Monday, May 29, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የዘውግ ፌዴራሊዝምና የቀውስ መዘዞቹ!

በገለታ ገብረ ወልድ

አገራችን እንደ ብዙዎቹ የሦስተኛው ዓለም አገሮች በፊውዳላዊና ወታደራዊ አገዛዞች ዘመናትን ከማሳለፏ ባሻገር ድህነትና ኋላ ቀርነት ገጽታዎቿ ሆነው ነበር የቆዩት፡፡ እነዚህ እውነታዎች ደግሞ ከታሪካዊነቷና ከጥንታዊነቷ በላይ በነፃነት ከመኖሯ ጋር የሚጋጩ የታሪካችን ክፋዮች ሆነው ዘልቀዋል፡፡

ይሁንና ካለፉት ሦስት አሠርታት ወዲህ ምንም እንኳን ዘውግ መራሽና  አጨቃጫቂ ባህሪ የተላበሰ ቢሆንም ፌዴራላዊ ሥርዓትን ስትከተል ቆይታለች፡፡ የጠራ መግባባት የተፈጠረበት ባይሆንም አዲስ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ጉዞ ተጀማምሮም ታይቷል፡፡ በዚህም በአንድ በኩል በአገራችን ለዘመናት የኖሩ ብሔር ብሔረሰቦች ታሪካቸውን፣ ባህላቸውንና  እምነታቸውን ማራመድ፣ ማስተዋወቅና ማስፋፋት ሲችሉ፣ በሌላ በኩል በራሳቸው ቋንቋ መማርና መዳኘት መቻላቸውን፣ ባልተማከለ አስተዳደር በመመራታቸውም የተሻለ ልማት እየገኙ መሆናቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ እየተከተልነው ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓት በታሪካዊ ቅራኔዎች ላይ የተመሠረተ፣ ጎሳና ማንነትን አልፋና ኦሜጋ በማድረግ አገራዊ ኅብረትና አንድነቱን የደፈቀ፣ ዴሞክራሲያዊነት አጅቦት ባለመቆየቱም ባልተመለሱ በርካታ ፍላጎቶች የሚላጋ መሆኑ ዳፋው ለአሁኑ ብቻ ሳይሆን ለመጭውም ትውልድ የሚተርፍ እየመሰለ ነው፡፡ ከወዲሁ ካልታረመም ድግሱ የፍጅት እየሆነ ነው፡፡

በመሠረቱ እንኳን ገና ለጋ ተሞክሮ ባለንና በተዛባ ቅኝት ፌዴራሊዝምን  በጀመርነው ሕዝቦች ዘንድ ይቅርና በየትኛውም አገር ቢሆን፣ ፌዴራሊዝምና ርዕዮተ ዓለም (አይዲኦሎጂ) የሚምታቱበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ነገሩን ከሥሩ ለመመርመር ጊዜም ሆነ ፍላጎት የሌለው ሰው ወይም ቡድን ደግሞ ፌዴራሊዝም የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ‹‹ርዕዮተ ዓለም›› ከሚለው የአመለካከት ሒደት ጋር ያመሳቅለዋል ወይም ሆን ብሎ ያጋጨዋል፡፡

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቢታሰብም ነባራዊው ሁኔታ ሊያስተናግደው የማይችለውን አሃዳዊነት እንደ ማስፈራሪያ በመቁጠር፣ ፌዴራሊዝምን የልዩነት መቆስቆሻ ፍልጥ የማድረግ ዝንባሌ አየሩን እየሞላው ይገኛል፡፡ ፌዴራሊዝም ደግሞ ርዕዮተ ዓለም አይደለም፡፡ ፌዴራሊዝም የመንግሥት አደረጃጀት ሥርዓት ማለት ብቻ ነው፡፡ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ራሳቸውን የቻሉ ክልሎች በፌዴራል ደረጃ ዕውቅና ያለው መንግሥት የሚመሠርቱበትና በዚያም መንግሥት የሚተዳደሩበት ሥርዓት ብቻ ነው፡፡

