Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና​​​​​​​በሰሞኑ ሁከት ተጠርጥረው ከታሰሩት መካከል ዋስትና የሚገባቸው እንዲለዩ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አሳሰበ

​​​​​​​በሰሞኑ ሁከት ተጠርጥረው ከታሰሩት መካከል ዋስትና የሚገባቸው እንዲለዩ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አሳሰበ

ቀን:

  • ሁለት ተጠርጣሪዎች ላይ ያልተገባ አያያዝና ድብደባ እንደተፈጸመባቸው እንደገለጹለት አስታውቋል

በድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ሳቢያ ሰሞኑን በተከሰተው ሁከት ተጠርጥረው ከተያዙት መካከል በዋስትና ወይም በምርምራ ውጤት ሊለቀቁ የሚገባቸው በአፋጣኝ እንዲለዩ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መንግሥትን አሳሰበ።

ኮሚሽኑ ይህንን ማሳሰቢያ የሰጠው በድምፃዊው ግድያና ሰሞኑን በተቀሰቀሰው ሁከት ተጠርጥረው በአዲስ አበባ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቁጥጥር ሥር የሚገኙትን ግለሰቦች፣ ባለፈው ሳምንት በአካል ተገኝቶ ከጎበኘ በኋላ ነው።

ተጠርጣሪዎቹን በአካል ተገኝተው የጎበኙት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) እና ሁለት የኮሚሽኑ ከፍተኛ አማካሪዎች የተካተቱበት ቡድን መሆኑን፣ ኮሚሽኑ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ አስታውቋል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያሰማራው ቡድን በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቁጥጥር ሥር የሚገኙትን የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ ፓርቲ አባል አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ሐምዛ ቦረና፣ እንዲሁም የባልደራስ ፓርቲ አመራሮች አቶ እስክንድር ነጋና አቶ ስንታየሁ ቸኮልና ሌሎች 31 ተጠርጣሪዎችን ጎብኝቷል።

አብዛኞቹ ተጠርጣሪዎች በተያዙ በ48 ሰዓት ውስጥ ወደ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን፣ የተጠረጠሩበትንም ጉዳይ የሕግ አስከባሪ አካላት በአፋጣኝ ለማጣራት ጥረት ማድረጋቸውን በመግለጽ ጥረቱን የሚበረታታ እንደሆነ አስታውቋል።

በሌላ በኩል ግን በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል በዋስትና ወይም በምርመራ ውጤት ሊለቀቁ የሚገባቸውን የተያዙ ግለሰቦች፣ በአፋጣኝ መለየት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ኮሚሽኑ አሳስቧል።

ይህንን ማሳሰቢያውን በተመለከተ ከሚመለከታቸው የፍትሕ አስተዳደር አካላት ጋር መወያየቱን የገለጸው ኮሚሽኑ፣ የተሰጠውን ምክረ ሐሳብ በጥንቃቄ እንደሚያጤኑት የሚገልጽ ምላሽ እንዳገኘም አስረድቷል።

ኮሚሽኑ ተጠርጣሪዎቹን በአካል ተገኝቶ ባነጋገረበት ወቅት ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ ጥሰት እንደተፈጸመባቸው እንደገለጹለት በመጥቀስ፣ ድርጊቱ ትክክል እንዳልሆነ አስታውቋል።

ጥሰት እንደተፈጸመባቸው ለኮሚሽኑ ቡድን የገለጹት ተጠርጣሪዎች አቶ እስክንድር ነጋና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ባልደረባ አቶ ሸምሰዲን ጠሃ መሆናቸውን፣ የኮሚሽኑ መግለጫ ያመለክታል።

እነዚህ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር በዋሉበት ወቅት ተገቢ ያልሆነ አያያዝና ድብደባ በፖሊስ እንደተፈጸመባቸው ለኮሚሽኑ ባለሙያዎች የገለጹ መሆኑን፣ ኮሚሽኑም ስለሁኔታው ከፖሊስ ማብራሪያ ጠይቆ ምላሽ ማግኘቱን ጠቁሟል።

