Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ተስፋ መቁረጥ አይታሰብም!

ሰላም! ሰላም! ውዷ ማንጠግቦሽ ሰሞኑን ‘ኧረ መላ መላን’ ማንጎራጎር አብዝታብኛለች። ‹‹‘ምን አስገለበጠኝ ወተቱን በጋን፣ ችዬ እገፋዋለሁ የማልለውን’›› ስትል ስሰማት ሆዴ ተገለባበጠ። ደግሞ ምን ተገኘብኝ ብዬ ነዋ። ቅሬታ እየሰፋ የሚሄደው እኮ በየጓዳችን ተጀምሮ ነው። እናላችሁ ደግሞ ‘አመሌ መቼ ከፍቶ ታይቶ ይሆን?’ ብዬ ስብሰለሰልላችሁ የልብ አውቃዋ ማንጠግቦሽ፣ ‹‹አይዞህ በአንተ አይደለም…!›› አለችኝ። የልባችንን የሚያውቀው ተመናምኖ ልብ የሚያደርቀው በበዛበት ዘመን፣ እንደ ማንጠግቦሽ ያለ አሳቢ ሰው ይስጣችሁ እንጂ ሌላ ምን እላለለሁ? ‹‹እህ ለማን ነው ታዲያ መላ መላው?›› ስላት ታዲያ፣ ‹‹መብራት ጠፍቶብኝ መስሎኝ በከሰል ጭስ የምጨናበሰው…›› ብላ ቆጣ አለች። በስንት ጥንቃቄና ጥገና የያዝኩት የጎጆዬ ፍቅር ደህና መሆኑን ሳረጋግጥ ልቤን ደስ አለው። የቸገረው ግን አገር ጤና እያጣች እኛም ጤና ማጣታችን ነው፡፡ አንዱን ደላላ ወደጄን፣ ‹‹ምን ሆነን ነው እንዲህ አገራችንን ጤና አሳጥተን እኛም እንደ ሕመምተኛ የምናቃስተው?›› ስለው፣ ‹‹እርግማን ነው እባክህ…›› ብሎኝ እብስ አለ፡፡ እርግማኑ ምን ይሆን ብዬ ራሴን በራሴ ስጠይቀው መልሱ ተከሰተልኝ፡፡ የንፁኃን ደም ሳያቋርጥ በሚፈስበት አገር ውስጥ እንዴት ሰላምና ጤና ይኖራል ነበር መልሱ፡፡ እንዲያ ነው ነገሩ!

እየቆየ ሠፈሩን ያጨለመው መብራት አራትና አምስት ቀናት ጭልጥ ብሎ ጠፍቶና በዚያው እልም እንዳለ ሲቀር ማንጠግቦሽም ብሶቷ አይሎ፣ ‹‹‘እሳቱን አንድዱት ምንድነው ጨለማ፣ የዚህ አገር ልጅ ነኝ ያውም የከተማ’›› ማለት ስትጀምር ቤት መዋል አቆምኩ። ‘ሰው በሰው ይገኛል’ ሲባል አልሰማችሁም እንዴ? ታዲያስ! እንዲህ ነዋ የእኛ ኑሮ። ዘለሰኛውና እንጉርጉሮው አፍ ላይ ከተለመደና ከተደጋገመ፣ የአየር ንብረቱ ከከፊል ደመናማነት ሊያልፍ ይችላል። እንደኔ ፈሪ የእናቱ ልጅ የሚያውቀው መሸሽ ነውና ገለል ያልኩት ወድጄ አይደለም። ምንም ቢሆን ፈርተንና ሸሽተን ያሰነበትናት ነፍስ መስላኝ ይህችን ታህል የምታሳየን? ይህንን አባባል ብዙ ሰው ያውቀዋል። በአሳዶ ማሳደድ፣ በአጥፍቶ መጥፋት፣ በገንብቶ ማፍረስና በአንድዶ ማጋየት የተቃኘው ታሪካችን እንዲህ አንገት ደፍተን በሒደት ለሚታይ ለውጥ እጅ ሰጥተን ካልተቀየረ፣ እኛ የዛሬዎቹ ከትናንትናዎቹ በምን ተሻልን ነው ጥያቄው፡፡ አይደለም እንዴ? ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ፈሪ የሚለውን ቃል ስለማይወደው፣ ‹‹ብልኃትና ብልጠት ብለህ ብታርመው ይሻላል…›› ቢለኝም፣ ጉልበተኞችና አደፍራሾች መሀል ሲገኙ መሸሽን የመሰለ ጥበብ የለም እላለሁ፡፡ ምን ይደረግ ታዲያ!

እንግዲህ የኑሮ ነገር መላ መላ እያስባለን አይደል? አንዳንዱ ነገራችን ግን እንኳን መላ ውልም ያለው አይመስልም። በቀደምለት ድንገተኛ ሥራ ተገኝቶ፣ ዘመናዊ ‘ጂ ፕላስ ቱ’ ቤት ይሸጣል ተባልኩና ክው ክው ማለት ጀመርኩ። ያም ሆኖ ልፋቴ መና አልቀረም ገዥ ነን ያሉ ሰዎች አገኘሁ። መቼም ቤቱ ከምነግራችሁ በላይ የሚያምር፣ ናላ በሚያዞር ወጪ በተገዙ የቤት ዕቃዎች የዘነጠ ነው። ገዥዎቹ ይኼን ሲያዩ፣ ‹‹ለመሆኑ ይህ ሰው ለምን ይሆን ቤቱን የሚሸጠው?›› አሉኝ። የእኛ ነገር ‘ፕራይቬሲ’ ምናምን አናውቅም አይደል? ኑሯችን በአደባባይ ነዋ። ልብ ላለው ጣራና ግድግዳዎቻችን ከብርድና ከፀሐይ ሌላ ከምንም አይከላከሉንም እኮ። እና እኔም ስመልስ፣ ‹‹ምኑን አውቄ?›› አልኳቸው። ሰዎቹ ወስነን እንደውላለን ብለው ሲሄዱ ግን ከንክኖኝ፣ አከራዩን በጨዋታ ዳር ዳር አልኩት። እሱም ያጫውተኝ ጀመር። ቀልቤን ሰብስቤ ስላዳመጥኩት ነው መሰል ከጫፍ እስከ ጫፍ ሕይወቱን ዘከዘከልኝ። የሁላችንስ ገመና ደጅ አይደል እንዴ ያለው!

‘ሰው ግን እንዴት የሚያዳምጠው አጥቷል?’ አልኩ መናገር የሌለበትን ሁሉ እየነገረኝ ስሰማ። የእሱን ያህል በጉድ የተወረረ የግለሰብ ታሪክ አሁን ባልዘከዝክላችሁም በአጭሩ በሚስቱ ላይ ሄዶ ትዳሩን ካፈረሰ በኋላ፣ በአራጣ ተበድሮ ሲነግድ በመክሰሩ ቤቱን ለመሸጥ እንደተገደደ ነበር የነገረኝ፡፡ ለአብሮ አደጉ እንደሚናዘዝ የትም ለማያውቀኝ አንድ ደላላ የነገረኝ ነገር አስገራሚ ቢመስልም፣ ብዙዎቻችንን ሊገጥመን የሚችል መሆኑን ሳስብ ብዙም አልገረመኝም። ውሎ አድሮ ቤቱ ሲሸጥ ያን የመሰለ የቤት ዕቃው ወጥቶ ወናውን ገዥዎች ሲረከቡት ሳይ፣ የምቀበለው ኮሚሽን ሊያስፈነድቀኝ እየተገባ በጥቂት ጥቂት መንሸራተት ነገር ዓለሙን ገደል የሚሰደው ምስኪኑ የሰው ልጅ ኑሮ አስተከዘኝ። ትካዜ የማይሰለቸን ፍጡራን በመሆናችን እንጂ አማኑኤል ሆስፒታል ወይም አንዱ ጠበል የሚያስገባ መከራ ነው እኮ ተሸክመን የምንዞረው፡፡ በአንድ ወቅት 27 በመቶ የምንሆነው የአዕምሮ ሁከት እንዳለብን ሲነገረን ቀልድ የመሰለን፣ አሁን እውነት መሆኑን ለማመን መቃረብ ብቻ ሳይሆን ይህ ቁጥር በእጥፍ ላለማደጉ ምንም ማስተማመኛ የለንም፡፡ አዕምሮ በመከራና በጭንቀት ተወጥሮ ምን ሰላም አትሉም እንዴ!

በመውጣትና በመግባት ዓይን የማያየው ጆሮ የማይሰማው ነገር የለም። በዚህ በእኛው አገር ደግሞ ደህና አምነውት ሐሳብን ትውት አድርገው ከተጋደሙበት አልጋ ብንን እንዳሉ፣ ከንፈር አስመጣጭ ዜና ይዞ ብቅ ይልባችኋል ከጎረቤት። ሰሞኑን በአገራችን ላይ የተከሰተው ዕልቂትና ውድመት ከተለመደው ውጣ ውረዴ ጋር ተደራርቦ ነው መሰለኝ፣ በነጋታው ድካሜ አልወጣልኝ ብሎ እስከረፋዱ ተጋድሜያለሁ። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ማንጠግቦሽን አስፈቅዶ ገብቶ፣ ‹‹ድሮስ እንዳንተ ዓይነቱ ቀብራራ ደላላ ምን አለበት? በል ተነስ አሁን ቀብር ልንሄድ ነው…›› አይለኝ መሰላችሁ? ከተቀበርንበት የእንቅልፍ ጉድጓድ ሳንነቃ ቀብረን የጨረስነው ስንቱ ይሆን እናንተ? ክው አልኩና ተስፈንጥሬ ተነስቼ፣ ‹‹ማን ሞተ?›› ስለው፣ ‹‹ማን ያልሞተ አለ?›› አለኝ እየሳቀ። በሙታን አጉል ሲሳለቅ ሳየው ይኼው የእኔ ወዳጅ መቃብር ቆፋሪ መሰለኝ። ‹‹ቀልዱን ትተህ ምናለበት ብትነግረኝ? እኔ የሰማሁት ነገር የለም አልኩህ እኮ?›› ብለው ኮስተርና ቆምጠጥ ብዬ እሱ ግን አልተለወጠም። ለውጥ ላይ ሆነን አንለወጥም እንደሚሉት ይሆን እንዴ!

ጭራሽ ‘የአገር ልጅ በገንዘብ ይለወጣል ወይ፣ ሲሞቱ የሚቀብር ሲታመሙ የሚያይ’ ብሎ ይሞዝቅልኛል። ጉድ እኮ ነው! ‹‹ኧረ እባክህ አንተ ሰው?›› ብለው ብሠራው ሊሰማኝ አልቻለም። በስንት መከራ የሞተውን ሰው ማንነት ሲነግረኝ ለካስ በሠፈሩ የታወቀ የዋህ ሰው ኖሯል። ‹‹በነገራችን ላይ…›› አለኝ ጉድ የማያልቅበት ምሁሩ የባሻዬ ልጅ። ‹‹ስንትና ስንት መሰሪዎችና ሴረኞች በሰው ሕይወት የሚቆምሩ እያሉ ደጋጉና የዋሁ ሲሞት ያበሳጨኛል…›› ሲለኝ ማንጠግቦሽ ወጣ ገባ ስትል ሰምታው ኖሮ፣ ‹‹ምን ዋጋ አለው? እነሱ ለሥልጣናቸውና ለጥቅማቸው ሲሉ የዋሁን እየነዱ እየላኩ ምስኪኖችን ያስፈጃሉ፡፡ እነሱ ጠያቂና አንበርካኪ ሕግ አስፈጻሚ ዝንባቸውን እሽ ስለማይል ጠግበው ያፋጁናል..›› አለችው። እነሱ በጉዳዩ የተግባቡ ይመስላሉ። በርካታ የሚያግባቡን የጋራ ጉዳዮች እያሉን መግባባት አቅቶን ለዕልቂትና ለውድመት የምንጣደፈው ለምን ይሆን? ልጆቻችን የአገር አጥፊዎች ጉዳይ አስፈጻሚዎች ሆነው የገዛ ወገኖቻቸውን ሲገድሉና የደሃ አገር ንብረት ሲያወድሙ እንዳላየ ሆነን የምናልፈው ለምንድነው? ያ ሁሉ ውርጅብኝ ከደረሰ በኋላ አስተዛዛኝ መስለንስ የአዞ ዕንባ ለምን እናነባለን? አስመሳይነትና አድርባይነት በዛ እኮ እናንተ!

አንድም ወዳጅ ዘመድ ባልታየበት የቀብር ሥነ ሥርዓት ባሻዬ ማልቀስ አላቆም ብለው ስላስቸገሩ ቀስ ብዬ ቤታቸው ይዣቸው ሄድኩ። ‹‹ይተው እንጂ ባሻዬ! ትልቅ ሰው አይደሉም እንዴ?›› ብላቸው፣ ‹‹ውይ አምላኬ! ውይ! ውይ! ቀባሪማ አታሳጣኝ አደራህን! አደራህን!›› እያሉ እንባቸውን ማዝራታቸው ቀጠሉ። በስንት ንዝንዝ በረድ ሲልላቸው፣ ‹‹አንበርብር ለዚህ ምስኪን ልጅ ብቻ መሰለህ ይኼን ያህል የማለቅሰው? በጀብደኞችና በጥጋበኞች ምክንያት ያለ ጥፋታቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ለተገደሉ ወገኖቼ ጭምር ነው፡፡ በኃጢያተኞች ምክንያት እየተገደሉ የትም ለተጣሉ የሰው ልጆች ጭምር በሙሉ ነው የማለቅሰው። እውነቴን ነው። ሁሉም ነገር ኖሮህ ሁሉንም ሰው ከምታጣ ምንም ነገር ሳይኖርህ የሰው ፍቅር አትጣ። ሰው ነው የሰው ተስፋው፡፡ የሰውን ልጅ ጠልተው በብሔርተኝነት ያበዱ ዘረኞች ግን በምድርም በሰማይም ይቅር እንደማይባሉ ግን አትርሳ…›› ሲሉኝ ቀዝቀዝ አልኩ። የሚያቀዘቅዝ የአገር ሽማግሌና የእምነት መሪ የሚያስፈልገው በዚህ ጊዜ መሆኑ ትዝ ሲለኝ፣ ንዴት ግንፍል እያደረገኝ እንገበገብ ጀመር፡፡ እነሱም ውስጥ ጥቅም ፈላጊዎችና ሰላም አደፍራሾች እንዳሉ ሲነገር አላምንም ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን እየገባኝ ነው፡፡ በሰው ልጅ ሕይወት ላይ የሚነግዱና የሚደለሉ ሞልተዋል፡፡ የእነሱን ነገር ለሕግና ለህሊና ብቻ ሳይሆን ለሰማዩም ጌታ ማሳቀል ያስፈልጋል!

ዕድሜ ሲያበስል ሁሉን ነገር ያመላክታል ያሰኛል አዛውንቱን ባሻዬን ለሚያውቃቸው። ሲበዛ የነገር ሥር ማስተዋልና መለየት የተካኑ ናቸው። እርጅናን ብፈራውና ብጠላውም የሚለግሰውን የማስተዋል ጥበብ በባሻዬ ሕይወት ስለማጤን አልፎ አልፎ ይናፍቀኛል። ባሻዬ ጋቢያቸውን እንደተከናነቡ እንቅልፍ ሸለብ ሲያደርጋቸው ተነስቼ ወጣሁ። እንዳይሆን ሆኖ የዋለ ቀኔ የሥራ ሞራሌን አድቅቆት፣ አንድ ካፍቴሪያ ሻይ ፉት ልል ተጎለትኩ። ለግላጋ ወጣት ልጅ መጣችና አጠገቤ ቆመች። አስተናጋጅ መሆኗ ነው። ‹‹እ?›› አለችኝ። ደነገጥኩም ፈራኋትም። ዘንድሮ መንገዱንና መሬቱን ሁሉ ጉልቤው ነዋ የያዘው። ‹‹አቤት?›› አልኩ ስፈራ ስቸር። ‹‹ምን ፈልገህ ነው?›› ብላ በአንዴ ዘረጠጠችኝ። የገባሁትስ ስም ያለው ካፌ ነበር። ዳሩ ምን ያደርጋል? የሞራልና የሥነ ምግባር ዝቅጠታችን ደረጃ እዚህ ደርሶ ይህች አንድ ፍሬ አስተናጋጅ ዘረጠጠችኝ፡፡ ባለቤቱ የሥራ ላይ ሥልጠና ሰጥቶ ማሰማራት ሲገባው፣ ይኼኔ እሱም መደበሪያ ብሎ የጀመረው ሥራ ሆኖበት ያስገላምጠናል፡፡ ፖለቲካውም እንዲህ መላ ቅጡ የጠፋው እኮ ያለ ዕውቀትና ክህሎት መደበሪያ ያደረጉ ተጧሪዎችና አፍለኞች ተሰግስገውበት ነው፡፡ ፌስቡክ ላይ የምናስተውላቸው ስድቦች፣ ዘለፋዎችና ጋጠወጥ ንግግሮች ከውድመት ቅስቀሳዎች ጋር የሚቀናጁት እኮ ፖለቲካችን ብልሽትሽቱ ስለወጣ ነው፡፡ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ይህች እኮ አትጠፋኝም፡፡ ብዙ እናውቃለን ለማለት ያህል ነው!

