Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርከሩብ ዓመት አርቀን ስናልም!

ከሩብ ዓመት አርቀን ስናልም!

ቀን:

በመንበሩ አለባቸው

ያው ሁላችንም እንዴት እንደባጀን አስታዋሽ አያስፈልግም፡፡ በፍርኃትም፣ በሥጋትም በሆነ እርግጠኝነት በጎደለው የሥጋትና የጥንቃቄ ቅንፍ ውስጥ መቀንበባችን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ስለዚህ ሕይወትን ተለምዶ እንደለገሰን ሳይሆን፣ የየወቅቱ ዓውድ እንደፈቀደልን ማስተናገድ፣ እግረ መንገድም ሕይወታችን በምንፈልገው ተገማች ዓውድ የተገራ እንዲሆን መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ረዥም ዓይተን የሕይወትን ግብ የማንጥል ከሆነ ሁሌም ቢሆን በድንገቴ የጅረት ፈረሰኛ ሕይወታችን፣ ኑሯችንና እኛነታችን ማላጋት መቀጠሉ የማይቀር ነው፡፡ እንደ እኛ አገር ያልሠራው ጉዳይ ሚዛን ከደፋ ደግሞ እያንዳንዱ ጧት ሁሌም የተወሳሰበ አጀንዳ እየሰጠ የመልካሙን ጊዜ ጥባት ጭላንጭሉም እንዳይታይ ማድረጉ አይቀርም፡፡ እስኪ ዝም ብለህ የዛሬ ጧትህን አገራዊ ጭንቀት አስተውል፡፡ ኮሮና፣ ሰላም፣ ህዳሴ፣ ማንነት፣ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ኑሮ፣ ወዘተ. ሌላም አጀንዳ መጨመር ይቻላል፡፡ ስለዚህ ሁሌም ወቅት ጥሎን ሳይሄድ ፍላጎታችንን በደርዝና ቅደም ተከተል ተረድተንና ሩቅ ተመልክተን መሠረት ካላስያዝን፣ እንደተለመደው ያልተገባ ዋጋ እየከፈልን፣ የምንፈልገውንም ሳናገኝ የሾተላይ እምቡላሌውን መዞር እንቀጥላለን፡፡ ስለዚህ ቀልብ መግዛትና የምንሠራውን ማወቅ የጊዜው ቅድሚያ አጀንዳ ነው፡፡ ለዚህ ልቦና ይስጠን፣ ፈጣሪም ይርዳን፣ ምጡንም አጭር ያድርግልን!

ለዛሬ ያው ሌላውን ታሪካዊ ወረርሽኝ የዓባይን ጉዳይ ባወጋ አንባቢያን ጆሮ አይነፍጉኝም ብዬ አስባለሁ፡፡ እንግዲህ ስለዓባይ ስናወራ ሁልጊዜ ጉዳዩን ለምን ከግብፅ አንፃር ብቻ እንደምናየው ይገርመኛል፡፡ እሷ ራስዋን ከዓባይ አንፃር ትመልከት፣ ምክንያቱም የዓባይ ስጦታ ነኝ ብላ ታምናለች፡፡ እኛ ለምን ብለን ራሳችንን በእሷ እምነትና አጀንዳ ውስጥ እንቀረቅራለን? እዚህ ጋ ሁሌም የሚገርመኝ ጉዳይ ግብፅን ለቀቅ አድርገን ስናጤን ሥነ ቃሉ፣ ፉከራውና ተረቱ ከጥቅሙ ይልቅ እህህታ፣ እየየ፣ ቁጭት የበዛበት መሆኑን ስንገነዘብ ታዝበን በዝምታ መዋጥ ብቻ ሳይሆን መጠየቅ አለብን፡፡ ለምን ሁልጊዜ በትካዜ የምንዋጥበት ወንዝ ሆነ ማለት አለብን፡፡ ለምን ለሌሎች 86 በመቶ የውኃ መጠን የሚለግስ ቸር ወንዝ፣ አንተና እኔ አገር ለያዥ ለገራዥ አስቸግሮ ለፈረቃ ቦኖ ጣለን ማለት አለብን፡፡ ግብፅ ባጉረመረመች ቁጥር ራሳችን ተግ እያልን ነው ወይስ ከልባችን ልናስገብረው ጥረት አድርገን አጉራጠናኝ ብሎናል? ማለት አለብን፡፡ ውድድራችንና እልህአችንን ለምን ከግብፅ ጋር እናያይዛለን? ከራሳችን ጋር የምንወዳደረው መቼ ነው? ፍላጎታችንና አቅማችንን እናውቀዋለን? ወይስ ምኞት ብቻ ነን? ፍላጎታችንን ለማሳካት ምን እንደሚጠይቅ ተገንዝበናል? ወይስ ግብፅ አጀንዳውን ስትሰጠንና በሜዳችን ስትጫወት ተቀብለን እያማረርን ከርመናል? የሚሉ የተለያዩ ጉዳዮችን በጥልቀት ማየት ይኖርብናል፡፡

- Advertisement -

ሰሞኑን ከህዳሴ ግድቡ ድርድርና ውኃ ሙሌት ጋር በተያያዘ የስሜት መጦዝ፣ እልህ፣ ማብራሪያና አስተያየት ሲዘንብ እየሰማን ነው፡፡ አንዳንዱ በመገናኛ ብዙኃን የምንሰማው ሐሳብ ጉዳዩን ከተርታው ሕዝብ በላይ ሳይረዱ እንደገባቸው ሆነው ከሚያወሩና በምሁር ስም ከሚቀርቡ እንግዶች መሆኑን ስናይ፣ አሁንም መንገዳችን ውዥንብር እንዳንዣበበት ያሳብቃል፡፡ አንዱን በምሁር ካባ የቀረበ እንግዳ በሰሞኑ የዓረብ ሊግ ዜና ምክንያት ስሜቱን መቆጣጠር ተስኖት፣ ‹የዓረብ ሊግም የአፍሪካ ኅብረትም አባል የሆኑ አገሮችን የአፍሪካ ኅብረት ማባረር አለበት› ሲል ሰማሁት፡፡ ወዳጄ. . . ፕሮፌሰር መስፍን እንዳሉት ከጀርባው ማለፊያ የጠላፊ ሠፈር ጠጅ የጋለበው ይመስለኛል፡፡ ሰውየው ሰሜን አፍሪካ ዓረብም አፍሪካም መሆኑን ዘንግቶታል፡፡ የምናወራት ግብፅ ራሷ አፍሪካም፣ ዓረብም፣ ሲለጠጥ እስያም መሆኗን ማን በነገረው? ምናልባት ስሜቱን ያነሳሳው ዓረብ ያልሆኑት አፍሪካውያን ጎረቤቶቻችን ሊሆኑ ይችላሉ፣ ‹ቢሆንም› ነው ያሉት ሃምሳ አለቃ ገብሩ? ለምን ግብፅና የተወጫበሩ አጃቢዎቿ በተነፈሱ ቁጥር ወጀብ እንደመታው መርከብ እንዋላለን? የሚለው ነው መሠረታዊ ጉዳይ፡፡

ከእኛ በዕድሜና ይኼን አገር በመረዳት የላቁ አባቶች ከዚህ በፊት የነገሩንን ስናስታውስ ቁጭታችን ሰማይ ሊነካ ይችላል፣ ግን ቁጭት ያው ስሜት ነው፡፡ ከትናንት ወደ ተሻለ ዛሬ ካልተለወጥን ትናንትም ተቆጨን ዛሬ ልዩነት የለውም፡፡ ነፍሳቸውን ይማርና በአንድ ወቅት ደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ሥላሴ ግብፅን የተቀየሙ የቀድሞ የሱዳንና የግብፅ ጌቶች እንግሊዞች፣ በአንድ ወቅት ትነት ቆጣቢ ትልቅ ግድብ መሰል ማጠራቀሚያ ጣና ሐይቅ መውጫ ላይ ለመሥራት ጥያቄ ሲያቀርቡ በወቅቱ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አንድም ተዛማጅ የግዛት ጥያቄን በመፍራት፣ በሌላ በኩልም ከዓባይ ማዶ የሚነሳ የዙፋን ተገዳዳሪን በመሥጋት፣ እንዲሁም ለፓን አፍሪካ ንቅናቄ ለሚያደርጉት ጥረት የፕሬዚዳንት ናስርን ድጋፍ ላለማበላሸት አጉራጠናኝ ብለው ዕድሉን እንዳልተጠቀሙበት አውግተናል፡፡

ይኼንኑ ሀቅ በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ምርምር የሚያደርጉት ወዳጄ ተስፋዬ ታፈሰም (ፕሮፌሰር) ደግመው ነግረውናል፡፡ ታዲያ የቤት ሥራውን ያልጨረሰ አገር ላይ ሆነህ ግብፅ ምን ታድርግህ? እየተግባባን ነው? በወንዙ ላይ በምዕተ ዓመት የሚገኝ መናን ለመቀበል እንኳን በቂ የውስጥ ዝግጅት ኖሮን አያውቅም እያልኩ ነው፡፡ ይኼ እውነት ነው፡፡ በግብፅ በኩል ግን ቅኝ ገዥዎቿ ዳተኝነት ሲያሳዩና ዳቦ መከራ ሲሆንባት፣ ወደ ያኔዋ ሶቪዬት ኅብረት ዞራ አስዋንን ለመገንባት ብዥታ አልነበራትም፡፡ ሌሎች የቀደሙ ወዳጆቼ ምን ይሉኛል ብላ ግራና ቀኝ ለትዝብት አላማተረችም፡፡ ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር እንዴት እንደምትቆርጥ ጠንቅቃ ታውቅ ነበር ማለት ነው፡፡ እዚህ ጋ አንድ እውነት ልብ ማለት ይገባል፡፡ ግብፅ ሌላ አማራጭ ቢኖራትም፣ አራት በይፋ የሚታወቁና ዋና ዋና የከርሰ ምድር ውኃ ቋቶች (Aquifers) ባለቤት ብትሆንም፣ እኔ የዓባይ ስጦታ ነኝ ብላ ራዕይዋን ቀርፃለች፡፡ አገሩን፣ ሕዝቡንና ሥርዓቷንም በዚያ ረዥም ሥዕል መሠረት በእውነትም፣ በውሽትም ስትቀርፅ፣ ስትገነባና ስትሠራ ኖራለች፡፡ ውኃ ህልውናዬ ነው ብላ ሳትታክት፣ ሳትሰለች፣ ሳትደክምና ሳታርፍ ሠርታለች፡፡ ይኼ ደግሞ ዝም ብሎ የሚነገር አይደለም፡፡

ለምን ይመስልሃል? በርካታ ዜጎቿ በውኃና ተዛማጅ መስኮች ስታስተምር የኖረችው? በየትኛውም የዓለም ጥግ በውኃ ዙሪያ የታወቁ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የተማሩ ኢትዮጵያውያንና ግብፃውያን ቁጥር አወዳድር፣ ምኗም ላይ አንደርስም፡፡ እነሱ ሩቅ ተልመው ያስተምራሉ፣ እኛ ‹በዕድሉ ይደግ› አስተሳሰብ እንጓዛለን፡፡ የመረረው ቀን መጥቶ በዘርፉ የተማሩ ወገኖችን ስንሻ፣ ማግኘቱ ጣር ሲሆን ትታዘባለህ፡፡ ለዚያውም ብዙ ጊዜ መንግሥቶቻችን ሊቆቻችንን ለመጠቀም ሲተጉ አናስተውልም፡፡ አስቦና አቅዶ የሠራና ውኃ ችግሬ አይደለም ብሎ ሞፈር ከደጁ የሚያስቆርጥ አገር ምን ታወዳድራለህ? አወቅንም አላወቅንም በወንዙ ጉዳይ አጀንዳ ሲሰጠን ብቻ እንድንጮህና አጀንዳ እስኪሰጠን በዘፈን እያሞጋገስን እንድትቆዝም ተደርገን ተቀይጠን ኖረናል፡፡ ተቃኝተናል ልንለው እንችላለን፡፡

