በአሰፋ አደፍርስ
ሰላምን የሚሻ ሰላም አያደፈርስም። ከአንዱ ቢጣሉ ሁሉን ማስቀየምም አያሻም። ሰሞኑን በአንድ የብዙኃን መገናኛ የተመለከትኩት የአቶ ሥዩም መስፍን ቃለ መጠይቅ አስገርሞኝ ነው። አቶ ሥዩም የሚናገሩትና የሚያቀርቡት አስተያየትም ሆነ ገለጻ የሚያቀራርብ ሳይሆን፣ እጅግ የሚያራርቅና የሚያለያይ ስለሆነ የታሪክ ምሁር ባልሆንም የእሳቸውን ያህል ዕውቀት አላጣም፡፡ እንዲያው ለማለያየት የሚያደርጉትን ዘመቻ ገታ ቢያደርጉት ይሻላል በማለት፣ ይህችን ማስታወሻ እንዲያነቡና ወደ ልቦናቸው እንዲመለሱ ነው። በመጀመርያ አቶ ጌታቸው ረዳ የተባሉ ፖለቲከኛ ንግግራቸው ኃይለ ቃል የታከለበትም ቢሆንም ግን ጥፋተኛ ነን፣ ለዚሁም ይቅርታ ጠይቀናል በማለት የሕዝቡን ይቅርታ ስለሚጠይቁ አዳማጭም ይቅር ባይም ሊያገኙ ይችሉ ይሆናል፡፡ ግን እሳቸውም ቢሆኑ በግልጽ ጥፋታችን ይህ ነው፣ ወይም የእነዚያ ነው ሳይሉ እንደ ምሳሌ ስለሚናገሩ እርግጠኛውን ለማወቅ ቢያስቸግርም ለሽምግልና መንገድ የከፈቱ ይመስላል።
የአቶ ሥዩም ግን ‹‹የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን. . .›› ዓይነት አዝማሚያ የያዘ ስለያዘ፣ አሁን በአንድ ዘር ላይ የቂም በቀል ያላቸውና ትንሽ ዕድል አግኝቼ ባሳየኋቸው የሚሉ ይመስላል። ይህ ደግሞ የበለጠው ጉድጓድ ይቆፍር እንደሆን እንጂ ሰላምን የሚያመጣ አይመስልም፡፡ ቁጭትና ብሶትን ከመግለጽ ይልቅ ወደ አስማሚነት የሚያዳላ አቀራረብ ቢመርጡ የተሻለ በሆነ ነበር። አሁንም አልዘገየም። በዓብይና በእነሱ መካከል ያለውን ልዩነት ለመግለጽ ሲሉ መላውን ኅብረተሰብ እያስቀየሙ ነው። ባለፈው በእነሱ አገዛዝ ዘመን ሁሉ የተደሰተና ግሩም የሆነ አስተዳደር እንደነበር አድርገው ሲያሽሞነሙኑት፣ የነበረ ምን ይል ይሆን የሚለውን ጥያቄ ውስጥ አላስገቡም። ይህ ደግሞ የሰውን የማስታወስ ችሎታ የመናቅ ያህል እንዳያስቆጥራቸው ቢያስቡበት መልካም በሆነ ነበር፡፡
ነገር ግን ሁሌም ‹‹መበደሉን ወታደር በድሏል፣ ግን ገበሬ ይካስ›› ዓይነት ሆነና በትዝብት የሚታለፍ ሳይሆን፣ መልስ ሊሰጠው ይገባል በሚል ነው የተነሳሳሁት። ነገሩ ጠያቂውም እንደ ጋዜጠኛ ሳይሆን፣ የእሳቸውን ብሶት እንዲናገሩ የተመቻቸ ይመስላል፡፡ ይህ ደግሞ የባሰውን እምነት ያሳጣልና በትክክል የጋዜጠኝነት ሙያ የተካነ ጋዜጠኛ ጋር ቢያደርጉ ከስህተቱ ወደ ፍሬ ነገሩ በመራቸው ነበር። ለመሆኑ ይህ ሁሉ ግርግር ለምን ይሆን? በአስተዳደሩ የማይስማሙ ከሆነና የመምከርም ዕድል ከነበራቸው ጠንከር ብለው ይህ አልሆነም፣ ይህ አያዋጣም ብለው መከራከርና መስመር ማስያዝ ሲችሉ ለማን ይድላው ብለው ነው ለቀው የወጡት? ይህ ነው ታዲያ የታላቅ አገር መሪ የሚያደርጋቸው? በእጃቸው የያዙትን ለቀው ዳር ቁጭ ብለው ልክ እንደ እኔ ተመልካችነትን ለምን መረጡ? ይህ ነው ታዲያ ታላቅ ፖለቲከኛ የሚያደርጋቸው? ያስቡበት፡፡ ምናልባትም ተመልሰው ለቦታው ከበቁ ከጥፋታቸው ተምረው ሌላውንም ያስተምራሉና!
ስለአቶ ስመኘው በቀለ (ኢንጂነር እንዳልላቸው በጣሊያንና በእንግሊዝ አገር ሊስትሮ ሁሉ እንጂነር ስለሚባል እንደዚያ እንዳይሆን ብዬ ነው) እጅግ አድርገው ያዘኑ ይመስላሉ፡፡ ገዳዩንም የማወቅ አዝማሚያ ያሳያሉ፡፡ ታዲያ ምነው ወዲያውኑ በጉዳዩ ላይ ተከታታይ ምርመራ አድርገው የዚህ የንፁህ ሰው ደም በከንቱ ፈሰሰ ብለው አልተነሳሱ? ይህንን የመሰለ ጉዳይ ወራት አይደለም ቀናትም መውሰድ አያሻም ነበር፡፡ ግን የቁጭት መወጫ ያደረጉት ስለሚመስል አሁኑኑ ይህ ጉዳይ የሚጣራበትን መንገድ ቢመሩ፣ በእውነት ተቆርቋሪነታቸውን ያስመሰክራሉና ሳይውሉ ሳያድሩ ይህ ጉዳይ እንዲጣራ መንገድ መንገዱን ያሳዩ።
ስለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መዳከምና ዋጋ ቢስነት ተናግረዋል፡፡ እርሳቸው በቀጥታ ከጫካ መጥተው ነው እዚያ መሪ የሆኑት፡፡ ቀጥሎ የነበሩት ግን ቢያንስ የሥራ ልምድም ከሕዝብ የመገናኘትም ተሞክሮ ነበራቸውና እንዴት ከጫካ መጥተው የያዙትን ቢሮ ሌሎቹ ሊይዙ አልቻሉም? ወይስ ከእኔ ጀምሮ ማለታቸው ይሆን? ይህ ግልጽ ቢደረግ መልካም ቸውነው፡፡ አዎን የውጭ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም እሳቸውና ፓርቲያች አዳክመው ለደካማ አሳልፈው መሄዳቸውን ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው። አቶ ሥዩም መስፍን ብዙ ነገር እየቆሰቆሱ ነው። የአንድ ዘር ጥላቻቸውን በተዘዋዋሪ መንገድ ለመግለጽ የፈለጉ እንደሆነ በግልጽ ይታያል። ይህ ለማንም አይበጅም፡፡
አሁን ባለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ወደ አንድነት መጥተን አገራችንን በቴክኖሎጂ፣ በኢንዱስትሪና በመገናኛ ዘዴዎች ወደፊት አስቀድመን ሌሎች ቢያንስ አንግሊዞች በ17ኛውና በ18ኛው ከፍለ ዘመን ወደ ደረሱበት እንድረስ፡፡ በዘርና በሃይማኖት መለያየት የሞኞችና የደንናቀሩት ሥራ ነው ብለው ወደ አንድነት ከመምጣት ይልቅ፣ እሳሳቸውና ጓዶቻቸው የፈጸሙት ስብጥርጥር ሁኔታ ያደረሰብንን፣ የቁልቁለት መንገድ ይሆን የተራቀቀና የተስተካከለ አስመስለው የሚያወሩን? ስለኤርትራ ያነሱት ጉዳይ በጣም የሚያሳፍርና ትንሽ ፊደል የቆጠረን ኢትዮጵያዊ አይደለም ጣሊያንንም ሳያስቆጣ አይቀርምና ከእንዲህ ዓይነት አሉባልታ ቢታቀቡ ይሻል ነበር፡፡ ግን ምንትስ ያለ ምንትስ ሳያደርግ አይቀርም እንዲሉ አንዴ ከገባሁበት ብለው የጥፋቱን መንገድ ከመከተል፣ እንደ አቶ ጌታቸው ረዳ ጥፋትን አምኖ ወደ ዕርቅ መምጣቱ የተሻለ ይሆናልና ያስቡበት።
ለመሆኑ የውጫሌ ውል መፍረሱን ያውቁ ይሆን? የውጫሌ ውልማ ፈርሶ ታላቁን የዓድዋን ጦርነት ፈጥሮ ኢትዮጵያንም ለመጀመሪያ ጊዜ ከእስያ፣ ከእነ ደቡብ አሜሪካ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅና ከመላው አፍሪካ አኅጉራት ለይቶ ከታላላቅና ከኃያላን መንግሥታት ጎን አሠለፋት፡፡ ይህም ለመሪዋ ታላቅነት በተሰጠው ክብር ምክንያት ለሉዚያና ግዥ (Louisiana Purchase) በአሜሪካን መገዛት ምክንያት ንጉሠ ነገሥቱ የደስታው ተካፋይ ሆነው መጋበዛቸው፣ ለመላው አፍሪካ የሰጠው ክብር ለመሆኑ አንብበውት ይሆን? ንጉሡ ግን ሊገኙ አልቻሉም፣ በነበረው ሁኔታ። ኤርትራን በውጫሌ ውል ነው ያስወሰዱት ብለው አፄ ምኒልክን ለመውቀስ ለመሆኑ ታሪኩን ያውቁታል? ወይስ በደመነፍስ ነው? ኤርትራን ለጣሊያን ያስረከበ ማነው ብለው ጠይቀው ያውቃሉ? ወይስ ከጥላቻ የተነሳ ይሆን? ትዝብት ውስጥ አንግባ፡፡
በዘመናችን ጥሩ ጥሩውን ሠርተን ለመጪው ትውልድ ትተን ማለፍ ብቻ ሳይሆን፣ የአገራችንን የመቶ ዓመታት ሳይሆን የሦስት ሺህ ዘመናትን ታሪክ አጉልተን ብናልፍ የተሻላ ይሆናልና ወደ ልቦናችሁ ተመለሱ። አንድ ጊዜ ተመረጠም አልተመረጠ የመንግሥትን ሥልጣን ይዞ በሕገ መንግሥት ሥር ከተገኘ፣ በትክክለኛው መንገድ እስኪወርድ ድረስ ባለው ሕገ መንግሥት መገዛት የአንድ ሕዝብ ግዴታ መሆን አለበት። ይህም ማለት ያ በቦታው ላይ የተቀመጠ ሰው አይወርድም ማለት ሳይሆን፣ ሕገ መንግሥቱ በትክክል መጠበቅ ይኖርበታል ማለት ነው።
ዛሬ እርስዎና ፓርቲዎ የምታደርጉት ነገር አገርን የማፍረስ እንጂ የመገንባት ስለማይመስል ያስቡበት። አገር የጋራ መሆኑንም ልቦናችሁ ውስጥ አስቀምጡት፡፡ ያለበለዚያ ሁሌ የሚቀናችሁ መስሏችሁ አትታለሉ። ታላቋን ትግራይን ለማሳነስ አትሞክሩ፡፡ ጥንት የነበረውን ትተን በአዲሱ ዘመን የፖለቲካ አስተሳሰብ ፈር ይዘን፣ ሁሉን አክብረንና ተከብረን ለማስተዳደር ብንሞክር የተሻለ ይሆናል እንጂ ወገንን ከወገን ለማለያየት ባንሯሯጥ ያስከብረናል። ክቡር አምባሳደርንና ጓዶችዎን የምለምነው ኢትዮጵያን ለመገንባት ልክ እንደ እነ ቴዎድሮስ፣ ዮሐንስ ባይወዷቸውም፣ እንደ ምኒልክ ለታላቅነት እንሽቀዳደም እንጂ አገር በቀዬ ለመከፋፈል አንሞክር!!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