Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዋሽ ባንክ ከታክስ በፊት ከ4.19 ቢሊዮን ብር በላይ አተረፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከግል ባንኮች ቀዳሚውን የገበያ ድርሻ ይዞ የዘለቀው አዋሽ ባንክ፣ በ2012 የሒሳብ ዓመት ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ከ4.19 ቢሊዮን ብር በላይ አተረፈ፡፡ ይህ ትርፍም ከግል ባንኮች የመሪነት ሥፍራ በመያዝ እንዲቀጥል አድርጎታል፡፡

የ2012 የሒሳብ ዓመት የባንኩን አፈጻጸም የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ ተመዝግቧል፡፡  

ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ይህንን ያህል ትርፍ ያስመዘገበው በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት፣ በብድር ወለድ ምጣኔዎች ቅናሽ አድርጎ ጭምር መሆኑ ተገልጿል፡፡ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ የተወሰዱ ዕርምጃዎች ከወለድ የሚገኘውን ገቢ በተወሰነ ደረጃ ቢቀንሱም፣ አሁንም የግል ባንኮች ቀዳሚ የተባለውን ትርፍ ይዞ መቀጠሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡  

በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት አዋሽ ባንክ ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ አዳዲስ ብድሮች የሰጠ ሲሆን፣ ይህም የ20 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ በሰኔ 2012 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ 56.8 ቢሊዮን ብር መድረሱ ታውቋል፡፡ በተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ ረገድም ውጤት እንዳገኘም የሚያመለክተው የባንኩ መረጃ፣ በሒሳብ ዓመቱ አዳዲስ ቅርንጫፎችን ከፍቶ ለአገልግሎት ማብቃቱን አመልክቷል፡፡ ከ716,000 በላይ አዳዲስ ደንበኞች ወደ ባንኩ ማምጣት በመቻሉ ለባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት አስተዋጽኦ አድርጓል ተብሏል፡፡

በቀዳሚው በጀት ዓመት ትልልቅ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንና የግል ድርጅቶችን የባንኩ ደንበኞች ማድረግ መሆኑን፣ የባንኩ የኤቲኤም፣ የሞባይል ባንኪንግና የኢንተርኔት ባንኪንግ አዳዲስ ተጠቃሚዎችንም ለማፍራት በመቻሉም፣ የባንኩ ጠቅላላ የተቀማጭ ሒሳብ መጠን ከ73.6 ቢሊዮን በላይ መድረሱ ተገልጿል፡፡  የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ1.6 ቢሊዮን ብር ወይም የ19 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ተብሏል፡፡

ከተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች የሚያገኛቸው ገቢዎች በመጨመራቸው አዋሽ ባንክ የገቢ ምንጮቹን ለማስፋትና ለማሳደግ መቻሉን፣ ከዚህ መሠረት ከዲጂታል ባንኪንግ የአገልግሎት ዘርፍ፣ ከአገልግሎት ክፍያ፣ እንዲሁም ከመንግሥት የግምጃ ቤት ግዥና ከብሔራዊ ባንክ ቦንድ ግዥ የተገኙ ገቢዎች በአማካይ ከ30 በመቶ በላይ ጭማሪ ማሳየታቸው ተጠቁሟል፡፡ በአኃዛዊ መረጃው መሠረት ባለፈው ዓመት 7.9 ቢሊዮን ብር የነበረው የባንኩ ጠቅላላ ገቢ፣ በ2012 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ 10.2 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡  

ባንኩ ከግል ባንኮች ብልጫ ያሳየበት ነው የተባለለትን ጠቅላላ ሀብት በ15.93 ቢሊዮን ብር በማሳደግ 95.6 ቢሊዮን ብር ማድረሱ ታውቋል፡፡ ባለፈው ዓመት መጨረሻ  የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 79.6 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስገዳጅ የቦንድ ግዥ መመርያን በማስቀረቱ፣ አዋሽ ባንክ ለሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች ከሚሰጠው ብድር ላይ የሚከፈለውን የወለድ ምጣኔ እስከ 4.5 በመቶ የወለድ ቅናሽ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃና በኢትዮጵያም የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመቀነስ፣ በተለይም በወረርሽኙ ክፉኛ የተጎዱትን የኢኮኖሚ ዘርፎች ማለትም ለሆቴሎች ለአስጎብኝ ድርጅቶችና ለአበባ አምራቾች የወለድ ምጣኔ ወደ ሰባት በመቶ ዝቅ እንዲል ማድረጉ አይዘነጋም፡፡

አዋሽ ባንክ በ1987 ዓ.ም. ከደርግ ውድቀት በኋላ የመጀመርያው የግል ባንክ በመሆን ሥራ የጀመረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የተከፈለ ካፒታሉ 5.84 ቢሊዮን ሲደርስ፣ የቅርንጫፎቹ ብዛትም 466 ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች