባለፉት 200 ዓመታት መከታተሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ ከመምጣቱ በተጨማሪ፣ ተፋሰሱን ያለ መተማመንና የውጥረት አካባቢ አድርጎታል፡፡

- Advertisement -

በሌላ በኩል ደግሞ ምንም እንኳ በበጋ ወቅት ወንዙ የሚፈሰው ከነጭ ዓባይ ከሚያገኘው ውኃ ቢሆንም፣ ከናይል አራት ዋና ዋና ገባሮች ውስጥ ሦስቱ ከኢትዮጵያ የሚመነጩ በመሆናቸውና አብዛኛው ዓመታዊ የውኃ መጠን (86 በመቶ) ከኢትዮጵያ የሚገኝ ስለሆነ፣ በኢትዮጵያ ድርቅ ተከስቶ የወንዙ መጠን በቀነሰ ቁጥር ግድቦች ተሠርተዋል በሚል ፍራቻ አካባቢው ወደ ጦርነት ሥጋት ሲገባ ኖሯል፡፡ በተለይ እ.ኤ.አ. ከ1825 እስከ 1875 ድርስ የወንዙን ምንጭና ተፋሰስ ለመቆጣጠር ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ቦታዎች ጦርነት እንደከፈተች ይታወሳል፡፡ እነዚህ ጦርነቶች ያልተሳኩ ቢሆንም፣ ግብፅ በታላቋ ብሪታኒያ ቅኝ ከተያዘችበት እ.ኤ.አ. ከ1882 ጀምሮ አካሄዷ የተለየ አቅጣጫ እየያዘ መጥቷል፡፡ በተለይ ብሪታኒያ ሱዳንን እ.ኤ.አ. በ1898 እንደ ገና ከያዘች ጀምሮ፣ ወንዙ በዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ ሥር እየወደቀ መጥቷል፡፡ በታላቋ ብሪታኒያ ውስጥ የነበሩ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ የግብፅና የሱዳን ጥጥ ምርት ላይ ጥገኛ እየሆኑ መምጣታቸው፣ ቅኝ ገዥዋ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ከሌሎች በአካባቢው ቅኝ ግዛት ካላቸው አገሮች ጋር ስምምነት እንድትዋዋል አስገድዷታል፡፡ ለምሳሌ ከፈረንሣይ እ.ኤ.አ. በ1906፣ ከቤልጀም እ.ኤ.አ. በ1906 ከጣሊያን እ.ኤ.አ. በ1891፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ጋር እ.ኤ.አ. በ1902 በአመዛኙ ወደ ኃያሏ አገር ያመዘኑ ውሎች ተፈርመዋል፡፡ ቆየት ብሎ እ.ኤ.አ. በ1925 ብሪታኒያና ጣሊያን የጣናን ሐይቅና የባሮ ወንዝን በተመለከተ ማስታወሻ የተለዋወጡ ቢሆኑም፣ በጊዜው የነበረው የሊግ ኦፍ ኔሽን ማብራሪያ እንዲያቀርቡ ሲጠይቃቸው በተጠቀሱት ጉዳዮች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት መገዳደራቸውን ክደዋል፡፡

ከእነዚህ ውጪ በተለይም ባለንበት ወቅት የናይልን ወንዝ በተመለከተ በተደጋጋሚ ጊዜ የሚነሱት እ.ኤ.አ. የ1929 እና የ1959 ስምምነቶችም መሠረታቸው፣ የታላቋ ብሪታኒያ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ እ.ኤ.አ. የ1902 ስምምነት ወንዙን ሙሉ በሙሉ መዝጋት የሚል ስለሆና ይህም አሁን ባለው የሰው ልጅ ሥልጣኔ የማይቻል ስለሆነ ብዙ ጊዜ አይጠቅሱትም፡፡ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ታመርተዋለች ተብሎ የሚጠበቀው ወደ 75 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውኃ በየዓመቱ አራት ወይም አምስት ቦታ ላይ ግድብ እየሠራች፣ በዚያው ዓመትም ሙሉውን ውኃ እየያዘች ለማስቀረት ይቅርና አንድ ግድበ ለመሥራት አሥር ዓመት እየወሰደብን ነው፡፡ ለመሙላትም ቢያንስ የዚህን ግማሽ ሊወስድ ይችላል፡፡ በአጠቃላይ አሁን ያለንበት ሁኔታ እ.ኤ.አ. የ1902 ስምምነት በፍፁም የሚያስነሳ አይደለም፡፡ ይሁንና ግብፅ በተደጋጋሚ የምታነሳቸውና የድርድር አካል እንዲሆኑ የምትጠቅሳቸው እ.ኤ.አ. የ1929 እና የ1959 ሁለት ስምምነቶች እንደሚከተለው ተተርጉመው ቀርበዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በግንቦት 7 ቀን 1929 በግብፅና በእንግሎ ግብፃዊ ሱዳን በተፈረመው ስምነት መሠረት፣

 1. ግብፅ 48 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ሱዳን ደግሞ አራት ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር ውኃ ዓመታዊ ድርሻ ይኖራቸዋል፣
 2. የወንዙ የበጋ ፍሰት (ከጥር እስከ ሐምሌ) ለግብፅ ይተዋል፣
 3. ግብፅ የላይኛውን ተፋሰስ አገሮች የመከታተል ወይም የመቆጣጠር መብት ይኖራታል፣
 4. ግብፅ ማንኛውንም የላይኛውን ተፋሰስ አገር ሳታስፈቅድ ወንዙ ላይ ግንባታዎች ልትሠራ ትችላለች፣
 5. ግብፅ ጥቅሟን የሚነካ ማንኛውንምን ግንባታ ሥራ ልትከለክል ትችላለች፡፡

ይህ ስምምነት ለግብፅ ሙሉ ሥልጣን የሰጠ ሲሆን፣ ከሱዳን በስተቀር ስለላይኛው ተፋሰስ አገሮች ያለው ነገር የለም፡፡ እ.ኤ.አ. በ1959 በግብፅና በሱዳን (እ.ኤ.አ. በ1956 ነፃ ከወጣች በኋላ) በተደረገው ስምምነት መሠረት፣

 1. ቀደም ብሎ ስለውኃው ዓመታዊ ፍሰት የነበረው ብዥታ የመጀመርያው አስዋን ግድብ ላይ 84 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ሆኖ እንዲወሰድ፣
 2. ግብፅ 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር፣ ሱዳን ደግሞ 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ዓመታዊ ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ በተጠቀሰው ቦታ ላይ ዓመታዊ የትነት መጠኑ አሥር ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ሆኖ ከክፍፍሉ ውጪ እንዲሆን፣
 3. በሱድ ረግረጋማ ቦታ (ደቡብ ሱዳን) እየባከነ ያለውን ውኃ ወደ ወንዙ ለማስገባት ሱዳን ከግብፅ ጋር በመተባበር ፕሮጀክቶች ትገነባለች፡፡ ከሌሎች የላይኛው ተፋሰስ አገሮች የመብት ጥያቄ ቢነሳ ግብፅና ሱዳን በጋራ ይቆማሉ፣
 4. የላይኛው ተፋሰስ አገሮች የመብት ጥያቄ ጠንክሮ ከወጣና ውኃውን መከፋፈል ካለባቸው ከሁለቱ አገሮች በእኩል መቶኛ ወይም መጠን ተቀንሶ ይሰጣል፣
 5. ግብፅ የወንዙን ዓመታዊ ፍሰት ሊይዝ የሚችል የአስዋን ትልቁን ግድብ እንድትሠራ መብት ይኖራታል፣
 6. ሱዳንም እስከ ድርሻዋ ድረስ የሮዛሪስ ግድብንና ሌሎች የመስኖና የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጩ ፕሮጀክቶች ልትገነባ ትችላለች፣
 7. የሁለቱን አገሮች የጋራ ትብብር  ለመመሥረት የጋራ የቴክኒክ ኮሚሽን ይቋቋማል፡፡