ሌላም ማለት ይቻላል፡፡ ግብፅ በውኃ ዙሪያ የሚሠራ ትልቅ የምርምር ተቋም አላት፡፡ ውኃ ህልውናዬ ስላለች ይህ ተቋም በሦስት ፈረቃ ለ24 ሰዓታት ይሠራል፡፡ ለሁለት ዓመት ያገለገሉ ወጣት ተመራማሪዎች ወዲያው በተለያዩ የውጭ አገሮች ለከፍተኛ ትምህርት ተልከው እንዲማሩ ይደረጋል፡፡ ለምን ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ የሚያቅዱ ለምዕተ ዓመቱ እንጂ እንደኛ ለሩብ ዓመቱ አይደለም፡፡ ለማቀድም፣ ለመወሰንም፣ ለመደራደርም በትውልድ ላይ ያረፈ፣ በዕውቀት የተሣለ፣ አገሩን ከማወቅና ከመውደድ የዘለለ ዝግጁነት ይጠይቃል፡፡ እንኳን በውኃው ዘርፍ ዋና ጉዳዬ በምንለው ግብርና በሦስት ፈረቃ እንሠራለን ወይ? ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ የቤት ሥራችንን በአግባቡ ሳንሠራ በእህህታ መክረም ስለለመድን፣ አጀንዳ ከመስጠት ይልቅ በሰው አጀንዳ ተቀርቅረን ከመለካከያ ወረዳ መውጣት እንደተሳነን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ያ ዘመንና ልማድ የአሁኑ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ምዕራፍ ላይ ጥሎናል፡፡

ሌላም መጨመር ይቻላል፡፡ ሰሞኑን ከመገናኛ ብዙኃን እንደምንሰማው ብዙ የግብፅ ሕዝብ ስጦታው ነኝ የሚለው የዓባይ ወንዝ በአብዛው ከግብፅ እንጂ ከኢትዮጵያ እንደሚመነጭ እንዳያውቅ በጥናት ተሠርቶበታል፡፡ ዕድሜአቸው ከአምስት እስከ 11 ዓመት ለሚሆናቸው ሕፃናት የተዘጋጀ የመዝሙር መጽሐፍ፣ የዓለም ረዥሙ ወንዝ በደቡብ ከአስዋን እስከ ካይሮ በሰሜን የተዘረጋ ይለዋል፡፡ እኛ የ11 አገሮች ሀብት እንላለን፡፡ እርግጥ ነው የእነሱ ዋናውን የወንዙ ምንጭ የሆነችውን አገር መግደፍ ጉዳዩን ከኢትዮጵያውያን አዕምሮ ላይ መፋቅ እስካልቻለ ድረስ ችግር ባይሆንም፣ በተቃራኒው እኛ ደግሞ በዚህ ወንዝ ላይ ያለን ሀብት፣ መብት፣ የመጠቀም ራዕይና ተጨባጭ ጥረት ከተገቢ ቁጭር ጋር ምን እንደሆነ ግን በተጠና ሁኔታ የተሠራብን አይደለንም፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ ሳስበው ይገባናል ከሚለው ሥነ ልቦና ይልቅ ግብፅ ለምን ትከለክለናች ከሚል የተደፈርኩ መንፈስ የምንነሳ ይመስለኛል፡፡

ስለዚህ ቀድመን ግብፅን የጎሪጥ እናያለን (ከባህሪዋ ስንነሳ ዋጋዋ ነው፣ ግን አስባ ሠርታበታለች)፣ በቁጭት ጥርስ እናፋጫለን፣ ግብፅ ስትፈልግ እንወያያለን፣ መስመር ያለፈች ከመሰለን አንድ ሰሞን እሪታችንን እንለቃለን፡፡ የግብፅን ሚዲያና ጋዜጠኞች ከእኛዎቹ ጋር ስናወዳድር እነሱ ሳይታክቱ ሥራዬ ብለው ዓባይ የግብፅ ስለመሆኑ ይሠራሉ፡፡ የእኛ የወቅት ወዠብ ሲያመጣው እንደ ሰሞኑ ይዘምታሉ፡፡ ዘመቻ ደግሞ ዘላቂ ሊሆን አይችልም፡፡ ሐሳቡን ለመደገፍ ሌላም ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል፡፡ በአንድ ወቅት በግብፅ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚደገፈውን (SGP) የአነስተኛ የገንዘብ ድጋፍ ፕሮግራም ለመጎብኘት ዕድል ገጠመኝና ካይሮ ተገኘሁ፡፡

የፕሮግራሙ አስተባባሪ ልክ የዓባይ ተፋሰስ ፕሮግራም እንዳዘጋጀው ዓይነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሲዲ መዘጋጀቱን ነገረንና በመሰብሰቢያው አዳራሽ ውስጥ መዝሙር ተለቀቀልን፣ አዳመጥኩ፡፡ የናይል ልጆች ይልና የአሥር አገሮች ስም በዜማ ይጠራሉ፡፡ ኢትዮጵያ የሚል ስም በመዝሙር ውስጥ የለም! ይኼ የአጋጣሚ ግድፈት ይመስልሃል? ይኼን መዝሙር እየሰማ ያደገ የግብፅ ሕፃን በትውልድ እየተቀባበለ ስለናይል ኢትዮጵያ ምን አገባት ቢል እነሱ ግባቸው ነው፡፡ እኛ ግን ለምን የአገሬን ስም በመዝሙሩ አላካተተም ብለን አንብሰለሰልም፡፡ እንዲዘምር የሚያስገድደው ዘላቂ ሥራ መሥራት ግን ግዴታችን ይሆናል፡፡ ያንን አላደረግንም እያልኩ ነው፡፡ እንደ ህዳሴው እንቅልፍ የማያስተኛ ቁርጥ ያለ ጅማሮና ውሳኔ በአውሎ ንፋስ ውስጥ እውነትን የመቀበል ግዴታ እንደሚጥልባቸው መረዳት አያዳግትም፡፡ እያየን ያለነውም ይኼው ነው፡፡

ወዳጄ. . . በዚህ አትገረም፡፡ ይኼን የራስን ዜጋ ማደንቆ በአገርህ ትውልድም ላይ ለማስፋፋት ሲሠሩ እንደነበረ ስታውቅ የጉዳዩ ግዝፈትና በግብፅ አጀንዳ ገዥ መሬትህን ስትለቅ እንደኖርክ ይገልጽሃል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2005 እስከ 2009 በነበረው ወቅት ተማሪ ልጆች ከነበሩህና የልጆችህን ደብተር የማስቀመጥ ልማድ ካለህ፣ ደብተሮቹን ፈላልገህ ጀርባቸውን ተመልከት፡፡ ግብፅ የናይል ስጦታ ናት የሚል ባማረ የተፋሰሱ ንድፍ የታጀበ ጽሑፍ ያለው አንድ ደብተር አታጣም፡፡ በወቅቱ ደብተሮቹ ከራሷ ከግብፅ ወይም ከዱባይ የሚጫኑ እንደነበሩ ስታስብ፣ የሚገባህ ይገባሃል፡፡ እነሱ አስበው ደብተሩን ለኢትዮጵያዊ ሕፃናት ያዘጋጁታል፣ የዚህ አገር አስመጪ ነጋዴ ሳያስብ አስመጥቶ ይሸጥልናል፣ ልጆቻችን ግብፅ የዓባይ ስጦታ ነች የሚለውን እያመኑ ያድጋሉ፣ በኋላ ጨክኖ ከመለካከያ ወረዳ ወደ ገዥ መሬቱ ለመመለስ አቅመ ቢስ ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ በእንጉርጉሮ ‹ዓባዬ ቢሞላን› ከትውልድ እንደወረሱት እያፏጩት ልማዱን ወደ መጪው ትውልድ እያወረሱ ይቀጥሉልናል፡፡

ለምን ይመስልሃል ግብፅ በየዓለም አቀፍ ድርጅቱ አገራችን የፕሮጀክት ድጋፍ እንድታገኝ ተፅዕኖ ማሳደር የቻለችው? በተለያዩና ለዚህ በሚረዱ ቦታዎች ዜጎቿን ቦታ እንዲያገኙ በመንግሥት ድጋፍ አጥብቃ ስለምትሠራ ነው፡፡ የእኔና የአንተ አገር አስባ ማስገባቱ ቢቀር ምናልባትም በልፋት እዚያ ደረጃ ልጆ ሲደርሱ ሾተላይ በወረረውና ሩቅ በማያይ ፖለቲካዋ ስባ ታስወጣለች፡፡ ስለዚህ የጭንቅ አማላጅ ለመሆን ልጆቿን በተገቢው ጊዜ አታገኝም፡፡ የእኛ አገር ልጆቿን ስታስወርድ፣ ግብፅ ልጆቿን ትወልዳለች፡፡ ይኼ እውነት ነው ወዳጄ፡፡ ቢመርም እንውጠዋለን፡፡ ቁም ነገሩ ካለፈው ተምረህ ተሽለህ መገኘት ነው፡፡ እሱን ካላደርግን ምን እናማርራለን? ለዚህ ነው ከሌሎች ምን ያወዳድረናል? እኛ መጀመርያ ከራሳችን ነው መወዳደር ያለብን የምንለው፡፡

ወዳጄ. . . የህዳሴ ግድብ የትልቁ አጀንዳ አንድ ቅጠል ነው፡፡ ምንም እንኳን በቴክኒክ መለኪያ ከህዳሴ ቀድመው ማንደያና ካራዶቢ ቢሠሩ የተሻለ እንደነበረ በግሌ ባምንም፣ ህዳሴ በግዝፈቱና ባስተላለፈው የእንችላለን የፖለቲካ መልዕክት ሳትወላዳ ወደ ማጥቃት ቀጣና የሚያሸጋግር መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ እርማችንን አጀንዳውን ለመድፈር ብንችልም፣ የባለቤት ሌባ የሆነውም እኛው ስለሆንን የሾተላዩ ተጠያቂ ግብፅ ልትሆንልን አትችልም፡፡ ሳናስተምር፣ ሳንሠራ፣ ዓባዬ ቢሞላ ላይ ቆመን ከቀረን የለመዱትን ሞፈር ለመቁረጥ የመጨረሻ ትንፋሻቸውን መሞከራቸው አይቀርም፡፡ እያደረጉ ያሉትም ይኼንኑ ነው፡፡ እኛ በጥም ሙቱ አላልንም፣ እነሱን ለማጠጣት ግን እኛ ተጠምተንና ተርበን፣ ጨለማም ወርሶን በድህነት ሹቀን እንደተዋጥን መሞት የለብንም፣ ይህ ግን በምኞች አይሆንም፡፡ በመጀመርያ ሩቅ ያለመ ሀብቱን የተረዳ ራዕይ ይጠይቃል፡፡ ለዚያ የሚያበቃው መፈክር ሳይሆን ወጣት አዋቂዎችን አስቦ ማስተማርን፣ በዘርፉ መመራመርን፣ ሀብቱን ማወቅን፣ ከመደበኛው በተለየ መልክ ሌት ተቀን መሥራትን፣ የመነጋገር፣ የማስረዳትና የመወሰን አቅምንም ይጠይቃል፡፡ ውኃ የእኛም ችግራችን መሆኑን ማመን፣ ሕፃናቱም ሐሰቱን እውነት ብለው እንዳያድጉ፣ አውቀው ወይም ሳያውቁ በደብተር ወይም በሌላ ቁስ ዝግ ያለ ማደንዘዣ ሰለባ እንዳይሆኑ ሁልጊዜም ዓይንን ከፍቶ መከላከል ይጠይቃል፡፡ የእኛ ሕፃናት በደብተራቸው ሮናልዶን ከሚያመልኩ አገራቸው የዓባይ፣ የአዋሽ፣ የኦሞ፣ የሸበሌ፣ የባሮ፣ ወዘተ. ስጦታ መሆኗን በአዕምሯቸው መቅረፅ ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ በወቅታዊው ህዳሴ ግድብ ጠባብ ጦር ሜዳ ታጥረን፣ ሌላውን ትልቅ ሥዕል እንዳናይ የሚደረገውን ዘመቻና ጫና እንደ ተጀመረው ማርከስ ይኖርብናል፡፡

ወዳጄ. . . የኮካ ኮላ ካምፓኒ አድራጊ ፈጣሪ ጀምስ ኩዊንሲ (James Quincy) እንዳሉት የምንገነባው ለምዕተ ዓመት እንጂ ለሩብ ዓመት እንዳይሆን፣ የጀመርነውን መጨረስና በቀሪው የሀብታችን ጉዳይ እንደ ማንዴላ ረዥም ጉዞ ወደ አርነት መጀመር ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡ ለዚህ ነው ውድድራችን ከራሳችን ጋር ከሆነና ራሳችንን ካሸነፍን፣ በተሠራልን አጀንዳ ጉልበት አናጠፋም፡፡ ግብፅ በሰጠችን አጀንዳም እውነታችንን ለዓለም ለማስረዳት እንደ ሰሞኑ ማገዶ አንጨርስም፡፡ ለዓባይ ብቻ ሳይሆን ለሌች አገራዊ ጉዳዮች የተቋም ምላሽና በዕውቀት ተሟሽቶ ረዥም የሚያይ ራዕይና ሥራ ወሳኝ ነው፡፡ የዘመቻ ወዠብ አጭር ርቀዝትን አይሻገርም፡፡ ከሩብ ዓመት አርቆ ማለም ጥቅሙ ይኼው ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...