የማኅበራዊ ሕይወታችን ግዴታዎች እንደምታውቁት ነው። የምትወጡበትና የምትገቡበት ኅብረተሰብ መሀል ይሉኝታ ቢስ ሆኖ መኖር ለአዲሱ ትውልድ እንጂ፣ ለእኛ ለእኛው የሚታሰብ አልሆነም። ታዲያ ምን ታዘብኩ መሰላችሁ። ቅጥቅጥ አይሱዙ በወረደ ዋጋ አገበያይቼ የጠበቅኩትን ያህል ሳላገኝ ወደ ቤቴ ሳዘግም ዝናብ ያዘኝ። ለካስ ዝናቡ ጀማምሮት እያወረደው ነው፡፡ አንዷን ጃንጥላ የያዘች እመቤት ጠጋ ብዬ፣ ‹‹መጠለል ይቻላል?›› አልኳት። ‹‹አይ የእኛ ኑሮ? የጃንጥላን ያህል መጠለያ የምትሆን ዛኒጋባ ማቆም ያቃተን እኮ ነን፤›› የሚለኝ ወዳጄ ትዝ አለኝ። ‘ዝናብ ጠብቆ ትዝ የሚለኝ ነገር ክፋቱ’ እያልኩ መልሷን ስጠብቅ፣ ‹‹ከከፈልክ ይቻላል!›› አለችኝ እየሳቀች። አባባሏ አልገባኝ እንዳለ ተጠግቻት ለጥቂት ከዶፍ ተረፍኩ። አልፎ አልፎ ላናግራት ስሞክር የፈረደበት ‘ስማርት ፎን’ ስልኳ ላይ ተተክላ ህልውናዬን እየካደች አስቸገረችኝ። በቴክኖሎጂ ከተቀራረብነው የተራራቅነው ማየሉን ልብ በሉልኝ። በዚህ መሀል ሠፈሬ የሚያደርሰኝ ሚኒ ባስ ታክሲ መጣ። ወያላው ሲያሳፍረን ‹‹እዚህች ጋ ጠጋ በይለት! ቅርብ ወራጅ አለ፤›› ቢላት አንዷን ቀዘባ፣ ‹‹በዘመነ ኮሮናማ ቅድሚያ የስድስት ወር…›› አለችው እየሳቀች። ‹የቤት ኪራይ እንዳማረራት ነገረችን ማለት ነው?› እያሉ አንዳንዶች እያሟት ነው። ሠፈሬ ደርሼ ወረድኩና ወደ ቤቴ ሳዘግም ከአቅም በታች የምትኖር ሴት ከአቅሟ በላይ ከሱቅ የሸመተቻቸውን ዕቃዎች ተሸክማ ሳይ፣ ‹‹ላግዝሽ!›› ብዬ ቀረብ አልኩ። እኔ ከድሮ ጀምሮ የማውቀው መተጋገዝና መረዳዳት ያደግንበት ነበር። በመገረም አይታኝ፣ ‹‹በኋላ የማይሆን ገንዘብ ብትጠይቀኝ እንዳንጣላ!›› ብላኝ አረፈችው። ‹‹ሰውን ምን ነካው?›› በማለት የሆንኩትን ሁሉ ዘክዝኬ ለማንጠግቦሽ ብነግራት፣ ‹‹ፖለቲካውና ኑሮው አንጎሉን አዙሮት ነዋ!›› ብላ በስላቅ መለሰችልኝ። የባሰ አይምጣ እንበል እንጂ የምናየውና የምንሰማው ነገር ምኑም ደስ አይልም። ነገር ግን ሕይወት መቀጠሉ ስለማይቀር ዘመኑን መስለን እንኖራለን፡፡ ተስፋ መቁረጥ አይታሰብም፡፡ መልካም ሰንበት!      

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት