Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ሐሰተኛ ወሬ እንዴት አድርጎን እንደ ከረመ ሁላችንም ስለደረሰብን እናውቀዋለን፡፡ እኔና ጎረቤቶቼ በዚህ በኩል ቤተ ክርስቲያን ተቃጠለ፣ በዚያ በኩል ቤቶቻችን በእሳት ሊያወድሙ እየመጡ ነው፣ ራቅ ካሉ ሥፍራዎች ደግሞ ከተማው ሙሉ በሙሉ እየነደደ ነው የሚሉ ወሬዎች ሲያምሱን ከርመዋል፡፡ በተጨማሪም ውኃ ተበከለ ተብሎም ተተረማምሰናል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ ደግሞ ከምናውቃቸው ሰዎች ከሚደርሱን የተጣሩ መረጃዎች በላይ፣ እጅግ በጣም አስደንጋጭ ወሬዎችም እየደረሱን ተሳቅቀናል፡፡ ምንም እንኳ ሕይወታቸውን በጭካኔ ያጡ ወገኖቻችንና ንብረታቸው የወደመባቸውን ምስኪኖች ስናስብ የእኛ ጭንቀት ያን ያህል ቢሆንም፣ በአገር ላይ የሚፈጥረው ችግር እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ይህንን መንደርደሪያ በማድረግ ‹‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው›› የድሮ ገጠመኜን ልንገራችሁ፡፡

በጎልማሳነቴ ዘመን የማያቸው በርካታ ነገሮች ከድሮው የወጣትነቴ ዘመን ያን ያህል ፈቅ ባለማለታቸው በጣም ይገርመኛል፡፡ ለምሳሌ ድሮ ተማሪዎች በነበርንበት ጊዜ ‘የተማሪ ተንኮል’ ውጤት የሆኑ በርካታ ድርጊቶች ይፈጸሙ ነበር፡፡ አንደኛው የሆነ ነገር ፈጥሮ ማስወራት ነው፡፡ አንድ ጊዜ የ11ኛ ክፍል የእንግሊዝኛ ቋንቋ አስተማሪያችን ክፍል ውስጥ ፈተና እየሰጡን ሳለ፣ ማን እንደጻፈው የማይታወቅ በአራት ማዕዘን ቅርፅ የተጻፈ ጽሑፍ ተሠራጨ፡፡ ጽሑፉ የሚለው፣ ‹‹ትምህርት ቤታችን በወታደር ተከቦ ሁለት መምህራን እየተፈለጉ ነው፤›› የሚል ነው፡፡ በዘመነ ደርግ እንዲህ ዓይነት መረጃ ሲሰማ የማይደነግጥ ስላልነበር ጽሑፉ ለመምህራችን እንዲደርሳቸው ይደረጋል፡፡ ሲያነቡት በጣም ይደነግጣሉ፡፡ ‹‹ቆይ አጣርቼ ልምጣ፤›› ብለው በር ከፍተው ሲወጡ ፈተናው የከበዳቸው ተማሪዎች ተኮራርጀው ካበቁ በኋላ ከየአቅጣጫው ሳቅ ይሰማ ጀመር፡፡

መምህራችን ዳይሬክተሩ ቢሮም ሆነ የተለያዩ ቦታዎች አዳርሰው ሲመለሱ ድንጋጤያቸው ወደ ቁጣ ተለውጧል፡፡ ‹‹ማን ነው ይኼንን ሐሰተኛ ወሬ ያመጣው?›› ብለው ሲጠይቁ አንዲት በረባሽነቷ የምትታወቅ ጓደኛችን፣ ‹‹በመስኮት በኩል ነው የተወረወረልን፤›› ብላ አቀዘቀዘቻቸው፡፡ ምንም ያልነቁት መምህር የፈተና ወረቀታችንን ሰብስበው ከክፍላችን ሲወጡ ሁካታው ቀጠለ፡፡ ሐሰተኛው ወሬ የተሠራጨው ለፈተና ባልተዘጋጁ ተማሪዎች ምክንያት መሆኑ ዘግይቶ ወሬው ቢደርሰንም፣ በነጋታው ውጤታችንን ይዘው ይመጣሉ ያልናቸው መምህራችን፣ ‹‹ፈተናው በመኮራረጅ ምክንያት ያልተጠበቀ ውጤት ስለተገኘበት ተሰርዟል፡፡ ስለዚህ አሁን ሌላ ከባድ ፈተና ይዤ ስለመጣሁ እንቀጥል. . .›› ሲሉ የተንኮሉን ድራማ ያቀነባበሩት በድንጋጤ ተመቱ፡፡ እንደተባለውም ጎበዞች ሲያልፉ፣ ሰነፎች ተገቢውን ዋጋ አገኙ፡፡

አንድ ጊዜ ደግሞ ለማትሪክ ፈተና ስንዘጋጅ አንድ ተንኮል ተጠነሰሰ፡፡ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ትራንስክሪፕታችን ላይ ጥሩ ውጤት ማግኘት የተለመደ ስለነበር፣ ጎበዞቹ ሰነፎቹን በተቻላቸው መጠን እንዲረዱ ትዕዛዝ በጥብቅ ተላለፈ፡፡ የትዕዛዙ አስተላላፊዎች በክፍላችን ውስጥ ያሉ ጉልቤዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ከዱላና ከስድብ በስተቀር ምንም ችሎታ የሌላቸው ጉልበተኞች በኃይላቸው ተማምነው ሳያጠኑ ለትምህርት ቤት ፈተና ይቀርባሉ፡፡ በተባለው መሠረት መልስ እየተሠራ በዘዴ ይተላለፍላቸዋል፡፡ ሁሉንም የትምህርት ዓይነቶች በዚህ ዘዴ ከኮረጁ በኋላ ውጤት ሲመጣ ያልጠበቁትን ማርክ አገኙ፡፡ በሁሉም ትምህርት ወድቀዋል፡፡ በዚህ የተነሳ ከፍተኛ አምባጓሮ ተፈጠረ፡፡ ከክፍላችንና ከሰክሽናችን አንደኛ በመውጣት የሚታወቀው ጎበዙ ተማሪ፣ ‹‹እኛ መልሱን በብርቄ (ረባሿ ተማሪ) በኩል ስንልክ የሆነ ችግር ተፈጥሮ እንጂ ሽወዳ አልነበረም፤›› ሲላቸው ረባሿ ተማሪ ደግሞ፣ ‹‹ባንኮርጅ ምን እንሆናለን ብዬ ነው መልሱን እየቀየርኩ የላኩላችሁ. . .›› ብላ ኩም አደረገቻቸው፡፡ እንዲያውም፣ ‹‹ከመኮረጅ ሞት ይሻላል!›› ብላ መፈክር ስታወርድ አብረው አስተጋብተው በሰላም ተለያየን፡፡

ይኼው በዚህ ዘመን ኩረጃ የአገር ጠላት ሆኖ በመንግሥት ደረጃ ብዙ እየተባለበት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የትምህርት ቤት ኩረጃ ለአገር ፀር በመሆኑ ሊወገዝ ይገባዋል፡፡ በኩረጃ ውጤት ማግኘትና ተመርቆ ለሥራ መዘጋጀት የሚጎዳው አገርን በመሆኑ በእርግጥም ዘመቻ ያስፈልገዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቤተሰብ፣ ማኅበረሰቡ፣ የትምህርት ባለሙያዎችና የመንግሥት አካላት ርብርብ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ አሁን ግን ኩረጃን በተመለከተ እዚህ ላይ ላብቃና ስለሌሎች ኩረጃዎች የታዘብኩትን ልንገራችሁ፡፡ ድሮ በዚያ ዘመን እንደ ዛሬው ቴክኖሎጂ ባልተስፋፋበት መጻሕፍትንም ሆነ ሌሎች የሚነበቡ ነገሮች መዋዋስ የተለመደ ነበር፡፡ በእርግጥ ብዙ ባይሆንም ዛሬም አለ፡፡ በዚያን ጊዜ ከሚያነበውና ግንዛቤውን ከሚያሳድገው ይልቅ በወሬ ቅብብሎሽ ብቻ ያልተጣራ መረጃ የሚሰበስበው ይበዛ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ሐሜትና አሉባልታ የበላይነት ነበራቸው፡፡

በአንድ ወቅት ሞራል ገንቢ ድርጅት (ሞገድ) እና ተስፋ አስቆራጭ ድርጅት (ተአድ) በሚባሉ ምህፃረ ቃላት ራሳቸውን የሰየሙ ወገኖች የወሬ ፋብሪካውን ይመሩት ነበር፡፡ ለአንዱ ወገን የሚያስደስት ወሬ ሲነገር ‹‹ሞገድ›› ሲባል፣ የሚያናድድ ወሬ ያመጣው ደግሞ ‹‹ተአድ›› እየተባለ አገሩ ሥራ ፈትቶ ሐሜትና አሉባልታ መሰለቅ የተለመደ ነበር፡፡ በዚህ ዘመን በዚህ ስያሜ የሚታወቁ ባይኖሩም መረጃን ከምንጩ ከመቅዳት ይልቅ መያዣ መጨበጫ የሌላቸው ወሬዎች ይሰማሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ የሰዎችን ሰብዕና፣ መልካም ስምና ዝና የሚያጎድፉ አሉባልታዎች ሲናፈሱ ለምን? እንዴት? መቼ? የት? ወዘተ. ከማለት ይልቅ አብሮ ማናፈስ የተለመደ ነው፡፡ እኔን ከመሰለ ተራ ግለሰብ አንስቶ ታታሪ ገበሬዎች፣ መምህራን፣ ነጋዴዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ወዘተ. በአሉባልታ ምክንያት ችግር ውስጥ ሲገቡ ታዝቤያለሁ፡፡ ሰዎችን አሳዝኖ ሕይወታቸውን ማበላሸት ‹‹የተማሪ ተንኮል›› ሳይሆን፣ አገር አጥፊነት ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሰዓት ዕላፊ ታወጀ አልታወጀ ከመባባል ይልቅ አፍ ዕላፊ በራስ ላይ ማወጅ ይሻላል፡፡ አይመስላችሁም? ሰሞኑን አገሪቱ ከባድ ችግር ውስጥ ገብታ በርካቶች ሲሞቱና ንብረት ሲወድም፣ በየመንደሩ ሲሰማ የነበረው ወሬ የሚያሳብድ ነበር፡፡ ወሬውን እንደ ሰደድ እሳት አገር እንዲያዳርስ ከማድረግ ይልቅ፣ ከምንጩ ለማጥራት የሚደረግ ጥረት አይታይም፡፡ በመንግሥት በኩልም ፈጣን ምላሽ ስለሌለ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ነገር ግን ራስንም አገርንም ከጥፋት ለመታደግ መረጃን ጥራት ያለው ማድረግ ላይ መበርታት ያስፈልገናል፡፡ ካልሆነ ግን ችግሩ የከፋ ነው የሚሆነው፡፡

(ታመነ ገበየሁ፣ ከቄራ)       

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...