- ለትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የውጭ ዜጎች ዝግ የነበሩ የተወሰኑ የማዕድን መስኮች ተፈቅደዋል
ለግንባታ ዘርፉ የሚያገለግሉ እንደ ጠጠርና ገረጋንቲ ያሉ ግብዓቶችን የማምረት ፈቃድ ለውጭ ዜጎች እንዳይሰጥና የተሰጣቸውም እንዲሰረዝ፣ በዘርፉ ኢትዮጵያውያን ብቻ እንዲሰማሩ በአዋጅ ተወሰነ።
በዚህም መሠረት የተገለጹትን የግንባታ ዘርፍ ግብዓቶች የማምረት ፈቃድ የተሰጣቸው የውጭ ባለሀብቶች ፈቃድ ወይም የተገባ ውል፣ የተሰጠው ፈቃድ ወይም የውል ስምምነት ፀንቶ ለሚቆይበት ቀሪ ጊዜ ብቻ እንዲያገለግል ተወስኗል።
በመሆኑም ለውጭ ባለሀብቶች የተሰጠው የማምረት ፈቃድ እንዲሰረዝ ወይም እንዳይታደስ ተወስኗል።
ይህ ውሳኔ የተላለፈው በማዕድን ሥራዎች አዋጅ ቁጥር 678/2002 ላይ በተደረገው ማሻሻያ ሲሆን፣ ይህንን ሌሎች የማሻሻያ ድንጋጌዎችን የያዘው አዋጅ ባለፈው ሳምንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት ከተካሄደበት በኋላ፣ ወደ ቋሚ ኮሚቴ ሳይመራ በዚያው ዕለት ያለ ተቃውሞ ፀድቋል።
የግንባታ ዘርፉ ግብዓት የሆኑ የድንጋይ ማዕድናት ማለትም እንደ ጠጠር፣ አሸዋ፣ ገረጋንቲና የመሳሰሉትን በማምረትና በማቅረብ የሥራ ዘርፍ ላይ በርከት ያሉ የውጭ፣ በተለይም የቻይና ኩባንያዎች ተሰማርተው እንደሚገኙ ይታወቃል።
የውጭ አገር ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ሲደረግ የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር እንደሚኖር ታሳቢ ተደርጎ ቢሆንም፣ ይህ የሥራ ዘርፍ ግን እጅግ ቀላልና የተወሳሰበ ማምረቻ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም ባለመሆኑ፣ የሚጠበቅ የዕውቀትም ሆነ የቴክኖሎጂ ሽግግር አለመኖሩን የማሻሻያ አዋጁ ማብራሪያ ያስረዳል።
በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን ብቻ የሚሳተፋበት ዘርፍ አድርጎ መንግሥት ከያዘው መካከል የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ፕሮግራም ጋር የሚስማማ እንደሚሆንም ያስረዳል። ውሳኔውም ይህንኑ አመክንዮ መሠረት ያደረገ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ለውጭ ባለሀብቶችና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ክልክል የነበሩ ሌሎች የማዕድን ዘርፍ የሥራ ዓይነቶች እንዲከፈቱ ተወስኖ በማሻሻያ አዋጁ ተካቷል። ከእነዚህም መካከል የማዕድን ቤተ ሙከራ ፈቃድ ለውጭ ኩባንያዎች እንዲሰጥ የሚፈቅደው የማሻሻያ ድንጋጌ ይገኝበታል።