የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ለማገዝ ከሰጠው 1.7 ቢሊዮን ብር ውስጥ የተወሰነው፣ የኮሮና ወረርሽኝ ጫናን ለመቋቋም እንዲውል ተወሰነ፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ እያስከተለ ባለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ምክንያት እንቅስቃሴዎች በመቀዛቀዛቸው፣ መንግሥትም ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ያለውን ጥረት አሟጦ እየተጠቀመ በመሆኑ፣ እየገጠመው ያለውን የበጀት ክፍተት ከዓለም ባንክ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ብድር በማዘዋወር መጠቀም እንዲችል ጥያቄ አቅርቧል፡፡
የዓለም ባንክ የሰጠው 1.7 ቢሊዮን ዶላር ብድር ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ትግበራ የሚውል በመሆኑና አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ትግበራ ሊገቡ የማይችሉ ፕሮጀክቶች በቀጣይ ዓመት እንዲከናወኑ በማድረግ፣ አሁን የተያዘላቸው በጀት ተተኪ እንደሚሆን ታሳቢ ሆኖ ለመንግሥት የቀጥታ በጀት ድጋፍ እንዲውል መንግሥት ጥያቄ አቅርቧል፡፡
በዚህ መሠረት 250 ሚሊዮን ዶላር የኮሮና ወረርሽኝ ጫናን ለመዋጋት በቀጥታ በጀት ድጋፍ ወደ መንግሥት ካዝና እንዲዘዋወር ተጠይቆ፣ በገንዘብ ሚኒስቴርና በዓለም ባንክ መካከል ስምምነት ተፈርሟል፡፡
በዚህም መነሻ ስምምነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በመጀመርያ ንባብ እንዲፀድቅ ተደርጓል፡፡ ይህ 250 ሚሊዮን ዶላር ከዚህ ቀደም ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ በብድርና በዕርዳታ ከተገኘው 1.7 ቢሊዮን ዶላር ላይ ተቀናሽ ተደርጎ፣ በአዲስ ዓላማ በበጀት ድጋፍ መልክ በአፋጣኝ በአንድ ዙር ፈሰስ የሚደረግ መሆኑንም የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በዚህ ሁኔታ የዓለም ባንክን ይሁንታ አግኝቶ ከፀደቀው 250 ሚሊዮን ዶላር በተጨማሪ፣ በተመሳሳይ 500 ሚሊዮን ዶላር እንዲዘዋወርለት መንግሥት ጥያቄ ማቅረቡን የገንዘብ ሚኒስቴር ሰሞኑን ገልጿል፡፡