የፌዴራል ሥርዓቱ አባል የሆነ እያንዳንዱ ክልል፣ በማዕከላዊው ፌዴራል መንግሥት መርሆዎች ላይ ተመሥርቶ እንደ የራሱ ልዩ የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ታሪካዊ ሁኔታዎች የሚያደራጅበት ሥርዓት አለው፡፡ እዚያው ላይም አንድ የጋራ አገርና ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ መሠረት የሚገነባባት ሀቅ ነው፡፡

የፌዴራሊዝም ጽንሰ ሐሳብ ዓላማ በብዝኃነት ውስጥ አንድነትን፣ ልማትና ዕድገትን፣ በዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም አሠራር አማካይነት ማምጣት መሆኑም ለድርድር የሚቀርብ አይደለም፡፡ ብዝኃነት ያላቸውን ሕዝቦች አንድ ለማድረግ ከዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም የተሻለ ሥርዓት የለም የሚባለውም ከዚሁ እውነታ በመነሳት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ዜጎች በዘርና በጎሳ እየተቦደኑ እንዲባሉ፣ አንዱ ሌላውን እያጠቃ የሚተራመስበት ሳይሆን፣ ሁሉም ሕዝቦች በአገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሕይወት ውስጥ በጋራ የመሳተፍ፣ እኩል ዕድል የሚያገኙበት ዴሞክራሲያዊነትን ይበልጥ ለማራመድ የሚረዳ  ሥርዓት ነው፡፡

የፌዴራሊዝም ሥርዓት ከባዶ ሜዳ ዝም ብሎ የሚበቅል ሳይሆን የብዙ ባለድርሻ አካላት ተዋናይነት ያለበት መሆኑም የሚታወቅ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (NGO’S) እና በውጭ አገሮች የሚኖሩ ዜጎች (ዳያስፖራዎች) እጅ ያለበት ነው፡፡ ሥርዓቱን በመገንባት ሒደት የተሳካላቸው ኢኮኖሚዎች (አገሮች) ልምድ ይቀመርበታል፡፡ ያልተሳካላቸው አገሮች ልምድም ይመረመርበታል፡፡ ከእነሱ ውድቀት ተሞክሮ በመውሰድ ትምህርት ይቀስምበታል. . . ከነዚህም ሁሉ ውስብስብ ሒደቶች በኋላ ተረቅቆ የአገሪቱ ምክር ቤት የሕዝብ ተወካዮች ባሉበት ሕገ መንግሥት ሆኖ ይፀድቃል፡፡ የአገሪቱ የበላይ ሕግ ይሆናል፡፡

ይህን እውነታ ከእኛ አገር አንፃር ስንመለከተው ምንም እንኳን ለዘመናት አብረው የኖሩ ሕዝቦችና ብሔረሰቦች ያሉ ቢሆንም ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳዳር የተሟላ ዴሞክራሲያዊነትና ፍትሐዊ ልማትን ለማምጣት ፌዴራላዊ ሥርዓት መገንባታቸው መልካም ዕርምጃ ነበር፡፡ ነገር ግን ምናልባትም በዓለም ላይ ከሁለት አገሮች (እነ ሩሲያ) በላይ አገር ያልተገበረውን የመገንጠል ሐሳብ የሚያቀነቅን፣ ከሥነ ልቦና መልክዓ ምድርና የኢኮኖሚ ትስስር ይልቅ ብሔርን ብቻ የክልል አጥር ለማድረግ የሚዳዳው፣ ለዚያውም ዜጎች ተገልለውና በአሸናፊው ወገን (ሕወሓት/ኢሕአዴግ) መሪነት ብቻ የፀደቀ ሕገ መንግሥት መተግበሩ ነገሮችን ያወሳሰበና ዜጎች በሒደት እንኳን እያደበሩ ለመሄድ የተቸገሩበት ሁኔታን ደንቅሮ ይገኛል፡፡

