በናታን ዳዊት
አገራችን የምትፈተንበት ነገሮች እየበዙ ነው፡፡ ከሰሞኑ የተመለከትነው እጅግ አስከፊ ተግባር የዜጎችን ስሜት ነክቷል፡፡ ሰዎች ስሜታቸውን በአግባቡ መግለጽ እየቻሉ ለአመፅ መጋበዝ ፈጽሞ ተቀባይነት ያለው ነገር ሊሆን አይችልም፡፡ ኃላፊነት አለባቸው የተባሉ አንዳንድ አካላትም ነገሩን በማባባስ ሲያካሂዱ የነበረው ቅስቀሳ ማን አለብኝነትን ከማሳየቱም በላይ፣ በአገር ላይ ሕግ እንደሌለ ለማሳየት የሞከሩበት ተግባር ነው ማለት ይቻላል፡፡
ባለፉት ቀናት ያየነው ትርምስ ከአሳዛኝነትም በላይ ነው፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አልፈዋል፡፡ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ንብረት ወድሟል፡፡
ይህ ለምን ሆነ ሲባል ይኼ ነው የሚባል አዎንታዊ ምክንያት አይገኝም፡፡ ነገር ግን ከደረሰው ጥፋት አንፃር ሆን ተብሎ የተፈጸመ ዝግጅት ሲደረግበት የነበረ ስለመሆኑም ማሳያ ነው፡፡
ኃላፊነት የሚሰማው ሕዝብ ተቃውሞውንም ሆነ ድጋፉን የሰው ሕይወት እየቀጠፈና ንብረት እያወደመ አይገልጽም፡፡ የሰሞኑ ድርጊት ግን ከዚህ በተለየ የሚታይና በዝምታ ከታለፈም ነገ ከዚህ የከፋ ነገር ሊያስከትል የሚችል መሆኑን ያሳየናል፡፡
የዜጎች ንብረት የአገር ነው፡፡ ሕዝብ የሚገለገልበት ስለሆነም ነገም ለሁላችን የሚያስፈልግ መሆኑ እየታወቀ፣ እንዲህ ባለ ደረጃ ንብረት ለማውደም መነሳትና በጥላቻ ስሜት ሌሎችንም ለመጉዳት መፎከር በምንም መመዘኛ ቢሆን ይቅር ሊባል አይችልም፡፡
በአመፅ ወይም በአቋራጭ ሥልጣን ለመያዝ የሚደረግ ሙከራ ከሆነም፣ አሁንም በምንም መሥፈርት ቢሆን ተቀባይነት ያለው ተግባር አይሆንም፡፡
በ21ኛው ክፍለ ዘመን በዚህ መንገድ መጓዝ ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑ በግልጽ ሊታወቅ ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነት ትርምስ ለመፍጠር ቀን ከሌት የሚሠሩ ወገኖች ይጠፋቸዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡
ነገር ግን ጥቂቶች በሚለኩሱት እሳትና በሚነዙት ጭፍን ፕሮፓጋንዳ የሚቀሰቀሰው ግርግር፣ ብዙኃኑን እየጎዳ በመከራ ያፈሩትንም ንብረት እያወደመ ነው፡፡
የዚህ ተግባር መንስዔው ምንም ይሁን ምን ተቀባይነት የሌለው መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ዜጎች በገዛ አገራቸው ተሳቀው እንዲኖሩ መፈቀድ የለበትም፡፡ ሕግ መከበር አለበት፡፡ እርግጥ በአመዛኙ ከለውጡ ወዲህ ነገሮችን በሰላማዊ መንገድ ለማስኬድ ብዙ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ ችግሮችን በኃይል ከመፍታት ይልቅ በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት የበዙ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ በተደጋጋሚ ነገሮችን በሽምግልና ለመፍታት የተሞከሩ ሙከራዎችንም ዓይተናል፡፡ በዚህ መሀል ግን የሰው ሕይወት ከመጥፋቱና ንብረት ከመውደሙ ባሻገር የሃይማኖት ተቋማት ላይ ጥቃት ደርሷል፡፡
ይህ ሲሆን ዓይቶ እንዳላየ ታልፏል፡፡ ነገሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች ግን በሌላኛው ወገን በመልካም የታዩ ባለመሆናቸው፣ ይኸው እንደ ሰሞኑ ያለ ሌላ ቀውስ ይዘው መጥተዋል፡፡ ግርግሩ ብቻ ሳይሆን የጥላቻ መረጃዎችንም በማከል ሕዝብ በሕዝብ ላይ እንዲነሳ በማድረግ ትልቅ ብጥብጥና ጥፋት እስከመደገስ ተደርሷል፡፡ የሰሞኑ ሁከት ከተከሰተው ጥፋት በላይ ጉዳት ሳያደርስ ረገበ እንጂ፣ እንደ አያያዙ ቢሆን የአገር ህልውናን እስከ መፈታተን ሊደርስ ይችል ነበር፡፡ ስለዚህ በተወሰኑ ቡድኖችና ግለሰቦች በሚያሰሙት አመፅ አገር እየተረበሸች መቀጠል የለባትም፡፡ ዜጎችም ሠርቶ የመኖር መብታቸው መፈተን ስለሌለበት መንግሥት ሕገወጦችን አደብ ሊያስገዛ ይገባል፡፡
የበዛ ትዕግሥትም የሚያስከፍለውን ዋጋ በመገንዘብ ይኖርበታልና ሕግ የማስከበሩን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል ብቻ ሳይሆን እንዲህ ያሉ ድርጊቶች እንዳይደገሙ መተማመኛ መሰጠት አለበት፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን እንዲህ ያሉ ግርግሮች የተፈጠሩበትን ምክንያት በመመርመር ለችግሩ እልባት የመስጠትም ኃላፊነት እንዳለበት መዘንጋት የለበትም፡፡
አገርን የሚያተረማምሱና ዜጎች ላይ ሥጋት የሚችሉ ተግባራት እንዳይደገሙ ከተፈለገም እገሌ ከእገሌ ሳይባል ጥፋተኞች ላይ ዕርምጃ መውሰድ ተገቢነት ላይ መተማመን ግድ ይላል፡፡ ካልሆነ ነገም ተመሳሳይ ችግሮች ይገጥመናልና ሕግ ይከበር፡