Monday, November 28, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናመንግሥት የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ መኢአድ አሳሰበ

  መንግሥት የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ መኢአድ አሳሰበ

  ቀን:

  ዜጎች በአገራቸው በነፃነት ውለው መግባት ይችሉ ዘንድ መንግሥት አስፈላጊውን የሕግ ማስከበር ሥራ እንዲሠራ በተደጋጋሚ ሲያሳስብ መቆየቱን የገለጸው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የዜጎችን በሰላም የመኖርና የመንቀሳቀስ መብት ከምንጊዜውም በላይ ማስጠበቅ እንዳለበት አሳሰበ፡፡

  መኢአድ ይህን ማሳሰቢያ ያቀረበው ሰኞ ሰኔ 29 ቀን 2012 ዓ.ም.፣ ‹‹መንግሥት የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ሊያረጋግጥ ይገባል›› በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ  ነው፡፡

  መኢአድ በመግለጫው፣ ‹‹መንግሥት ሁልጊዜ ለቅሶ ደራሽ ከመሆን ይልቅ የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት እንዲያረጋግጥና ከማንኛውም ጥቃት እንዲከላከል አጥብቀን እንጠይቃለን፤›› በማለት መንግሥት ዕርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል፡፡

  ከዚህ ጋር በተያያዘ መንግሥት ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ዕርምጃ ሲወስድ ወደ አምባገነንነት ሊቀየር ይችላል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች ስላሉ፣ መኢአድ መንግሥት ዕርምጃ ይውሰድ በማለት ሲጠይቅ እንዲህ ያሉ አስተያየቶችን እንዴት ይመለከታል? በማለት ሪፖርተር ላቀረበው ጥያቄ፣ ‹‹አሁን መኢአድ መንግሥት ዕርምጃ ይውሰድ ሲል ግደል ወይም እሰር ብቻ ማለት ሳይሆን፣ የአገርን ሉዓላዊነትና የዜጎችን ደኅንነትና ሰላም አስጠብቅልኝ ማለት ነው፡፡ ይህ መሠረታዊ የዜጎችና የአገር መብትን የማረጋገጥ ሒደት ውስጥ መንግሥት ዓይን ያወጣ አምባገነን እየሆነ ከመጣ በቀጣይ የምንታገለው ይሆናል፤›› ሲሉ፣ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙሉጌታ አበበ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

  መንግሥትን የዜጎችን ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው በነፃነት የመኖርና ሀብት የማፍራት መብታቸውን እንዲያረጋግጥ ከመጠየቅ ባሻገር፣ ‹‹በሥልጣን ጥማት የሰከሩ፣ የወደቀና የተሸነፈ የፖለቲካ አጀንዳ ያነገቡ ቡድኖች በወሰዱት ዕርምጃ ሕይወታቸውን ላጡና ቤተሰቦቻቸው ለተበተኑ ወገኖች አስቸኳይ ጊዜያዊ መጠለያና አስፈላጊውን ድጋፍ ያድርግ፤›› በማለት መኢአድ ጠይቋል፡፡

  የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ሕልፈተ ሕይወት ተከትሎ በተፈጸሙ ጥቃቶች የተሳተፈ ማንኛውንም አካል መንግሥት የማያዳግም ሕጋዊ ዕርምጃ ወስዶ ለፍርድ እንዲያቀርብም ጠይቋል፡፡

  የድምፃዊው ሕልፈተ ሕይወት ተከትሎ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባና አቶ እስክንድር ነጋ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውና ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ዕለት ፍርድ ቤት መቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ‹‹እስክንድር የተከሰሰበትን ወንጀል ፈጽሟል ብለን አናምንም፤›› ሲሉ አቶ ሙሉጌታ አስታውቀዋል፡፡

  ከወራት በፊት በአቶ እስክንድር ነጋ የሚመራው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) እና መኢአድ ቅንጅት መመሥረታቸው የሚታወስ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የአቶ እስክንድር መታሰር በቅንጅቱ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ምን ሊሆን ይችላል? ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ፣ ‹‹የመሪ መታሰር ተፅዕኖ አይኖረውም ማለት ባይቻልም፣ እስክንድር ስለታሰረ ግን ቅንጅቱ አይቀጠልም ማለት አይደለም፤› ሲሉ አቶ ሙሉጌታ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

  ከዚህ ባለፈ ግን፣ ‹‹በእስክንድር መታሰር የአገሪቱ የዴሞክራሲ ጉዞ ትናንት ወደ ነበረበት እንመለስ ይሆን? እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ሒደቱን ያጨልመዋል የሚል ሥጋት አለን፤›› በማለት፣ እስሩ በሁለቱ ፓርቲዎች አማካይነት ከተመሠረተው ቅንጅት ይልቅ፣ አጠቃላይ የአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሒደት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እንደሚያሠጋቸው አቶ ሙሉጌታ አስታውቀዋል፡፡

  የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ሕይወት ያጠፉትም ሆነ የተባበሩ ቡድኖችም ሆነ ግለሰቦች ጉዳያቸው በአስቸኳይ ተጣርቶ አስተማሪ የሆነ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ፣ ውጤቱም ለሕዝብ ይፋ እንዲሆንና ‹‹ኮሽ ባለ ቁጥር የብሔር የጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙ ቡድኖችና ግለሰቦች እንዲሁም በመገናኛ ብዙኃን ላይ አስፈላጊው ሕጋዊ ዕርምጃ ተወስዶ ለማኅበረሰቡም በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንዲሰጥ፤›› በማለት መኢአድ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...