ከፖሊስ የተሰጠው ማብራሪያ በተለይ አቶ እስክንድር ነጋ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ በሚደረግበት ወቅት፣ በግለሰቡና ትዕዛዙን በሚያስፈጽሙ የፖሊስ አባላት መካከል መጠነኛ ፍጥጫና የኃይለ ቃል ልውውጥ እንደነበር የሚገልጽ እንደሆነ ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ይሁን እንጂ ፖሊስ የሰጠው ማብራሪያ ከሰብዓዊ መብት አያያዝ አኳያ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የኮሚሽኑ መግለጫ ያመለክታል።
‹‹ምንም እንኳን በፖሊስና በቁጥጥር ሥር እንዲውል በሚደረግ ተጠርጣሪ መካከል አለመግባባት ሊፈጠር እንደሚችል ቢታወቅም፣ ሁልጊዜም የፖሊስ ተግባር በተሟላ የሙያ ሥነ ምግባርና ሰብዓዊ መብቶችን በማክበር ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል፤›› ሲል ኮሚሽኑ በመግለጫው አመልክቷል።

በመሆኑም በሁለቱ ግለሰቦች ላይ ተፈጽሟል ስለተባለው ያልተገባ አያያዝ ፖሊስ ተገቢውን ማጣራት በማድረግ፣ እንዳስፈላጊነቱ ዕርምጃ እንዲወሰድ ኮሚሽኑ ምክረ ሐሳብ መስጠቱን ገልጿል።

ጥሰት እንደተፈጸመባቸው የገለጹት ሁለቱ ተጠርጣሪዎች፣ ጤንነታቸውና አካላዊ ደኅንነታቸው በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ጉብኝቱን ያካሄደው ቡድን እንደተመለከተ ኮሚሽኑ አስታውቋል።

በሌላ በኩል ቡድኑ የጎበኛቸው አብዛኞቹ በቁጥጥር ሥር የሚገኙ ተጠርጣሪዎች በአፋጣኝ ከቤተሰብ መገናኘት እንዳልቻሉና ስልክም ለመደወል ዕድል እንዳላገኙ፣ በዚህ ምክንያትም ምግብና ልብስ ከቤተሰብ ማግኘት እንዳልቻሉ የሚገልጽ ቅሬታ ማቅረባቸውን ኮሚሽኑ በመግለጫው ገልጿል።

ይህንን አስመልክቶ ከፖሊስና ከሌሎች የበላይ አመራሮች ጋር መነጋገሩን የገለጸው ኮሚሽኑ፣ የምግብና ልብስ አቅርቦት ችግር የመነጨው የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና መመርያዎች ምክንያት እንደሆነ መገንዘቡን አስረድቷል።

ይሁን እንጂ ጉዳዩን በተመለከተ በፖሊስ ጣቢያውና በሌሎች የበላይ አመራሮች የተባለው ችግር በአፋጣኝ መፍትሔ እንደሚያገኝና እንደሚሻሻል፣ በዚህ መሠረት ለሁሉም ታሳሪዎች ምግብና ልብስ ከቤተሰቦቻቸው እንዲቀርብ እንደሚደረግ እንደተገለጸለት ኮሚሽኑ በመግለጫው አመልክቷል።

የተወሰኑ ታሳሪዎች ያቀረቡት የሕክምና ጥያቄ ክትትል እንደሚደረግበት፣ እንዲሁም ከጠበቆቻቸው መገናኘት ለሚፈልጉ ተጠርጣሪዎች ተገቢው ሁኔታ እንደሚመቻችላቸው ፖሊስ እንዳረጋገጠለት ኮሚሽኑ ገልጿል።

ከላይ ለተገለጹት ምክረ ሐሳቦች አፈጻጸምና ተጠርጣሪዎች ላቀረቧቸው ቅሬታዎች ማስተካከያ መፍትሔ መደረጉን፣ ኮሚሽኑ እንደሚከታተል አስታውቋል።

በማከልም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በተመሳሳይ ጉዳይ እንደታሰሩ የተገለጹትን ከአንድ ሺሕ በላይ ተጠርጣሪዎች የድምፃዊ ሃጫሉ ግድያን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ከፍተኛ ሁከት የሰብዓዊ መብት ጥሰት መከሰቱ እንደሚመረምር ኮሚሽኑ በመግለጫው አረጋግጧል።

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...