Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአፍሪካ ኅብረት በህዳሴ ግድቡ የድርድር ውጤት ሪፖርት ላይ ሊመክር ነው

የአፍሪካ ኅብረት በህዳሴ ግድቡ የድርድር ውጤት ሪፖርት ላይ ሊመክር ነው

ቀን:

ግድቡ ውኃ መያዝ በመጀመሩ ግብፅ አቤቱታ አሰማች

የአፍሪካ ኅብረት ጠቅላላ ጉባዔ ቢሮ በህዳሴ ግድቡ ድርድር ዙሪያ ሦስቱ ተደራዳሪ ወገኖች ስምምነት በደረሱባቸውና ባልተግባቡባቸው ጉዳዮች ላይ መክሮ ውሳኔውን ለማሳወቅ፣ በዚህ ሳምንት እንደሚሰበሰብ ታወቀ።

በወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ የሚመራው የኅብረቱ ጠቅላላ ጉባዔ ቢሮ አባል አገሮች ኬንያ፣ ኮንጎ፣ ግብፅና ማሊ ናቸው። የቢሮው አባል አገሮች የሚወከሉትም በመሪዎች መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

ቢሮው ከቀናት በኋላ እንደሚሰበሰብ የጠቆሙት የሪፖርተር ምንጮች፣ ጉዳዩም ሰሞኑን ያለ ስምምነት የተጠናቀቀው የህዳሴ ግድቡ የውኃ ሙሌትና አስተዳደርን የተመለከተው ድርድር አጠቃላይ ሪፖርትን በመገምገም፣ በቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫ ላይ መወሰን እንደሆነ ገልጸዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ጠቅላላ ጉባዔ ቢሮ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ባካሄደው ስብሰባ ታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት የአደራዳሪነት ሚናውን የአፍሪካ ኅብረት እንዲይዝ በወሰነው መሠረት፣ ሦስቱ አገሮች ለ11 ቀናት ሲደራደሩ መቆየታቸው ይታወሳል።

በዚህ ድርድር ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም መሠረታዊ በሚባሉ ጥቂት ነጥቦች ላይ መቀራረብ ባለመቻላቸው፣ ሐምሌ 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ያለ ስምምነት መቋረጡ ይታወሳል።

በዚህም ምክንያት የድርድሩን አጠቃላይ ይዘትና የልዩነት ጭብጦችን ከእነ ምክንያቶቻቸውና የመፍትሔ ሐሳቦቻቸው፣ ሦስቱም አገሮች በተናጠል ለኅብረቱ ሪፖርት እንዲያቀርቡ መደረጉን ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ከምንጮች የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በተመሳሳይ የአፍሪካ ኅብረትን በመወከል ድርድሩን ሲመሩ የነበሩት የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ተወካይና የኅብረቱ የባለሙያዎች ቡድን የጋራ ሪፖርትም፣ ለኅብረቱ መቅረቡን ምንጮች አስረድተዋል።

የኅብረቱ ጠቅላላ ጉባዔ ቢሮም ከቀናት በኋላ በሚያካሂደው ስብሰባው የቀረቡትን ሪፖርቶች ገምግሞ፣ በቀጣይ አቅጣጫ ላይ ከሦስቱ አገሮች መሪዎች ጋር እንደሚወያይ ይጠበቃል።

የሱዳን መንግሥት ሐሙስ ሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ድርድሩን የተመለከተ ሪፖርት ለኅብረቱ መላኩን ያስታወቀ ሲሆን፣ ከሪፖርቱ በተጨማሪ በኢትዮጵና በግብፅ መካከል ያለውን ልዩነት ለመፍታት ያስችላል ያለውን የመፍትሔ አማራጭ እንዳቀረበም ጠቁሟል።

ሰሞኑን በተቋረጠው የሦስቱ አገሮች ድርድር የልዩነት ምንጭ ሆነው የተጠቀሱት መሠረታዊ ነጥቦች በድርድር በሚደርሱበት ስምምነት አፈጻጸም ወቅት አለመግባባት ቢከሰት እንዴት ይፈታል የሚለው ነጥብ አንደኛው ሲሆን፣ ከዚህ የልዩነት ነጥብ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ሌላው የልዩነት ነጥብ ደግሞ የተራዘመ ድርቅ ወቅት ቢያጋጥም የግድቡ አስተዳደር ምን ሊሆን ይገባል የሚል የቴክኒክ ጉዳይ ነው።

የተራዘመ ድርቅ የሚለው ጉዳይ የሚወሰነው ወደ ታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች ማለትም ወደ ግብፅና ሱዳን የሚፈሰው ዓመታዊ የውኃ መጠን 37 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብና ከዚያ በታች ከሆነ የድርቅ አመላካች እንደሚባል፣ ይህ ሁኔታ ከሁለትና ከዚያ በላይ ዓመታት የቀጠለ እንደሆነ ደግሞ የተራዘመ ድርቅ የሚል ትርጓሜ እንዲኖረው የቀረበ ሐሳብ ቢኖርም፣ ግብፅ ደግሞ የታላቁ አስዋን ግድብ የውኃ ከፍታ ከባህር ጠለል በላይ 165 ሜትር ሲደርስ የድርቅ አመላካች እንደሆነ፣ ይህ ሁኔታ ከሁለት ዓመታት በላይ ከቀጠለ የተራዘመ ድርቅ ሊባል ይገባል የሚል አቋም ታራምዳለች።

የድርቅ አመላካች ሲከሰት ኢትዮጵያ ግድቡን እንዳትሞላና ወደ ግድቡ የመጣው ውኃ ኃይል አመንጭቶ እንዲያልፍ መሠረታዊ ስምምነት በአገሮቹ መካከል ቢደረስም፣ የድርቅ አመላካች ላይ ግን ሙሉ ስምምነት አልተደረሰም።

በተመሳሳይ የተራዘመ ድርቅ አመላካች ላይ ስምምነት ባይደረስም፣ የተራዘመ ድርቅ ሲከሰት ኢትዮጵያ ግድቡን መሙላት አቁማ የመጣውን ውኃ እንድታሳልፍና በግድቡ ከያዘችው ውኃ ላይም ስምምነት የሚደረስበትን ያህል ውኃ እንድትለቅ መሠረታዊ መግባባት በአገሮቹ መካከል ይስተዋላል። ነገር ግን ሁለቱንም የድርቅ ሁኔታዎች በሚያመላክቱ ጉዳዮች ላይ ስምምነት አልተደረሰም።

ግብፅ የአስዋን ግድብ የውኃ ከፍታ 165 ሜትርና ከዚያ በታች ከሆነ የድርቅ አመላካች እንዲሆን የምትፈልግ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ የአስዋን ግድብን ማስተዳደር በማትችልበት ሁኔታ የአስዋን ግድብን የውኃ መጠን የድርቅ አመላካች አድርጎ መቀበል ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚይዘውን አጠቃላይ የውኃ መጠን ላለመያዝ እንደ መስማማት እንደሆነ በመጥቀስ፣ ይህንን አማራጭ ውድቅ አድርጋዋለች።

ነገር ግን አሁንም የተራዘመ ድርቅ አመላካች ላይ ስምምነት ያልተደረሰ በመሆኑ፣ ሌላኛው የልዩነት ነጥብ የሆነው የስምምነቱ አፈጻጸም ላይ ልዩነት ቢከሰት እንዴት ሊፈታ ይገባል የሚለው ጉዳይም ሰፊ የልዩነት ጭብጥ ሆኗል።

በስምምነቱ አተገባበር ወቅት አለመግባባት ቢከሰት ወደ ልዩ ፍርድ ቤት ወይም ወደ አሸማጋይ ተሄዶ ውሳኔ እንዲሰጥበት፣ ይህ ውሳኔም ይግባኝ የማይቀርብበት ሊሆን ይገባል የሚል ሐሳብ በግብፅና በሱዳን በኩል መቅረቡን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ኢትዮጵያ ግን በአተገባበር ወቅት አለመግባባት ከተፈጠረ በሦስቱ አገሮች ሚኒስትሮች ወይም በመሪዎች እንዲፈታ፣ በእነሱ ካልተፈታ ደግሞ በጋራ የሚወስኑት አሸማጋይ እንዲፈታ የሚል ሐሳብ አቅርባለች።

ለዚህም መነሻ ያደረገችውም ሦስቱ አገሮች እ.ኤ.አ. በ2015 የተፈራረሙት የትብብር መግለጫ ስምምነት ልዩነቶች በዚሁ አግባብ እንዲፈቱ የሚል መሆኑን፣ አሁን የሚደረገው ድርድርም በዚሁ ስምምነት መሠረት እንደሆነ በመጥቀስ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ስለተራዘመ ድርቅ ግልጽነትና መግባባት ሳይኖር፣ ይግባኝ የማይጠየቅበት ልዩነትን የመፍቻ ስምምነት ማድረግ ተገቢነት የሌለውና የህዳሴ ግድቧንም ሆነ በዓባይ ውኃ ላይ ወደፊት የምታካሂደውን ልማት ሊገድብ እንደሚችል በመከራከሪያነት አንስታለች።

የአፍሪካ ኅብረትም ከቀናት በኋላ በእነዚህ የልዩነት ነጥቦች ላይ አስታራቂ የመፍትሔ መንገድ ይጠቁማል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የታላቁ የህዳሴ ግድብ መካከለኛ ክፍል ቁመት ከባህር ጠለል በላይ 560 ሜትር ከፍታ ላይ በመድረሱ፣ ከግድቡ አልፎ ወደ ታች የሚፈሰው የውኃ መጠን ቀንሷል። በዚህም ምክንያት በግድቡ ውኃ መጠራቀም ጀምሯል።

ይህንን ተከትሎም የግብፅ መንግሥት አቤቱታውን ለደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ማቅረቡ የተሰማ ሲሆን፣ ቅሬታውም ስምምነት ሳይደረስ ኢትዮጵያ ውኃ መሙላት መጀመሯን የሚገልጽ ነው።

ይሁን እንጂ በትብብር መግለጫ ስምምነቱ አንቀጽ አምስት ላይ ድርድሩና ግንባታው ጎን ለጎን እንደሚካሄድ የሦስቱ አገሮች መሪዎች መስማማታቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ በወቅቱ በግብፅ በኩል ስምምነቱን የፈረሙት አሁንም ሥልጣን ላይ የሚገኙት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ መሆናቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በሚዲያ በሰጠው ምላሽ የግድቡ ግንባታ ካለፈው ዓመት ከፍ በማለቱ፣ ወደ ግድቡ የሚገባው የውኃ መጠን ሙሉ በሙሉ መውጣት እንደማይችልና ከግድቡ ጀርባ ተንጣሎ የሚታየው ውኃ የተፈጠረውም በዚሁ ምክንያት መሆኑን አስታውቋል።

ይህ የተፈጠረው በግንባታው ተፈጥሯዊ ሒደት እንደሆነና ግድቡ ካልፈረሰ በስተቀር የተጠራቀመው ውኃ ሊወጣ እንደማይችል ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሦስቱ አገሮች ድርድራቸው ላይ በማተኮር፣ አለመግባባታቸውን እንዲፈቱ ጠይቋል፡፡ በአፍሪካ ኅብረት የተጀመረው ድርድር ዳግም በመቀጠል ውጤት እንደሚያስገኝ እምነት እንዳለው አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...