በአብዱ ሻሎ
ከኮቪድ 19 መከሰት ወዲህ ዓለም አቀፉን የሚዲያ ትኩረት መሳብ የቻሉ አንዳንድ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ኩነቶች ቢኖሩም፣ ጆርጅ ፍሎይድ የተባለ ጥቁር አሜሪካዊ በነጭ ፖሊስ በሚኒአፖሊስ ጎዳና ላይ ሲገደል የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል በአሜሪካ ብሎም በመላው ዓለም በማኅበራዊ ሚዲያ መሠራጨቱን ተከትሎ፣ በአሜሪካ የተቀሰቀሰውን አመፅ/ተቃውሞ ያህል ትኩረት የሳበ ሰሞነኛ ጉዳይ የለም ማለት ይቻላል። ተቃውሞው በአሜሪካ ሚኒአፖሊስ ቢጀምርም ይህንን ጽሑፍ በመጻፍ ላይ እስከ ነበርኩበት ጊዜ ድረስ ሰባቱንም ክፍለ ዓለማት ማዳረስ ችሎ ነበር፡፡ ከተቃውሞዎቹ በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ፖለቲካና ምጣኔ ሀብት ዙሪያ አንቱታን ያተረፉ ጎምቱ ተመራማሪዎች ስለአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ፣ አገሪቱ አሁን ላይ ለምትገኝበት ቀውስ ገፊ ምክንያቶች፣ ስለአሜሪካ ቀጣይ ዕጣ ፈንታና ምናልባትም ከአሜሪካ በኋላ ሊመጣ ስለሚችለው የዓለም ሥርዓት (Global Order) ሰፋፊ ትንታኔዎችን እያዥጎደጎዱ ይገኛሉ።
አሁን በአሜሪካ የቀጠለው ተቃውሞ ምንም እንኳ የጆርጅ ፍሎይድን በፖሊስ መገደል እንደ ገፊ ወቅታዊ ምክንያት (Immediate Cause) ይጠቀም እንጂ፣ ተቃውሞውን የሚያስተባብሩ አክቲቪስቶች፣ በተቃውሞው ላይ የሚንፀባረቁ መልዕክቶች፣ ብሎም አጠቃላይ የሒደቱ መንፈስ ተቃውሞው ከፍሎይድ ሞት ባሻገር ለረጅም ጊዜ በቆዩ ምናልባትም ከአገሪቱ አጠቃላይ ሥሪት ጋር የተሰናሰሉ ታሪካዊ ተቃርኖዎች፣ በዘረኝነት ላይ በተመሠረቱ የአገረ መንግሥቱ ምሰሶዎች፣ ለዘመናት በሁለቱም ፅንፍ ለሚገኙት (የዴሞክራት/ሊበራልና ሪፐብሊካኑ/ወግ አጥባቂ) የፖለቲካ ልሂቃኖች ቀኖናዊ መሠረት ሆኖ ደሃውን እያደኸየ፣ ለባለሀብቱ ፀጋ የሚጨምረው የኒዮ ሊበራል ፍልስፍና ላይ የተቃጣ ስለመሆኑ አያሌ ማስረጃዎች አሉ፡፡
ከሰሞነኛው የአገሪቱ ውስጣዊ የፖለቲካ ቀውስ በተጨማሪ በውጭ ግንኙነት ዘርፉም አንዲሁ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት በስፋት በሚስተዋልበት መካከለኛው ምሥራቅ፣ በተለይም በአፍጋኒስታን፣ በኢራቅ፣ በሳዑዲና በኢራን አካባቢዎች አገሪቱን ወደ ማፈግፈግ የዳረገ ከፍተኛ ጫና መታየት ከጀመረ የሰነባበተ ሲሆን፣ እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ከመሳሰሉ ትልልቅ ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ጋር ግጭት ውስጥ በመግባቷ፣ በቆየው ተቀባይነቷ ላይ በቀላሉ የማይሽር ጉዳት እያደረሰ ይገኛል፡፡
አሁን ደግሞ የታላቁን ህዳሴ ግድብ በተመለከተ የትራምፕ አስተዳደር በግልጽ ግብፅን ደግፎ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር አንዴ በግምጃ ቤቱ ሌላ ጊዜ ደግሞ በአገሪቱ ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት (National Security Counsel) በኩል የሚያደርገው እንቅስቃሴ ፣ኢትዮጵያዊያን በተለይም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ስለአገሪቱ የውጭ ፖለሲና አካሄድ ቆም ብለው እንዲያሰላስሉ ግድ ብሏል፡፡ ይህ ጽሑፍ “የአገሪቱ የውጭ ግንኙነት አሁን ምን ላይ ይገኛል?”፣ “አሁን እየሆነ ያለው ለምን ሆነ?” እንዲሁም “የነገሮች አዝማሚያ ወዴት ሊያመራ ይችላል?” በሚለው መሠረታዊ የትንታኔ አቅጣጫ (Analytical pattern) በመከተል የተለያዩ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና አጥኚዎችን ዋቢ በማድረግ የአገሪቱን የውጭ ፖሊሲ ለመረዳት በሚደረገው ጥረት ላይ ግብዓት ሊሆን በሚችል ደረጃ ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡
ሁለቱን የሁለተኛው ዓለም ጦርንት አሸናፊዎች (አሜሪካና የቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት) ዳግም ያፋጠጠውና ለሃምሳ አራት ዓመታት የዘለቀው ቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት (በነገራችን ላይ ይህ ዘመን ”ቀዝቃዛ” የነበረው ለሁለቱ ኃያላን አገሮች ይሁን እንጂ እንደ አፍጋኒስታን፣ ኮሪያ፣ ቬትናም፣ ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያና የላቲን አሜሪካ አገሮች ዜጎችን ደም ያጎረፈ የዝሆኖች ፀብ ነበር) በአሜሪካ አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ በድል አድራጊነት ስካር ውስጥ የነበሩት የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ መሀንዲሶች አዲስ ፕሮጀክት ነደፉ፡፡
እ.ኤ.አ. በ1993 የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የነበሩት አንቶኒ ሌክና ሴክሬታሪ ኦፍ ስቴት ዋረን ክሪስቶፈር “Doctrine of Imperial Hegemony” የሚባል የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ቀመሩ፡፡ ይህ ፖሊሲ በፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬጋን የሥልጣን ዘመን ሥሩን ሰዶ እስከ 46ኛው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቢዘልቅም፣ አሁን አሁን ለአሜሪካ የቁልቁለት ጉዞ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳበረከተ ይነገራል፡፡ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ፓትሪክ ፖርተር እንደሚሉት፣ “አሜሪካ ወታደራዊ ጡንቻዋን በማፈርጠም አገሮች የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን እንዳይታጠቁ መከላከል፣ ለዓለም አቀፍ የንግድ ትስስር ማነቆ የሆኑ ግንቦችን ማፈራረስና አሁን ለምትገኝበት (እ.ኤ.አ.1993 መሆኑ ነው) ኃያልነት መነሻ የሆነውን የሊበራል ፖለቲካል ኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለም በዓለም ዙሪያ ማስፋፋት አለባት፤” በሚሉ ሐሳቦች ላይ የሚያጠነጥነው ይህ ፖሊሲ፣ አሜሪካ ከ17 ዓመታት በኋላ አሁን ለምትገኝበት የውጭ ግንኙነት ክሽፈትና የቁልቁለት ጉዞ አስተዋፅኦ አለው፡፡
ፖሊሲው በመጀመሪያ ድንበር አልባ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር በሚደረገው ሒደት አንዱ አካል የሆነው የዓለም የንግድ ድርጅት (WTO) በመፍጠር ምርትና አገልግሎቶች ያለ ማንም ከልካይነት በአባል አገሮች እንዲዘዋወሩ መደረጋቸው፣ ለአሜሪካ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆኑ አገር በቀል ካምፓኒዎች/ኮርፖሬሽኖች ‹‹ርካሽ የሰው ጉልበት ፍለጋ›› በሚል አገሪቱን ለቀው ወደ ቻይናና ሌሎች የእስያ አገሮች እንዲሰደዱ ሲያደርግ፣ በተመሳሳይ በቻይና መንግሥት የሚደጎሙ ቻይናዊያን ካምፓኒዎች የሚያመርቱት ሸቀጥ በአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ የማይደረግላቸውን የአሜሪካውያን ካምፓኒ አቻዎቻቸውን (በተለይ የእርሻ፣ የብረታ ብረት፣ የአሉሚንየምና የቴክኖሎጂ ካምፓኒዎች) በገዛ ሜዳቸው ዘርረው ከውድድር ውጭ አደረጓቸው፡፡ በውጤቱም መካከለኛ ገቢ የነበራቸው የአገሪቱ ላብ አደር ዜጎች ሥራ አጥ ሆነው አየር ላይ ተንሳፈፉ (በነገራችን ላይ አብዛኞቹ የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች እነዚህ ወገኖች፣ ሲሆኑ ፕሬዚዳንቱ ቻይና ላይ በከፈቱት የንግድ ጦርነት ክፉኛ ተዳክመው የነበሩ የብረት፣ የአሉሚንየምና የእርሻ ካምፓኒዎች እንዲያንሰራሩ ለማድረግ ችሏል)፡፡ በሌላ በኩል አሜሪካ ልታስፋፋ ከምትሻው የፖለቲካል ኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለም በተፃራሪ ለቆሙ እንደ ቻይና ያሉ አገሮች ሲሳይ ሆነላቸው፡፡ በአጠቃላይ ከላይ የተመለከትነው ፖሊሲ በኢኮኖሚው ዘርፍ አሜሪካን በሒደት እየገዘገዘ ሲያዳክም፣ ቀደም ሲል ”የምናልባት ጠላት” (Potential Enemies) የነበሩና አሁን ጠላትነታቸው ጎልቶ የወጣ (Actual Enemies) አገሮችን ሲያፈረጥም ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ሌላው የዚህ ፖሊሲ መርዛማ ውጤት እንደሆነ የሚነገረው አሁን አገሪቱ የምትገኝበትና ልታሸነፍ ያልቻለቻቸው የጦርነት አዙሪቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ጦርነቶች በፖሊሲው የተገለጸው “የርዕዮተ ዓለም ማስፋፋት” አጀንዳ ቅጥያዎች ሲሆኑ፣ በቀጥታ ወታደራዊ ዘመቻ (Direct Military Confrontation) እና በእጅ አዙር ጦርነት (Proxy War) የሚካሄዱ ናቸው፡፡ አለፍ አለፍ አደርገን ለመመልከት እንሞክር፡፡
የአፍጋኒስታን ጦርነት
አሜሪካ እ.ኤ.አ. ከ2001 እስከ 2019 በአፍጋኒስታን ታሊባንን ስትዋጋ 2,400 ወታደሮቿን ያጣች ሲሆን፣ 150,000 አፍጋኒስታናዊያን ለሕልፈት ተዳርገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ይህ የተራዘመ ጦርነት የአሜሪካ መንግሥትን ሁለት ትሪሊየን ዶላር ከማስወጣቱ በላይ፣ አፍጋኒስታን እንኳን የሊበራል ዴሞክራሲ አገር ልትሆን ይቅርና አሥራ ስምንት ዓመት የተዋጉትን ታሊባንን በኳታር አደራዳሪነት ዶሃ ላይ ተደራድረው፣ አገሪቱን በመልቀቅ ላይ ናቸው (ተሸንፈን ወጣን ከማለት ይሻላል)፡፡