አሁን አሁን በተጨባጭ እንደምንመለከተው በዚች አገር ዴሞክራሲን ዕውን ለማድረግ የተሻለ ዕድል እየተፈጠረና መንግሥታዊ ሆደ ሰፊነት እየታየም በየጊዜው ለሚነሱ የብሔር ግጭቶችና የፀጥታ ችግሮች መነሻዎቹ ግልጽ እየሆኑ ነው፡፡ ይኸውም ከዚህ ቀደም በመሸፋፈን እንደሚባለው የአፈጻጸም ችግር ብቻ ሳይሆን፣ ራሱ ሕገ መንግሥቱና ወይም የፌዴራል ሥርዓቱ እሴቶች አለመሻሻልና በጥናት ላይ የተመሠረተ አሳታፊ ዕርምት አለመደረጋቸው ሥጋት አጥልተዋል፡፡ ከይሉኝታ በድፍረትና በቅንነት ወደ መነጋጋር ካልተገባም ከትናንት የተሻለ ዛሬን ማረጋጋጥ መክበዱ አይቀሬ ነው፡፡

በተለይ ለተራ የፖለቲካ ትርፍ ሲባል የአገር ህልውናንም ሆነ የሕዝብ አንድነትን ለመናድ ለሚሹ ኃይሎች በር የሚከፍቱ ሕግጋትን መፈተሽ ግድ የሚል ሆኗል፡፡ ትውልዱም በየዋህነት ወይም በግብዝነት፣ በስህተት ወይም በሌላ ሥውር ዓላማ ሰበብ የፌዴራሊዝሙን ይዘት በማዛባት ወደ ሌላ ግብ ለመምራት የሚጎትቱትን ጽንፈኛ የብሔር ፖለቲከኞች የሚያርምበት ስክነት ማጣቱ አደጋውን ሲያከፋው እየታየ ነው፡፡

ለዚህም ነው ከለውጥ በኋላም ቢሆን በሕዝቦች መካከል ፀንቶ የቆየውን የአብሮ መኖር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ሁኔታዎችን የማፈራረስ ዓላማ ያላቸው ወገኖች አገር እያተራመሱ የሚገኙት፡፡ በተለይ ኦሮሚያ በተባለው ሰፊና “አቃፊ” ሲባል በኖረ ክልል ውስጥ ጽንፈኞች በሚያካሂዱት አስከፊ ቅስቀሳ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ብቻ (አንዴ ሳይሆን ተደጋግሞ) እየተገደሉ ነው፡፡ ሺዎችም ሀብት ንብረታቸው እየወደመ ለዕርዳታ ከመጋለጣቸው ባሻገር፣ ሚሊዮኖች የተፈናቀሉበትን (የጌዴኦ ያስታውሷል) ሁነትም ማየት ተችሏል፡፡

በክልሉ ውስጥ ለዘመናት የኖሩ ዜጎችን ደም ለማቃባትና ተስፋቸውን ለማጨለም፣ ብሎም የተጀመረውን የዕድገት ጉዞ ለማደናቀፍ እየተፈጸመ ያለው ሴራም እየተከተልነው ያለው የዘውግ ፌዴራሊዝም መፈተሽ እንዳለበት አመላካች ነው፡፡ በተለይ አሁን ያለውን የለውጥ ኃይል በመቃወም ስም መደመርና የአብሮነት አስተሳሳብ የፌዴራሊዝም ተቃራኒ አስመስሎ መንጎድ በርትቶ የተያዘው፣ በወያኔዎችና በኦነግ
ሽኔ ጭፍራዎች፣ ብሎም የአክራሪ ብሔርተኝነት በለከፋቸው ኢሊቶች መሆኑ ሲታይ ብርቱ አገር የማዳን ሕዝባዊ ትግል መቀስቀስ እንዳለበት ያመላክታል፡፡