ይህ ስምምነት እንዲደረግ ጥያቄ ያነሳችው ሱዳን ስትሆን፣ እ.ኤ.አ. በ1929 ስምምነት ለግብፅ የተሰጠውን ፍፁም ሥልጣንና በሱዳን ፕሮጅከቶች ላይ የተጣለውን ግድብ በመቃወም ነበር፡፡ በጊዜው የነበሩት የአገሪቱ መሪ እ.ኤ.አ. በ1959 ስምምነት ረቂቅ ደስተኛ ስላልነበሩ በግብፅ ዕርዳታ መፈንቅለ መንግሥት ተከናውኖ ሲወገዱ፣ የግብፅን ፍላጎት የሚደግፍ መሪ ከተቀመጠ በኋላ ስምምነቱ እንዲፈረም ተደረጓል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም በጊዜው የግብፅ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጋማል አብደል ናስር ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጋር ወንዙን በተመለከተ ተመሳሳይ ስምምነት ማድረግ ቢፈልጉም ኢትዮጵያ ፈቃደኛ ስላልነበረች፣ ቀደም ብሎ በታላቋ ብሪታኒያ የተጀመረውን ኢትዮጵያን ብድርና ዕርዳታ ከማስከልከል በተጨማሪ ውስጣዊ ሰላሟን የማናጋት ሥራ በስፋት ተያያዘው፡፡ በእርግጥ እ.ኤ.አ. ከ1927 ጀምሮ አሜሪካኖች በኢትዮጵያ ዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ላይ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለመሥራት ቢንቀሳቀሱም፣ በታላቋ ብሪታኒያ ተቃውሞ የቀሩ ሲሆን፣ በተለይ እ.ኤ.አ. ከ1956 እስከ 1964 የአሜሪካ የግብርና ቢሮ በእዚያ ያሉ ፕሮጀክቶችን ቢያጠናም በተመሳሳይ ተቃውሞ እንዲቀሩ ተደርጓል፡፡ በተጠቀሰው ዘመን ግብፅ ትልቁን የአስዋን ግድብ ለመሥራት የገንዘብ አቅርቦት እያፈላለገች የነበረችበት ወቅት ሲሆን፣ ከምዕራባውያን ብድርና ዕርዳታ ማግኘት ስላልቻለች ወደ ሶቭየት ኅብረት ያጋደለችብት አጋጣሚም ነበር፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ በወንዝ ውኃ አጠቃቀም፣ በባህር ላይ ጉዞ፣ በውቅያኖስና ባህሮች ዓለም አቀፍ ድንበር፣ በውኃ ብክለትና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ዓለም አቀፍ ደንቦች ወይም መመርያዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ እ.ኤ.አ. በ1966 በሄልሲንኪ የወጣው በአብዛኛው ይጠቀሳል፡፡ ይህ ሰነድ ማናቸውም የተፋሰስ አገሮች የሚያደርጉትን ስምምነት የሚቀበል ሲሆን፣ ዋናው የመመርያው መሠረት ፍትሐዊና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ የውኃ ክፍፍል (Reasonable and Equitable Distribution) ነው፡፡ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ቀድመው የተሠሩ ፕሮጅክቶችን በማይጎዱ መንገድ እንዲከናወኑ ቢያመለክትም፣ አለመግባባቶች በውውይትና በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንዲታዩ ያመለክታል፡፡ በተመሳሳይ የዓለም ባንክ፣ የዓለም ገንዘብ ድርጅትና አበዳሪዎች (Safeguarding Policy) በሚል ሽፋን ወደ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የሚፈስ የመሬት ላይ ወይም የመሬት ውስጥ ውኃ (Surface and Groundwater) ባለበት አካባቢ ፕሮጀክቶች በተፋሰሱ አገሮች ድጋፍ ካላገኙ አይረዱም፣ ወይም ጥንቃቄ ያደርጋሉ፡፡ ይህም በይዘት ቀደም ብሎ በናይል ተፋሰስ ላይ በቅኝ ግዛት ወቅት ከተቀመጡ ደንቦች ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው፡፡

ደንቦችና መመርያዎች እንደተጠቀሰው ቢሆንም፣ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ባለመኖራቸው ሀብትና አቅም ያላቸው አገሮች ከመመርያዎች በተቃራኒው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ለምሳሌ አሜሪካ ከሜክሲኮ ጋር በምትጋራው ኮሎራዶና ሪዮ ግራንዴ ወንዝ፣ ቱርክና ሶሪያ ከኢራቅ ጋር በሚጋሯቸው ኤፍራጥስና ጤግሮስ ወንዞች ላይ፣ ህንድ ከባንግላዴሽ ጋር በምትጋራው ብራሃምፓትራ ወንዝ ላይ፣ ቻይና ከቬትናም፣ በርማ፣ ከካምቦዲያ፣ ላኦስና ታይላንድ ጋር በምትጋራው ሜኮንግ ወንዝ ላይ፣ እንዲሁም ሌሎች ተመሳሳይ ሁኔታዎች በተለያዩ ዓለም አካባቢዎች ይስተዋላሉ፡፡

የኤፍራጠስና ጤግሮስ መነሻ የሆነችው ቱርክ በተለይም እ.ኤ.አ. ከ1960 ጀምሮ የ22 ግድብ ፕሮጀክቶችን መተግበር ከጀመረች አንስቶ አለመግባባት ቢኖርም፣ ግድቦችን ከመገንባትና መስኖ በመጠቀሟ የወንዞች መጠን እስከ ግማሽ መቀነስ ኢራቅ ላይ ችግር ቢያመጣም ያገዳት የለም፡፡ ሶሪያም በተለይ በኤፍራጠስ ወንዝ ላይ ከስድስት በላይ ግድቦች መገንባቷና በተለይም ኢራን አንዳንድ ትልልቅ የጤግሮስ ወንዝ ገባሮችን አቅጣጫ ማስቀየሯን ኢራቅ ማስቆም አልቻለችም፡፡ አሜሪካ በሪዮ ግራንዴ ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ የውኃው መገኛ ከመሆኗ አንፃር፣ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ልዕለ ኃያል ባልነበረችበት እ.ኤ.አ. ከ1848 እስከ 1948 ድረስ የተደራደረች ሲሆን፣ ቆይቶም ወንዙ መጨረሻው ላይ ውኃ ሳይሆን አሸዋ እስኪተፋ ድረስ ውኃውን ተጠቅማለች፡፡ ኮሎራዶ ወንዝ ላይ ከ105 በላይ ግድቦች ስትሠራ ሜክሲኮ ምንም ማድረግ አልቻለችም፡፡ ምናልባትም ብሪታኒያ ከግብፅና ከሱዳን ይልቅ ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛት ይዛ ብትሆን ኖሮ ተቃራኒ አሠራሮች እናይ ነበር፡፡

በአጠቃላይ እ.ኤ.አ. እስከ 1999 ድረስ ግብፅ በናይል ወንዝ ላይ የቅኝ ገዥ አገሮች ጥቅማቸውን ለማስከበር የተጠቀሙባቸውን አሠራሮችንና የምዕራባውያንን ድጋፍ በመመርኮዝ፣ እንዲሁም በአፍሪካና በዓረቡ ዓለም የነበራትን ዲፕሎማሲያዊ የበላይነት በመጠቀም የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ከወንዙ ውኃ ከእነጭራሹ እንዳይጠቀሙ ስታደርግ ቆየታለች፡፡ በተጨማሪም የላይኛው ተፋሰስ አገሮችን ከውኃው የመጠቀም ዕድል ሙሉ ለሙሉ ለመዝጋት ቅድሚያ ተጠቃሚ (Principles of Acquired Rights) በሚለው አስተሳሰብ፣ ሁሉንም የወንዙን ውኃ ሥራ ላይ አውየዋለሁ ለማለት ፕሮጀክቶች ከመሥራቷ በተጨማሪ፣ እ.ኤ.አ. በ1959 ስምምነት መሠረት ከሱዳን 300 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውኃ እዳ እንዳለባት ትጠቅሳለች (ምንም እንኳ በየክረምቱ እስከ አራት ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ትርፍ ውኃ ወደ በረሃ ብትለቅም)፡፡ የውኃውን ጉዳይም በአገራዊ ደኅንነት ምክንያት ሕገ መንግሥቷ ውስጥ ማካተቷ መንግሥትን የድርድር ጫና ውስጥ ከትቶታል፡፡ እ.ኤ.አ. የ1959 ስምምነት የፈቀደውን ዘግይቶ የወጣው/የተሻሻለው ሕገ መንግሥት ከልክሎታል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ በላይኛው ተፋሰስ አገሮች ውስጥ ያሉ የቅኝ ግዛት ሕግ ክፍተቶችን በማጉላት፣ የውስጥ ችግሮችን በማባባስ፣ እንዲሁም ሆን ብሎ በሕዝቦች መካከል ቁርሾዎችን በመፍጠርና አገሮችን እርስ በርስ በማጋጨት ጥቅሟን ለማስቀጠል የተቻላትን ስታደረግ ኖራለች፡፡

ሆኖም እ.ኤ.አ. በ1999 የተጀመረው የናይል ተፋሰስ አገሮች ትብብር ጥረት እ.ኤ.አ. በ2010 የስምምነት ሰነድ በማዘጋጀት፣ እንዲሁም በአብዛኛው አገሮች ስምምነቱን በመፈረም ሲጠናቀቅ የግብፅ ተቃውሞ ጫፍ ደርሷል፡፡ እንደሚነገረው ግብፅና ሱዳን ስምምነቱን ያልፈረሙት ወቅታዊ የውኃ አጠቃቀምን ያካትት በሌላ መንገድ እ.ኤ.አ. የ1959 የእነሱን ስምምነት የሚቀበል ይሁን በማለታቸው ነው፡፡ ትርፍ ውኃ በሌለበት የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ለምን እንደሚፈርሙ ግልጽ አይደልም፡፡ አዲሱን እ.ኤ.አ. የ2010 የናይል ተፋሰስ ስምምነት በአብዛኛው አገሮች ከመፈረማቸው በተጨማሪ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መበሰር የአዲስ ፍትሐዊ አጠቃቀም መሠረት መጣሉን አመላካች ሆኗል፡፡

አንዳንድ የግብፅ ሚዲያዎች አጠቃላይ እውነታውን ለሕዝብ ከማስገንዘብ ይልቅ፣ ክስተቶችን እንደ ምክንያት እያቀረቡ አሉታዊ ሚና ሲጫወቱ ይታያሉ፡፡ ጸሐፊዎች መንግሥታቸው ኢትዮጵያንና የተፋሰሱን አገሮች በተመለከተ ግልጽ ዕቅድ የለውም ሲሉ ይወቅሳሉ፡፡ ለምሳሌ የመንግሥት ሚዲያ የሆነው አል አህራም ዊክሊ ኢትዮጵያ የግብፅን ብጥብጥ እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅማ እየሠራች እንደሆነ በተደጋጋሚ ያወሳል፡፡ እንደ እነሱ ከሆነ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመርያ ዕቅድ 14 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ለመያዝና አሁን የታቀደውን 60 በመቶ ኃይል ለማመንጨት የነበረ ቢሆንም፣ በግብፅ ግርግር ምክንያት ወደ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ከፍ ማለቱን በምሬት ይገልጻሉ፡፡ ሌላው የእነሱ ከፍተኛ ሥጋት የግድቡ ቦታ ከአጠቃላዩ የናይል ውኃ 60 በመቶ የሚያልፍበት ስለሆነ፣ ግድቡ እስኪሞላ የሚቀንስባቸው የውኃ መጠን ነው፡፡ ግድቡ በሚሞላበት ከአራት እስከ ሰባት ዓመት ድረስ በግብርናና በኃይል ምርት ላይ የሚያደርስው ተፅዕኖ የሚመለከታችው መሥርያ ቤቶች ሥጋት እንደሆነ ይገለጻል፡፡ በጣም የሚገርመው በባለሙያዎች ቡድን የቀረበውን ሪፖርት ማጣጣላቸውና እነሱ የገነቡት ታላቁ የአስዋን ግድብ 50 ዓመት ሲያገለግል፣ ብዙ ልምድ ባላቸው የጣሊያንና ሌሎች ካምፓኒዎች  እየተሠራ ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከ25 ዓመታት በላይ ስለማያገለግል ፈርሶ ግብፅና ሱዳንን ያጥለቀልቃል እያሉ የሚያነፍሱት ወሬ በሱዳናውያን ውሳኔ ላይ ተፅዕኖ ሲፈጥር ቆይቷል፡፡፡

