Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገር​​​​​​​ኢትዮጵያዊያን የሥርዓተ አልበኞች ሰለባ መሆናቸው ይብቃ!

​​​​​​​ኢትዮጵያዊያን የሥርዓተ አልበኞች ሰለባ መሆናቸው ይብቃ!

ቀን:

በሰይፈ ሚካኤል ክፍሌ

አገር እንደገና አስጨናቂና አስፈሪ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች፡፡ በተደጋጋሚ ያጋጠሙ ዕልቂቶችና ውድመቶች በዚህ ከቀጠሉ፣ እንደ አገር ለመቀጠል የማንችልበት አዘቅት ውስጥ መግባታችን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንን በገዛ አገራቸው መግደልና ማፈናቀል ሳይበቃ፣ አገር ለማፍረስ የሚደረገው ሴራ ሥሩ መታወቅ አለበት፡፡ ለዛሬ ግን በተወሰኑ አንኳርና ወቅታዊ ችግሮች ላይ አንዳንድ ነጥቦችን በማንሳት፣ በአገራችን የተጀመረው ሁለንተናዊ ለውጥ የሚጎለብትበትን መንገድ በማመላከት እንቅፋቶችን ቀድሞ መለየትና መጥረግ ወሳኝ ዕርምጃ መሆኑ ሊዘነጋ እንደማይገባ ማሳሰቢያ ለመስጠት እፈልጋለሁ፡፡ በእርግጥ ችግሮቻችን ለዘመናት የተጠራቀሙ እንደ መሆናቸው፣ ሁሉንም ጉዳዮች በአንድ ጊዜ ጠራርጎ ማፅዳት ሊያዳግት ይችላል፡፡ ነገር ግን መነጋገርና መደማመጥ፣ ብሎም በሐሳብ ልዕልና መተማመን ከተጀመረ የማይፈታ ችግር፣ የማይደረስበት ግብ የለምና ቀናውን መንፈስ ይዞ መገስገስ ተገቢ ነው፡፡ ለሁሉም  ጉዳዮቹን አንድ በአንድ እንመልከታቸው፡፡

በዘር ፖለቲካ ከመጦዝ መውጣት

- Advertisement -

በኢትዮጵያ ዘረኝነትና ጠባብነትን ፊት ለፊት ከመዋጋትና በሥርዓት ደረጃም ፈጣን ማስተካከያ እንዲያገኝ ከማድረግ ውጪ አማራጭ የለም፡፡ በእርግጥ የኢሕአዴግ የአራት አሥርት ዓመታት ጉዞ ከመደብ ይልቅ በብሔር የመብት ጥያቄ ላይ ተጠንስሶ፣ በልዩነት መዘውርና በነጣጣይ ፖለቲካ ተረግዞ የወለደልን ጽንፈኛ ብሔርተኝነትን፣ የፖለቲካ ጥላቻና መገፋፋትን  መሆኑ ተደጋግሞ የተነገረ ነው፡፡  ያም  ሆኖ አገሪቱ  ይነስም ይብዛም በኢኮኖሚ ለውጥ ውስጥ በመቆየቷ፣ ቁርሾውና የብሔር ግጭቱ የመዳፈን ሁኔታ ታይቶበት ነበር፡፡ አሁን ግን ሕወሓት/ኢሕአዴግ ይባል በነበረው ድርጅት ውስጥ በበቀለ መርዝ ምክንያት በአመድ የተዳፈነው የዘረኝነትና የጥላቻ እሳት ተንቀልቅሏል፡፡ ሰደድና ቋያ እየሆነም አገር ማጋየት ጀምሯል፡፡

አሁን ማን ይሙት የብሔር ፌዴራሊዝም አዋጭና ዘላቂ የአገር አንድነት የሚያስከብርና የኖረውን የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የፖለቲካ ጥያቄ የሚፈታ ቢሆን “ተለወጥን!” እያልን፣ ይኼን ያህል አገራዊ ትርምስ ይታይ ነበር? እስኪ በጥሞና እናጢነው፡፡ ችግሩ የተዘራው በ27 ዓመታት አገዛዝ ቢሆንም፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ምናልባት ከትግራይ ክልል በስተቀር (እዚያም ቢሆን ጥብቅ አፈናና የአንድ ብሔር መሰባሰብ ስላለ) ግጭት፣ መፈናቀልና ግድያ ያልተስተዋለበት ክልል የት አለ? ሁሉም እንደሚያስታውሰው፣ ቀውሱ ሲጀመር በየክልሉ “መጤ“ የተባለው የሌላ አካባቢ ወገን መግቢያ መውጫ እስኪያጣ ተሳደደ፡፡ ባለሀብቱ ጭምር በነውጥና በሥርዓት ተቃውሞ ስም ብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ እንዲገባ ተደረገ፡፡ ሲቀጥል በክልል ደረጃ ኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ተፋጠጡ፣ ብዙዎች ሞቱ፣ ቆሰሉ፡፡ አልፎ ተርፎ በሚሊዮኖች ለመፈናቀልና ለመበተን ተዳረጉ፡፡ በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች የሆነውንም ቢሆን የምናስታውሰው ነው፡፡

በትግራይና በአማራ ክልሎች መሀል ከመለስተኛ ግጭቶችና ውዝግቦች ባሻገር የተረገዘው ፍጥጫ ለትውልድም የሚሻገር እየመሰለ ነው፡፡ በተለይ የወልቃይትና የራያ የማንነትም ይባል የመሬት ጥያቄ ዜጎች በቀላሉ የሚስማሙበት እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው፡፡ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች መካከልም የይገባኛል ውዝግብ ግጭት አስነስቶ ዓይተናል፡፡ በመሀል አገር አዲስ አበባ/ፊንፊኔ ዋነኛው የዘር ፖለቲካ መፋጠጫ እንዲሆን የሚሹ ኃይሎችም አሉ፡፡ የዘር ፖለቲካ የወለደው መካረርና የመስገብገብ ዛር ከክልል ወደ ዞን ቢወረድም ተመሳሳይ ነው፡፡ ይኼው ችግር ዛሬ የሲዳማና የወላይታን ሕዝቦች በአንድ ማዕድ እንዳይበሉ እያደረገ ነው፡፡ እንኳንስ ለእነሱ ለሁላችንም ቢሆን የጋራ ከተማችን መሆን የሚገባትና የምትቸለው ሐዋሳ ከተማ ውስጥ በነፃነት የሚኖሩ ዜጎች (ሌላው ቀርቶ የደቡብ ክልል ተወላጆች) ቁጥር ተመናምኗል፡፡ ‹‹የራሳችንን ክልል፣ ልዩ ዞን፣ ወረዳ. . .›› እንመሠርታለን የሚሉ የክልሉ ብሔረሰቦች፣ ገና ከወዲሁ የእርስ በርስ ግጭት እንደሚከሰትባቸው መረዳት አያዳግትም፡፡

“ትንሿ ኢትዮጵያ!!”  እያልን ስንሸነጋገልባት የቆየችው ደቡብ ክልል ሰሚ ያላገኙ በርካታ ግጭቶች፣ መፈናቀሎችና ሞቶችን ያስተናገደች መሆኗን መካድ ከቀውስ ለመውጣት አለመዘጋጀት ነው፡፡ ሌላው ቢቀር በአንድ ዞንና ወረዳ ውስጥ የሚኖሩ የተለያዩ ብሔረሰቦች በምን ያህል ፍጥጫ ውስጥ እንዳሉ፣ በደቡብ ምዕራብ የሚገኙ የደቡብ ክልል ሕዝቦችን ነባራዊ ሁኔታ መፈተሽ ብቻ በቂ ነው፡፡ ግጭቱ በአንድ መንደር እየኖረ፣ “እኔ የራሴ ማንነት አለኝ/የለህም” የሚለውንም እያባላው ነው፡፡ እውነት ለመናገር ለበርካታ መቶ ዓመታትና ለዘመናት አብሮ ከመኖር አልፎ በአንድ ዓይነት ታሪክና ማንነት ውስጥ የዘለቀው፣ ከመጋባትና ከመዋለድ በላይ መከራና ሐዘኑን ለዘመናት በጋራ ሲያራምድ የኖረው የጎንደር/ቅማንት ሕዝብ እንዲህ ጦር እየተማዘዘ ይገዳደላል ብሎ የሚገምት ማን ነበር? ጠባብ ብሔርተኝነትና የጎሳ ፌዴራሊዝም ውጤቱ ይኼው ነው፡፡ ሥልጣንን፣ ሀብትንም ሆነ ሁለንተናዊውን ማኅበራዊ መስተጋብር በዘርና በማንነት መነጽር ብቻ የመመልከቱ አዙሪት ፍፃሜው  አደጋ መሆኑን፣ በርካታ የዓለም አገሮችም በምሳሌነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ መካረሩ ሲሰፋ ደግሞ በእጅጉ አውዳሚና አጥፊ መሆኑን ለመናገር ነብይ መሆን አይጠይቅም፡፡

