Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርእኔ ካልሆንኩ ማን? ዛሬ ካልሆነ መቼ?

እኔ ካልሆንኩ ማን? ዛሬ ካልሆነ መቼ?

ቀን:

በተስፋዬ ወልደ ዮሐንስ ኃይሌ

የዓመታት የትውልዶችን ቅብብል ይዘን፣ በደግም ይሁን በከፉ ታሪኮቻችን ታጅበን፣ በምንስማማውም በማንስማማውም ትርክቶች ተሞልተን ከዛሬዋ ኢትዮጵያ ላይ ደርሰናል፡፡ ትናንት ለዛሬ ታሪክ በሚሆነው አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ የታሪክ ክስተት ውስጥ ሳይሆን በዓመታት ድርጊቶች ነው፡፡ በቅርብ የስድሳዎቹ ዘመናት አልያም በሦስቱ ሰኔዎች እንኳ የሚያሰማማ ከሆነም የሚያቀራርብ አንድምታ ማምጣት ከባድ መሆኑን፣ ከታሪካችንም ሆነ ከሌሎች ሁነቶችና ታሪኮች መረዳት ቀላል ነው፡፡

ባለፉት ሃምሳ ዓመታት አገራችን ያስተናገደቻቸው ፖለቲካዊ፣ ርዕዮተ ዓለማዊና አስተዳደራዊ ውሳኔዎች የመሪዎች፣ የፖለቲካ ልሂቃንና ቡድኖች የተከሏቸው መንገዶች ለዛሬይቱ ሁለንተናዊና ነባራዊ ሁኔታዎች መከሰት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡ አምስት አሠርት ዓመታት ተጉዘው እስከ ዛሬ ድረስ ላልፈታናቸው ችግሮቻችን፣ ባለመግባባት ለመጋደላችን ምክንያት እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ ልዩነቶቻችንን መስበክ አስመርጠውናል፡፡

ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የነበሩት የፍትሕ፣ የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ ተቋማዊ ነፃነትና ኃላፊነትን መወጣት፣ ወዘተ. የመሳሰሉ ጥያቄዎች በርካቶች በበረሃና በከተማ ጊዜያቸውንና ዕውቀታቸውን ብሎም ሕይወታቸውን ቢሰውላቸውም፣ አሁንም ድረስ አካላቸውንና ሕይወታቸውን እየገበሩላቸው ቢሆንም፣ ጨለማውን የሚያሸንፍ ብርሃን ለማየት ከጉጉት በላይ የሆነ ተግባር መመልከት ሩቅ እየሆነብን  ነው፡፡ ከተስፋ ይልቅ ጨለምተኝነት፣ በአገር ከመሥራትና የራስንም ሆነ የሌሎችን ሕይወት ከማሸነፍ ይልቅ ሳይፈልጉ የልብ መሸፈትን የሚጋብዙ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ለዚህ ጉዳት በየቀኑ መባባስና መጨመር ከመፍትሔ ይልቅ፣ ችግሮቹ ላይ ብቻ እንድናተኩርና በማኅበረሰብ ደረጃ ለውጥን እንዳናስብ ያደረጉ ሦስት ቁልፍ ጉዳዮችን አስተውላለሁ፡፡

በረከትና መርገምት

ለአገሮች ዕድገት ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ ከሚያበረክተው አንዱ የሕዝቡ የዕድሜ እርከን እንደሆነ የሥነ ሕዝብ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በተለይ ደግሞ በሥራ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው ሕዝብ ብዛት ከፍ ባለ ቁጥር ለኢኮኖሚው የሚኖረው አስተዋጽኦ ጉልህ መሆኑን አስበው ‹‹ዴሞግራፊ ዲቪደንድ›› (Demography Dividend) ሲሉ ሰይመውታል፡፡ የእዚያኑ ያህል ኃይል በበቂ ሁኔታ ወደ ኢኮኖሚው መግባትና በመሥራት አምራች መሆን ካልተቻለ፣ በረከተ መርገምትነት አይቀሬ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ሰባ ከመቶ የሆነው ሕዝብ ከሰላሳ አምስት ዓመት ዕድሜ በታች በሆነባት ኢትዮጵያ፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሳይንሱ እንደሚለው በረከት ከመሆኑ ይልቅ መርገምት እየሆነባት የሆነ ይመስላል፡፡ ከፖለቲካዊና ሪፖርት ፍጆታ ውጪ በቂ ትምህርት፣ ሥራ ፈጠራና የኢኮኖሚ ድጋፍ ላለፉት በርካታ ዓመታት የተነፈገው ይህ የኅብረተሰብ ክፍል ማንኛውም ቡድን የፈለገውን የብሔር፣ የተበድለሃል፣ የተገፍተሃል ካርድ ስቦ ለፈለገው ዓላማ በፈለገው ሰዓት ለማንቀሳቀስ ዕድሉን አመቻችቶለታል፡፡