በመሠረቱ ምንም ያህል ስለአብሮነትና ነባር እሴቶች ብንነጋገር፣ አንዱ ብሔር የራሱን ክልል ብቻ ይዞ በሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ላይ በሩን ዘግቶ ‹‹አትድረሱብኝ›› የሚል አቋም እንዲኖረው ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች መሠረታቸው ጥፋት ብቻ ነው፡፡ የቀደሙ አገዛዞችን ክፍተት (ያውም በተጋነነ ትርክት እያጨማለቁ በመተንተን)፣ በምንም መለኪያ ከኃጢአቱ ጋር ግንኙነት በሌለው ትውልድ ላይ ለማወራረድ ማስላትስ ምን የሚሉት ዝቅጠትና ዕብደት ይሆን ብሎ በድፍረት መነጋጋር ካልተቻለ ከፊት ያለውን ገደል አደገኛ ያደርገዋል፡፡ አስፈሪነቱም እንደቀላል ሊታይ አይገባውም፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግልጽ እንዳየነው ሴቶችን ‹‹የሌላ ብሔር ወንድ ለምን አገባሽ? መፍታት አለብሽ? የራስሽ ብሔር ወንድ እያለልሽ ከሌላ ሕዝብ ጋር መጋባት የለብሽም!›› (ወንዶቹንም በተመሳሳይ በማስፈራራት) የሚል ሐሳብ የሚሰጡ ኋላ ቀሮች መድረክ እየያዙ ነው፡፡ ይኼ የለየለት የፋሽዝምና ዘረኛ መንገድ እንኳንስ ለዘመናት ተሳስሮና ተዋልዶ ለኖረ ሕዝብ ይቅርና በዚህ ዘመን በየትኛውም አገር ሊታይና ሊነገር እንደማይገባው ደፍሮ የታገለው አለመኖሩ ነው አሳሳቢ፡፡ ዛሬ አንድ ሕዝብ እየተጠቃ ቢመስልም ይህ አካሄድ ነገ መላው አገር ወዳድ የሆነውን ብሔር ብሔረሰብም ለጥቃት ማጋለጡ እንደማይቀርም መታመን አለበት፡፡

እንደው ለመሆኑ የትኛው ፌዴራሊዝምስ ወይም ብሔርተኝነት ነው እንዲህ ያለውን ኋላ ቀርነት ዕውን እንዲሆን የሚሻው? ብሎ በአንክሮ ማየትም ይኖርብናል፡፡ ነገ ደግሞ የሚፈለገውን ብሔር ቋንቋ የማይናገር ሰው ቤት ለመከራየትም ሆነ፣ የሆቴል አልጋ ለማግኘት የሚቸግርበት፣ መሥራትና መገብየት የሚታገድበት አሳፋሪ ክስተት ዕውን ላለመሆኑ ምን ዋስትና ይኖራል?

እውነት ለመናገር በተለይ ኦሮሚያ ውስጥ ኦሮሞ ባልሆኑ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ሥጋት፣ ሰቆቃና ጥቃት ምንም እንኳን የብዙኃኑ አገር ወዳድ ኦሮሞ መገለጫ ነው ባይባልም፣ አመለካካቱ የሚመነጨው ከአክራሪው ብሔርተኛ የፖለቲካ ሥምሪት ብቻ ሳይሆን፣ ከራሱ ከዘውግ ፌዴራሊዝሙ አተገባበርም ነው ብሎ ደፍሮ አለማንሳት ውድቀትን እንደማስቀጠል የሚቆጠርም ነው፡፡ በተለይ የተዛባው አስተሳሳብ በመንግሥታዊ መዋቅሩ ውስጥ በተወሸቀው አንዳንዱ ጥገኛም የሚራመድ መሆኑ የአደጋውን ክብደት ያሳያል፡፡

በዚህ ሁኔታ ከቀጠለም ነገም በሌሎች አካባቢዎች ‹‹ወደ ክልሌ ለምን መጣችሁ? ለምን ቤት ሠራችሁ? ለምን ሠርታችሁ ትኖራላችሁ፣ ለምን ከምርታችን ትቃመሳላችሁ (ትቀራመታላችሁ)›› የሚባልበት ሁኔታ መበራከቱ አይቀሬ ነው፡፡ ዛሬ ደቡብን በመሰሉ ክልሎች ከሞላ ጎደል ሁሉም ዞኖች  በሚባል ደረጃ  ወደ ክልልነት ለማደግ የማይፈጸም ጫናና ግፊት የለም፡፡ የነባሩን መጤ ሕዝብ ፍረጃውም ቢሆን ያው የወያኔ ሥርዓት በተለመለት ቦይ እየፈሰሰ ነው፡፡

