የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ከተሞች የወደመውን ንብረት ለመተካት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ መንግሥትም የወደመውን ንብረት ለመተካት እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽንም ሀብትና ንብረታቸውን ያጡ አሠሪዎችን ለመደገፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡
የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ታደለ ይመርና የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት ሞገስ፣ ሐምሌ 7 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ላይ ወቅታዊ ጉዳዮችን መነሻ በማድረግ በተለይ ባልተገባ መንገድ በርካቶችን ቀጥረው በሚያሠሩ ዜጎች ንብረት ላይ የደረሰውን ኪሣራ ለማካካስ እንደሚጥሩ ገልጸዋል፡፡
አቶ ታደለ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የምትገኝበትን ችግር ከግንዛቤ በማስገባት ሁሉም የበኩሉን ለማድረግ ዘጠኝ አባል ፌዴሬሽኖችን ያካተተው ተቋም፣ አሠሪዎች ላይ የደረሰውን አደጋ ከግምት በማስገባት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ውሳኔ ላይ ተደርሷል፡፡
በተፈጠረው ግርግር የአገር ሀብት በመውደሙ፣ እንዲሁ እንደማይታለፍ፣ ሀብት ንብረታቸውን ያጡ ወገኖችን ለማቋቋም በየደረጃው የድጋፍ እንቅስቃሴ እንደሚደረግ፣ የኮንፌዴሬሽኑ አባላትን በማስተባበር ለማገዝ ዝግጅት መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡ የአሠሪዎች አስተባባሪ ኮሚቴ በማቋቋም የወደሙ ንብረት የሚተካበትን ሥራ ለመሥራት እንቅስቃሴ ተጀምሯል ያሉት አቶ ዳዊት በበኩላቸው፣ የተፈጸመው ጥፋት አሠሪዎች ከኮሮና ጋር በተያያዘ አጣብቂኝ ውስጥ በገቡበት ወቅት መሆኑም ሁኔታውን የበለጠ አሳዛኝ አድርጎታል ብለዋል፡፡
ዜጎች ጥረው ግረው ያፈሩትን ሀብትና ንብረት እንደዘበት ማጣታቸውን የኮነኑት አቶ ታደለ፣ ዳግመኛ እንዲህ ያለው አሳዛኝ ድርጊት እንዳይፈጸም መንግሥት ከሌላውም የበለጠ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚጠበቅበት ጊዜ አሁን መሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል በማለት አሳስበዋል፡፡ መንግሥት ለአሠሪውና ለኢንቨስተሩ ዋስትና ሊሰጥ እንደሚገባም ያመለከቱት ኃላፊዎቹ፣ ይህ ካልሆነ የአገሪቱ ልማትና ዕድገት እየቀጨጨ ይሄዳል በማለት መንግሥት ቁርጠኛ ሊሆን እንደሚገባ ሳያሳስቡ አላለፉም፡፡
‹‹በዚህ ሁከት የበርካታ ሰዎች ንብረት ወድሟል፡፡ በአገሪቱ ድህነት ላይ ንብረት መቃጠሉና መውደሙ በእጅጉ አሳዝኖናል፤›› ያሉት አቶ ታደለ፣ እንዲህ ዓይነቱን ጥፋት በማውገዝ አሠሪዎች ዕድሜያቸውን ሁሉ ታትረው ያፈሩት ንብረት በአንድ ጀምበር ዶግ አመድ መሆኑ እንደሚያሳዝናቸው ገልጸዋል፡፡
‹‹በዚህ ጥፋት ሠራተኞች ሥራ አጥ ሆነዋል፡፡ የዕለት ጉርሻ ማግኘት የተቸገሩበት ጭምር በመሆኑ መንግሥት ድርጊቱ እንዳይደገም ዕርምጃ ይውሰድ፤›› በማለት አደራቸውን አሰምተዋል፡፡
የኮንፌዴሬሽኑና የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንቶች አቋም የያዙበት ሌላው ጉዳይ የህዳሴውን ግድብ የተመለከተ ነው፡፡ የአሠሪዎች ፌዴሬሽን ከዚህ ቀደም ለሦስት ጊዜያት አባላቱን ወደ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ቦታ መውሰዱንና ለግድቡ የመጀመርያውን ዙር የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራ መሥራቱን ያስታወሱት አቶ ታደለ፣ አሁንም የግድቡን የውኃ መሙላት ሥራ በተመለከተ መንግሥት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በመዳሰስ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆኑ አስታውቀዋል፡፡