በኢትዮጵያ የሥራ ኮሚሽን ሪፖርት መሠረት 14 ሚሊዮን ሥራ አጥ ወጣቶች ባሉበት አገር ውስጥ፣ የፖለቲካ ልሂቃንና የታሪክ ምሁራንን በሚያስማማ የታሪክ ትርክት ውስጥ፣ ወጣቱ የሰዎችንም ሆነ የራሱን ንብረትና ሕይወት ሲያጣም በእየ ደጃፎቻችንና በዓይናችን ተመልክተናል፡፡ ለዚህም ድርጊት ትልቁን ሚና የሚጫወቱት ከአጠገባችን ያሉ በመንግሥት፣ በነፃነትና በነገ የሥልጣን ፍለጋ ስም የተሰባሰቡ በካበተ የፋይናንስ ድጋፍ በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ፓርቲዎች የሚካሄደው ድርጊት ነው፡፡ አንዳንዴ ከዕውቀት ነፃ የሆነ የሕዝቦችን የጋራ አብሮ መኖር የቆየ የደም ትስስሮሽን በመካድ የሚደረግ የፕሮፓንዳ ውዥንብር፣ ዜጎች የሥራ ዕድል ያገኙባቸውን ተቋማት እስከ ማፍረስና ወደ ሥራ አጥነት እንዲገቡ አድርጓቸዋል፡፡

በዚህ የለውጥ ሒደት በሚባለው ጊዜ እንኳ በሚደረጉ የፖለቲካ ውይይቶችና ፕሮግራሞች፣ ይህንን ወጣት በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ የተጨበጠ ፕሮግራም የማያቀርቡ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ከዚህ ወጣት ሕይወት ላይ አልወረዱም፡፡ እንዳሻቸው ይሰይሙታል፣ ያነሳሱታል፣ ይማግዱታ፡፡ ሲሻቸው ደግሞ ያገሉታል፡፡ ይህ በወጣትነት ኃይል ላይ የሚገኝ የኅብረተሰብ ክፍል አፍላነቱ ላይ ሥራ አጥነቱ ተጨምሮ በሚከሰቱ ግጭቶች ሁሉ፣ በአብዛኛው ውጤቱንና ዓላማውን ከግምት ውስጥ ሳያስገባ ይሳተፋል፡፡ ይህም በየጊዜው የሚደርሰውን ጉዳት የከፋ እያደረገው ይገኛል፡፡

ተቋማዊ ልዕልና ለዜጎች ደኅንነት

መንግሥት የሕዝብና የአስተዳደርን መስተጋብር ከመፍጠር አንፃር ትልቁን ሚና የሚጫወተው፣ ለተቋማዊ ልዕልናና ለዜጎች ደኅንነት በሚሰጠው ቦታ ነው፡፡ ተቋማዊ ልዕልና ሊያሳካ የሚፈልገው ግልጽ የሆነ ራዕይ ከማስፈር ጀምሮ፣ እስከ አስፈጻሚው አካል ድረስ የሚካሄድ ሁሉን አቀፍ የአቅም ማጎልበትና ማብቃት ሥራ ድረስ ይጓዛል፡፡ በተለይም ደግሞ የዜጎችን ደኅንነት፣ መብትና ሰላም ከማስጠበቅ አንፃር የሚንቀሳቀሱ ተቋማት ያለባቸው ኃላፊነትና ሚና ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ተቋማት፣ በተለይም ደግሞ ተቋማዊ ልዕልና ከማረጋገጥ አንፃር የሚሄዱበት ርቀት የፖለቲካ መሪዎቹ መልካም ፈቃድና ነፃነት ላይ የተጣለ በመሆኑ፣ ሙያዊ የሆኑ ጉዳዮች እንኳ ሰለባዎች መሆናቸው ዕሙን ነው፡፡ እነዚህ ትልልቅ የተቋማዊ ልዕልና መፋለሶች እስከ ቤተ እምነቶቻችን ድረስ ዘልቀዋል፡፡

ለዚህ ጉዳይ ሁልጊዜም እንደ ምሳሌ የማነሳው የየተቋማቱን ራዕይ ነው፡፡ አብዛኛው የፌዴራል፣ የክልል ብሎም የወረዳ ጽሕፈት ቤቶች ሳይቀሩ የተጻፈ ራዕይ በየመግቢያ በሮቻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡ የአብዛኞቹ ራዕይ ከሌላኛው የተወሰዱና ፎቶ ኮፒ የተደረጉ መሆናቸው እንዳለ ሆኖ፣ የተቋሙ ሠራተኞች ራዕዩን ካለማወቅና ካለመጋራት አልፎ በተቃራኒው ቆመው ማግኘት የተለመደ ሆኗል፡፡

መንግሥታት ካደላቸው በሕጋዊ ምርጫ ካልሆነም በኃይል ወደ መንበረ ሥልጣን ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ፡፡ ሕዝብ ግን ያለ፣ የነበረና የሚኖር በመሆኑ ይቀጥላል፡፡ መንግሥታት ቢቀያየሩም፣ አመራሮች ከፍ ዝቅ ቢሉም፣ የሕዝብን ዘላቂ የአኗኗር ሥርዓት ለመጠበቅና ለማስቀጠል ከሚረዱ ግንባበር ቀደም ሥርዓቶች መካከል ተቋማትና ልዕልናቸው ወሳኝ ነው፡፡ ይህ ዘላቂ ችግር አገሪቱ አንዱን ተሻግራ ወደ ሌላው እንዳታልፍ መሰናከል ሆኖባታል፡፡

የሁልጊዜ ተማሪነት የኢትዮጵያ አስተዳዳሪዎች ልክፍት

በማንስማማበት የታሪካችን የቁጥር ክፍል ውስጥ ቀላል የማይባሉ አስተዳዳሪዎች፣ በምርጫም ይሁን በኃይል ይህችን አገር ለዚህኛው ትውልድና ለዛሬው ጊዜ አሻግረውታል፡፡ በቅርብ ጊዜ ታሪካችን እንኳ ትልቁን ሥፍራ ይዞ የሚገኘው አለመግባባት፣ ግድያ፣ የእርስ በርስ ጦርነትና ረሃብ ነው፡፡ ከካቻምናው ሰኔ የአምናው ሰኔ ያደረሰብን ጉዳት፣ ከአምናው ሰኔ የዘንድሮ ሰኔ ያወረደብን ውርጅብኝ፣

የገደለው ባልሽ፣

የሞተው ወንድምሽ፣

ሐዘንሽ ቅጥ አጣ፣

ከቤትሽ አልወጣ፣

ከሚለው የተለመደ ሙሾ እንጉርጉሮ እኩል የሚነገረው የሁልጊዜ ተማሪነት የኢትዮጵያ አስተዳዳሪዎች ልክፍት ነው፡፡ የየተቋማቱ አመራሮች በየምክር ቤቱ ለሹመት ሲቀርቡ የሚነገራት የትምህርት ማስረጃዎች፣ ከወረቀትነት ባሻገር ረብ የለሽነታቸው የሚታየው እንዲህ ዓይነት የአመራር ጥበብ የሚጠይቅ ጊዜና ጉዳዮች ሲከሰቱ ነው፡፡