በአገራችን ፌዴራላዊ ሕገ መንግሥት ክልል መሆን ምንም እንኳን ሕጋዊ መብት ቢሆንም፣ የሕዝብ ሀብትን በክልል ሕዝብ ሥልጣን ይዞ ለመቀራመትም ሆነ፣ አጥርን ከልሎ በብሔር ዋሻ ለመወሸቅ ያለው የኢሊቱ ፍላጎት፣ አንዱ ብሔር ከሌላው ብሔር ጋር ተጣምሮ የጋራ ክልል ለመመሥረት እንኳን እየገደበ ይገኛል፡፡ ይህ ጥገኝ አሳሳብ እስከ መቼ ሊገፋ ይችላል ነው መባል ያለበት፡፡

በአንዳንድ ክልሎች ውስጥ አሁንም የመገፋፋት ብሎም፣ የዘውግ መሳሳብ ችግር አለ፡፡ ችግሩን በሙሉ ለመናገርም ሌላ ችግር  አለ፡፡ ይህ ሁሉ ያልተገባ ዝንባሌ ግን  ሕገ መንግሥቱ በግልጽ ያስፈረውን ዜጎች በአገሪቱ የትኛውም ክልል ተዘዋውረው ሠርተው የመኖር መብት ያላቸው የመሆኑን የበላይ ሕግ ሊጥስ አይችልም፣ አይገባም፡፡  አንዳንዶች የክልላቸውን በር በሌሎች ዜጎች ላይ የመከርቸም መብት ያላቸው እስኪመስሉ ድረስ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎችም ሆነ የፌዴራሊዝሙን ራዕይ ወደ ቅዠት ለመለወጥ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች መኖራቸው የተረጋገጠ ነው፡፡

ይህ የተዛባ የፖለቲካ አቋም የፌዴራሊዝሙን ትርጓሜና አሠራር ከርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰብ ጋር ያጋጫል፡፡ ፌዴራሊዝም የመንግሥት አወቃቀር ሥርዓት ነው ብለን ስናበቃ፣ ዘረኝነት ግን ርዕዮተ ዓለም መሆኑንስ ለምን ቸል እንላለን፡፡ ይህ አገር የሚያፈራርስ አስተሳሰብ በማንኛውም መንገድ ካልተቀጨ ደግሞ ወደ ደቡብ አፍሪካው ዓይነት የዘር ጥላቻ (Xenophobia)፣ ወይም እንደ ሩዋንዳውያን ወደ እርስ በርስ መባላት መሸጋገሩ እንደማይቀር ማሰብ ሞኝነት አይደለም፡፡

በእርግጥ አሁን ለሚታዩት ችግሮች መባባስ በክልሎች ውስጥ ያሉ ዜጎች እጅ ብቻ አይደለም ያለው፡፡ ጽንፈኛ አክቲቪስቶች፣ ኃላፊነት የማይሰማቸው ፖለቲከኞችና መቀመጫቸውን አሽሽተው የሕዝቡን መከራ የማይጋሩ ዳያስፖራዎች በዋነኛነት የሚንቀሳቀሱበት ሒደት ነው ያለው፡፡ እስካሁን እንደሚታየው የዘውግ ፌዴራሊዝሙን የተለጠጠ መንደርተኛ እሳቤ በማቀንቀን በመንግሥት መዋቅር ውስጥም ተወሽቀው የሁከቱና የፀጥታ ችግር ስፖንሰሮች  የሆኑ ጥገኞች የሉም ማለት አይቻልም፡፡

ቀደም ያለውን ውድመትና በለውጥ ፍለጋ ስም የተፈጸመውን ያልተገባ ድርጊት አቆይተን ባለፉት ሦስት ዓመታት ገደማ ብቻ እየሆነ ያለውን ብንመረምር፣ በዋነኛነት በክልሎች (በተለይ በኦሮሚያ) የሚንቀሳቀሱ ማንኛውም የሌላ ዘር ድርጅት (በስም እየተጠቀሱ) የግል ባለሀብቶች፣ የግለሰቦች፣ ድርጅቶችና ቤቶችን ማቃጠልና መዝረፍ፣ ንፁኃንን መግደል፣ መንግሥት የፀጥታ ችግሩን ለማረጋጋት ወደ ክልሉ እንዳይገባ ድንጋዮችን፣ ግንዶችንና ጎማዎችን በመማገድ መንገድ መዝጋትን. . . ተግባራዊ ማድረግ ዋነኛ መገለጫዎች እየሆኑ ነው፡፡ እነዚህ ድርጊቶች ደግሞ በየደረጃው ባሉ መንግሥታዊ አካላት ቢወገዙ ከከፋ ጥፋት ማዳን የሚቻል ነው፡፡

 (ከሰሞኑ የታየውን ጉዳት አስከፊነት የሚያሳየው በፖሊስ መረጃ መሠረት በአንድ ቀን ሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ብቻ በአንድ ክልል 167 ዜጎች መገደላቸው፣ 500 ቤቶች፣ 197 ሆቴሎች፣ ስምንት ፋብሪካዎችና በመቶዎች የሚቆጠሩ ተሸከርካሪዎች መቃጠላቸው ሲታይ በእርግጥም ጽንፈኛው ኃይል በሕዝብና በአገር ላይ ያሴረውን  አደገኛ ተንኮል ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው)፡፡

አስከፊው ድርጊት የመንግሥት ኃይል እንዳይደርስ መንገዱን አጥሮ ሰላማዊውን ሕዝብ በዘር እየለየ መጨፍጨፍ፣ ባንኮች፣ መኖሪያ ቤቶችን ትምህርት ቤቶች፣ ቤተ እምነቶችን፣ ፍርድ ቤቶችና አምቡላንሶችን በእሳት ማጋየት ምን የሚሉት አብዮት ሊባል ይችላል? ወይስ ዕብደት/ምቀኝነት እንበለው? መንግሥትስ እያለ እስኪደርስ ድረስ ባለው አጭር ጊዜ ይህን ዓይነትና ግፍ በዜጎች ላይ የሚፈጽሙ ኦነግ ሸኔን የመሰሉ ቡድኖች መንግሥት በሆነ ምክንያት ባይኖር ወይም በማንኛውም ዘዴ እነሱ ሥልጣን ላይ ቢወጡ የተቀረው ኢትዮጵያዊ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን ነበር? ብሎ ማየትም ግድ ይለናል፡፡

ሁከት ፈጣሪ ቡድኖች በተለይ ዛሬ፣ ላደረሱት ሰብዓዊነት ለጎደለው ጥፋት ምንም ዓይነት ተቀባይነት ያለው ምክንያትም ሆነ ሰበብ ማቅረብ አይችሉም፡፡ በቅርቡ ለተከሰተው የፀጥታ ችግር መነሻ የሆነው የታዋቂው ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ነበር፡፡ እርግጥ የዚህ ብዙ ሊሠራ የሚችል፣ የነፃነት ታጋይ ወጣት ሕልፈት ማንንም ቢሆን ያሳዝናል፣  ያስደነግጣል፡፡ ነገር ግን ባልተጣራ መረጃ ላይ ተመሥርቶና የአጥፊ ኃይሎችን የጥፋት ትርክት ብቻ አዳምጦ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር አምራች ኃይል ወጥቶ ያን ሁሉ ጥፋትና የንፁኃን ግድያ መፈጸሙ ነውርና ሊወገዝ የሚገባው ነው፡፡ በምን መለኪያስ የፌዴራሊዝም ጠበቃ ሊያስብል ይችላል!

የጥፋቱን ለማድረስ ሲዶለት የከረመውን ሴራ ለመረመረውም የቀውሱ ምክንያትም ሆነ ሰበብ  የድምፃዊው  ሕልፈት  አይደለም  ያስብላል፡፡ ዋነኛው ምክንያት አስነዋሪ ቡድኖቹና የፖለቲካ ሴረኞቹ ከጎረቤት ጠላቶች (በተለይ ከግብፅ) ጋር በመተባበር አገሪቱን ለመበታተን የተነሱ መሆናቸው ነው የሚያሳየው፡፡ ከዚህ ከነሱም በመጠላለፍ የሥልጣን ኮርቻ ላይ ለመፈናጠጥ በመቋመጥም ነው፡፡

ይህ ነገር ይበልጥ ግልጽ የሚሆነው ደግሞ አገራችን በዓባይ ጉዳይ ከግብፅ ጋር ተፋጣ ያለችበት ወቅት ላይ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ የግድቡ ውኃ ሙሊት ሊጀምር ቀናት ሲቀሩት ነበር፡፡ ያ ባይሆንማ ሐዘንም ሆነ የፖለቲካ ቅሬታ ብቻ እንዴት የግጭትና የዚህ ሁሉ ጥፋት መንስዔ ሊሆን ይችላል፡፡ የተጀመረው ለውጥ አላረካንም፣ ቢባል እንኳ ከመንግሥት ጋር በመወያየት የሚፈታ እንጂ፣ ከምንም ነገር ጋር የማይገናኙ ዜጎችን ሕይወት የሚቀጥፍና የአገሪቱን ሀብት የሚያወድም እስከመሆን ሊደርስ አይችልም፡፡ አይገባም፡፡

በመሠረቱ በአሁኑ ወቅት አገራችን የጀመረችው ለውጥ የሕዝብ ትዕግሥትና ድጋፍ ቢታከልበት ካለፈው ሥርዓት የተሻለ ተስፋ የሚሰጥ ጅምር ነበር፡፡ ከዴሞክራሲ ምኅዳሩ መስፋት ባሻገር በፌዴራሊዝሙ አተገባባርም ቢሆን የተሻለ ጅምር እየታየበት ያለ ለመሆኑ የሲዳማ ሕዝብን የዘመናት የክልልነት ጥያቄ የመለሰበት አግባብ አንድ ማሳያ ነው፡፡ መንግሥት የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ በውጭ ግንኙነትና በልማት መስክ የጀማመራቸው ተግባራትም ሊበረታቱ የሚገቡ ናቸው፡፡ ከዴሞክራሲ ውጭ ሲንጠራወዝ የነበረውን ፌዴራሊዝም ተብዬ የአሻጥር መንገድም ለማስተካካል እየሞከረ ያለው ይኼው ጊዜ ነበር፡፡

መንግሥት ከዚህ ቀደም የዜጎች የጎን ውጋት የነበሩትን የፍትሐዊ ልማት ሥርጭትና  የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ቆርጦ የተነሳበት ብቻ ሳይሆን አገራዊ አንድነትን መልሶ ለመገንባት  እየተጋ መሆኑ፣ መገፋፋቱን ለመግታት ላይ ታች የሚልበት ጊዜም ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ይህን ዓይነት ሁከትና የፀጥታ ችግር መቀስቀስና ማካሄድ ታዲያ ለምን ተመረጠ? የሕዝቡን ብሶት በየሰበቡ እየቆሰቆሱ መንግሥትን መፈናፈኛ ለማሳጣትና መልካም ስሙን ለማጠልሸት መሞከርስ ማን ሊጠቅም ይችላል፡፡ እውነት ይህ እሳቤ ፌዴራላዊነት የወለደው ነው ጽንፈኛ ብሔርተኝነት ተብሎ መመርመር ነው ያለበት፡፡

በእርግጥ  አሁን በደረስንበት ደረጃ መንግሥት የሕግ የበላይነትን በማስከበር የአገርንና የሕዝብን ደኅንነት ለማስጠበቅ ከብዙ ቸልተኝነት በኋላ፣ የጀመረው ጥረት መበረታታ ያለበት ነው፡፡ በተለይ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና መላው የፀጥታ ኃይል የድምፃዊውን ገዳዮች በቀናት ውስጥ አድኖ ለመያዝም ሆነ፣ ቅጥረኞችና የመንጋ ፈራጆችን በሕግ ለመዳኘት የጀመረው ጥረት አገርን እንደመታደግ ነው መቆጠር ያለበት፡፡ ሕዝቡም ይህን የአገርን ደኅንነትና ገጽታ የማዳን ተግባር ማገዝ ይኖርበታል፡፡ የዜግነት ግዴታውም ነው፡፡