አንዳንድ ጸሐፊዎች በውኃ ምክንያት ጦርነት የመነሳት ዕድሉ አናሳ መሆኑን ሲያብራሩ የሚያቀርቡት ምክንያት፣ ከውኃ ጥቅም ይልቅ ሌሎች አካባቢያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ስትራቴጂካዊ ግንኙነቶች፣ ፖለቲካዊ ፍልስፍናዎችና የመሳሰሉት ተፅኖዎች ከፍ ያለ ነው ይላሉ፡፡ በተጨማሪም የውቅያኖስ ውኃ የማጣራት ቴክኖሎጂ (Disalination) መስፋፋት እንደ ተጨማሪ ምክንያት ይቀርባል፡፡ ለምሳሌ ግብፅ በተለያዩ ውኃ አጠር ቦታዎች በተከለቻቸው መሣሪያዎች እስከ አንድ ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውኃ በቀን እንደምታመርት ይጠቀሳል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በእነዚህና በሌሎች እውነታዎች ግብፅ በህዳሴው ግድብ ምክንያት፣ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት እንደማትጭር ይገመታል፡፡ 162 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውኃ የያዘ ግድብ አናትዋ ላይ አስቀምጣ የሰው እግር እቆርጣለሁ ብትል ወዲው መልስ ባታገኝም እንኳ፣ ለዘለዓለም በሥጋት እንቅልፍ ሳትተኛ ነው የምትኖረው፡፡ ወደ 95 በመቶ የሚሆነውን ሕዝብና የአገሪቱን ሀብት በዓባይ ሸለቆ (በአምስት በመቶ የአገሪቱ ስፋት) አስቀምጣ ሌላ መውጋት በእሳት መጫወት ነው የሚሆነው፡፡ ስለግድቡ በግብፅ ሚዲያዎች በሚወጡ የመንግሥትና ደጋፊዎች አስተያየት ላይ የሚሰጡ መልሶች ሙሉ በሙሉ በሚመስል፣ ኢትዮጵያውያን ሲበዙ ይህ ነው የሚባል ምክንያት ወይም ተሳታፊ በግብፅ በኩል አይታይም፡፡ ምናልባትም ከኢትዮጵያውያን የተሻለ ጠንካራ አመክንዮና አሳማኝ ምክንያት ስለሌላቸው ይሆናል፡፡ ከግድቡ በፊት ግን በተለያዩ ዓለማት በሁለቱ አገሮች ዜጎች መካከል በሚደረጉ ክርክሮች፣ የግብፃውያን አቋም ተቀባይነት ነበረው፡፡ ስለዚህ እየሠሩ መከራከር ለኢትዮጵያ ተቀባይነትን አስገኝቷል፡፡

ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ በታሪካዊ ምልክቷና በተፈጥሯዊ ስጦታዋ ላይ አንድ ግድብ መሥራቷ መዘግየቷን ነው የሚያመለክተው፡፡ በሌላ በኩል ግብፅ በዓባይ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖራት ግንኙነት በሌሎች ጥቁር አፍሪካውያን አገሮች ግንኙነት ላይ አንድምታ ይኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ መስክ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተቀባይነት፣ የፕሮጅክቱ ፍትሐዊነትና የሚፈጥረው የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር፣ ግጭት እንኳ ቢነሳ የውጤቱ በጣም ውሱንነት፣ የወትሮ የግብፅ ደጋፊዎች ያሉበት ወቅታዊ ሁኔታና በአሁኑ ወቅት ስለአገሪቱ ያላቸው ምልከታ፣ የፕሮጀክቱ ገንቢዎችና አበዳሪዎች ጥቅምና የመሳሰሉት ግጭት ቢፈጠር ለግብፅ የበለጠ መንሸራተትን እንጂ ጥቅምን አያስገኝላትም፡፡ በአሁኑ ወቅት ከትራምፕ አስተዳደርና በቀጥታ ተፅዕኖ ከሚያሳድርባቸው ተቋማት ውጪ፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትን ጨምሮ አውሮፓውያን፣ ቻይናና ሩሲያ ድርድሮች በሰጥቶ መቀበል መርህ እንደፈጸሙ ይሻሉ፡፡ ግብፅ ሁሉንም ሞክራ አልሳካ ሲል ድሮም ለኢትዮጵያ ወይም ለአፍሪካውያን ያደላል ወደምትለው አፍሪካ ኅብረት መመለሷ የዓለም አቀፍ ድጋፍ መሳሳቱን ያመለክታል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ቀድሞ የተጠቀመ፣ ታሪካዊ ተጠቃሚና የኃይል ሚዛንን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ የውኃ ፖሊሲና ሕግ ተመራማሪዎችም ቢሆኑ ፍትሐዊና በእኩልነት ላይ የተመሠረቱ የውኃ አጠቃቀም ላይ እንዳሁኑ ደፍርው ሲጽፉ አይታዩም ነበር፡፡ ለምሳሌ የዛሬ 16 ዓመት አካባቢ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በአውሮፓ በአንዱ ተቋም ስለውኃ ተማሪ ነበር፡፡ በአንድ ትምህርታዊ ፕሮግራም የታወቁ በዓለም ውኃ ፖሊሲና አጠቃቀም ላይ ምርምር የሚያደርጉ ምሁር (ፕሮፌሰር) በጊዜው የተናገሩትን በማስታወስ፣ እ.ኤ.አ. በ2012 (በኢትዮጵያ 2005 ዓ.ም.) ስለናይል ተፋሰስ አገሮች የትብብር ስምምነት ያላቸውን አስተያየት በኢሜይል ጠይቋቸው ነበር፡፡ ፕሮፌሰሯም እ.ኤ.አ. በ2011 የጻፉትን፣ “RECENT CHANGES IN THE NILE  REGION MAY CREATE AN OPPORTUNITY FOR A MORE EQUITABLE SHARING OF THE NILE RIVER WATERSየሚለውን ባለ 385 ገጽ ጹሑፋቸውን ልከውለታል፡፡ የጽሑፉ ይዘት እንደ ርዕሱ ግልጽ ሲሆን፣ ማጠቃለያውም ኢትዮጵያ በተናጠል ግድቡን መጀመሯ፣ የትብብሩ ማዕቀፍ አነሻሽ መሆኗና የፍትሐዊና የእኩል ውኃ ተጠቃሚነት አቀንቃኝ መሆኗ ግብፅና ሱዳን ወንዙን በጋራ እንዲጠቀሙ ጫና እያሳደረባችው እንደሆነ ያትታል፡፡ በእርግጥ ይህ በጣም ከፍተኛ ለውጥና የሥራ ውጤት ነው፡፡ ተመራማሪዋም በወቅቱ አዲስ አበባ ለሥራ እንደመጡ ገልጸዋል፡፡ የሆነ ሆኖ በተፋሰሱ አገሮች የተፈረመው (እየተፈረመ ያለው)  ስምምነትም ሆነ፣ የታላቁ ህዳሴው ግድብ ግንባታ ወደ ኋላ እንደማይቀለበስ ከሚያመላክቱ እውነታዎች መካከል (ይህ ከሰባት ዓመት በፊት የተጻፈው ነው)፡፡

 1. የላይኛው ተፋሰስ አገሮች የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ መምጣት ሕዝባቸውን ለመቀለብ ጫና ውስጥ መግባታቸው (እ.ኤ.አ. በ1995 ከነበረው ከ290 ሚሊዮን የተፋሰሱ አገሮች ሕዝብ የግብፅ ሕዝብ 62.9 ሚሊዮን 21.7 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ በ2025 ከሚጠበቀው 590 ሚሊዮን የተፋሰሱ አገሮች የግብፅ ሕዝብ ወደ 16 በመቶ ዝቅ እንደሚል መጠበቁ)፣ በአንፃሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከ18.9 በመቶ ወደ 22 በመቶ እንደሚያድግ ይጠበቃል፣
 2. የቅኝ ግዛት ሌጋሲ በፍጥነት እየተዳከመ መምጣት፣ እንዲሁም የምዕራባውያን ተፅዕኖ መቀዛቀዝ፣ ብዙ ቅድመ ሁኔታዎች የሚያበዙት የምዕራባውያን የገንዘብ ተቋማት መዳከምና በመጠቃቀምና ድህነትን በመታገል ዙሪያ የሚሠሩ የእስያና የደቡብ ደቡብ አገሮች እየተጠናከሩ መምጣት፣
 3. ዓለም በተለያዩ ርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰብና ኢኪኖሚያዊ የዕድገት ምሰሶዎች እየተመራች መምጣቷ፣
 4.  የአፍሪካ አገሮች ውስጣዊ ሰላማቸውንና ኢኮኖሚያቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጠናከሩ መምጣታቸው፣
 5.  ዓለም ከመቼውም ጊዜ በተሻለ በጋራ፣ በውድድርና በፍትሐዊ አጠቃቀም መርህ እየተመራች መምጣት፣
 6. የአፍሪካውያን የማገዶ እንጨት አጠቃቀም በየጊዜው እያደገ መጥቶ በአሁኑ ወቅት በዓመት 40 ቢሊዮን ቶን መድረሱ፣ የአካባቢ ተቆርቋሪ ድርጅቶችንና የዘርፉን ባለሙያዎች ትኩረት በመሳቡ ሌላ አማራጭ የኃይል ምንጮች (ኃይድሮ ፓወር) እንዲጠቀሙ መገፋፋቱ፣
 7.  የፓን አፍርካኒዝም ስሜት እየጎለበተ መሄድ፣ እንዲሁም ከድንበር መካለል አልፎ የአፍሪካውያንን የሀብት አጠቃቀም ጠፍንጎ የያዘው የቅኝ ግዛት ሕግ ጥያቄ ውስጥ መግባትና ግብፅ ከዚህ አስተሳሰብ በተቃራኒው የመሠለፍ አዝማሚያ፡፡ ለምሳሌ የግብፅ ሚዲያዎች ኢትዮጵያ ከናይል ውኃ አጠቃቀም ጋር የሚኖራትን አረዳድ ኢትየጵያ ኦጋዴንን በተመለከተ ከእንግሊዝ ጋር ከተዋዋለችው የድንበር ውል ጋር ማቆራኘትና የቅኝ ግዛት ውሎችን ዕድሜ ለማራዘም አጠንክሮ የመፍጨርጨር አዝማሚያ፡፡ እንደሚታቀው እንግሊዝ እንደ ቀድሞው ለሰላማችሁ የቅኝ ግዛት ሕጎችን አክብሩ ከማለት ይልቅ፣ በተለያየ ዘዴ ጉዳያችሁን ራሳችሁ ጨርሱ ለችግሮች ሁሉ እኔን አትውቀሱ የማለት አዝማሚያ እያሳየች መምጣቷ፣
 8. የታላቁ ህዳሴ ግድብ የገንዘብ ምንጭ በአገር ውስጥ የሚሸፈን መሆኑ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቁርጠኛ አቋም መያዟ፣
 9. ግድቡ ከሱዳንና ግብፅ ከበረሃ ይልቅ አነስተኛ ትነት ባለበት በኢትዮጵያ መሠራቱ ውኃ መቆጠቡ፣ ለምሳሌ የአስዋን ግድብ የትነት መጠን ከ12 እስከ 14 በመቶ ሲሆን፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከአራት እስከ ስድስት በመቶ እንደሆነ ይገመታል፣ ይህም በቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ በመቆጠቡ ለኢትዮጵያ መስኖ ፕሮጀክቶች ሊበቃ መቻሉ፣
 10.  ዓመቱን ሙሉ የተመጠነ ውኃ ከመፍሰሱ በተጨማሪ ደለል ይቀንስላቸዋል፣

11. ከዚህ ውጪ በጣም የሚገርመው ግብፅ የኤርትራ ጉዳይ በሪፍረንደም እንዲጠናቀቅ    ብዙ እንዳልደከመች ሁሉ የደቡብ ሱዳን ጉዳይ በሪፍረንደም እንዳይወሰን ያልፈነቀለችው ድንጋይ አልነበረም፡፡ የሌላ አገር መፈጠር ሌላ ችግር ከማምጣቱ በተጨማሪ ኢትዮጵያንና ኡጋንዳን በዛ አቅጣጫ እየገባች የመበጥበጥ ዕድሏን ያጠብባታልና፣

12. ከቴክኒካዊ ጉዳዮች አንፃር ግብፅ ውኃውን ከተፋሰሱ አውጥታ በቶሻክ በረሃ ከማልማት በተጨማሪ ከሌሎች ዓረብ አገሮች የውኃ ኪራይ እየሰበሰበች መሆኗ፣

13. ኢትዮጵያ 65 በመቶ ሕዝቧ በጨለማ እየኖረና ከአሥር ሚሊዮን በላይ ሕዝቦቿ በምግብ ዕርዳታ እየተዳደሩ ወደ 18.5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ በየዓመቱ ወደ ሜዲትራኒያን ባህር ይፈሳል፡፡ የግብፅ ሕዝብም ከወንዝ በሚገኝ የኤሌክትሪክ ኃይልና የመጠጥ ውኃ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የሕዝቧን ፍላጎት አሟልታለች፡፡ በመጨረሻም ከለይ ስለተጨራረፈው የኃይል አሠላለፍና ስለመፍትሔዎች ጠቅሼ ጽሑፌን ላጠናቅቅ፡፡

 1. ምዕራባውያን አፍሪካን በተመለከተ ቅድሚያ የሚሰጡት አክራሪነትና ፀጥታ ቢሆኑም፣ እየታየ ያለውን የፓን አፍሪካኒዝም ስሜት ከመጋፈጥ ይልቅ በሚመቻቸው መንገድ እያስታመሙ ሊሄዱ ይችላሉ፡፡
 2. አፍሪካውያን በተለይ ውኃን በተመለከተ የተገቡ የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን በጋራ በግልጽ ከመቃወም አልፈው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡ የኅብረቱ ድርጅትም በውኃ ላይ የተደረጉ ስምምነቶች በቅኝ ገዥዎች ሕግ ሳይሆን፣ በትብብር መንፈስ እንዲወሰኑ በግልጽ ተናግሯል፡፡
 3. የቻይና አቅም መገንባት ቀደም ሲል ፈታኝ ነበረውን የአውሮፓና የአሜሪካ ኮንትራክተርና አማካሪ የማግኘቱ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻለ መጥቷል፡፡
 4. ግብፅም ብትሆን አሁን በአፍሪካ ካለው አሠላለፍ አንፃር የተለመደውን የውክልና ጦርነት ከማጠናከር ውጪ አማራጯ ጠባብ ነው፡፡ የቅኝ ግዛት ውሎችን የሙጥኝ ማለቱ ከአፍሪካውያን ጋር የሚያጋጭ አቋም መሆኑ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ የአሁኑ ግርግር ዋና ዓላማው በተፋሰሱ አካባቢ ሌሎች የታቀዱ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንዳይሆኑ፣ ከተቻለም የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመሙያውን ጊዜ ለማራዘምና ለግብፅ ሕዝብ መንግሥት ጥረት እያደረገ እንዳለ ለማመላከት ይመስላል፡፡ አፍሪካውያንም የኢትዮጵያን መሪነት በአንክሮ እየተጠባበቁ ናቸው፡፡ በእርግጥ ለምን ተደፈርን የሚለው እስከሚለመድ ድረስ የግንኙነቶች መሳናክል እንደሚሆን ይገመታል፡፡
 5. የተፋሰሱ አገሮች ድህነትን ለማሰወገድና የተፈጥሮ ደኖችን ለመጠበቅ የሚደረጉት ጥረትም ሌላው ዓለም አቀፍ ድጋፍ የሚያስገኝላቸው አጀንዳ ነው፡፡ ምዕራባውያንም አካባቢያዊ ሰላምና ልማት የስደተኛውን ቁጥር እንደሚቀንስላቸው ያምናሉ፡፡ ለዚህም ነው መስማማት ካልተቻለ ኢትዮጵያ ግድቡን ባለመሙላት የምታጣውን ገንዘብ እንዴት መካስ እንደሚቻል እያዩት ያለው፣
 6. በመጨረሻም ጉዳዩ ከቁጥጥር ውጪ ቢሆንና ግብፅ ጥቃት ብትፈጽም የሚለው አወያይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በመጀመርያ ግብፆች ራሳቸው የኢትዮጵያን የመከላከያ አቅም አሳንሶ ማየት አደጋ እንዳለው በግልጽ ስብሰባቸው አስጠንቅቀዋል፡፡ ከ1‚000 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዞ የሌላ አገር ግዛት ውስጥ ውጤታማ ጥቃት መፈጸም ቀላል አይሆንም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ጎረቤት አገሮችን እንደ መረማመጃ የመጠቀም ዕድል አናሳ ቢሆንም፣ ይሆናል ቢባልም ውጤቱ ለአገሮቹ ከባድ ዋጋ የሚያስከፍላቸው እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ኢትዮጵያም እ.ኤ.አ. በ2012 ከአልጄዚራ ቴሌቪዥን ለቀረበላት ጥያቄ እንደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ያለ ፕሮጀክት ያለ ጥንቃቄ እንደማይጀመር አሳውቃ ነበር፡፡ ይሆናል ቢባል እንኳ በሰርጎ ገቦች መበጥበጡ የለመድነው ሲሆን የሚጎዳውም ግብፅን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ግን አሁንም ይሁን አንድ ቀን አስዋን ግድብን የመምታት ዕድል ብታገኝ ግብፅ ባለፈው 50 ዓመት የገነባችውን ልማትና ሕዝቧን የሚያጠፋ ነው የሚሆነው፡፡ ለማንኛውም ከጥቃት መልስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጫና በጣም ከፍተኛ ነው የሚሆነው፡፡

ግብፆች ለዘመናት ጠብታ ውኃን በደም ጠብታ እንደሚያስከብሩ ቢናገሩም፣ አሁን ከጠብታ አልፎ በቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውኃ ለድርድር የተቀመጡት ምናልባትም ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ሊሆን ይችላል፡፡

የጋራ ጥቅም ያሸንፋል!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...