ስለሆነም በዴሞክራሲ ምኅዳር መስፋት፣ በሰብዓዊና በዴሞክራሲያዊ መብት መከበር፣ በአገር ገጽታ መሻሻል የተጀመረውን ለውጥ በሁሉም መስክ ለማስቀጠልም ሆነ፣ አገርን ቢያንስ ባለችበት ደረጃ እንኳን ለማፅናት ዋናውን የችግሩን ሰንኮፍ መንቀል ያስፈልጋል፡፡ ይኼን ለማድረግ ደግሞ ያለ ይሉኝታ፣ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ፣ ብሎም በሐሳብ ትግል ዘረኝነትንና ጠባብነትን መጋፈጥ ግድ ይላል፣ አስፈላጊም ነው፡፡ ለዚህም ምሁራን፣ የፖለቲካ ኃይሎችና ራሱ መንግሥት ዋነኛ ተዋናይ መሆን አለባቸው፡፡ ሰፊው ሕዝብ ፍላጎቱም ሆነ እምነቱ ምን እንደሆነ ቢገመትም፣ የሚናገርበትና የሚወስንበት ዕድል እየተመቻቸ በዘረኝነትና በብሔር ንትርክ መወገድ ላይ፣ እንዲሁም በአገራዊ አንድነት ግንባታ ረገድ መምከርና መተማመን ካልተቻለ ፈተናው መክበዱ አይቀርም፡፡ ስለሆነም በብሔራዊ ደረጃ ‹‹የዘር ፖለቲካን በማጦዝ በየቦታው ወገኖቻችን ከማፋጀት እንቆጠብ! ቆም ብለንም አናስብ!›› የሚል ጥብቅ አቋም ከዳር እስከ ዳር ሊስተጋባ ይገባል፡፡    

 በመለያየት ያተረፍነውን ማጤን ይበጃል

ያለፉት 29 ዓመታት የአገራችን ሕዝቦች ዋነኛ መገለጫ በብሔር፣ በሃይማኖትና አለፍ ሲልም በመንደር መፈላለግና መሰባሰብ ነው፡፡ ይህ እውነት ያለ ጥርጥር ለዘመናት ተዘንግተውና ማንነታቸው ተደብቆ ለነበሩ ሕዝቦች ፋይዳ አልነበረውም ባይባልም፣ ከልክ በላይ እየተለጠጠ አገራዊና ብሔራዊ አንድነት በመዘንጋቱ መከፋፋል ብቸኛው መንገድ መስሏል፡፡ ይህን እውነት ዛሬም በፖለቲካ አደረጃጀት፣ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ወይም በማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ ሁሉ ሳይቀር ወለል ብሎ እናየዋለን፡፡ እየኖርነውም ነው፡፡ ከመነሻው  በኢትዮጵያ አሁን ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓት፣ በልዩነት ውስጥ ጠንካራ አንድነት እንደሚፈጥር ተስፋ የተጣለበት ነበር፡፡ ይሁንና ገና ከአስተዳደር ክልል አወሳሰኑ ጀምሮ በዋናነት ቋንቋና ብሔር ላይ ብቻ በመንጠልጠሉ፣ የሁሉም ክልሎች አከፋፈል ወጥ የሆነ መሥፈርትን የተከተለ ባለመሆኑ፣ አወዛጋቢ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ተድበስብሰው በይደር በመቆየታቸው፣ ለአሁኑ ትውልድ ጭቅጭቅ አውርሶታል፡፡ በዚህ ላይ በብዙ ፌዴራላዊ መንግሥታት የሌለና ለመለያየት የሚገፋ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ (አንቀጽ 39) በሰነዱ መሸንቀሩ፣ ብሎም እንደ ብሔር ብሔረሰብ ዋስትና መቀንቀኑ ችግሩን እንዳባባሰው የሚገልጹ በርካቶች ናቸው፡፡

በዚህ ላይ ከሕገ መንግሥቱ ከሚመነጩ ፖሊሲዎችም ሆነ ኢሕአዴግ በሚባለው ድርጅት የተሳሳተ አተያይ በአንድ አገር ውስጥ ለዘመናት ተሳስረው የኖሩ ሕዝቦች የመቃቃር፣ የመገፋፋትና የመፋጠጥ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ተደርጓል፡፡ ይኼ መሆኑ ሳይበቃን አሁንም የዜግነት ፖለቲካ አራማጆችን በመግፋትና በማስጎንበስ፣ አክራሪ ብሔርተኝነትን ለማስቀጠል መሻት መታየቱ እንደ ነውር መቆጠር ያለበት ነው፡፡ በተለይ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል በዘለቀው ዘውጌ ተኮር የፖለቲካ ንትርክ የደረሰብንን ኪሳራና ትርፍም ካለ ጥቅሙን  ሳንመዝን፣ አሁንም በእሱ ላይ ለመጣበቅ መመኘቱ ለማንም ቢሆን የሚበጅ አይደለም፡፡ በእውነቱ አሁን ያለንበት ሁኔታ ካለፉት ዘመናት በባሰ ሁኔታ የከፋ ነው፡፡ እነሆ ዛሬ በአንድነት መንፈስ ቆም ብሎ የሚነጋገሩ ፖለቲከኞች፣ ልሂቃንም ሆኑ ዜጎች ጠንከር ባለ መንገድ ተገናኝተው ለመነጋገር ተቸግረዋል፡፡ በዚህ ምክንያት አክራሪዎችና ጽንፈኞች በተደጋጋሚ ያልበሰሉ ወጣቶችን በቅጥረኞች እያሰማሩ አገር እያወደሙ ነው፡፡

ሁሉም በራሱ አጥርና ጎሬ ተደብቆ በአንድ የጋራ አገር ላይ ዕድገትና ብልፅግናን  ማረጋገጥ ስለማይቻልም፣ በአገር የጋራ ጉዳይ ላይ በጥብቅ መነጋገር ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡  በተለይ ወጣቱ ኃይል ሁሉንም ነገር “የእኔ! የእኔ!” ባይነትን ዋነኛ ባህሪ ከማድረግ ወጥቶ  “የእኛ“  እና “የአገራችን” የሚለውን የአባቶቹን ዕሳቤ መገለጫው አደርጎ፣ በወሰንና በመንደር አጀንዳ ብሎም በጎጥ አስተሳሰብ ማዶና ማዶ ሆኖ መተጋተጉን ሊገታ ይገባዋል፡፡ ታሪካዊ ኃላፊነቱ መሆኑንም ማስገንዘብ ይኖርብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ በዋናነት የመንግሥት ሲቀጥልም የሕዝቡ ተሳትፎና ቁርጠኝነት ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡ መቼም ሆነ የትም በሕዝብ ላይ የሚጫን አስገዳጅ ዕዳ ስለማይኖር፣ ነገሮችን በሠለጠነ መንገድ መመልከት ለሁሉም ይበጃል፡፡ በዚህ መሀል እየታየ ያለውም ሥርዓተ አልበኝነትና ነውጠኝነት ይገታ፡፡

በአገራችን በተለይ በከተሞች አሁን ከመጣው ለውጥም ቀደም ብሎ፣ ማኅበራዊ ህፀፆቻች (ሱሰኝነት፣ ሴተኛ አዳሪነት፣ ሌብነት፣ ያለ ሥራ መቀመጥና መሰል ችግሮች) እየተባባሱ ከመጡ ሰነባብተዋል፡፡ በሌብነት ደግሞ በተለይ የከተማው ሕዝብ  በጣም ተቸግሯል ቢባል ግነት የለውም፡፡ ምሬቱም አዲስ አበባን ጨምሮ በብዙዎቹ የክልልና የዞን ከተሞች  ሠፈር፣ ወቅትና ሁኔታ ሳይለይ እየተባባሰ ይገኛል፡፡ ዛሬ በሌብነት ውስጥ ሊከተቱ የሚችሉት ማታለል፣ ዘረፋ፣ ማጅራት መችነትና አስገድዶ መቀበል የመሳሰሉት ሥርዓተ አልበኝነቶች ናቸው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች አይደለም ለነዋሪዎች ለፖሊስና ለፀጥታ ኃይሉም የማይገዙ የቡድን ጉልበተኞች በመሣሪያ እየተደገፉ ነው፡፡ ከለውጡ ወዲህ ይኼ ችግር ለመባባሱ ከባንክ ዘረፋ ጀምሮ በጠራራ ፀሐይና በምሽት ተሸከርካሪ አስቁሞ መዝረፍ፣ የመኪና፣ የሞተርና የባጃጅ ተሽከርካሪዎች ስርቆት በመከሰታቸው ብቻ አይደለም፡፡ ነጣቂዎችና አሰማሪዎቻቸው ከፍ ያለውን ጉዳት እያስከተሉ መሆናቸውም ግልጽ ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ አገራችን በጅምር ለውጥና ሽግግር ላይ መሆኗ ብቻ ሳይሆን፣ በዴሞክራሲ ማጠናከር ስም ሁሉ ነገር ለቀቅ መደረጉም አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ አንዳንድ በፖሊስና በፀጥታ ዘርፍ ላይ የነበሩና ያሉ የሌባ ተባባሪዎችም ችግሩ እንዲባባስ እያደረጉ መሆናቸውን፣ ራሱ የፖሊስ መዋቅሩ በተለያዩ ሕዝባዊ ስብሳባዎች ላይ አስታውቋል፡፡ ለውጡን ማደናቀፍ የሚሻውም ሌባና ወሮበላ እንዲስፋፋ ለማድረግ አይቦዝንም፡፡ ስለዚህ ሌብነትና ውንብድና እንዲወገድ ወይም እንዲቀንስ መንግሥትን ጨምሮ ሁላችንም ካልተባበርን፣ የተጀመረው ተስፋ እስከ መጨለም መድረሱ ያሳስባል፡፡