ከሁለቱ ሰኔዎች፣ ከጥቅምቱ የንፁኃን አካል ጉዳትና ሕይወት ሕልፈትና የዕድሜ ልክ ልፋት ውጤት የሆነው ንብረት ውድመት ትምህርታችን ያተረፍነው የዚህኛው ሰኔ ጉዳት፣ የጥፋት ዕድገት እንጂ የመቀነስ አይደለም፡፡ ሥልታዊ ዕርምጃና የሥጋት አመራር ጥበብ ‹‹አልታዘዘንም›› ከሚል የሰላምና የደኅንነት አስከባሪ ኃይል መስማት፣ ውጤቱ የዜጎችን እሮሮና ሲቃ ከማብዛት በተጨማሪ ዜጎች በተቋማቱ ህልውና፣ እሴትና አመራሮች ላይ ተዓማኒነት እንዳይኖራቸው ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሄዱ አድርጓል፡፡ እንደ ተማሪ አሁንም መቁጠራቸው ሌላ ችግር ሆኗል፡፡

መፍትሔ

በዚህች አገር ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ ውስጥ ዝምታን የመረጠው የኅብረተሰብ ክፍል ብዙ መሆኑን አምናለሁ፡፡ ዝምታው በአደባባዩ ተሳትፎ ውስጥ እንጂ በግል፣ ከጓደኞችና ከቤተሰቦች ጋር በሚደረግ ውይይት አገራዊ ርዕሰ ጉዳዮቻችንን ከማንሳት ቦዝነን አናውቅም፡፡ ብዙ ጊዜ ስታዘብም እንዲህ ዓይነት ውይይቶቻችን አብዛኛውን የቢሮ፣ የቤተሰብና ተመሳሳይ የማኅበራዊ ኑሮ ጊዜያችንን እንደሚወስድ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ለማኅበረሰብ የሚጠቅሙ ውይይቶችና ለአገር ግንባታ የሚጠቅሙ ድምፆች ወደ አደባባይ አናመጣቸውም፡፡ ከዚህም በባሰ ሁኔታ ልክ ባልሆኑ ድርጊቶችና ጉዳቶች ተጠቂ ስንሆን እመለከታለሁ፡፡

ከዚህም ባለፈ የምንሻውን ለውጥ የምንፈልገው በሌሎች ተሳትፎና ድምፅ እንጂ፣ በራሳችን በእያንዳንዳችን ተሳትፎ ውስጥ መሆኑን ማመንም መቀበልም አይታይብንም፡፡ ውሻ ነከሰኝ ብለን መልሰን አንነክሰውም፣ የበደሉንንም ሁሉ መልሰን መበደል ጥበብ አይደለም፡፡ ሁሌ ተበደልኩ እንጂ በደለክ ከማይል ግፈኛ ጋር በደልከኝ እያልን መከራከርም ነፍስን መበደል ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይልቁኑም ትክክል ስለሆነው ጉዳይ በኃላፊነትና በሐሳብ ለመሞገት መቆም በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡

ያሉንና የኖርንባቸው አስተሳሰቦችና ሰነዶች የሕግና የፖለቲካ ውሳኔዎች ችግር ፈቺነታቸው፣ በራሳቸው መቆማቸውን መመልከትና ማጤን በኅብረተሰብ ዕድገት ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ አለው፡፡ እንደ ግለሰብ፣ ቤተሰብ ጓደኞቻችንንና አካባቢያችንን ለመለወጥ ሙከራ አድርገን አናውቅም፡፡ ነገር ግን አገራዊ ለውጥና ውይይት እንሻለን፡፡ ከፍ ባለ ደረጃ ብቻ ለውጥን እንፈልጋለን፡፡

ያሉብንን ችግሮች ለመፍታት ችግሮቻችንን ማመን ቀዳሚው ጉዳይ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ ስለአገራችንም፣ ስለራሳችንም ሆነ ስለዜጎች ኃላፊነት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጦች ለማምጣት የምናስብ ከሆነ ከትንሹ እንጀምር፡፡ ስለአገራችን ራሳችን ከማወቅ፣ ከመመርመርና ከመፈተሽ እንነሳ፡፡ ሌሎችን ለማስከተል ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡ ግለሰቦች ለውጥ ማምታት ይችላሉ የሚለውን ማመን አለብን፡፡ ለዚህም እኔ ከሚለው መጀመር ያስፈልጋል፡፡ መቼ ለሚለው ደግሞ ዛሬን አንድ ብሎ ከመጀመር ይነሳል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...