ሌላው የአገሪቱ የውጭ ግንኙነት ውድቀት እንደሆነ የሚገለጸው በኢራቅ ያለው ሁኔታ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2003 አምባገነኑ የሳዳም ሁሴን መንግሥት ”ጅምላ ጨራሽ የጦር መሣሪያ እያብላላ ስለመሆኑ እርግጠኛ ነን” በማለት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ላይ ጫና በመፍጠር አሜሪካና አጋሮቿ ኢራቅን ወረሩ፡፡ ለወረራው ከተሰጠው ግልጽ ምክንያት ባሻገር ከላይ የተገለጸው የውጭ ጉዳይ ዶክትሪን ለጦርነቱ ገፊ ምክንያት እንደነበረ ብዙዎች ይስማማሉ፣ ኢራቅን ምዕራባዊ/ሊበራል ማድረግ፡፡
ይሁን እንጂ ኢራቅ እንኳን ሊበራል/ምዕራባዊንን የመሰለ አገር ልትሆን እንደ አይኤስኤስና አልቃይዳ የመሳሰሉ የሽብር ቡድኖች መፈንጫ ሆነች፡፡ ይባስ ብሎ የአገሪቱ መንግሥትና ኢኮኖሚ በቀጣናው የአሜሪካን ተፅዕኖ ለመቀልበስ በግልጽ የምትንቀሳቀሰው ኢራን የግል ንብረት ለመሆን በቃ፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰደው እየጨመረ የመጣው የኢራቅ በኢራን የኢኮኖሚ ጥገኝነት ዋነኛው ሲሆን፣ በዚህም እ.ኤ.አ. በ2017/18 የሁለቱ አገሮች የንግድ ልውውጠጥ 13 ቢሊዮን ዶላር ደርሶ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በ2013/14 በኢራን መከላከያ ኃይል ድጋፍ በአያቶላህ ዓሊ አልሰስታኒ ቡራኬ አይኤስን እንዲዋጋ የተመሠረተው ”ሀሽ-አልሻዕቢ” (Popular Mobilization force) በመባል የሚታወቀው ስብስብ በአሜሪካኖች የተፈጠረውን ክፍተት በመሙላት የአገሪቱ ብሄራዊ ጦር አካል ለመሆን በቅቷል።
ከዚሁ ከኢራቅ ሳንወጣ አንድ ሌላ ጉልህ ኩነት ልጥቀስ፡፡ የኢራቅ ፓርላማ ጉዳይ፡፡ እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ 2020 የኢራን የጦር ጄኔራልና በመካከለኛው ምሥራቅ የኢራንን የውክልና ጦርነት በብቃት እየተወጣ የነበረው ጄኔራል ቃሲም ሱሌይማኒ በቀጣናው ከሚገኝ የአሜሪካ የጦር ይዞታ በተተኮሰ ሚሳይል መገደሉ ይፋ ሆነ። ይህንን ተከትሎ በኢራን ከፈጠረው ከፍተኛ ቁጣ በተጨማሪ በኢራቅ ሕዝቡ የአሜሪካን ኤምባሲ ላይ ጥቃት ማድረሱን፣ በትልልቅ ዓለም አቀፋዊ ሚዲያዎች ላይ እጃችንን አፋችን ላይ አድርገን ታዝበናል፡፡ ይባስ ብሎ በጃንዋሪ 5 2020 የኢራቅ ፓርላማ በአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አደል አብዱል ማህዲ መሪነት በኢራቅ የሚገኘው የአሜሪካን ጦር አገሪቱን ለቆ እንዲወጣ የሚያስገድድ ውሳኔ ማፅደቁ ይታወሳል። እነዚህ ኩነቶች አሜሪካኖቹ ከአፍጋኒስታን ቀጥሎ በመካከለኛው ምሥራቅ የተሸነፉበት ሀቅ ማሳያ ሆኖ ይቀርባል።
በሌላ በኩል የአሜሪካ የውጭ ቅርቃር በሳዑዲ ዓረቢያ ይገለጻል፡፡ እንደ መርዋን ቢሻራ ያሉ ከፍተኛ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ሳዑዲ እንደ አገር ስትቆም በሦስት ምሰሶዎች ላይ ሲሆን፣ እነርሱም አንድ በውስጥ በነዳጅ ላይ በተመሠረተ ኢኮኖሚ፣ ሁለት የዘውዱን የሞራልና የሕግ ቅቡልነት (Moral and legal legitmacy) ሳይታክቱ በሚሰብኩ የአገር ውስጥ ሼሆች፣ ሦስት ስርወ መንግሥቱን በውጭ ከማንኛውም የውጭ ጠላት (በተለይም ከኢራን) በጦርና በዲፕሎማሲ እንደሚጠብቋት ቃል በገቡላት ምዕራባዊያን አገሮች ጡንቻ መሆኑ ግልብ እውነታ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይም ከዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች ቀውስና ከየመን ጦርነት መቀስቀስ በኋላ ሦስተኛው ምሰሶ መሰንጠቁ ተስተውሏል፡፡ መቀመጫውን በየመን ሰንዓ ያደረገውና በኢራን የቀጥታ ድጋፍ እንደሚደረግለት የሚታማው የሁቲ ተዋጊ ቡድን እ.ኤ.አ. ሴፕተምበር 14 ቀን 2019 የሳዑዲ ጉሮሮ በሆነው አራምኮ የነዳጅ መሠረተ ልማት ላይ የወሰደውን ጥቃት ተከትሎ፣ አሜሪካና አጋሮቿ በኢራን ላይ ወታደራዊ ዕርምጃ እንዲወሰዱ ሳዑዲ ብትወተውትም፣ በቀጠናው ሊፈጠር የሚችለውን ከባድ ቀውስ በመፍራት ውትወታውን ጆሮ ዳባ ልበስ አሉት፡፡
ኢራን፣ ኢራቅን ወይም ሊቢያን እንዳልሆነች በደንብ ያውቃሉና፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ የኢራን መንግሥት ለዓለማችን ነዳጅ ንግድ ትልቅ ሚና ባለው የፋርስ (ፐርዢያ) ባህረ ሰላጤ በሚተላለፉ መርከቦች ላይ በሚደርሰው ጥቃት ከሚቀርብበት ክስና ዛቻና በቀር የቀጣናው ኃይል ሆኖ ቀጥሏል (የጃፓን፣ የኦማንና እ.ኤ.አ. በሴፕተምበር 2019 በኢራን የታገተው የእንግሊዝ ስቴና ኢምፔሮ የነዳጅ ጫኝ መርከብ ልብ ይሏል)። በዚህም ”የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም” የሚለው የአገራችን ብሂል የገባው የሚመስለው የመሐመድ ቢን ሰልማን መንግሥት ከየመን ጦርነቱ ያፈገፈገቸውን የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስን እግር በመከተል ከኢራን ጋር በድብቅ ድርድር መጀመሩ፣ ብሎም ከኢራን ጋር ያለውን ውጥረት መቀነሱ የምዕራባዊያኑንና አጋሮቻቸው በቀጣናው እየተሸነፉ መምጣትን ከመረዳት የሚመነጭ ሊሆን እንደሚችል ይነገራል፡፡
ወደ ላቲን አሜሪካ የተመለከትን እንደሆነ ከ1950 እስከ 1960ዎቹ መጨረሻ ድረስ በቀጣናው እንደ ልቡ መንግሥት ሲሾምና ሲገለብጥ የነበረው የአሜሪካ መንግሥት፣ እ.ኤ.አ. በ2019 የቬንዙዌላ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ በመንበረ ሥልጣኑ ላይ እያሉ ጁዋን ጉዋይዶ የተባለውን የአገሪቱን ተቃዋሚ ”ፕሬዚዳንት እንደሆነ ዕውቅና ሰጥቻለሁ” ሲል በኋይት ሀውስ ዌብሳይቱ አሳወቀ፡፡ ይሁን እንጂ በኢራን፣ በቻይናና በሩሲያ ጠንካራ ድጋፍ የሚደረግለት ኒኮላስ ማዱሮ ፍንክች ካለማለቱም በላይ ያ እንደፈለጉ የሚሾሙና የሚሽሩበት ዘመን ማክተሙን ቁልጭ አድርጎ አሳየ፡፡
ይህን የተረዳችው የፖለቲካ ተንታኝ ዳንዔላ ፕላክታ በአልጀዚራ ‹‹Bottom Line›› የሚባለው ፕሮግራም ላይ ቀርባ፣ “While our values are good and well placed our capabilities were not! We are much better at winning wars that we are winning peace.” በማለት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ላይ ጠንከር ያለ ትችት መሰንዘሯ መነጋገሪያ ነበር፡፡
ከዓለም አቀፍ ተቋማትና ድርጅቶች ጋር ያለው ግንኙነት
አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የትራምፕ አስተዳደር የውጭ ግንኙነት ወይም ዓለም አቀፋዊ አመለካከት (International outlook) ለመረዳት ለሰውየው የሥልጣን ምንጭ የሆነውን የኅብረተሰብ ክፍልና ፍልስፍናቸውን መመርመር ሒደቱን እንደሚያቀለው ይታመናል።
የትራምፕን ማኅበራዊ መሠረት በተመለከተ እ.ኤ.አ በ2017 ጄፍ ማናዝና ኔድ ክሮውሊ የተባሉ የማኅበራዊ ሳይንስ ተመራማሪዎች “Working Class Hero? Interrogating the Social Bases of the Rise of Donald Trump” በሚል ርዕስ ባስነበቡት ጥናት፣ የትራምፕ ማኅበራዊ መሠረት በአብዛኛው በግሎባላይዜሽንና በኒዮ ሊበራሊዝም መስፋፋት የአገር ውስጥ አኮኖሚ በመዳከሙ ሥራ ያጡ፣ ነጭ አውሮፓዊ የዘር ሀረግ ያላቸው፣ የኢቫንጀሊካን ፕሮቴስታንትና ዕእድሜ ገፋ ያሉ ወግ አጥባቂው የኅብረተሰብ ክፍሎች መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
የዚህ ኅብረተሰብ ክፍል ፖለቲካዊ ሥነ ልቦና አሜሪካ በጥቂት ቢሊየነሮች የተጠለፈች፣ በዴሞክራቶችና በግሎባላይዜሽን አራማጆች ስደተኞችን ወደ አገሪቱ በገፍ በማስገባት ነጩን በአገሩ አናሳና ሥራ አጥ ለማድረግ እየተሴረ እንደሆነ፣ እንደ ተመድ ያሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የአገሪቱን ሉዓላዊነት እየሸረሸሩ መሆኑና አገሪቱ ታላቅነቷን እያጣች ስለመሆኑ እንደ ፎክስ ኒውስ ባሉ ሚዲያዎቻቸው ቀን ከሌት ይናገራሉ፡፡ በዚህ የተነሳ አሜሪካ የተመድ አካል ከሆነው የዓለም የጤና ድርጅት፣ ከኢራን ኑክሌር ስምምነት፣ ከቻይና ንግድ ስምምነቶች፣ ከካናዳና ሜክሲኮ ጋር የገባቸውን የሰሜን አሜሪካ የንግድ ስምምነት (NAFTA)፣ ከሩሲያ ጋር የገቡት የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳይልና የኑክሌር ቅነሳ ስምምነት፣ ብሎም አሜሪካ በኢራቅ የፈጸመችውን የጦር ወንጀል መመርመር ከጀመረው አለም አቀፍ የጦር ወንጀል ፍርድ ቤት ካሉ ዓለም አቀፋዊ ተቋማትና ትብብሮች በተፃራሪ ለመቆም በቅታለች።
በአጠቃላይ የአሜሪካ ወጥ ያልሆነ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ፣ በዓለም አቀፉ መድረክ እየጨመረ የመጣው የአገሪቱ ተዓማኒነት ማጣት፣ በውስጥ ፖለቲካው የሚታየው ፅንፍ የያዘና ሊታረቅ የማይችል ተቃርኖ (በዘርና በርዕዮተ ዓለም)፣ የአዳዲስ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ኃያላን አገሮች እየፈረጠሙ መምጣት፣ የአገሪቱ ሃይማኖት የሆነው ኒዮ ሊበራሊዝም ፖለቲካል ኢኮኖሚ ፍልስፍና መዳከም ለአገሪቱ ኃያልነት ማብቂያ ምልክቶች ተደርገው መወሰድ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡
እናም የአገሬ ህዝብ ሆይ በኪሳራ ቁልቁለት እየተምዘገዘገ ከሚገኝ ፀሐይዋ ከጠለቀችበት አገርና ሥርዓት የምትሰማው ዛቻ ሳይሆን፣ የሲቃ ድምፅ በመሆኑ ከቶውኑ አትረበሽ። የእነሱ ጀምበር ስትጠልቅ የአንተ እየወጣች ነውና ሰላምህን በማጠናከር አንድነትህን ጠብቀህ ወደፊት ገስግስ። ዳይ ወደ ሙሌት!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