Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኢንተርኔት አገልግሎት በአፋጣኝ እንዲጀመር ኢሰመጉ ጠየቀ

የኢንተርኔት አገልግሎት በአፋጣኝ እንዲጀመር ኢሰመጉ ጠየቀ

ቀን:

የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ሕልፈተ ሕይወት ተከሎ የተፈጠረውን አለመረጋጋትና የዜጎች ሞትን ተከትሎ መንግሥት የወሰደው  የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ ማቋረጥ የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብትና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በእጅጉ የገደበ በመሆኑ፣ መንግሥት በአፋጣኝ አገልግሎቱን እንዲያስጀምር የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ጠየቀ፡፡

በዘላቂነትም የኢንተርኔት አገልግሎት ገደብን በተመለከተ ግልጽ የሆነ መመርያ እንዲዘጋጅም አሳስቧል፡፡

ሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ሕልፈተ ሕይወት ከተሰማ በኋላ ለተቃውሞ የተሰባሰቡ ወጣቶች በድምፃዊው ላይ የተፈጸመውን ግድያ ማውገዝ ሽፋን በማድረግ በፈጸሟቸው ብሔርና ሃይማኖት ተኮር ጥቃቶች በርካታ ሰዎች በስለት በመውጋት፣ በዱላና በድንጋይ በመደብደብ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን፣ አካላቸው መጉደላቸውን፣ ንብረቶች መዝረፋቸውንና እንዲሁም መውደማቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ አስታውቋል፡፡

ጉባዔው ይህን ያስታወቀው ማክሰኞ ሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም.፣ ‹‹በሥርዓት አልበኝነት አገር እንዳይታመስ ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት ይወጣ›› በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ ነው፡፡

ጉባዔው ‹‹አንዳንድ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት ግልጽ በሆነ መንገድ፣ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ውስጥ የሚኖሩ የሌሎች ብሔር ተወላጆችን የጥቃት ዒላማ የሚያደርጉ ቅስቀሳዎች ሲያደርጉ ተስተውሏል፤›› ሲልም አስታውቋል፡፡

በተቃውሞ ሽፋን የተሰባሰቡት ወጣቶች ካደረሱት ጥፋት በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ነዋሪዎች የሆኑ ወጣቶች ‹‹ፀጥታ ለመጠበቅ›› በሚል ምክንያት፣ በቡድን የተሰባሰቡበት ሁኔታም በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ኢሰመጉ አሳስቧል፡፡

‹‹ምንም እንኳን ዜጎች ሕይወታቸውንና ንብረታቸውን ከጉዳት የመጠበቅ ሕጋዊና ተፈጥሯዊ መብት ቢኖራቸውም፣ ሕግ የማስከበር ኃላፊነት በዋነኛነት የመንግሥት በመሆኑ ሕጋዊ ዕውቅና የሌላቸው ቡድኖች በአካባቢ ፀጥታ ጥብቃ ስም መንቀሳቀሳቸው በኋላ የማኅበረሰቡን ደኅንነት ሥጋት ላይ የሚጥሉ አደረጃጀቶች እንዲፈጠሩ መንገድ እንዳይከፍት፣ የማኅበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ይበልጥ ተደራሽ የሚሆንበት ሥርዓት በአስቸኳይ መዘርጋት አለበት፤›› ሲልም በመግለጫው ጠይቋል፡፡

የድምፃዊውን ሕልፈት ተከትሎ በተፈጠሩ አለመረጋጋቶች መንግሥት የተለያዩ ሕግ የማስከበር ዕርምጃዎች መውሰድ መጀመሩን ያስታወሰው ኢሰመጉ፣ ‹‹ምንም እንኳ መንግሥት በመደበኛ የብዙኃን መገናኛ ተቋማትም ሆነ በማኅበራዊ ድረ ገጾች የሚተላለፉ መልዕክቶች ይዘት እኩይ ዓላማ ያነገቡ እንዳይሆኑ የመከታተል ኃላፊነት ቢኖርበትም፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት ያሳየው ከልክ ያለፈ ዝምታ በአገሪቱ እየተባባሰ ለመጣው አለመረጋጋት የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል፤›› የዘገየውን የመንግሥት ዕርምጃ ተችቷል፡፡

ታዋቂ ግለሰቦችና የመንግሥት ባለሥልጣናትን ዒላማ አድርገው የሚፈጸሙ ጥቃቶች ዓላማቸው በማኅበረሰብ ውስጥ ድንጋጤ ከመፍጠር በላይ፣ መንግሥት ያልተመጣጠነ የኃይል ዕርምጃ እንዲወስድ መተንኮስ መሆኑን የገለጸው ኢሰመጉ፣ ‹‹መንግሥትም ይህን በመረዳት የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች ከበቀል ስሜት ፀድተው፣ በሕግ ማዕቀፍ ብቻ የሚፈጸሙ መሆናቸውን ያረጋግጥ፤›› በማለት አሳስቧል፡፡

ኢሰመጉ ዜጎች በብሔር ወይም በሌሎች የማንነት መገለጫዎቻቸው ምክንያት የጥቃት ሰለባ ሳይሆኑ በሕይወት የመኖር በመረጡት አካባቢ የመዘዋወርና ኑሮአቸውን የመመሥረት መብታቸውን እንዲያስከብር፣ በዚህ ሕገወጥ ድርጊት ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ የሆኑ አጥፊዎችን በፍጥነት አጣርቶ ለፍርድ እንዲያቀርብ፣ እንዲሁም ጥቃት ለደረሰባቸውና ንብረቶቻቸው ለወደሙባቸው ዜጎች ዳግም መቋቋሚያ ድጋፍ እንዲያደርግ መንግሥትን ጠይቋል፡፡

በተጨማሪም ፖለቲከኞች ዜጎችን ለጥቃት ከሚያጋልጥ አደገኛ እንቅስቃሴ ራሳቸውን እንዲያቅቡ፣ ዜጎችም ከሕገወጥ ተግባር እንዲቆጠቡ አሳስቦ፣ ‹‹በሥርዓተ አልበኝነት የባህልና የእምነት መገለጫዎች በሆኑ ተቋማትና ሐውልቶች ላይ ጥፋት ከማድረስ ይቆጠቡ፤›› ሲል ኢሰመጉ በመግለጫው ጥሪ አቅርቧል፡፡

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...