Tuesday, December 5, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ቤተ መንግሥትን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የ477 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ከፈረንሣይ መንግሥት ተገኘ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብሔራዊ ቤተ መንግሥት የቱሪዝም መዳረሻ አድርጎ ለሕዝብ ክፍት ለማድረግ ለታቀደው ፕሮጀክት፣ 477 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ከፈረንሣይ መንግሥት ተገኘ።

ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የፈረንሣይ መንግሥት የ796.9 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በዕርዳታ መልክ ለመስጠት፣ ሐሙስ ሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ስምምነት ተፈርሟል።

ስምምነቱን የፈረሙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴና የፈረንሣይ መንግሥት የልማት ኤጄንሲ የኢትዮጵያ ተወካይ ቫሌሪ ቲዎ መሆናቸው ታውቋል።

የፈረንሣይ መንግሥት በዕርዳታ መልክ ከሰጠው 796.9 ሚሊዮን ብር ውስጥ 477 ሚሊዮን ብር የሚውለው፣ ብሔራዊ ቤተ መንግሥትን በማደስ የቱሪስት መዳረሻ ፓርክ ለማድረግ ለተያዘው ፕሮጀክት የሚውል ነው።

ይህ ፕሮጀክት ከታቀደ በርካታ ዓመታት ያለፉት ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ አዲስ አበባን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በሰጡት ትኩረት ከተለዩ ግንባር ቀደም ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው።

በአሁኑ ወቅት ብሔራዊ ቤተ መንግሥት የፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጽሕፈት ቤትና መኖሪያ ሲሆን፣ ለቀደሙት የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንቶችም ተመሳሳይ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ መሆኑ ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ይኼንን ቤተ መንግሥት ለቱሪዝም መዳረሻነት እንዲያገለግል የያዙትን ሰፊ ዕቅድ ባብራሩበት ወቅት፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤትና መኖሪያ አራት ኪሎ በሚገኘው ታላቁ ቤተ መንግሥት ወይም በአሁኑ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መኖሪያ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንደሚዘዋወር መግለጻቸው ይታወሳል።

ብሔራዊ ቤተ መንግሥትን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የታቀደው ፕሮጀክት በሦስት ምዕራፎች የሚከናወን ሲሆን፣ የመጀመርያው ምዕራፍ የቤተ መንግሥቱን የፊት ለፊት ክፍል አድሶ ለጎብኝዎች ክፍት ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ የቤተ መንግሥቱ መካከለኛ ክፍልን የግንባታ ይዘቱን ሳይለቅ ማደስና ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻ መናፈሻዎችን ማካተት ነው፡፡

የመጨረሻው ምዕራፍ ከቤተ መንግሥቱ የጀርባ ክፍል እስከ ፍል ውኃ ዳርቻ ያለውን ተፋሰስ ማልማት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ የግንባታ ጥበብ በቤተ መንግሥቱ የሚገኙ አጠቃላይ ቅርሶችን በልዩ እንክብካቤ በመጠበቅና በማልማት የሚከናወን እንደሚሆን፣ ከፈረንሣይ መንግሥት የተገኘውም የገንዘብ ድጋፍ ይህንኑ ለማረጋገጥ ለሚያስፈልግ የቴክኒክና አቅም ግንባታ ሥራ እንደሚውል ታውቋል፡፡

ቤተ መንግሥቱን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የተያዘው አጠቃላይ ፕሮጀክት ግን ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የፈረንሣይ መንግሥት በዕርዳታ ከሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ውስጥ የተቀረው መጠን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍ እንደሚውል የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች