Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከማኅበረሰቡ ጫንቃ በላይ የሆኑ አካሄዶች

ከማኅበረሰቡ ጫንቃ በላይ የሆኑ አካሄዶች

ቀን:

በኢትዮጵያ የሚታዩትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በደም መፍታት ይቻል ይመስል፣ የንፁኃንንም ሆነ የፖለቲከኞችን ደም ማፍሰስ ተለምዷል፡፡ ከቅርብ አራት አሠርታት ወዲህ ያለው እንኳን ሲታይ፣ በደርግ ዘመን በኢሕአፓ፣ በደርግና በተለያዩ የፖለቲካ አመለካከት ባላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት  ታሪክ የማይረሳው ስህተት ተፈጽሟል፡፡

በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ፖለቲከኞችና ንፁኃን ደም እንደ ዋዛ ቀርቷል፡፡ በወቅቱ የተፈጸመው ዕልቂት ግን ለኢትዮጵያ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ዕድገት ይዞ አልመጣም፡፡

በደርግና በኢሕአዴግ በኩል ለ17 ዓመታት የዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነትም አገሪቷን አንኮታኩቷት አልፏል፡፡ በ1983 ዓ.ም. ሥልጣን የተቆጣጠረው ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ የተሻሉ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን ያስመዘገበ ቢሆንም፣ በፖለቲካው ዘንድ ውጣ ውረድ የበዛበት ነበር፡፡ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ የመጡ ለውጦችም ከሙስና የፀዱ አልነበሩም፣ በኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔረሰቦች ቢኖሩም ፍትሐዊ የሀብት አጠቃቀም አልነበረም፣ ሥልጣን ወደ አንድ ወገን ያደላ ነው በሚል በተለያዩ ጊዜያት በተቀናቃኝ ፖለቲካ ፓርቲዎችና በመንግሥት በኩል ፍጭቶች ተከስተዋል፡፡

በየአካባቢው ከፖለቲካው፣ ከኢኮኖሚውና ከማኅበራዊ ችግሮች የሚመነጩ ችግሮችን ለመፍታት የተሄደበት ወደ ኃይል ያደላ መንገድም ሕዝቡ በኢሕአዴግ ላይ ጥያቄ እንዲያነሳ አድርጎታል፡፡

የአገሪቷን ዕድገት ማስቀጠል እንዳለ ሆኖ፣ የማኅበረሰቡን ማኅበራዊ ችግር መፍታትና የፍላጎቱን ያህል ማሟላትም አልተቻለም፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን ችግር ለመፍታት አቅሙ አለን ያሉ ፖለቲከኞች በ1997 ዓ.ም. በተደረገ ምርጫ ተሳትፈው፣ የአብዛኛውን ሕዝብ በተለይ በአዲስ አበባ ይሁንታ አግኝተው የነበረ ቢሆንም፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁኃንን ደም አፍስሶ መና ቀርቷል፡፡

ከዚህ ዓመት በኋላ የነበሩ አካሄዶች በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጭምር ሲወገዝ የነበረና በርካቶችም በእስር የተሰቃዩበት እንደነበር በተለያዩ ጊዜያት የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ በጤናው ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ የታየበት፣ ኢኮኖሚው በሁለት አኃዝ ያደገበት ቢሆንም፣ በየጊዜው የፈሰሰው ደም ለኢትዮጵያ በሚፈለገው መጠን ዕድገትንና ለውጥን ያላመጣ መሆኑን ያመላከተው ከ2009 ዓ.ም. መገባደጃ ጀምሮ በተለይ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ሥፍራዎች የተቀሰቀሰው አመፅ ነበር፡፡ ይህ ክስተት የብዙዎችን ሕይወት ነጥቋል፡፡ በደቡብ ክልል መጣ ሄደት የሚለው ፖለቲካዊም ሆነ ፖለቲካዊ ያልሆነ ግጭት፣ በአማራ ክልል የነበረው ውጥረትና በኋላም ወደ ተቃውሞ መግባት ንፁኃንን ለእስራትና ለሞት የዳረገም ነበር፡፡ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የጠነከረው አመጽ ለመጋቢት 2010 ዓ.ም. ለውጥ ወሳኝ የነበረ ሲሆን፣ በደም መፍሰስ ጭምር የመጣ ነበር፡፡

ከመጋቢት 2010 ዓ.ም. በኋላ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ተስፋ የታየበት ሕዝቡ ልማትን የናፈቀበት እንደነበር በወቅቱ ሕዝቡ ስሜቱን የገለጸበት መንገድ ያመለክታል፡፡  በየክልሉ ያሉ ማኅበረሰቦች በየመድረኩ የቀደመ በደላቸውንና የተፈጸመባቸውን ግፍ የመሰከሩበት፣ መገናኛ ብዙኃንም ጡንቻ ያወጡበትም ነው፡፡

የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የተኩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲንና የልማት ተስፋ ይዘው የመጡ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ ጊዜያት ግጭትና ሐዘን አስተናግዳለች፡፡  

በሰኔ 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን እንኳን ደህና መጡ ለማለት ሕዝቡ መስቀል አደባባይ በተሰበሰበበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመግደል በተቃጣው የቦንብ ጥቃት የንፁኃን ሕይወት ማለፍ፣ በዓመቱ በ2011 ዓ.ም. ሰኔ ወር የመከላከያ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን፣ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አምባቸው መኰንን (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ደም የፈሰሰበት ወቅት ነበር፡፡ 2011 ዓ.ም. ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ግድያ ባለፈም በኦሮሚያ፣ በደቡብና በሶማሌ ክልሎች በተፈጠረ ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቅለው በሰላም ሚኒስቴር አማካይነት ዕርቅ እንዲወርድ ተደርጎ ወደ ቀዬአቸው የተመለሱበት ወቅትም ነው፡፡ ግጭቱ ግን የበርካቶችን ደም ያፈሰሰ፣ ሥነ ልቦና የሰበረና መተማመንን ያመናመነ ሆኗል፡፡

በጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. በፖለቲካ ወትዋቹ አቶ ጃዋር መሐመድ በተጠራ ‹‹የተከብቤያለሁ›› ጥሪ የንፁኃን ደም ፈሷል፡፡ በወቅቱ የአዲስ አበባ መግቢያ መንገዶችን በመዝጋትና ትራንስፖርት በማቋረጥ ሕዝቡ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ቀውስ ውስጥ እንዲገባ ሆኗል፡፡ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተፈጠረ ግጭትም ሰዎች ሞተዋል ንብረት ወድሟል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በወቅቱ በሰጡት መግለጫ፣ በኢትዮጵያ አንዳንድ ቦታዎች በተፈጸመው አንገት የሚያስደፋ ድርጊት 86 ሰዎች ተገድለዋል ብለዋል፡፡

በዚህ መሀል ልማትን ማስቀጠል ከባድ ቢሆንም፣ አዲስ አበባን ማዘመንን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች በተለይ ግብርናው እንዲበለፅግ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ቢሆኑም፣ የሕዝቡን በሰላም ወጥቶ የመግባት ዋስትና የሚሸረሽሩ ሁነቶች መከሰታቸው አልቀረም፡፡

በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውና በኢትዮጵያም ከመጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የታየው የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ ግብፅ የኢትዮጵያን ታላቁ የህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት በመቃወም ያነሳችው የቃላት ጦርነት ኢትዮጵያን ከ2012 ዓ.ም. አጋማሽ ወዲህ የፈተኑ ጉዳዮች ሆነዋል፡፡ ከምርጫው ጋር ተያይዞ የሚነሱ ‹‹ምርጫው መካሄድ አለበት›› የሚሉ አመለካከቶችን ለማስተናገድ አለመቻሉና በአገሪቱ በተከሰተው ኮሮና ምክንያት ለምርጫ መደረግ የነበረበት ዝግጅት በመስተጓጎሉ፣  የምርጫ ቦርድ ምርጫ መፈጸም እንደማይችል ማስታወቁን ያልተቀበሉ ወገኖች መኖራቸው ተጨማሪ ችግር ነው፡፡

በኮቪድ-19 ምክንያት አገሪቱ የከፋ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ እንዳትገባ በተለይ ግብርናው ላይ በማተኮር የምግብ እጥረት እንዳይከሰት እንዲሁም በወረርሽኙ ምክንያት የሚሞቱም ሆነ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ጉልህ እንዳይሆን የሚሠራው ሥራ አገርን በወጠረበት፣ ከህዳሴ ግድቡ ጋር ተያይዞ ግብፅ በዓለም አቀፍ ተቋማት በኩል የምታደርገውን ግብግብ ለማክሸፍ በሚሠራበት ወቅት ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በተተኮሰ ጥይት ሕይወቱ ማለፉን ተከትሎ ሌላ ጫናን ፈጥሯል፡፡

ሰኔ 23 ቀን የድምፃዊው ሃጫሉን አስከሬን ከአዲስ አበባ ወደ ትውልድ ቀዬው አምቦ በተሸኘበት ወቅትና ከዚያም በኋላ በተፈጠረ ግጭት የ87 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች ተቋማት ሲወድሙ፣ በአዲስ አበባ ደግሞ በተለይ በአውራ ጎዳናዎች አካባቢ የሚገኙ ሕንፃዎች መስታወቶች ረግፈዋል፡፡ ከ200 ያላነሱ መኪኖች ተሰባብረዋል፡፡ አዲስ አበባ በተለይ ሰኔ 24 እና 25 ቀን ፀጥ ብላ ውላለች፡፡ ነዋሪው ከቤቱ ለመውጣት ያልፈቀደበት፣ ባለው ሰላም ያልተማመነበትም ነበር፡፡ በየመንገዱ የሕንፃ መስታወቶች ሲረግፉ፣ ሱቆች ሲዘረፉ የመኪና መስታወት በዱላና በድንጋይ ሲሰበርም ሃይ ባይ አልነበረም፡፡

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የአዲስ አበባ ሕዝብ ከሰኔ 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ መደበኛ ሥራው እንዲገባ መመርያ በሰጡበት ወቅት፣ ከዚህ በኋላ አዲስ አበባ ሕገወጥነትን የማትታገስና ሰላሟ የተጠበቀ እንደሚሆን አምርረው መናገራቸው በዕለቱ ሕዝቡ ወደ ሥራው እንዲመለስ አድርጓል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በሰጡት መግለጫም፣ ከዚህ በኋላ በብጥብጥ መቀጠል እንደማይቻል አስረግጠው መናገራቸው፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አዳነች አቤቤ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን አስፈላጊው ፍትሐዊ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ማስታወቃቸው ሕዝቡ ወደ ሰላማዊ ሥራው እንዲመለስ አቅም የፈጠረ ነው፡፡

በተለያዩ ጊዜያት በፖለቲካ አመለካከቶች ምክንያት የተከሰቱ ግጭቶች ለኢትዮጵያ ውድቀት እንጂ ዕድገትን አላመጡም፡፡ በዚህም የተጎዳው መላው ኅብረተሰብ እንጂ ፖለቲከኞች አይደሉም፡፡ ከኅብረተሰቡ ጫንቃ በላይ የሆኑ አማራሪ ድርጊቶችም ተፈጽመዋል፡፡ ችግሮችንና ጥያቄዎችን በሰላም ጥላ ሥር ሆኖ በውይይት መፍታት ቢቸልም በኢትዮጵያ ይህንን መሬት ማስረገጥ አልተቻለም፡፡ የጥላቻ ንግግሩና ጽንፍ የረገጠው የፖለቲካ ሽኩቻ፣ በማኅበረሰቡ ዘልቆ ቂም መፍጠሩን የሚያሳዩ ድርጊቶችም ተፈጽመዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት መፍታት ደግሞ በተለይ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ የኃይል ዕርምጃ የራሱ አስተዋጽኦ ቢኖረውም፣ መሠረታዊ የሆኑ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሳይፈቱ የሚወሰድ የኃይል ዕርምጃ መሠረታዊ ለውጥ እንደማያመጣ በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ ውይይቶች ተነግሯል፡፡  

ከዚህ ቀደም ከሪፖርተር ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት በመቻቻልና አብሮ በመኖር ላይ ጥልቅ አስተያየት የሚሰጡት አቶ መሐመድ ካሳም፣ ግጭቶችን በኃይል ማስቆም ጊዜያዊ መፍትሔ ያመጣ እንደሆን እንጂ ዘላቂነቱን እንደማያረጋግጥ ተናግረው ነበር፡፡

