በታደሰ ኃይለ ሥላሴ (ኢንጂነር)
ይህ ሐሳብ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በሚያደርጉት በናይል ውኃ ክፍፍል ያልተስማሙባቸውን ነጥቦች ለአፍሪካ መሪዎች በ15 ቀናት እንዲያቀርቡ በተጠየቁት መሠረት፣ ኢትዮጵያኖችን ለአፍሪካ መሪዎች ማቅረብ ያለባትን የእኛው መሪዎች ታሪካዊ ስህተት ውስጥ እንዳይገቡ ማሳወቅ አለብኝ ብዬ ያቀረብኩት ነው፡፡
ለኢትዮጵያችን
የውኃ ማማ የሚል ስም የተሰጣት ኢትዮጵያችን በዓመት የምታገኘው ውኃ በጠቅላላው ከ150 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ አይሞላም፡፡ እ.ኤአ. በ2050 የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 200 ሚሊዮን ስለሚሆን፣ ለዚህ የሕዝብ ብዛት በቂ ምግብ ለመስጠት ይህ በየዓመቱ በተፈጥሮ የምናገኘው ውኃ ለራሳችን የምግብ እህል ማምረትም ስለማይበቃ፣ ወደ ውጭ የምንልከው ምንም ውኃ እንደማይተርፈን ለአፍሪካ መሪዎችም ሆነ ለመላው የዓለም ሕዝብ ማሳወቅ አለብን፡፡ ይህን ሀቅ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ሶማሊያና ጂቡቲም መቀበል አለባቸው፡፡ ሀቁ እንደ ኮሶም ቢመራቸው በግድ መጋት አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አገር መቀጠል የምትችለው በተፈጥሮ የምታገኘውን ውኃ ለራሷ ስትጠቀም ብቻ ነው፡፡
በንጉሡም፣ በደርግም፣ በኢሕአዴግም መንግሥታት ይህ ሐሳብ አልተነገረም፡፡ የአሁኑ በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው መንግሥታችን ይህን የውኃ ጥያቄ በጥራት አውቆ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ለአፍሪካውያን ጭምር የሚጠቅም ውሳኔ ላይ እንዲደርስ ሐሳቤን በጩኸት አሰማለሁ፡፡
ከምዕራብ ኢትዮጵያ የሚፈሱት ተካዜ፣ ዓባይና ባሮ በየዓመቱ 80 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃችንን ይዘውብን ይሄዳሉ፡፡ የመጀመርያው የኢሕአዴግ መንግሥት የኤሌክትሪክ ኃይል ለአገራችን ያስፈልጋል በማለት በተከዜና በዓባይ ወንዞች ትልልቅ ግድቦች ለኤሌክትሪክ ማመንጫነት ሠርቷል፡፡ እነዚህን ግድቦች ለሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ኤሌክትሪክ አመንጭተው ያወጣንባቸውን ገንዘብ ይመልሱልን፡፡ አሁን የተቋቋመው የአፍሪካ መሪዎች ለሁላችንም ለአፍሪካ አገሮች ኤሌክትሪክ ኃይልና ለእርሻ ሥራ በቂ ውኃ የምናገኝበትን ዘዴ ተነጋግረው መፍትሔውን ይስጡን፡፡
ግብፅ እኛ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቃ ለመኖር የምታቅደው በዚህ የአፍሪካ መሪዎች ውሳኔ ለመጨረሻ ጊዜ መቋጨት አለበት፡፡ ግብፅ ቢያንስ ሦስት አማራጮች አላት ከቀይ ባህርና ከሜዲትራንያነ ባህር ጨው አጣርታ ንፁህ ውኃ ማግኘት ችላለች፡፡ በተፈጥሮ መሬቷ ውስጥ የተገኘውን ውኃ አውጥታ መጠቀም ትችላለች፡፡ በኮንጎ ወንዝ ለአፍሪካውያን በኮንጎ አገር ባሉ የተፈጥሮ ተዳፋቶች ተጠቅመን የኤሌክትሪክ ኃይል እስከ 100‚000 ሜጋ ዋት ማመንጨት እንችላለን፡፡ ይህ የኤሌክትሪክ ኃይል ናይጄሪያን፣ ግብፅን፣ ኬንያን፣ ደቡብ አፍሪካን ከጨለማ ወደ ብርሃን ከማምጣቱም በላይ ለኢንዱስትሪ የሚፈለገውን የኤሌክትሪክ ጉልበት ይሰጣል፡፡ ለኮንጎ ዴሞክራቲክ ሕዝብ ከዚህ 100‚000 ሜጋ ዋት ሽያጭ ብቻ እስከ 60 ቢሊዮን ዶላር በየዓመቱ ያስገኛሉ፡፡ በአውሮፓ ግሪክና ጣሊያን ይህን የኤሌክትሪክ ኃይል በመጠቀም የካርቦን ልቀታቸውን ይቀንሳሉ፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ የኑክሌር ኃይል ማመንጨቱን ሥራ ትታ ከዚህ ከኮንጎ ወንዝ የኤሌክትሪክ ኃይል ብትገዛ የሁላችንም በሕይወት መኖር ታረጋግጣለች፡፡
የኮንጎ ወንዝ ከላይ የጠቀስኩትን የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጭቶ አትላንቲክ ውቅያኖስ ውስጥ ከሚፈስ በ2‚000 ኪሎ ሜትር ዋሻ ወደ ናስር ሐይቅ እንዲፈስ ብናደርግ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ቱኒዚያ፣ ጆርዳን፣ እስራኤል፣ ሳዑዲ፣ የዓረብ ትንንሽ አገሮች በሙሉ የሚፈልጉትን ውኃ ያገኛሉ፡፡ ይህ ዋሻ በሚቆፈርበት ጊዜ ብዙ ጠቃሚ ማዕድናት እናገኛለን፡፡
የኮንጎ ወንዝን ኤሌክትሪክና የውኃ ጠለፋ በመሥራት አፍሪካን በሙሉ ከድህነት እናወጣለን፡፡ ይህን ፕሮጀክት ለመሥራት የአሜሪካን፣ የአውሮፓን፣ የሩሲያንና የቻይናን ዕውቀታቸውን ሆነ በገንዘብ በሥራውም በመሳተፍ ለራሳቸው ሕዝብ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፡፡ እኛ አፍሪካውያን በብዙ መንገድ እንጠቀማለን፡፡ ኢትዮጵያችን ሲሚንቶ ብታቀርብ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎታችን ምላሽ ያገኛል፡፡ ይህ ፕሮፖዛል ህልም አይደለም፡፡ አሁን ያሉንን የአፍሪካ መሪዎች የግብፅ፣ የሱዳን፣ የኢትዮጵያ፣ የኬንያ፣ የዴሞክራቲክ ኮንጎ፣ የሚሊ፣ የደቡብ አፍሪካ፣ ሁሉም ተባብረው ቢሠሩ ከቻይና መሪ አያንሱም፡፡ የቻይና መሪ የበፊቱን ሲልክ ሮድ ከቤጂንግ ተነስቶ ሩሲያን፣ ህንድን፣ ፓኪስታንን ሙሉ አውሮፓን እንግሊዝን ጨምሮና ሙሉ አፍሪካን በባቡር ለማገናኘት አቅደው ሥራውን ጀምረዋል፡፡
ኢትዮጵያችን በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት የዓባይንና የተከዜን ወንዞች ውኃ ለግብርና ሥራ የምታውልበትን ሥራዎች ከአሁን ጀምሮ አጥንታ፣ የሚያስፈልጉትን የኮንስትራክሽን ሥራዎች ጨርሳ ውኃችንን ለራሷ እንድታውል እመኛለሁ፡፡
የዛሬ 25 ዓመት ባቀረብኩት ግርድፍ ጥናት ዓባይን መርጦ ለማርያም አካባቢ (ከህዳሴ ድልድይ ትንሽ ከፍ ብሎ). . . በግሸን ማርያም አካባቢ በ300 ሜትር በመገደብ ተሬ ድልድይ ሥር 50 ኪሎ ሜትር ዋሻ ብንቆፍር፣ በዓባይ ወንዝ 20 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ወደ ምሥራቅ አገራችን እንዲፈስ በማድረግ ለመስኖ ሥራ እናውለዋለን፡፡ በተጨማሪም 2‚000 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እናገኛለን፡፡ ይህንን ውኃ መርሳና ውጫሌ መሀል በመቋጠር ሰፊ ሐይቅ ፈጥረን ከወልድያ ከተማ በታች ያለውን የደዲክሳላህ መሬት በመስኖ እናለማለን፡፡ በ20 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ በየዓመቱ ኢኮኖሚያችንን አሥር ትሪሊዮን ብር እናሳድጋለን፡፡ ሥራ ፈት እናጠፋለን፣ የውጭ ምንዛሪ በብዛት እናገኛለን፡፡
አሜሪካ ያለው ታማኝ በየነ ዶ/ር ዓብይን እግራቸው ላይ ወድቆ ሲቀበላቸው በቴሌቪዥን አይቻለሁ፡፡ እኔም ዶ/ር ዓብይን እግራቸው ሥር ወድቄ ይህን ሐሳቤን አስጠንተው ኢትዮጵያውያንን ከረሃብ፣ ከልመና፣ ከብጥብጥና ከመበታተን እንዲያወጡን እለምናቸዋለሁ፡፡
ከዚህ ፕሮጀክት የተሻለ የአገራችንን ችግር የሚያጠፋ የለም፡፡ ከ1950 እስከ 1960 በኢትዮጵያም ሆነ በአውሮፓና በአሜሪካ የነበረን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የአገራችንን ሕዝብ ከድህነት ያወጣን መስሎን፣ የሦስት ዕብድ ቄሶችን (የካርል ማርክስ፣ የኤንግልስና የሌኒንን) ርዕዮተ ዓለም፣ ከዚህ በተጨማሪ የቻይናውያንን መሪ የማኦን ጀብደኝነት በማመንና በማድነቅ ሶሻሊዝም የሚባለውን አስተሳሰብ በጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት ለአገራችን አስተዳደር ይጠቅማል ብለን ስንጀምረው መኢሶን፣ ኢሕአፓ፣ ደርግ፣ በሚባሉ ቡድኖች ተለያይተን የዕልቂት ጉዞን ጀምረነው ብዙ ወጣቶች እርስ በርሳቸው ተላለቁ፡፡ ብዙ አባቶችና እናቶችም የልጆቻቸው ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ይህ ሁሉ መዓት የወረደብን ከድህነትና ከኋላቀርነት ለመውጣት መሬት ለአራሹ በሚለው መፈክር በመመራታችን ነው፡፡
በሥራ ሕይወቴ የዚህን መፈክር ጠቃሚነት ስፈትሽ መሬት ለአራሹ ከውኃ ለአራሹ ጋር ካልተቀናጀ ባዶ ጩኸት ሆኖ ስላገኘሁት፣ ላለፉት 25 ዓመታት ውኃ ለአራሹ መፈክርን እያቀነቀንኩ ነው፡፡ የውኃ ለአራሹን መፈክር ጥቅም በሒሳብ ቀጥዬ ልግለጽላችሁ፡፡
1. ለአንድ ወጣት (በመጠኑ ዘመናዊ ትምህርት ለቀሰመ) አንድ ሔክታር ለጤፍ ተስማሚ መሬት እንስጠው፡፡
2. በአገራችን በኢትዮጵያ ሦስት ሚሊዮን ሔክታር ለጤፍ ተስማሚ መሬት አለ ይሉናል፡፡ ሆኖም ይህን አኃዝ ዘመናዊ ዕውቀትን በመጠቀም ወደ ስድስት ሚሊዮን ሔክታር ከፍ ልናደርገው እንችላለን፡፡
3. በአሁኑ ጊዜ ዶ/ር ታረቀ በርሄ የሚመሩ የግብርና ምሁራን 1ኛ/ዶ/ር ክበበው አሰፋ፣ 2ኛ/ ዶ/ር ጌታቸው በላይ፣ 3ኛ/ ዶ/ር ልኬለሽ ጉግሳ፣ 4ኛ/ ሚስተር ቶሲሪ ማዶ 5ኛ/ ዶ/ር ተስፋዬ ተሰማ ከአንድ ሔክታር በአንድ አዝመራ እስከ 85 ኩንታል ጤፍ ማምረት እንደሚቻል በጽሑፍ አሳውቀውናል፡፡
4. እነዚህ የግብርና ምሁራኖቻችን ይህን የምርት ብዛት ለማግኘት የጤፍ አዝመራ ሥራን በዝርዝር ጽፈውልናል፡፡
5. ከእዚህ መመርያ አንዱ በቂ ውኃ ማስገኘት ነው፡፡
6. በአንድ ዓመት አራት ጊዜ ብናመርት 4 x 85 = 340 ኩንታል እናገኛለን ማለት ነው፡፡ አሁን ገበሬው በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ በመዝራት ከ15 ኩንታል በታች ያገኛል፡፡
7. የክረምት ዝናብ ለምርት ስለማይመች የጤፍ ማሳውን በሙሉ እንደ አበባዎች ማሳ መሸፈን ይኖርብናል፡፡
8. ጤፍ በአሁኑ ጊዜ ሆድ ለመሙላት የምንመገበው ብቻ ሳይሆን መድኃኒትም ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዚህ ምክንያት አንድ የጤፍ እንጀራ በውጭ አገሮች በአማካይ በሁለት ዶላር እየተሸጠ ነው፡፡ በብር በትንሹ 60 ብር ማለት ነው፡፡ በዚህ ሒሳብ በዓመት ከአንድ ሔክታር 10‚200‚000 ብር ይገኛል ማለት ነው፡፡ ይህን ገቢ ለማግኘት ወጪያችን የሚከተለውን ይመስላል፡፡
ለአንድ ሔክታር የሚደረግ ወጪ
- ከቁጥር አንድ እስከ አምስት የተጻፉት ወጪዎች አንድ ጊዜ ብቻ የሚደረጉ ወጭዎች ናቸው፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ ለገበሬው በትርፍነት ሊካፈል ይችላል ወይም ተጨማሪ ማሳዎች ለማዘጋጀት ሊውል ይችላል፡፡ ወይም ለመንግሥት በግብር መልክ ይከፈላል፡፡
- ገበሬው የሚከፈለው ባመረተው ኩንታል መጠን ነው፡፡ ለውኃም የሚከፍለው በተጠቀመበት ብዛት ነው፡፡
9. እዚህ ጽሑፍ ውስጥ የአንድ ሔክታር ገቢና ወጪን በዝርዝር ያሳየሁት የዓባይን ከ50 እስከ 30 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ለእርሻ ብንጠቀምበት፣ ከ25 እስከ 15 ትሪሊዮን ብር ልናገኝ እንደምንችል ለማሳየት ነው፡፡ ውኃ ለብዙ ነገሮች ይጠቅማል፡፡ ከሁሉ የበለጠ ለእርሻ ሥራ ቢውል የበለጠ ይጠቅማል፡፡ ከህዳሴ ግድብ በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ይገኛል ተብሎ ተነግሮናል፡፡ ዕውቀትን ተጠቅመን በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ብንሠራ ከዓባይ ውኃ ብቻ 15 ትሪሊዮን ብር በየዓመቱ እናገኛለን እያልኩ፣ ከኤሌክትሪክ ከምናገኘው 500 ጊዜ የበለጠ ይሆናል ማለት ነው፡፡
10. ኢትዮጵያችን ስድስት ሚሊዮን ሔክታር በጤፍ ለማልማት 120 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ያስፈልጋታል፡፡ ይህንን ውኃ ለግብፆች ከለቀቅን እኛ እንደ አገር ለመቆም አንችልምና፡፡ ግብፆች ውኃ ከኮንጎ ወንዝ ወይም ከሌሎች አማራጮች ይጠቀሙ፡፡
ኢትዮጵያችንን ከድህነት፣ ከረሃብና ከመበታተን የምናተርፈው ባለን ውኃ ስንጠቀም ነው፣ ለማንም የምናጋራው ትርፍ ውኃ የለንም፣ አመሠግናለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሲቪል መሐንዲስና የበርታ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ተባባሪ መሥራችና ባለቤት ሲሆኑ፣ በዓባይ ውኃና በሌሎች ተፋሰሶች ላይ በርካታ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑን ጽሑፎችን አበርክተዋል፡፡ ይህም ጽሑፍ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