Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ስንቱ ይናፈቃል?

እነሆ ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሜክሲኮ። ፍጻሜው በድል እስኪጠናቀቅ ሁሉም ከጎዳናው ጋር ትንቅንቅ ላይ ነው። እጅ መስጠት እንዲህ በቀላሉ ከቶ የሚታሰብ አይመስልም። ‘ወኔ የሌለው ጀግና አይደለም’ የሚሉት መፈክር ነዳጅ ሆኖት ደክሞ ላይደክም፣ ታክቶ ላይታክት መንገደኛው ከመንገዱ ጋር ተናንቋል። ሁሉም በድል ይጠናቀቅና ፍጻሜው ያምር ዘንድ ያልሆነውን ሲሆን፣ የማያምነውን ሲሰብክ፣ የመጣበትን ሲተች የሚታየው እዚህ መንገድ ላይ ነው። እዚህ መንገድ ላይ የትውልድ የሽንፈት ዕትብት ተቀብሯል። እዚህ መንገድ ላይ የትናንት የብሶት ዕንባ ተዘርግፏል። እዚህ መንገድ ላይ ነው የእኛ ልጆች ሐሞት ኮስትሮ ለለውጥ ዘራፍ ያለው። የለውጥ ችቦ የተለኮሰው እዚህ ጎዳና ላይ፣ ዴሞክራሲ መዳህ የጀመረውና የሕዝብ መብት እንዲከበር የእሪታ ድምፅ የተቀጣጠለው። ያላየነው የለም! ጎዳናው ፍጻሜውን የናፈቀ ትናንት የተጻፈ መግቢያ ነው። መውጫውን ገና ወደፊት የሚጠብቅ። ወይ ሲሰምር ወይ ሲከሽፍ ሊታይ። ለዚህ ነው ሁሉም የሆዱን በሆዱ አምቆ ሕመሙን ወደ ውስጥ እያቃሰተ የደላው መስሎ፣ የጎደለበት ሳይመስል የድል ፍጻሜውን ናፍቆ ሲሮጥ የሚታየው። መሮጥ ነው እንግዲህ!

ታክሲ ተራው ዙሪያውን በተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጥ ነጋዴዎች ተወሯል። የወያሎች ጩኸት ከሰማዩ ማጉረምረም ጋር እየተጣመደ ሲያስገመግም አካባቢውን ያተረማምሰዋል። እዚያ ከሸቀጣ ሸቀጡ ሠፈር ገሚሱ ዓይቶ ለማለፍ ብቻ ጊዜውን ሰውቶ ቆሟል። አንዳንዱ እንዳቅሚቲ ያለችውን እንደተሸበለለች እያወጣ ቆጥሮ ይከፍላል። ምኞትና ኑሮው ሩቅ ለሩቅ ሆነው ፍዳውን የሚያየው ሰው ቁጥር ቀላል አልነበረም። የለበሰው ላዩ ላይ ነትቦ የሰልባጅ ልብስ የሕልም እንጀራ እየሆነበት፣ ዓይቶ እንዳላየ ሆኖ የሚያልፈው ዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል ሲያስተውሉት ቅስም እየሰበረ ከንፈር ያስመጥጣል። የሆነው ቢሆንም ድሉን የማታ ማታ እንደማያጣው ሳይጠራጠር የሚሮጠው ይኼው ሰፊው ሕዝብ ነው። ‹‹አሁንም ድል ለሰፊው ሕዝብ›› የሚለው መፈክር የሚናፍቅ ይመስላል፡፡ ለሰፊው ሕዝብ ሲሉ ሕይወታቸውን መስዋዕት ያደረጉ ስንት ጀግኖች ባለፉበት አገር ውስጥ፣ ምድረ ጥጋበኛና ዕብሪተኛ ሲንደላቀቁ ማየት ግን ያበግናል፡፡ ትናንት ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ለሕዝብ ልዕልና ቤዛ የሆኑ ወገኖቻችንን እያሰብን ባንፅናና ኖሮ፣ አገር ለማፍረስ የተነሱ ሴረኞች አኳኋን ያሳብደን ነበር፡፡ አሁንም እያበድን ነው!

ይህን ሁሉ የጎዳና ትዕይንት ቀልባችንን ሰብስበን በአትኩሮት የምንከታተልባት ታክሲያችን መንቀሳቀስ ጀመረች። ወያላው ጥድፍ ጥድፍ እያለ በዓይኑ አንዳች ነገር ይፈልጋል። ኋላ መቀመጫ ላይ የተሰየሙ ሁለት ጎልማሶች የመገናኛን የጎዳና የሸቀጥ ትዕይንት እያዩ እንዲህ ሲባባሉ እንሰማለን። ‹‹ከእነሱ ጋር ተጋፍተን፣ ለታክሲ ተጋፍተን እንዴት ነው መኖር የሚቻለው? ሲነግሯቸው አይሰሙ ቢያባርሯቸው ምንም አይመስላቸው፣ ምን ያድርጉ የእንጀራ ነገር…›› ሲል አንደኛው፣ ‹‹እነሱ ፀሐይና ዝናብ እየተፈራረቀባቸው ከኑሮ ጋር የሚታገሉ ባተሌዎች ናቸው፡፡ አሉልህ እንጂ የሠርቶ አደሩን የልፋት ንብረት እያወደሙ ትግል ላይ ነን ብለው የሚያናፉ…›› ብሎ በቁጭት ተነፈሰ። የመጀመርያው፣ ‹‹አታይም እንዴ እንዴት አድርገው አገሪቱን ምስቅልቅሉን እንዳወጡዋት?›› ሲል፣ ‹‹ከፈረሱ ጋሪው አለ የአገሬ ሰው። እንዲያው አሁን ማን ይሙት የት አገር ነው አዕምሮ ሳይገነባ አገር የገነባው? ለሚሠራ ሳይሆን ለሚያንዛርጥ ክብር እየተሰጠ እኮ ነው አገር የጃርት መጫወቻ እየሆነች ያለችው…›› ብሎ የኋለኛው ነገሩን መረር አደረገው። ምሬት ይነሰው እንዴ!

ይህ በእንጥልጥል እንዳለ ሾፌራችን ወያላውን ምን ጠፍቶት እንደሚቁነጠነጥ ሲጠይቀው እንሰማለን። ለድብርት ማጥፊያ ገዝቶ ጠቅልሎ ያስቀመጠው ጫት ድራሹ እንደጠፋ አጫወተው። ሾፌሩ፣ ‹‹ተወው እባክህ ተወው ስንመለስ ትገዛለህ፤›› ሲለው ወያላው ቆጣ ብሎ፣ ‹‹እስከዚያስ?›› ብሎ አፈጠጠበት። ሾፌሩ አመሉን ያውቅ ይመስል ዝም አለ። ‹‹እዚህ አገር ያለ ምርቃና ምን ዘመድ አለኝና ነው በኋላን የምጠብቀው? ዜጎች ለስታትስቲክስ ሪፖርት ብቻ በሚፈለግበት አገር፣ በእናት አገሩ መሬት ላይ እስካለ ድረስ እንደ ልቡ የመወራጨት አቅሙ በሰለለበት አገር ከምርቃና ሌላ ምን ዘመድ ይኖርሃል?›› ሲለው እየደጋገመ ሃያ ሁለት ማዞሪያ ደርሰን ስለነበር ቶሎ ገዝቶ እንዲመጣ ነገረው። ወያላውን ጥበቃ የተወሰኑ ደቂቃዎች ቆምን፡፡ አንዳንዴ ምናለበት ወገኖቻችን ለሚፈልጉት ጉዳይ ብንተባበራቸው ወይም ብንታገሳቸው? ትዕግሥት ከየት ይምጣ!

‹‹ወይ መንገድና ጉድ! አያሳየን የለ ዘንድሮ?›› ትላለች መሀል ወንበር ላይ የተቀመጠች ወጣት። ‹‹ዓይኔ እያየማ እሱን ባልጠበቅኩ?!›› ብላ ከኋላዋ የተቀመጠች አንዲት ወይዘሮ ወረደች። ሾፌሩ ለማባበል ቢሞክር አትሰማውም። ይኼኔ አንድ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን ማሊያ የለበሰ ቻይና ብቅ ብሎ፣ ‹‹የት ነው?›› ብሎ ጠየቀ። ‹‹ይህችን ይወዳል ጣሴ!›› ይላሉ የመጀመርያው ወንበር ላይ ያሉ አዛውንት። ሾፌሩ በወረደችው ሴት ምትክ ሌላ ስለመጣለት ደስ ብሎት፣ ‹‹ሜክሲኮ!›› አለው። አማርኛ ተናጋሪው ቻይናዊ ገብቶ ወይዘሮዋ የለቀቀችው ወንበር ላይ ተቀመጠ። አዛውንቱ ይሰማኛል ሳይሉ መናገራቸውን ቀጠሉ። ‹‹ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል አሉ። እውነትም ቀስ በቀስ የማናየው የለም! ቻይናም በፈረደበት ልማት ሰበብ ዜግነት ቀይሮ ሊያርፈው ነው?›› አሉና ወደ ቻይናው ዞር ብለው፣ ‹‹ብቻ በሚቀጥለው ምርጫ ምረጡን ስትሉ እንዳናያችሁ እንጂ ሌላውስ ግድ የለም…›› አሉት። ቻይናው ብዙም አልገባውም መሰል እያያቸው ‹‹ሃ…ሃ…›› ይላቸዋል። አዛውንቱ ስለምርጫ ሲያነሱ ሁለቱ ጎልማሶች ትዝ አሉዋቸው መሰል፣ ‹‹ሰሞኑን የህዳሴ ግድቡ ድርድር ሲካረር አመፅ የቀሰቀሱት ዕብዶች ነገር አልገረመህም?›› ይባባሉ ጀመር። ‹‹ይኼ እንደሚመጣ መንግሥት እያወቀ መጀመርያውንም ለምን ዝም ብሎ አያቸው?›› ብሎት በዚያው በተገረመበት መንፈስ ደርቆ ቀረ። ይኼኔ ከኋላ መቀመጫ ካሉት ተሳፋሪዎች፣ ‹‹እኔ የምለው አነዚህ ሰዎች የሚቃወሙት ኢትዮጵያን ነው? ግራ ገባን እኮ!›› ብሎ ቢጠይቅ ተሳፈሪዎች ሳይወዱ በግድ ፈገግ አሉ። ማሽላ እያረረ ዓይነት፡፡ ዘንድሮማ ከማሽላ በላይ ነው እርር ያልነው ያሰኛል!

ወያላው ጫቱን እየቀነጣጠበ ብቅ አለ። ያለ ውል ጀምረን ያቋረጥነውን ጉዞ ያለ ውል ቀጠልነው። ስታዲየም እስክንደርስ የሚወራው ስለአንድ ጉዳይ ብቻ ነበር። ስለ ዓባይ! ሾፌራችን ወያላውን፣ ‹‹መቼ ይሆን አንተ ከሱስ ተላቀህ የማይህ?›› ብሎ ጠየቀው ገና ከመምጣቱ። ወያላው አጭር መልስ መለሰ። ‹‹ዓባይ ተገድቦ አልቆ በኤሌክትሪክ ብርሃን ስንጥለቀለቅ…›› አለው። ‹‹ያላዋቂ ሰሚ… ይለቀልቃል አለ የአገሬ ሰው። እንዲያው ምናለበት እነዚህ የግብፅ ፖለቲከኞች የመላውን የግብፅ ሕዝብ አቋም የማይወክል ነገር እየተናገሩ አጉል እሰጥ አገባ ውስጥ ባይከቱን? አይ የሴራ ፖለቲካ?›› ብለው የጀመሩት ከጋቢና አዛውንቱ ናቸው። ይኼኔ ወኔ ተቀጣጥሎ ታክሲዋን አሞቃት። ከኋላ መቀመጫ አንድ ወጣት ጓደኛውን፣ ‹‹አሁን ጦርነት ቢጀመር የምትዘምት አትመስልም እዚህ ቁጭ ብለህ አንፈራም ስትል?›› ብሎ ክብርንና ሰብዕናን የሚፈታተን ጥያቄ ይሰነዝርበታል። ‹‹ሁሉም ዜጋ ተተናኳሽ አይሁን እንጂ ወታደር ማለት ነው። በዚህ ላይ በዓባይ እስካሁን የተቀለደብን ይበቃል። ወይ ገድበነው ያልፍልናል፣ አሊያም አብረነው እስከ ወዲያኛው እናልፋለን፤›› እያለ በወኔ ይናገራል። መመርቀን የጀመረው ወያላ፣ ‹‹ይኼ ፌስቡክ እንኳን ተዘግቶ ከረመ እንጂ ሰውን እንዴት አድርጎ ወኔያም አድርጎታል?›› እያለ ከራሱ ጋር የሚያወራ መስሎ ትዝብቱን ይሰነዝራል። ‹‹እንዴት?›› ስትለው ቆንጂት፣ ‹‹ምን ነካሽ? አይበለውና ጦርነት ብንጀምር እኮ የምንዋጋው እንዳሁኑ በቃላት በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ አይደለም። የውድ ዜጎችን ደምና አጥንት በሚከሰከስበት መስክ እንጂ…›› ብሎ ሳይጨርስ የተመካከረ ይመስል መላ ተሳፋሪው አቋረጠው። ‹‹ኧረ ምን አልንህ? የእስካሁን አልበቃ ብሎ ደግሞ! እኛ የምንፈልገው ሰላም ነው…›› እያለ አቋረጠው። የለውጥ ብርሃን ጭላንጭልን ያየ የጀርባ ታሪኩን ማሰብ እንደማይሻ ሁሉ፣ የታክሲዋ ተሳፋሪዎች ስለጦርነት ሲነሳባቸው ተንጫጩ። የአገር አተራማሾችና የኑሮ ጦርነት አልበቃ ብሎ ደግሞ ሌላ!

የወያላችን ሒሳብ አሰባሰብ ቅጥ አንባሩ የጠፋው ነው። መጀመርያ የሁለትና የሦስት ሰው ሒሳብ ተቀብሎ ተክዞ ይቀራል። ‹‹ነፍሴ መልስ የለኝም? ወይስ ቁጠባ መስሎህ ‘ብሎክድ አካውንት’ አደረግከው?›› ሲሉት ይነቃል። መልስ መመለስ ይጀምርና የሁለት ሰው ተቀብሎ ጭጭ። አብዛኛው መልስ ያልተቀበለና ጭራሹን ታሪፉን ያልከፈለው ተሳፋሪ ስታዲየም ስንደርስ ወራጅ ስለነበር ‘በአምጣ መልስ፣ እንካ ሒሳብ’ ያጣድፉት ጀመር። ‹‹ኧረ በፈጠራችሁ አታስጨንቁኝ? እንዴ ምነው በአመፅ ማግሥት እንዲህ ሰው ማጣደፍ?›› ይላል እያፌዘ። ‹‹እኛ በቃ ሁሌም በደላችንን የጋራ መሸሸጊያ ማድረግ ነው የምናውቀው?›› ትላለች መሀል ወንበር ላይ የተቀመጠችው ቆንጆ። ጋቢና ያሉት አዛውንት ሾፌሩን ጨምሮ ደግሞ እንዲህ ይነጋገራሉ። አዛውንቱ፣ ‹‹እውነት እንደሚባለው ነው ተሳስበን የኖርነው? አይመስለኝም። ጥሩ አልነበርንም። ግን ከሁሉ የታዘብኩት አሉባልተኞችን ነው። እኔ በበኩሌ ‘ትራጄዲ’ ቴአትርም እንዲያ ጭጭ ተብሎ የሚታይ አይመስለኝም እንኳን ውድመት። ምን አለፋችሁ ሁኔታችንን ለሚታዘብ አውሬ ነው የምንመስለው…›› ሲሉ፣ ‹‹እንግዲህ ነገራችን እንዲህ ነው። ግማሹ አገሬ እያለ ላይ ታች ሲራወጥ፣ ግማሹ ደግሞ ብሔሬ እያለ መከራውን ያያል። የቸገረ ነገር…›› ብሎ ተከዘ፡፡ ትካዜ በዛ እኮ እናንተ!    

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። እነሆ ቅድም የተጀመረው የድል አጥቢያ ጉዞ እዚህም መልኩን ሳይለውጥ ይስተዋላል። ፍጻሜውን ሊያሳምር ሁሉም ያለውን ሳይቆጥብ እየሮጠ የሕይወትን ተግዳሮቶች ይዋጋል። ‹‹አልናፈቃችሁም?›› አለ ወያላው በምርቃናው ዓለም ውስጥ እንደሆነ ሁላችንንም እየቃኘ። ‹‹ምኑ?›› አልነው ነገረ ሥራው እያስገረመን። ‹‹ሁሉ  ነገር አልቆ ማየት! በቃ ሁሉ ችግር አልፎ ማየት አልናፈቃችሁም?›› ሲለን አጉል ያልነው የእሱ የምርቃና ዓለም የእኛም እንደሆነ ተሰማን። ‹‹እንዴታ ልጄ? እንኳን እናንተ ወጣቶቹ እኔን ይናፍቀኝ የለም ወይ? በባቡር የሄድኩት በጃንሆይ ጊዜ ነው። የታላቅነቱን ያህል ከዓባይ ትልቅ ነገር ስጠብቅ የኖርኩት ዘመኔን በሙሉ ነው። እናም ችግራችን ሁሉ መጨረሻ እንዴት አይናፈቅ? መጨረሻውን ያሳምረው የሚባለው እኮ ለዚህ አይደል?›› አሉ አዛውንቱ። ከኋላ የተቀመጡት ሁለቱ ደግሞ ‹እኛም ያልተቀባባ ዴሞክራሲ፣ ያልተወሳሰበ ፍትሕ፣ የጥቂቶች ያልሆነ ሕጋዊነት ሲሰፍን ማየት ናፍቆናል…› ይባባላሉ። ወያላው ‹‹መጨረሻ!›› ብሎ ታክሲው ሲቆም፣ አንድ በአንድ በመውረድ ወደ ጉዳያችን ስንበታተን ብዙ ነገሮች እየናፈቁን ነበር፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት