(ክፍል ሦስት)
በያዳ ኡመታ
4. በሕወሓትና በለውጥ ኃይሉ አመራር መካከል የታዩ ቅራኔዎች
ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም. በተካሄደው ሕዝባዊ አመፅ በሕወሓት መዘውርነት ይመራ የነበረው ኢሕአዴግ የኃይል ሚዛኑ ተዛብቶ የበላይነቱ እንዲያበቃ ከተደረገ ጀምሮ፣ የለውጥ ኃይሉ አካሄድም ለሕወሓት በግልጽ ያልታየ ስለነበር ቀደም ሲል እንደነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ዶ/ር ዓብይንም ለማሽከርከር ይቻል ይሆን የሚል ግምት ሳይኖር አልቀረም፡፡ የለውጥ ሒደቱ በሰላም ሄዶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የለውጥ ኃይሉ በጥበብ እየገፋ ሲሄድ፣ ለሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች የማይዋጥ ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ በዚህ ጊዜ ይመስለኛል የማጥቂያ ጣቢያው ወደ መቀሌ ተቀየረ፡፡ በተለይ ባልፈራረሰው የደኅንነት ኃይሉ ሰንሰለትና በሙስና በተዘፈቁና የለውጥ ሒደቱ በሚያሠጋቸው የቀድሞ በሁሉም ክልል ከሚገኙ ጓዶቻቸው ጋር በነበረው የግንኙነት ሰንሰለት በመጠቀም ባደረጉት እንቅስቃሴ፣ በበርካታ ዜጎች ላይ የመፈናቀልና የንብረት ውድመት እንዲደርስ ተደረገ፡፡
ይህ ድርጊት “የቀን ጅብ፣ ፀጉረ ለውጦችን ተጠንቀቁ” የተባሉትን የዶ/ር ዓብይ ንግግሮችን አስከተለ፡፡ “የቀን ጅብ የተባልነው እኛ ነን፣ ፀጉረ ለውጦች ደግሞ የትግራይ ተወላጆች ናቸው” የሚል ዕሳቤ ተወስዶ በትግራይ ሕዝብና በለውጥ ኃይሎቹ በተለይ በዶ/ር ዓብይ ላይ ዘመቻ ተካሄደ፡፡ ይህንን ሕወሓት የትግራይ ሕዝብ ከለላ ለማግኘትና ሊያጠቁህ ነው፣ በጋራ እንከላከል በሚል ከትግራይ ሕዝብ ጋር ለመቀራረብም ተጠቅሞበታል፡፡
የሜቴክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጄኔራል ክንፈ ዳኘው መታሰርና በእስራቱ ሒደት ካቴና እጃቸው ላይ ገብቶ ከሔሊኮፕተር ሲወርዱ በቴሌቪዥን የታየው የትግራይ ተወላጅ በመሆናቸው፣ የተደፈሩና ይህንንም የትግራይ ሕዝብ ክብር እንደተነካ እንዲቆጠር ተደረገ፡፡ በሌላ በኩል በኢሕአዴግ የተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ረገጣን በተመለከተ በቴሌቪዥን የተላለፈ አንድ ዶክመንተሪ በማሰቃየት የተጠቀሱት ትግርኛ ተናጋሪዎች የሚል ስለነበረ፣ የትግራይ ተወላጆች በመሆናቸው በትግራይ ሕዝብ ላይ ጥቃት እንዲደርስና የትግራይን ሕዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር ለማጋጨት ሆን ተብሎ እንደቀረበ እንዲወሰድ ተደረገ፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በትግራይ በሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን እንዲራገቡም ሆነ፡፡ በተለይ ከአማራ ልሂቃን ጋር ከወልቃይትና ከራያ የማንነትና የወሰን ጥያቄ ጋር መወዛገብ ስለነበር፣ አማራ ሊያጠቃህ ነው በሚል የትግራይ ብሔርተኝነት እንዲጎላ በማድረግ ራስን ለመከላከል በሚል ወጣቶችን ለውትድርና በስፋት የመመልመልና የማሠልጠን ሥራ ተከናወነ፡፡
በትግራይ የሚደረገውን ፕሮፓጋንዳ ለመመከት ወይም የሕወሓትን ጉድለቶች ለማጋለጥ በሚል በመሀል አገር የሚካሄዱት የሚዲያ ሥርጭቶች፣ በትግራይ በሚካሄዱ ሆን ተብለው እየተፈበረኩ ከሚሠራጩ አሉባልታዎች ጋር ተዳምረው የትግራይን ሕዝብም የሚነካ ሆኖ እንዲታይም ተደርጓል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች የትግራይ ሕዝብ እንደተገለለና ተበዳይ እንደሆነ አደረጉ፡፡ ከአንዳንድ የትግራይ ሰዎች እልኸኛና ስሜታዊ የመሆን ባህሪም አንፃር የሕወሓት መሪዎችም ይህንን በደንብ ተጠቅመውበታል፡፡
ሕዝቡ በተበዳይነትና በመገለል ሥነ ልቦና ውስጥ ሆኖ፣ እንዲሁም የሚታደገው ጠንካራና አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲ ባልነበረበት ሕወሓትን አጠናክሮ ከዚሁ ኃይል ጋር ከመሠለፍ ውጪ አማራጭ አልነበረውም፡፡ ከአንዳንድ ሰዎች የሚሰማው ሕወሓት በትግራይ ሕዝብ የማይወደድና ሕዝቡን የበደለ ድርጅት ነበር፡፡ ግን አማራጭ ባለመኖሩ ድርጅቱ ተጠናክሮና ከሕዝቡ ጋር ታርቆ እንዲሠራ ከማድረግ ውጪ የተሻለ ሁኔታ ስላልነበረ፣ እንዲያውም የንግዱ ማኅበረሰብ ነው ለሕወሓት በሕዝቡ ተቀባይነት ማግኘትና ለሥርዓቱ መጠናከር አስተዋጽኦ ያደረገው የሚል ሐሳብም ይደመጣል፡፡ ለዚህም ማስረጃ የሚሆነው በ2011 ዓ.ም. የካቲት ወር፣ በ1993 ዓ.ም. ከተለዩት የቀድሞ ነባር የሕወሓት አባላት የነበሩትና በተቃዋሚነት ከተሠለፉት ጋር ዕርቅ እንዲደረግ የንግድ ማኅበረሰብ መሪዎች መሥራታቸው ነው፡፡ እነዚህም ይህን ለማድረግ የተገደዱት መንግሥት ተዳክሞና የሥልጣን ክፍተት ተፈጥሮ ሥርዓትን ወይም ፀጥታን ማስከበር አቅቶት፣ ሥርዓተ አልበኝነት እንዳይሰፍንና ንብረታቸውም ሆነ ሕዝቡ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ከመሥጋት አንፃር ይመስላል፡፡ ከለውጡ ወዲህ ከትግራይ ሕዝብ ጋር የበለጠ በመቀራረብ የሕዝቡን ፍላጎት በማሟላት ረገድ በርካታ የልማት ሥራዎችን፣ በተለይ በመቀሌ ከተማ የመንገድ መሠረተ ልማትን ለማሻሻል እያደረጉት ያለው ጥረት በሕዝቡ ዘንድ የሕወሓትን ተቀባይነት እንዲያድግ አድርጓል፡፡ በእርግጥ ይህ የትግራይ ሕዝብ ከለውጡ ያገኘው ውጤት ነው፡፡ ለውጡ ባይመጣ ሕዝቡ ከሕወሓት እንዲህ ዓይነት አገልግሎትን ሊያገኝ አይችልም ነበር፡፡ ስለዚህ የትግራይ ሕዝብም ከለውጡ ተጠቃሚ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ እንደሚወራው ሕወሓት ሕዝቡን በኃይል መፈናፈኛ በማሰጣት ይዟል የሚለው አባባል ትክክል አይደለም፡፡ ሕዝቡ ከላይ በቀረበው ምክንያትና በትግራይ በሚሠራጩ ሚዲያዎችና ቅስቀሳዎች ተፅዕኖም ሊሆን ይችላል፣ በራሱ ፈቃደኝነት ሳይገደድ ከሕወሓት ጎን መሠለፉን የመሀል አገር ሕዝብና መንግሥታችን ሊረዳና አፅንኦት ሊሰጠው የሚገባው ነው፡፡
በትግራይ ሕዝብ፣ በዚህ መንግሥት ላይ እንደ ቅሬታ ከሚቀርቡት ዋንኞቹ፣ የአማራና የትግራይ ክልሎችን የሚያዋስኑ መንገዶች ተዘግተዋል የሚባሉትና የትግራይ ሕዝብ እንዲገለል ተደርጓል የሚባለው ነው፡፡ የመንገዱን በተመለከተ ሕወሓት የፈጸማቸውን ስህተቶች ለመበቀል የየአካባቢው ወጣቶች በስሜት ተነሳስተው ያደረጉት በመሆኑና በወቅቱ የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግሥት ሊቆጣጠር በማይችልበት ወቅት እንደሆነ ዕውቅ ነው፡፡ ከዚያም በኋላ መንገዱ ክፍት ሆኖ ፀጥታን መቆጣጠር ካለመቻል የተፈጠረ ካልሆነ በስተቀር፣ የክልሉ መንግሥት መንገዱን አልዘጋም፡፡ በሌላ በኩል የሁለቱ ጎረቤታም ክልል አመራሮች በተለያዩ የፖለቲካ ጉዳዮች አንዱ በአንዱ ላይ መግለጫ በማውጣት በሚካሰሱበት ፣እንዲሁም ሕወሓት ከፌዴራል መንግሥት ጋር አተካሮ በገባበትና ግንኙነቱ በሻከረበት ሁኔታ የዚህን መንገድ ችግር ብቻ ለይቶ እንዲፈታ መጠበቅ ብዙም አያሳማም፡፡ መንገዶቹ እንደ ልብ ለሁሉም ነፃ ሆነው መመላለስ አለመቻሉ የሁለቱንም ክልሎች ሕዝቦች ብሎም አገሪቱን ነው የጎዳው፡፡ ለዚህ ግን ዋናው ችግር ከሕወሓት ጋር የተያያዘ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ሕወሓት ይኼንን ሁኔታ የትግራይ ሕዝብን ለመያዣም ሳይጠቀምበት የቀረ አይመስልም፡፡ መገለልንም በተመለከተ ከዚሁ ከሕወሓትና ከፌዴራል መንግሥቱ ግንኙነት ጋር የተያያዘ እንጂ፣ የለውጥ አመራሩ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለይቶ የትግራይን ሕዝብ ተጎጂ ያደረገበት የሚታይ ተጨባጭ ሁኔታ የለም፡፡
የትግራይ ሕዝብ ጨዋ ሕዝብ ነው፡፡ እውነትን ለማግኘት የሚጥር፣ ለእውነት ሕይወቱን የሚሰጥ ታማኝ ሕዝብ ነው፡፡ እውነቱ እየተዛባ እየቀረበለት ነው ችግሮች የሚፈጠሩት፡፡ መሠራት ያለበት ሕዝቡ እውነታዎችን እንዲረዳ ነው፡፡ ፖለቲከኞች ለራሳቸው ሥልጣንና ክብር ይህን ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ለማጋጨት የሚሠሩትን ተንኮል ነቅቶ ማክሸፍ ይኖርበታል፡፡ እስካሁን የተሠራውን ስህተት በቃ ሊል ይገባል፡፡ ሕዝቡ ከዚህ በፊት የደርግ ሥርዓትን ታግሎ ለአገሪቱ በሙሉ ውጤት አስገኝቷል፡፡ አሁን በተሳሳተ መንገድ የልጆቹን ደም ዳግም ፈፅሞ መገበር የለበትም፡፡ የቀድሞው የትግል ታክቲክ ለአሁኑ አይሠራም፡፡ ስለዚህ ይህንን ቆም ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በሐሳብ ትግልና በድርድር ችግሮችን መፍታት ነው ተመራጭ የሚሆነው፡፡
ይህ በእንዲህ እያለ በቅርቡ አሳሳቢ የሆነው ሕወሓት የማዕከላዊውን መንግሥት ውሳኔ ባለመቀበል በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተላለፈውን የምርጫ ጊዜ መራዘም ባለመቀበል፣ በክልሉ ምርጫ ካላካሄድኩ ብሎ መነሳቱ ነው፡፡ ይህ ሕገ መንግሥትን ለማክበር በየአምስት ዓመቱ የሚካሄደው ምርጫ መተላለፍ የለበትም የሚል ምክንያት የሚቀርብበት ሰበብ፣ ሕወሓት የምርጫ ጊዜው ቢረዝም እየተጀማመሩ ያሉትን ውስጣዊ የወጣቶች የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን ሠግቶ ወይም ሆን ብሎ ማዕከላዊ መንግሥትን ውጥረት ውስጥ ለማስገባት፣ ራሱን ድርጅቱንም ሆነ ሕዝቡን ሊጎዳ የሚችል ተግባር ውስጥ ገብቶ ይገኛል፡፡
ሕወሓት ሕዝባዊ ለውጡን መቀበል ተቸግሮ ይህን ለመቀልበስ አንዳንድ የኦሮሞ ተፎካካሪ ፖለቲከኞችን በመያዝ በአገሪቱ ሁከት በመፍጠር፣ የዶ/ር ዓብይን መንግሥት ለመጣል ይቻላል የሚባለው ከንቱ ምኞት ነው፡፡ ይህ ከዚህ በላይ ባሰፈርኩት ጽሑፍ እንደሚታየው የማይሳካ በመሆኑ፣ ታግዬለታለሁ ለሚለው ለትግራይ ሕዝብ ሲል ወደ ሰላም ቢመጣ ይሻለዋል፡፡ ዶ/ር ዓብይ በአንድ ወቅት ያሉት ቃል በቃል አይደለም፣ ‹‹ብልሆች የለውጥ ኃይሉን ለመጠቀም በንፋስ ኃይል የሚሠራ የእህል ወፍጮን ሲያቋቁሙ፣ ሞኞች የንፋስ ኃይልን ለመከላከል ግንብ ይሠራሉ የሚለው የቻይናዎች አባባል አለ፤›› ያሉትን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ሕዝቡ በፍላጎቱ ታግሎ ያመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ መመኘት የታሪክን ሒደት ያለመቀበልና ከጊዜና ታሪክ ጋር መጋጨት እንጂ፣ ይህንን መንገድ ወደ ኋላ መመለስ አይቻልም፡፡ በዚህ የእልህና ገታራ አቋሙ ከቀጠለ ሕወሓት ያለ ጥርጥር ከራሱ ሕዝብ ጋር ግጭት ውስጥ ይገባል፡፡ ሕዝቡ ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመነጠልም ሆነ መቀየም አይፈልግም፡፡ በሌላ በኩል ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ በክልሉ የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ይቆማል፡፡ ይህ የሥራ አጥ ቁጥሩን የበለጠ ይጨምራል፡፡ ከኤርትራ ጋርም የነበረው የድንበር ግንኙነትም ይቆማል፡፡ የትግራይ ሕዝብ መረዳት ያለበት ከኤርትራ ጋር የነበረው የድንበር መዘጋት፣ የሕወሓት አመራሮች ሥልጣን ላይ መቆየትና ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር ያላቸው ግንኙነት መበላሸት ውጤት መሆኑን ነው፡፡
የሕወሓት መሪዎች በቅርቡ ላነጋገሯቸው የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች እኛ ብቻችንን አይደለም የምንታረቀው፣ ሌሎቹን ሁሉ ያቀፈ አገራዊ ውይይት ያስፈልጋል ሲሉ አሁን የሽግግር መንግሥት ካልተቋቋመ የሚሉ ኦነግ ሸኔ፣ ኦፌኮና እነ አቶ ልደቱ የሚመሩት ኃይሎች ማለታቸው ግልጽ ሊሆንልን ይገባል፡፡ እነዚህን ስብስቦች በመያዝ እንዴት ዕርቅ መፍጠር ይቻላል? የእነርሱ ምኞትና ፍላጎት አሁን አገሪቱን እየመራ ያለውን የለውጥ ኃይል በሽግግር መንግሥት ለመተካት ነው፡፡ የእነሱ ሐሳቦች እንደተብራራው በፖለቲካ የሐሳብ ትግል እየሞቱ ያሉና የሚሞቱ በመሆናቸው፣ ቁርጣቸውን እስኪያውቁ ድረስ ሽምግልናውን ለመቀበል ይቸገራሉ፡፡
በተለይ አንዳንዶቹ የኦሮሞ ተፎካካሪ ፖለቲከኞች እኮ በቅርቡ በዋልታ ቴሌቪዥን በዘጋቢ ፊልም የተላለፈውን ከሕወሓት የደኅንነት ኃይሎችና ሌሎች ባለሥልጣናት ጋር በመመሳጠር የንፁህ ዜጎችን ሀብት ሲዘርፍ፣ ጭቁን አርሶ አደሮችን ሲያስለቅስ የነበረን ግፈኛ አቶ ድንቁ ደያሳን የሚደግፉና ሽፋን የሚሰጡ ናቸው፡፡ አቶ ሌንጮ ለታ እንዳሉት የዚህን ሰውዬ አጀንዳ ለማስለወጥ የኦሮሞ ብሔርተኛ ዘፋኝ ሃጫሉ ሁንዴሳን የውዝግብ ሐሳብ ይዞ ለኦኤምኤን ቴሌቪዥን እንዲቀርብ በማግባባት፣ የሕዝቦች አንድነት እንዲናጋ ሆን ብለው ሲሠሩ የነበሩ ናቸው፡፡ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ገፋፍተው አፄ ምኒልክን እንዲሳደብ በማድረግ፣ ከእዚያ በኋላ በፌስቡክ እንደ አማራ ተወላጅ በመምሰል በስድብ መመላለስ በተቀነባበረ መንገድ እንዲሠራ ተደርጓል፡፡ ይህ በኦሮሞ ሕዝብ በጀግንነቱና በዘፋኝነቱ ታዋቂና ተወዳጅ የሆነን ለጋ ወጣት፣ ለፖለቲካ ዓላማቸው ማሳካት ማስገደል ድራማ የሚመስል ወንጀልም ነው የተሠራው የሚለው ግምት አይሎ ይገኛል፡፡ በዚህ ሒደት የኦኤምኤን ቴሌቪዥንን የሚመሩ ፖለቲከኞች ስለመሳተፋቸው ጥርጥሩ ጎልቶ ይታያል፡፡ ባይሆን በኢንተርቪው በዚህ ጊዜ ለማቅረብ ለምን ተፈለገ? ከሆነስ ከአማራ ሕዝብ ጋር ሊያጋጭ ይችላል ተብሎ የታመኑ ጥያቄዎች ለምን በዚህ ጊዜ እንዲጠየቅ ተደረገ? ሃጫሉ እንደተገደለ ለተቃውሞ ያን ያህል ወጣት እንዴት በዚያ ፍጥነት ተሰባሰበ? ይህ ሁሉ የሚጭረው ጥያቄ አለ፡፡
ይህ ተወዳጅና ተፈቃሪ የሆነው ልጅ ለመስዋዕትነት የቀረበው በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ለመምታት ይመስላል፡፡ አንደኛው በአማራ ተወላጆች እንደተገደለ በማስመሰል የአማራንና የኦሮሞን ሕዝብ በማጋጨት ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥትና ፓርቲ በማፍረስ፣ አክራሪዎቹ የኦሮሞ ፖለቲከኞቹ ከሕወሓት ጋር ወደ ሥልጣን ለመምጣት፡፡ ሁለተኛው ሃጫሉ የኢትዮጵያ አንድነት ላይ የሚያጠብቅና ከለውጥ ኃይሎች ጋር የሚቆም ስለሆነ፣ ከእነዚህ አክራሪዎች ጋር በዚህ የኦሮሚያ ሪፐብሊክ መንግሥት ምሥረታ ዓይነቱ አካሄድ የተለየ አቋም ስላለውና ስለማይቀበላቸው፣ እንዲሁም በቄሮና በተቀረው የኦሮሞ ሕዝብ ተቀባይነቱ ከፍተኛ በመሆኑ የኦሮሞን ወጣቶች በማንቀሳቀስ ያሰቡትን ዓላማ ለማሳካት ዕንቅፋት ይሆንብናል በሚል ከመስመሩ ለማግለል የተወጠነ ሴራም ይመስላል፡፡ ሦስተኛው የፖለቲካ ትርፉ አነስተኛ ቢሆንም፣ ሕወሓት ለመበቀልም ተጠቅሞበታል የሚለውም የሚጣል ሐሳብ አይደለም፡፡ የመበቀሉ ጉዳይ ከተነሳማ ሕወሓት አቶ ጀዋር መሐመድና አቶ በቀለ ገርባንም ሆነ ኦነግ ሸኔን ለመበቀል ዕድሉን ተጠቅሟል ማለትም ይቻላል፡፡ ውጥንቅጥና የቁማር ጨዋታ ውስጥ እንዲገቡ በመደረጋቸው፡፡
ይህ ሁሉ ሃጫሉ በተለይ በኦሮሞ ሕዝብ ተወዳጅ በመሆኑ የአማራ ተወላጆች እንዳስገደሉት በማስመሰል፣ የኦሮሞን ወጣት (ቄሮ) በማነሳሳትና ከአማራ ሕዝብ ጋር በማጋጨት ለአገር መበጥበጥ የታሰበው ባይሳካም፣ በተደረገው ሴራ የተወዳጁን ሃጫሉ ሁንዴሳን ሕይወት በአጭሩ ቀጭቷል፡፡ የሌሎች ዜጎችም ሕይወት እንዲጠፋ አድርጓል፡፡ በርካታ ንብረትም ወድሟል፡፡ ይሁን እንጂ ሴረኞቹ ያሰቡትና የተመኙት አልሆነላቸውም፡፡ በእነዚህና በመሳሰሉት ጉዳዮች ለወደፊቱም እየተፈጠረ ያለውን የሕዝብ አንድነት መሸርሸር እንደማይቻል ግልጽ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ትልቅ የስህተት ምንጭ ሕወሓቶች እነዚህን የኦሮሞ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በእጃቸው እንዳለ ትልቅ አጋዥ መሣሪያ ማየታቸው ነው፡፡ አቶ ጀዋር መሐመድም በየመገናኛ ብዙኃን የሚሰጡዋቸው መግለጫዎች ቄሮን እንደፈለጉ የሚያንቀሳቅሱ፣ እንደ ባለፈው የአመፅ ጊዜ ጥሪ በማድረግ መንገድ እንደሚያዘጉ፣ ብሎም የለውጥ ኃይሉን አመራር ከሥልጣን እንደሚያባርሩ ሲናገሩ ይህ ከኦነግ ሸኔ ጋር ተቀናጅቶ የብልፅግና ፓርቲን ታሪክ በማድረግ ሥልጣን ሲቆናጠጡ፣ ሕወሓት ከእነርሱ ጋር ሥልጣን ለመጋራት መታሰቡ ነው፡፡
ይህ ከንቱ የሞኞች ምኞት ነው፡፡ ይህ የፖለቲከኞች ትንተና ውጤት አይደለም፡፡ ይህ የሚያሳየው ‹‹የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለም›› የሚለውን አባባል ያልተረዱ ተስፈኞችና ዝም ብለው ግልቦች መሆናቸውን ነው፡፡ የኦሮሞ ወጣት (ቄሮ) መስዋዕትነት ከፍሎ ከፋኖ፣ ከዘርማና ከሌሎች ኢትዮጵያን ጋር ያመጣውን ለውጥ በአቶ ጀዋርና ደጋፊዎቹ፣ እንዲሁም ኦነግ ሸኔ ሥልጣን ስላልያዙ ለእነርሱ እንዲመች ሕይወቱን እንደገና ለመገበር የሚነሳበት ምንም እውነታ የለም፡፡ አቶ ጀዋር እንደሚፎክሩት አመፅ ማነሳሳት የተካንኩ ኤክስፐርት ነኝ ከፈለግሁ አሁኑኑ አገር እገለብጣለሁ የሚሉት ከንቱ ምኞትና ፉከራ፣ ለአገርም ለእነርሱም የማይበጅ አጉል በእሳት የመጨዋት ሙከራ መሆኑ ታይቷል፡፡ በእርግጥ በየአካባቢው የእርሱንና የኦነግ ሸኔ ሐሳብ ተሸክመው አብረው የሚቸገሩ ወጣቶች አሉ፡፡ በእነዚህም የሚወናበዱ አይጠፉም፡፡ በየአካባቢው ባሉት ሕዝቦች ሙከራቸው እንዲከሽፍ ተደርጓል፣ ይደረጋልም፡፡ እነርሱም ራሳቸውን ለአደጋ ይዳርጋሉ፡፡ አሁንም ይኼው ዳርገዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ምንም ነገር አይኖርም፡፡ የሕወሓት መሪዎችም ሆኑ አቶ ጀዋርና ሌሎቹ የኦሮሞ የብልፅግና ፓርቲ ተገዳዳሪዎች ይህንን እውነታ ሊረዱትና ደጋግመው ቢያስቡበት መልካም ነበር፡፡
“የቸገረው እርጉዝ ያገባል” እንዲሉ አንዳንድ የትግራይ የፖለቲካ ልሂቃን ትግራይን ከሌላው ኢትዮጵያ ለመነጠል “የትግራይ ነፃነት ፓርቲ አቋቁመናል” አሉን፡፡ በቅርቡ ለዚህም ፓርቲ መቋቋም እንደ ምክንያት የሚጠቀሙት ትግራይ በጥንቱ የአክሱም ዘመነ መንግሥት ገናናና ሀብታም ነበረች፡፡ ከሌላው ኢትዮጵያ ጋር ስትሆን ነው በሥልጣኔ ወደ ኋላ የቀረችውና የደኸየችው የሚልና በሁለቱ ትልልቅ ብሔሮች ሥር ሆና በአሃዳዊ ሥርዓት አታድግም የሚል ነው፡፡ ሰዎቹ የፈለጉትን ማሰብ መብታቸው ነው፡፡ የዴሞክራሲ መብቶቻቸውን እየተጠቀሙ ስለሆነ፡፡ ግን ይህ አስተሳሰብ ጤናማ ነውን? ይህ የትግራይ ሕዝብ ፍላጎት ይሆናል? ለትግራይ ሕዝብ የትግራይ ክልል ብቻ በቂው ነው? የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን ያለችው ኢትዮጵያ በቂያችን አይደለችም በማለት የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችን በሙሉ ያካተተ አገር እንፍጠር የሚል ህልም ይዞ እየሠራ ባለበት፣ እነዚህ የትግራይ ጥቂት የፖለቲካ ልሂቃን ለትግራይ ሕዝብ ትንሽ አገር መመኘታቸው ጤናማ አይመስልም፡፡ የትግራይ ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያ ጋር በመሆኑ እንዴት ሊደኸይ ይችላል? ሌላው ክልል የትግራይን ሕዝብ ሀብት በዝብዟል ወይም ወስዷል? ሕዝቡ በራሱ ሀብት እንዳይጠቀምስ ምን አደረገ? ባለፉት 30 ዓመታት የትግራይ ሕዝብ በራሱ ልጆችና በሕወሓት ሲተዳደር አልነበረምን? በእነዚህ ዓመታት ለምን ከድህነት አልወጣም? ይህ አንዳንድ የሕወሓት አባላት ኢትዮጵያ የምትባለውን አገር እኛ ካልመራን ትግራይን እንገነጥላለን የሚለው የክልህና የግብዝነት አካሄድ ለሕዝቡ ጥቅም የለውም፡፡ የተገነጠሉ የጎረቤት አገሮችንም አይተናል፡፡ ምንም የተለየ ብልፅግናና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አላሰፈኑም፡፡ ይህን እያዩ ለጥቂት ቅብጥብጥ ንዑስ ከበርቴዎች ሥልጣንና ዝና ማስጠበቂያ፣ ለሕዝቡ የማይጠቅም ሐሳብ ማራመድ አግባብነት ሊኖረው አይችልም፡፡
ሌላው እውነት የአሁኑ በዶ/ር ዓብይ የሚመራው መንግሥት አሀዳዊ ሥርዓት ለመመለስ ነው የሚሠራው? እዚህ ማጠቃለያ ላይ ለመድረስ ያስቻለው የብልፅግና ፓርቲ ፕሮግራም ነው? ወይስ እንዲህ ሊሆን ይችላል የሚለው ጥርጣሬ? እነዚህን ጥያቄዎች በሙሉ ልመልስ አይደለም፡፡ ለአንባቢያንና ለትግራይ ሕዝብ እንዲመልሱ በመተው አንድ የማነሳው ጉዳይ ግን፣ እነዚህ ሰዎች በበታችነት ስሜት እየተቸገሩ የሚገኙ መሆናቸውንና ሕዝቡን ወደ አዘቅት እየወሰዱት መሆናቸውን ነው፡፡ ይታያችሁ በአራቱም አቅጣጫ ድንበሮችን የሚጠብቅ የመከላከያ ኃይል ወጪን ሸፍነው፣ በኢትዮጵያ ሙሉ ተሠራጭተው የሚገኙትን የትግራይ ተወላጆች ሰብስበው፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ሌሎች የምግብ ሰብሎችንና ሸቀጦችን ከኢትዮጵያና ከሌሎች አገሮች በዶላር እየገዙ ትግራይን የበለጠ ሀብታም ሲያደርጉ፡፡ የትግራይ ሕዝብ ከኢትዮጵያ መለየት ትግራይን ብቻ ሳይሆን፣ እንዲያውም የበለጠ ኢትዮጵያንና ሕዝቧንም ነው የሚጎዳው፡፡ ስድስት ሚሊዮን ኢትዮጵያን የሚገነባ ኃይል ይቀንሳል ማለት ነው፡፡ እርስ በርስ በመገበያየትና በቱሪዝም ግንኙነት የሚፈጠሩት ክፍተቶች ሁሉንም የሚጎዱ ናቸው፡፡ ብልፅግና የሚመጣው በአንድነት በጋር በመሥራት እንጂ፣ ለብቻ ትንንሽ አገር በመፍጠር በምንም ተዓምር ሊሆን አይችልም፡፡ የትግራይ ሕዝብ ይህንን የዕብደት ሐሳብ ይቀበላል የሚል እምነት ይህ ጸሐፊ የለውም፡፡ የትግራይ ሕዝብ ከኢትዮጵያ የሚገነጠል አይደለም፡፡ በዚህ ሊሠጋ አይገባም፡፡ መገንጠሉ አዋጪም አይሆንም፡፡ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራና ለዚህ መስዋዕትነት ሲከፍል የኖረው የትግራይ ሕዝብ፣ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በመገንባት በእውነተኛ የፌዴራል ሥርዓት በአንድነት በመተጋገዝ ማደግና መበልፀግ ነው የሚጠበቅበት፡፡ መፍትሔው የሚሆነው ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ለትግራይ ሕዝብም ሆነ ለተቀረው ኢትዮጵያ ብልፅግናና የመብት አከባበር የሚመች አገር በጋራ ለመገንባት መሥራት ነው፡፡
የትግራይ ሕዝብ በሰላም ነው እየኖረ በተቀረው ኢትዮጵያ ሰላም የለም ወይም አይኖርም የሚባለው ተገቢነት የለውም፡፡ ይህ ጊዜያዊ ነው፡፡ በሌላው የኢትዮጵያ አካል ሰላም የታወከው በሕወሓት የሴራ ፖለቲካ ቢሆንስ? በጋራ በአንድ ልብ ስንሠራ ይህ ሁሉ ይስተካከላል፡፡ ሌሎች አገሮችን የምታስቀና አገር ለመገንባት የሚያስችለን ቁመና ላይ የደረስን በመሆኑ፣ እነዚህ የትግራይ ልሂቃን ምንም ሊሠጉ አይገባም፡፡ አይቸኩሉ፣ ያዩታል፡፡ ለማንኛውም ወሳኙ የትግራይ ሕዝብ በመሆኑ ጉዳዩን ለሕዝቡ መተው ይመረጣል፡፡ በቅርቡ በአገራችን በተፈጠረው ከድምፃሚ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያና ከደረሱት አገራዊ አደጋዎች ጋር በተያያዘ እንደሚባለው፣ ከህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት አስቀድሞ ግብፆች የተሳተፉበት የተቀነባበረ ሥራ ነው እንደሚባለውና የሕወሓት መሪዎች እጅ ካለበት ሁኔታዎቹ ሌላ መልክ ይይዛሉ፡፡ የትግራይ ሕዝብ በህዳሴ ግድብ ላይ ይደራደራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ለዚህም ሐሳቡን ከተገበረው ራሱ በሕወሓት ከተመራው ኢሕአዴግ ጊዜ ጀምሮ፣ የዚህ ግድብ ባለቤትነትን የትግራይ ሕዝብ የመጋራት ጉዳይ ለጥያቄ የሚቀርብ አለመሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የምርመራው ውጤት ይህን ካረጋገጠና የሕወሓት ተሳትፎ ካለ፣ ጉዳዩ የትግራይ ሕዝብንም ህሊና የሚያቆስል፣ የሚጎዳ፣ ለትግራይ ሕዝብ ከፍተኛ የታሪክ ቁስል ትቶ የሚያልፍ ስለሚሆን ሕዝቡ ዝም ብሎ በቸልተኝነት የሚተወው አይመስልም፡፡ የሕወሓት ታሪካዊ ዳራም ይለወጣል፡፡
ለማንኛውም የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያ አገሩን ለማዳን ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ተሠልፎ፣ ከዚህ በፊት ያደረጋቸውን ገድሎች የሚያበላሹ ተግባራትን በሚፈጽሙና ታሪኩን በሚያንኳስሱ አካላት ላይ የራሱን ዕርምጃ ይወስዳል የሚል እምነት አለ፡፡
የሕወሓት መሪዎች እስካሁን የፈጸሙዋቸውን ተንኮሎችና ሴራዎች ለትግራይ ሕዝብና ለኢትዮጵያ ሕዝብ በዝርዝር ማቅረብና በተለይ የትግራይ ሕዝብ እውነታውን እንዲረዳ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ሁኔታዎች የቀለሉ ይሆናሉ፡፡ ይህ ሲደረግ ግን ማንኛውም የመሀል አገር ኅብረተሰብ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በሰላም በሚኖሩት የትግራይ ተወላጆች ላይ ምንም ዓይነት ክፉ ነገር ሊያስቡ አይገባቸውም፡፡ ሌሎች የትግራይ ተወላጆች እንደ ማንኛውም የተቀረው ሕዝብ ሰላማዊ ዜጋ በመሆናቸው እንደ ገዥዎቹ ሕወሓት መሪዎች ፈፅሞ ሊታዩ አይገባም፡፡ ቀደም ሲል የሕወሓት መሥራቾች የነበሩትና የአሁኑ መሪዎች ጭምር አብዛኞቹ በ1960ዎቹ የተማሪዎች ትግል ተሳትፎ የነበራቸው መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ያኔ የነበረው የታጋዮች መንፈስ ራስን ለሕዝብና ለአገር ጥቅም መስዋዕትነት ለመክፈል መስጠት ነው፡፡ የግል ጥቅምና ዝና ቦታ አልነበረውም፡፡ ያ ሁሉ ወጣትና ምሁር በኢሕአፓና በመኢሶን አባልነት፣ እንዲሁም በሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች በመሳተፍ ሕይወቱን የሰዋው በዚህ ዕሳቤ ነበር፡፡ ይህ ከሆነና የሕወሓት መሪዎችም ጥቂት አሮጌ ጠመንጃዎች ይዘው ጫካ የገቡት በዚሁ መንፈስ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ በዚህ ዓይነት ዓላማ ሌሎች ጓዶቻቸውን መስዋዕት አስደርገው የተቀሩት ለዚህ ኃላፊነት ሲበቁ፣ ይዘው የተነሱትን ማለት ለአገርና ለሕዝብ እስከ ሞት የሚያደርስ መስዋዕትነት መክፈልን ዓላማ እነዚህ የሕወሓት መሪዎች የት አደረሱት? ይህስ ሕይወታቸውን ለተቀደሰ ዓላማ ለመሰዋት የሰጡትን ጓዶቻቸው ይዘው የተነሱትን አደራ እንደበሉ አያስቆጥርባቸውምን? በሠሩት ስህተት ከሥልጣናቸው እንዲነሱ ሲደረጉ ይቅርታ፣ ይዘን የተነሳነውን አደራ በልተናል፣ ተሳስተናል በማለት ንሰሐ ገብተው፣ ሕዝቡን ይቅርታ ጠይቀው፣ የበደሉትን ክሰው፣ የሰወሩት የአገር ሀብትም ካለ መልሰው፣ የተጀመረው ለውጥ ግቡን እንዲመታና እነርሱ ይዘውት የተነሱት ዓላማ ከፍፃሜ እንዲደርስ ዕገዛ በማድረግ ከለውጥ አመራሩ ጋር አብሮ መሥራት አልነበረባቸውምን? በ1960ዎቹ በተራማጅነታቸው ስማቸው የሚነሳው እንደ አቶ ዓባይ ፀሐይ የመሳሰሉት እንደዚህ መውረዳቸው በሕይወት እንዳሉ ሳይሆን በቁመናቸው እንደ ሞቱ ይቆጠራል፡፡
ይህ አሁን እየፈጸሙ ያሉት ሕዝባዊ የሆነውን ለውጥ ለማደናቀፍ መሥራት፣ ለአገር ብተናና የትግራይን ሕዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝብ የማጋጨትና የመለያየት ተንኮል ውስጥ መግባት ከዚያ ትውልድ ከመጡ ዜጐች የማይጠበቅ ነውር የሆነ ተግባር ነበር፡፡ ስህተትን በስህተት ለማስተካከል አይቻልም፡፡ ውጤቱ ለኪሳራና ውርደት ይዳርጋል፡፡ ጀብደኝነትም የሊቢያ መሪ እንደነበሩትና እንደ ሌሎች አምባገነን የዓለም መሪዎች ያዋርዳል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ቆም ብለው ማሰብና ውሳኔያቸውን እንደ ገና በመመርመር ሽንፈታቸውን ተቀብለው እጃቸውን በሰላም ሰጥተው ይቅርታና ምሕረት ቢጠይቁ ለራሳቸው፣ ለልጆቻቸውና በልጅ ልጆቻቸው፣ እንዲሁም ለትግራይ ሕዝብና ብሎም ለኢትዮጵያ ሕዝቦች በሙሉ ትልቅ ሥራ እንደሠሩ ይቆጠርላቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ በሕወሓት ላይ የትግራይ ሕዝብ ተፅዕኖ ለመፍጠር መንቀሳቀስም ይጠበቅበታል፡፡
5. የለውጡን ሒደት ለማሳካት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ከሕዝብና ከመንግሥት የሚጠበቁ ተግባራት
5.1 ከተፎካካሪ ፓርቲዎች
ስለዴሞክራሲ ሲነሳ አንዱ በአብዛኛው የተፎካካሪ ፓርቲዎች መኖር እንደ አንድ አስፈላጊና ቅድመ ሁኔታ ሲቀመጥ ይታያል፡፡ ይህ ጉዳይ በዕድገት ወደፊት በገሰገሱት፣ የካፒታሊዝም ሥርዓት በገነቡትና የባህል ለውጥ በተካሄደባቸው፣ የተማረ የሰው ኃይል ከፍተኛ በሆነበት፣ በብሔርና ብሔረሰብ ፖለቲካ በማይወዛገቡ አገሮች ላይ ሊሠራ ይችላል፡፡ እንደ እኛ ባሉ ታዳጊና ለዴሞክራሲ ሥርዓትና ባህል እንግዳ በሆኑ ይህ ንድፈ ሐሳብ ስለመሥራቱ ማረጋገጫ የለም፡፡ ስለዚህ በአገራችን በሚገኙት ዓይነት ፓርቲዎችና የጨዋታ ሕጎቹ የዴሞክራሲ ሥርዓት መመሥረት ስለመቻላችን የሚያወያይ ሆኖ፣ አሁን ያለውን የተፎካካሪ ፓርቲዎቻችንን የፖለቲካ ባህል ለውይይታችን መነሻ እንደሚከተለው አቅርቤያለሁ፡፡
በአገራችን የሚገኙ ተፎካካሪ የሚባሉ ፓርቲዎች እንደ ኢዜማ ያሉና በርካታ ሌሎች ፓርቲዎችም የባህል ለውጥ በማድረጋቸው ቀጥሎ ከሚቀርቡት ወቀሳዎች ነፃ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ፓርቲዎችና የፖለቲካ አክቲቪስቶች ውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሌላቸው፣ እንደ ገዥ ፓርቲ እንኳን በውስጣቸው ተሃድሶ የማያካሂዱ፣ በቆሙበት ተገትረው የቀሩ፣ የመደማመጥ፣ የመከራከርና የመደራደር ባህል እምብዛም ያላዳበሩ፣ ሐሳባቸውንና እምነታቸውን በሌላው ላይ በመጫን ማሸነፍ እንጂ በሰጥቶ መቀበል መርህ ተሸናፊነትን ለመቀበል ዝግጁ ያልሆኑ፣ ለገዥ ፓርቲም ሆነ ለአገር አስቸጋሪዎች የሆኑ ናቸው፡፡
የዚህ አገር የፖለቲካ ባህልና የሕዝቡ ንቃተ ሕሊና እየተለወጠ ሲሆን፣ እነርሱ እዚያው በድሮው ግንባቸው ተቀርቅረው የቀሩ ያስመስልባቸዋል፡፡ ለመኖር የሚመኙት ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥትና ፓርቲ ጥቃቅን ስህተቶችን እየፈለጉ፣ ወይም በቀድሞ ታሪክ በማጥላላትና ሁልጊዜ በመንግሥት ስለሚሠሩ ሥራዎች አቃቂር በማውጣትና በመተቸት በተቃርኖ ውስጥ ነው፡፡ እነርሱ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ጥሩ ሥራ ሠርቶ ከሕዝቡ ምሥጋና እንዲያገኝ አይፈልጉም፡፡ መንግሥት ተወዳጅነት ካተረፈ ሕዝቡ ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት እንጂ እነርሱን የሚመርጥ ስላልሆነ፣ በዚህ አካሄዳቸው ሥልጣን ላይ ባሉት መቅናትና ምቀኝነት አንደኛው መገለጫ ባህሪያቸው ሆኖ ይታያል፡፡ እነርሱ የተለየና የተሻለ አማራጭ ሐሳብ ለሕዝብ በማቅረብ በሚሻሉበት ሕዝብ እንዲመርጣቸው ሳይሆን፣ አብዛኞቹ ሕዝቡን ከመንግሥት ጋር በማጋጨት፣ ተስፋ በማስቆረጥና የሕዝቡን ለልማት መነሳሳትን በመፃረር በሚመስል ተግባር ውስጥ ተቸንክረውና በብሔር ፖለቲካ ውስጥ ተደብቀው ለዝና ፍለጋና ለሥልጣን የሚያደቡ ይመስላሉ፡፡ በዚህ ዓይነት አስተሳሰባቸውና አመለካከታቸው ለሕዝብ አማራጭ ኃይሎች በመሆን ፋንታ፣ ደንቃራና ችግር ፈጣሪነታቸው ነው ጎልቶ የሚታየው፡፡
እነዚህ ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ በአብዛኛው የሚያውቁት የትግል ሥልት በኃይልና በማስፈራራት በተቃርኖ ላይ የሚመሠረት በመሆኑ፣ ከመንግሥት መሪዎች ጋር ያልሆነ ግጭት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ተግባብተው መሥራት ስለማይችሉ በጠላትነት መተያየት ይሆናል፡፡ የአንድ የሙያ ማኅበር ያህል እንኳን በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ማሳደርና እንወክላለን የሚሉትን ሕዝብ ጉዳይ ማስፈጸም የማይችሉና ተገልለው የሚኖሩ፣ አገርን የሚያምሱ ፍጡራን ይሆናሉ፡፡ የእነርሱ ግብ የሚመስላቸው መንግሥትን በመቃወም ጀግንነታቸውን ማሳየት ነው፡፡ እነዚህ ዓይነት ፓርቲዎች ናቸው በአብዛኛው 138 ሆነው በአገሪቱ የፖለቲካ ሜዳ የሚንጎማለሉት፡፡
(ክፍል አራት ሳምንት ይቀጥላል)
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