ግድቡ እስኪጠናቀቅ ቃል የገባንበት በመሆኑ፣ አሠሪዎችና ሠራተኞችን በማስተባበር አስተዋጽኦ መደረግ እንደሚጀመር ገልጸዋል፡፡
የህዳሴ ግድብ ሥራ ሲጀምር ዋና ተጠቃሚዎች አሠሪዎች እንደሆኑ የጠቀሱት አቶ ዳዊት፣ ‹‹በማንደራደርበት ሁኔታ ለግድቡ የሚያስፈልገውን አባሎቻችንን በማስተባበር የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት አቋም ይዘናል፤›› ብለዋል፡፡
ድርድሩ ወደ አፍሪካ ኅብረት እንዲመጣ የተደረገው ዲፕሎማሲያዊ ሥራና የተገኘው ድል እንደሚያኮራ በመጥቀስ፣ የግድቡን ሥራ ለማደናቀፍ የሚደረገውን ሙከራ በመኮነን ግንባታውን ለማጠናቀቅ የሚያግዝ ድጋፍ ማቅረብ ተገቢ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ሌላው ማብራሪያ የተሰጠበት ዓብይ ጉዳይ ከኮሮና ጋር የተያያዘው ነው፡፡ ኮሮና ኢትዮጵያ መግባቱ ከታወቀ በኋላ በመንግሥት፣ በሠራተኞችና በአሠሪዎች መካከል በስምምነት የሥራና የአሠራር ፕሮቶኮል መውጣቱን አስታውሰው፣ በዚህ ፕሮቶኮል መሠረት ማንኛውም ተቋም ሠራተኞችን እንዳያባርር መከልከሉን ጨምሮ ሌሎችም ድንጋጌዎች መውጣታቸውን አውስተዋል፡፡ እየተሠራበት ያለው ይህ ፕሮቶኮል ግን በርካታ ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ በአሠሪዎች ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ስለመሆኑ፣ በአማካሪ ድርጅት ያስጠኑትን ጥናት ለመንግሥት በማቅረብ ማሻሻያ እንዲደረግበት መጠየቃቸውን አስታውሰዋል፡፡
አሠሪ ገቢ ባይኖረውም ሠራተኛውን ይዞ እንዲቀጥል ግዴታ በተጣለበትና ወረርሽኙን ለመከላከል በገንዘብ ጭምር ዕገዛ ለማድረግ በተወጠረበት ወቅት፣ ንብረት መውደሙ ሌላ ጉዳት ነው ብለዋል፡፡ በፕሮቶኮሉ ላይ የተደረሰበትን ውጤት ወደፊት እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል፡፡
‹‹በአንድ በኩል የኮሮና ቫይረስ በሌላ በኩል የፖለቲካው ውዥንብር በአገሪቱ ላይ በፈጠረው ሁኔታ በአሠሪውም በሠራተኛውም ላይ ተደራራቢ ችግር እየመጣ ነው፤›› ያሉት አቶ ታደለ፣ በፕሮቶኮሉ መሠረት የሥራ ውል መቋረጥ አይችልም፡፡ ስለዚህ ባለው ፕሮቶኮል መሠረት መንቀሳቀስ ይገባል፤›› በማለት የሚመሩትን ተቋም ሐሳብ አንፀባርቀዋል፡፡ ክፍተቶችን በመድፈንና ለሚያልፍ ጊዜ የማያልፍ ታሪክ ይዞ አሠሪው እንዳይጓዝ የአደራ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የአሠሪዎች ንብረት እንዲጠበቅና እንደ ኢንሹራንስ ያሉ ዋስትናዎችን የመግባት ባህል ባለመኖሩ የአሠሪዎች ጉዳት እንዲባባስ ማድረጉ ተጠቅሷል፡፡በሁከት ለሚወድሙ ንብረቶች ዋስትና መግባት ባለመቻሉ ከሰሞኑ ለወደሙ ንብረቶች የመድን ካሳ እንዳላገኙ በመጥቀስ የነውጥ ዋስትና ሥርዓትን አሠሪዎች እንዲከተሉ ቀድሞውኑ ኮንፌዴሬሽኑ ለአሠሪዎች ቢያሳውቅም፣ የኢንሹራንስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተደረገው ጥረት እንዳልተሳካ አስታውቀዋል፡፡ አቶ ዳዊትም በሁከት ጊዜ ንብረት ሲጠፋ ካሳ የሚሰጥበትን አገልግሎት ለመግዛት ጥረት ቢደረግም፣ የኢንሹራንስ ሽፋኑ በርካቶች መግዛት አላስቻለም በማለት ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዚህ ረገድ ያለውን አገልግሎታቸውን ማሻሻል እንዳለባቸውም ጠቅሰዋል፡፡