መንግሥት ግን የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥና የዜጎች የመኖር ዋስትና እንዳይሸረሸር ነገሩን እንደ ቀላል ባለማየት፣ ከፍ ባለ የፖለቲካ ተነሽነት መሥራት ይኖርበታል፡፡ ሌብነትና ውንብድና በገጠርም ሆነ በከተማ የልማት፣ የሰላምም ሆነ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንቅፋት መሆኑ አይቀርምና፡፡ ስለሆነም በቀዳሚነት  በሕገወጥ እየተደራጀ እንደ ግሪሳ እየተሠማራ ላለው ወጣት፣ የሥራ ዕድልን በማስፋፋት ችግሩን ማዳከም ያስፈልጋል፡፡ ሲቀጥል ከዘረኝነትና ከመበላላት እየወጣ፣ በየትኛውም አካባቢ ተንቀሳቅሶ መሥራትና መኖር እንዲችል ሁኔታዎችን ማመቻቸትና ብሔራዊ አንድነትን ዳግም ማነፅ ይገባል፡፡ ሁሉንም አደረጃጀቶች አነቃቅቶ ማጅራት መችውንም ሆነ ሌባና ዘራፊውን መለየት፣ በሕግ መጠየቅና ልክ ማስገባትም ለነገ የማይባል ሥራ ነው፡፡  ከዚህ ሁሉ በላይ ለዘለቄታው የሞራልና የሥነ ምግባር ትምህርትን ማስፋፋትና ማጠናከር አገር ለማዳንና ሕዝብን ከችግር ለማውጣት ይረዳል፡፡

በአጠቃላይ በአገራችን የተጀመረው ተስፋ የሚቀጥልባቸው በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ የድጋፍና የትብብር አማራጮች አሉን፡፡ ይሁንና ለዘመናት እየተንከባለሉ የፖለቲካ ምኅዳራችንን ያቆሸሹ ሳንካዎችን በሒደት ማስተካከልና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሁሉም ጉዳዮች መሠረት ናቸው፡፡ ልማት ለምንለው መሠረታዊ ተግባርም ቢሆን ዋስትናው ዴሞክራሲያዊነት፣ የሕግ የበላይነት፣ አገራዊ አንድነትና ደኅንነት ናቸው፡፡ ስለሆነም መንግሥትና ሕዝብ በእንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ በልዩ ሁኔታ የማተኮርን ተግባር ለነገ ብለው ሳይዘናጉ መረባረብ  አለባቸው፣ ይኖርባቸዋልም፡፡ በድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ድንገተኛ ሕልፈት የተሰማኝን ሐዘን እየገለጽኩ፣ መንግሥት ከአሁን በኋላ እንዲህ ዓይነቱ ነውረኛ ድርጊት እንዳይፈጸም የሕግ ማስከበር ሥራውን ያጠናክር፡፡ የኢትዮጵያን አንድነት ለመበተን የተነሱ ኃይሎችንም በሕግ ሥርዓት ያስይዝ፡፡ ኢትዮጵያ የሥርዓተ አልበኞች መፈንጫ አትሁን፡፡ ኢትዮጵያዊያን የሥርዓተ አልበኞች ሰለባ መሆናቸው ይብቃ እላለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...