በዚህ መነሻ አጠቃላይ የሰላምና የፀጥታ ሥራን ለማጠናከር ብሎም የሴረኞችን አደገኛ ዝንባሌ ለማክሸፍም ሕዝቡ ሁከት ፈጣሪዎችን አጋልጦ ለመንግሥት እንዲሰጥ የተጀመረው ጥረት መጠናከር አለበት፡፡ በእርግጥ በአሁኑ ጊዜ በከተሞች ውስጥ ያለው ነዋሪ እርስ በራሱ የማይተዋወቅበት ደረጃ ላይ ቢመስልም ከጽንፈኞች ጥቃት ራሱን ለመከላከል የጀመረው ጥረት መበረታታት ነው ያለበት፡፡ ባለጌን ተው የሚል ከጠፋ እንዳሻው መፈትፈቱ ስለማይቀር ሕዝብ ዝምታውን መስበር አለበት፡፡ ያኔ መንግሥትም ሚናውን ያጠናክር ይሆናል፡፡

እንደ አገር ግን ዜጎችን ያሳተፈ አገራዊ ደኅንነት የማስጠበቅ ሥራ ብቻ ሳይሆን፣ በፌዴራሊዝም ስም በጥላቻ ትርክትና በቂም በቀል ፖለቲካ የተሳከረውን ኢሊትም ወደማረም መገባት አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ነው በብሔራዊ መግባባት ላይ የተመሠረተ ፌዴራሊዝምን ዕውን በማድረግ የሚለውን የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ይበልጥ ማረጋጋጥና አገርን ለመጭው ትውልድ ጠብቆ ማስተላለፍ የሚቻለው፡፡

አሁን ያንዣባበውን አደጋ በአፋጣኝ ለማስተካካል ብሎም፣ ፀጥታና ደኅንነትን ለማረጋገጥ ዋነኛው የመፍትሔው ባለቤት ግን ችግሩ የተነሳበት ክልል ሕዝብ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ብዙኃኑ ሰላምና አገር ወዳድ ሕዝብ፣ አጥፊዎችን አደብ ግዙ እንዲልና እንዲያወግዝ መደረግ አለበት፡፡ በአጥፊዎች ላይ ከሰላማዊ መግባባት እስከ ከፍተኛ ዕርምጃ አወሳሰድ ድረስ ክልሉ በተመጣጠነ መንገድ፣ ባለው ኃይል መጠቀም መቻልም  አለበት፡፡ ችግሩ ከአቅሙ በላይ ሲሆን ከአጎራባች ክልሎች ወይም ከፌዴራሉ መንግሥት ድጋፍ ሊጠይቅና ሊያገኝ ይችላል፡፡

በእርግጥ ትናንትም ሆነ ዛሬ መንግሥት ቢዘገይም ችግሮቹን በዘዴና በብልኃት፣ በትዕግሥትና በማስተዋል ይዞ ለመራመድ ከመጓጓት እንጂ፣ ችግሩን ስላልሰማ ወይም በቸልተኝነት አይደለም፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡ የአገሪቱን ህልውና፣ የሕዝቡን ሕይወትና ንብረት፣ የፌዴራል ሥርዓቱን መጠበቅና በብዙ የሕይወት መስዋዕትነት የተገኘውን ዴሞክራሲ፣ ሰላምና ልማት ዘላቂነት የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት፡፡

መንግሥት ይህን ወደር የሌለው ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያደርገውን ያውቃል፡፡ የማያዳግም ዕርምጃ ለመውሰድ ችግሩን ከሥር ከመሠረቱ ደጋግሞ መመርመር ግን አለበት፡፡ መንግሥት በሚወስደው ዕርምጃ የሚጎዱት ሽብርተኞችም ሆኑ ጽንፈኞች ቢሆኑ የሕዝቡ ልጆች ናቸው፡፡ ልጇ ቢሞትባት ወይ ቢቆስልባት የማታለቅስ እናት ደግሞ የለችም፡፡ የማያዝን ቤተሰብም የለም፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ልጆቹን እንዲመክር፣ ጊዜ መስጠቱም ክፋት አልነበረውም፡፡ ግን ሁሉም ገደብ አለውና ልምምጡ መቆም አለበት፡፡ መንግሥት የጀመረው የሕግ የበላይነትን የማስከበር ጥረትም መጠናከር አለበት፡፡

    ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles