- 39 ሺሕ ካሬ ሜትር ቁጥቋጦ ተመንጥሯል
በዚህ ዓመት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተደረገው የተፋጠነ ግንባታ የግድቡ መካከለኛ ክፍል ከፍታ በመጨመሩ፣ በዘንድሮው የክረምት ወቅት በግድቡ ውኃ መያዝ ግዴታ መሆኑ ተጠቆመ።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሆሮ (ኢንጂነር) የግድቡ የውኃ ሙሌትን በተመለከተ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የሚያደርጉት ድርድር ስምምነት ቢደረስበት መልካም መሆኑን ገልጸው፣ ስምምነት ባይደረስም ግድቡ አሁን በሚገኝበት የግንባታ ደረጃ ምክንያት ዘንድሮ ውኃ መያዝ እንደሚቻል ለሪፖርተር አስረድተዋል።
የዓባይ ውኃ ወደ ታችኞቹ የተፋሰስ አገሮች የሚፈስበት የተፈጥሮ መስመር ላይ በተለይ በዚህ ዓመት በተደረገው የተፋጠነ ግንባታ ምክንያት፣ ውኃው የሚወርድበት የግድቡ አካል የግንባታ ከፍታ ከባህር ጠለል በላይ 560 ሜትር በዚህ ሳምንት እንደሚደርስ ገልጸዋል።
ይህ በመሆኑም ወደ ግድቡ የሚመጣው የዓባይ ውኃ ወደ ታች ማለፍ የሚችለው፣ በግድቡ መካከለኛ ክፍል አናት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህም በግንባታ ዲዛይኑ ባህርይ የተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የኃይድሮሎጂ ተመራማሪ ኬቨን ዊለር (ዶ/ር) እና ሌሎች አራት ተመራማሪዎች በጋራ ሆነው “Understanding Risks and Managing Perceptions in the Nile Basin after the Completion of the GERD” በሚል ርዕስ በቅርቡ ይፋ ባደረጉት የህዳሴ ግድቡ ውኃ ሙሌትን የተመለከተ የጥናት ሥራ፣ በመጀመርያው ዓመት ሙሌት ለመያዝ ከታቀደው 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ውስጥ አመዛኙ፣ ከባህር ጠለል 542 ሜትር ከፍታ ላይ ከሚገኙት የተርባይን ውኃ ማስገቢያ በሮች (Lower Turbine Intake Level) በታች መሆኑን ገልጸዋል።
የግድቡ ግንባታ ከጀመረበት 500 ሜትር የባህር ጠለል እና 542 ሜትር ላይ ከተገጠሙት ውኃ ወደ ተርባይን የሚያሳልፉ የታችኛው በሮች መካከል፣ ሦስት ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ እንደሚያዝ ጥናታቸው ይገልጻል።
ይህ ሦስት ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ የሚያርፍበት አካባቢም ‹‹የሙት ዞን›› (Dead Zone) እንደሚባል የገለጹት ባለሙያዎቹ፣ በዚህ አካባቢ የሚያዘው ውኃ ከግድቡ መውጪያ ሌላ መንገድ የሌለው በመሆኑ ‹‹የሙት ዞን›› እንደሚባል አስረድተዋል።
ቅድመ ኃይል የሚያመነጩ ሁለት ተርባይኖች በሙሉ አቅማቸው ኃይል ማመንጨት የሚችሉት፣ ከባህር ጠለል 560 ሜትር ላይ በተገጠሙት የላይኛው የተርባይን ውኃ ማስገቢያ በሮች ውኃ ወደ ተርባይኖቹ ሲወረወር እንደሆነም ጠቁመዋል።
በመሆኑም የመጀመርያው ዓመት የውኃ ሙሌት ተጠናቀቀ የሚባለው ‹‹የሙት ዞን›› በሚባለው አካባቢ ከተኛው የውኃ አካል ከፍታ (ወይም ከባህር ጠለል 542 ሜትር)፣ እስከ 560 ሜትር ድረስ ያለው ቀሪ የግድቡ አካል በውኃ ሲሞላ እንደሆነ ገልጸዋል።
ከ542 ሜትር እስከ 560 ሜትር ድረስ ያለውን ከፍታ ለመሙላት የሚያስፈልገው 1.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ እንደሆነም ጥናታቸው ያስረዳል።
‹‹የሙት ዞን›› ከሚባለው ወይም ከ542 ሜትር ከፍታ በላይ የሚያዘውን ውኃ ማሳለፍ የሚቻለው 542 ሜትር ላይ የሚገኙትን ዝቅተኛ የተርባይን በሮች በመክፈት እንደሆነ የሚገልጸው ይኸው ጥናት፣ ይህንን ማድረግ የሚቻለው ግን ተርባይኖች ካልተገጠሙ ወይም ተርባይኖቹ ተገጥመው ኃይል ለማመንጨት በሚችሉበት ደረጃ ከደረሱ እንደሆነ ገልጸዋል።
ከባለሙያዎቹ ትንታኔ መረዳት የሚቻለውም ከፍተኛ ድርቅ ካልተከሰተ በስተቀር፣ የተገለጸው ሦስት ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ ከግድቡ በየትኛውም ጊዜ መውጣት አይችልም፡፡ ‹‹ሙት ዞን›› የሚለው ስያሜም ከዚሁ የመነጨ ነው።
የግድቡ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክፍሌ (ኢንጂነር) የመጀመርያው ዙር የውኃ ሙሌት ከሚያርፍበት የግድቡ ሥፍራ መካከል፣ 39 ሺሕ ካሬ ሜትር ይዞታ የሚሸፍን ቁጥቋጦ ተመንጥሯል ብለዋል፡፡