በሚነሱ ግጭቶች ሁሌም የሚጎዱት ላይ ያሉ ፖለቲከኞች ወይም ወትዋቾች ሳይሆኑ፣ ጉዳዩን በጥልቀት እንኳን የማያውቁ ንፁኃን መሆናቸውን በተመለከተም ‹‹የተጎዳነውም እኛ የተጎዳዳነውም እኛ›› የሚሉት አቶ መሐመድ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ጥሞና እንዲመጣ ‹‹የእኔ መንገድ ብቻ ልክ ነው›› የሚለው እንዲወገድ መሥራት እንዳለባቸው መክረዋል፡፡

በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ኅትመት ዳይሬክተር ሩቂያ ሐሰን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በሳይንስም ሆነ በሃይማኖትም አቅጣጫ ቢኬድ የሰው ልጅ 99 በመቶ አንድ ዓይነት መሆኑን እንደሚያሳይ ገልጸው፣ ቅድሚያ ሰው መሆንን ማክበር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ደረጃ ከ80 በላይ ብሔረሰቦች አሉ ቢባልም፣ አንድ ሰው ጠይቆ ካልሆነ ከየትኛው ብሔር እንደተወለደ እንኳን መናገር እንደማይችልና ተመሳሳይነት እንዳለ፣ አሁን በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ችግርም በሰዎች ጭንቅላት ውስጥ አሉታዊ ምልከታ ከመክተት የመጣ፣ የሰዎች አመለካከትና አስተሳሰብ በራሳቸው ምክንያታዊ የመሆን ችሎታ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በተሳሳተ መንገድ ሌሎች ወደ አዕምሯቸው ካስገቡት ጉዳይ የመነጨ ነውም ብለዋል፡፡

በተሳሳተ መንገድ የተማሩትን ግን መልሶ ማውጣትና በመልካም መተካት እንደሚቻል፣ የሚፈጽሙት ድርጊት በውልደት ወይም በተፈጥሮ ያገኙት ሳይሆን፣ ከተማሩት ያገኙት በመሆኑ ይህንን በአዎንታዊ መቀየር ዋናው መፍትሔ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ሰዎች በተቃራኒ የሚያደርጉትን አሉታዊ ተግባር ወደ መልካም መለወጥ፣ ድርጊቱ መተላለቅን እንጂ አገሪቷ ልትፈታቸው የሚገቧትን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካ ችግሮች እንደማይፈታ በትምህርት ማስረጽ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

‹‹ከዚህ ቀደም የተማሩትን የተሳሳተ አካሄድ በማስተማር ማስወጣት ብቻ መፍትሔ ነው፤›› የሚሉት ዶ/ር ሩቂያ፣ መንግሥት፣ ሕዝብና መገኛና ብዙኃን የተሳሳተውን አመለካከት ለመቀልበስ መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

የሰላም ትምህርት (Peace Education) እንደ ኢትዮጵያ ላለ ማኅበረሰብ የሚበጅ በመሆኑም፣ ልጆች ከትምህርት ቤት አንስቶ ስለሰላም እንዲማሩ ማድረግ መፍትሔ ይሆናልም ብለዋል፡፡

በመደበኛ መልኩ በትምህርት እስኪሰጥ ግን መገናኛ ብዙኃን ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስታውሰው፣ ማንም መርጦ ባልሆነው ዘሩ ምክንያት መገደልም ሆነ መገለል እንደሌለበት፣ ሁሉም ዘር ምርጥ መሆኑን ማመንና መቀበል እንዳለበት መክረዋል፡፡

‹‹መቀበል መቻል መላቅ ነው›› የሚሉት ዶ/ር ሩቂያ፣ ታሪካዊ ስህተትና የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚመጣው የሰው ልጅ በትምህርቱ ጫፍ ብቻ ይዞ በምክንያታዊነት መጽናት ከማይችልበት ደረጃ ሲቆም በመሆኑ፣ ይህ በኢትዮጵያ እንዳይመጣ፣ ችግሩ ሳይሰፋና የሚያስቆጭ ደረጃ ሳይደርስ ማረቅ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...