የኮሮና ወረርሽኝ በአገሪቱ ዋና ዋና የግብርና ምርቶች ግብይት ላይ ያሳድራል የተባለው ሥጋት በተቃራኒ እየሆነ ስለመምጣቱ አመላካች እንደሆነ የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ወርሐዊ የግብይት አፈጻጸም ሲሆን፣ የሰኔ 2012 ዓ.ም. ግብይቱም ይህንኑ የሚያመላክት ነው፡፡
ወርኃዊ የግብይት ሒደቱን በተመለከተ ምርት ገበያው ባወጣው መረጃ መሠረት፣ የኮሮና ሥርጭት እየተስፋፋ በመጣበት በአሁኑ ወቅት የወጪ ንግዱ በዘላቂነት እንዲካሄድ የሚያስችለው የዘመናዊ ግብይት ሥርዓት ተጠናክሮ፣ በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም. 62,542 ቶን ምርት በ3.72 ቢሊዮን ብር ማገበያየቱ ተገልጿል፡፡ በሰኔ 2012 ዓ.ም. በ22 የግብይት ቀናት 27,332 ቶን ቡና፣ 21,943 ቶን ሰሊጥ፣ 7846 ቶን ማሾ፣ 3922 ቶን ቦሎቄና 1,499 ቶን አኩሪ አተር ግብይት የተፈጸመ ሲሆን፣ የምርት አቅርቦቱም እንደጨመረ ገልጿል፡፡
በዚህ ወር በተፈጸመው ግብይት ቡና 44 በመቶ በመጠንና 66 በመቶ በዋጋ በመሸፈን ቀዳሚ ሲሆን፣ ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር በመጠን አምስት በመቶና በዋጋ 33 በመቶ እንደጨመረ ይኸው የምርት ገበያው መረጃ ያመላክታል፡፡ በወሩ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ 18,037 ቶን ያልታጠበ ቡና በ1.46 ቢሊዮን ብርና 419 ቶን የታጠበ ቡና በ53 ሚሊዮን ብር ሲገበያይ፣ 6,210 ቶን ለአገር ውስጥ ገበያ የሚቀርብ ቡና በ518 ሚሊዮን ብርና 2,665 ቶን ስፔሻሊቲ ቡና በ411 ሚሊዮን ብር ግብይታቸው መፈጸሙንም ገልጿል፡፡
በሰኔ 2012 ዓ.ም. የተካሄደው የሰሊጥ ግብይት ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ ጭማሪ የተያበት መሆኑን የጠቀሰው መረጃ 21,943 ቶን ሰሊጥ በ944 ሚሊዮን ብር የተገበያየ ሲሆን፣ ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር በመጠን 40 በመቶና በዋጋ 39 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ ከአጠቃላይ ግብይቱም 35 በመቶ በመጠንና 25 በመቶ በዋጋ ድርሻ ይዞ ቡናን ይከተላል ተብሏል፡፡ አያይዞም ይህ የሰሊጥ ግብይት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ ደግሞ በመጠን 281 በመቶ በዋጋ 168 በመቶ ጭማሪ ያሳየ መሆኑንም ከምርት ገበያው መረጃ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
የወሩን ተጨማሪ የግብይት ሒደቶች ላይ እንዳመለከተውም 7,846 ቶን አረንጓዴ ማሾ በ228 ሚሊዮን ብር የተገበያየ ሲሆን፣ ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር በሦስት እጥፍ ማደግ መቻሉን ነው፡፡ በሰኔ ወር 2,668 ቶን ነጭ ቦሎቄና 1,254 ቶን ቀይ ቦሎቄ በ88 ሚሊዮን ብር የተገበያየ ሲሆን፣ ካለፈው ወር በመጠን ስምንት በመቶ በዋጋ ዘጠኝ በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር በመጠን 127 በመቶና በዋጋ 148 በመቶ አድጓል፡፡ በወሩ 1,499 ቶን አኩሪ አተርም በ19 ሚሊዮን ብር ግብይቱ ስለመፈጸሙ ያሳያል፡፡
ወደ ሁሉም የምርት ገበያው ቅርንጫፎች በዚህ ወር የገባው የምርት መጠን ከ60 ሺሕ ቶን በላይ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ቡና 46 በመቶ ድርሻ እንዳለው በመጥቀስም ከቀደመው የግንቦት ወር አቅርቦት ጋር ሲተያይ ወደ ምርት ገበያው የመጣው ቡናና ሰሊጥ በተመሳሳይ በ19 በመቶ ከፍ ሲል ሲል፣ በተለይ የሰሊጥ አቅርቦት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር በሦስት እጥፍ ጭማሪ ማሳየቱንም ገልጿል፡፡