Wednesday, June 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዘመን ባንክ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ አተረፈ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለ11 ዓመታት በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው ዘመን ባንክ በ2012 ዓ.ም. በታሪኩ ከፍተኛ የተባለውን የ1.05 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገቡ ታወቀ፡፡

ሪፖርተር ከባንኩ ባገኘው መረጃ መሠረት፣ በ2012 ሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ያገኘው የትርፍ መጠን የ59 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡ ይህ የዓመቱ ከፍተኛ የትርፍ ዕድገት እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡ በ2011 ዓ.ም. ባንኩ ከታክስ በፊት ያስመዘገበው የትርፍ መጠን 658 ሚሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡

ዘንድሮ ያስመዘገበው የትርፍ መጠን በዘመን ባንክ እንቅስቃሴ ለመጀመርያ ጊዜ የተገኘ ሲሆን፣ የትርፍ መጠናቸውን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ ከቻሉ ጥቂት ባንኮች መካከል አንዱ አድርጎታል፡፡

ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ በማስመዝገብ የሚጠቀሱት አዋሽ፣ ዳሸን፣ ወጋገን፣ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ እንዲሁም አቢሲንያ ሲሆኑ፣ ዘመን ባንክም ከእነዚህ ከፍተኛ አትራፊ ባንኮች ጎራ መቀላቀል ችሏል፡፡  

እንደ ሪፖርተር ምንጮች ከሆነ፣ ዘመን ባንክ ይህን ያህል የትርፍ ዕድገት ያስመዘገበው የተለያዩ ዕርምጃዎችን በመውሰዱ ነው፡፡ ከትርፍ ዕድገቱ ባሻገር የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ወደ 14.5 ቢሊዮን ብር ማሳደግ እንደቻለ ሲጠቀስ፣ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ የነበረው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 11.4 ቢሊዮን ብር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ ረገድ ከቀደሙት ዓመታት የተሻለ ዕድገት የታየበት ውጤት ማስመዝገብ እንደቻለም ተወስቷል፡፡

የባንኩን የብድር እንቅስቃሴ ላይ ስለታየው ዕድገት በተገለጸው መሠረት፣ በዓመቱ መጨረሻ የብድር ክምችቱ አሥር ቢሊዮን ብር ላይ ደርሷል፡፡ ዓምና የባንኩ የብድር መጠን 7.7 ቢሊዮን ብር እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዘመን ባንክ በዓመቱ ከፍተኛ የተባለውን ትርፍ በማስመዝገቡ የትርፍ ድርሻ ክፍፍል መጠኑን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድገው ይጠበቃል፡፡ የትርፍ ዕድገቱ የ46 በመቶ የትርፍ ድርሻ ክፍፍል የሚያስገኝ ውጤት እንዳመጣ ተጠቅሷል፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ በኢኮኖሚው ላይ ጫና እያሳደረ ባለበት ወቅት፣ ዘመን ባንክም ሆነ ሌሎች ባንኮች ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ለተለያዩ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች የብድር ወለድ ቅናሽን ጨምሮ የብድር መክፈያ ጊዜን ማራዘምን ጨምሮ በተለያዩ አገልግሎቶቻቸው ላይ የሚያስፍሉበትን ዋጋ አሻሽለዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ለውጦችን ባደረጉበት ወቅትም ቢሆን ባንኮቹ ከአትራፊነታቸው ፈቅ እንደላሉ እየታየ ነው፡፡

ዘመን ባንክ በተለይ ለአበባና ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የሦስት ወር የብድር ወለድ ስረዛ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ እንዲህ ያሉ ተመሳሳይ ዕርምጃዎችን ወስዶም ቢሆን ከቀደመው ጊዜ በላይ አትራፊ ሊሆን ችሏል፡፡

የባንኩን ዓመታዊ አፈጻጸም የሚመለከተው ሌላው መረጃ ደግሞ የተበላሸ የብድር መጠኑን ከሁለት በመቶ በታች ማድረጉ ነው፡፡ እንደ መረጃው ከሆነ ባንኩ ዓምና የነበረው የተበላሸ የብድር መጠኑ 2.8 በመቶ ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ይህ መጠን ወደ 1.9 በመቶ ዝቅ እንዳለ ተጠቅሷል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ቅርንጫፍ ባንኮችን ባለመክፈት ከአገሪቱ ባንኮች በተለየ መንገድ ሲንቀሳቀስ የቆየው ዘመን ባንክ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ቅርንጫፎቹን በማስፋፋት ላይ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት 52 ቅርንጫፎችን በመክፈት አገልግሎቶቹን እያዳረሰ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች