Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ይድረስ ለሪፖርተርግልጽ ደብዳቤ ለጀርመን መራሒተ መንግሥት

ግልጽ ደብዳቤ ለጀርመን መራሒተ መንግሥት

ቀን:

ኢትዮጵያና ግብፅ በጥንታዊ ታሪክና ባህል የሚታወቁ አገሮች ሲሆኑ፣ ሁለቱም አገሮች በሺዎች በሚቆጠሩ ዓመታት በዓባይ ወንዝ ብቻ ሳይሆን በባህልና በማኅበራዊ ግንኙነት የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመካከላቸው ያለው የወዳጅነት ግንኙነት ኢትዮጵያ በግዛቷ ውስጥ በዓባይ ወንዝ ላይ በምትገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ምክንያት ከፍተኛ ውጥረት እየጨመረ ሊመጣ ችሏል፡፡

የሚያሳዝነው ሚዲያዎች መጪውን የግድቡን አሞላል በተመለከተ ለግብፅ ችግር እንደሚፈጥር ብቻ አድርጎ በማየትና ከዚያም በመነሳት በቀጣናው ውስጥ ግጭት የመነሳት ሁኔታ ከፍተኛ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በሌላ መልኩ ግድቡ በሁሉም የናይል ተፋሰስ አገሮች በርካታ ጥቅሞች እንዳለው ግን ግንዛቤ አይሰጡም፡፡ ከዚህ በመነሳት ስለግድቡ የተገናዘበና የተመዛዘነ መረጃ እንዲሆን በማለት በዚህ ደብዳቤ እናስረዳለን፡፡  ኢትዮጵያ 1,104,300 ካሬ ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋትና 114 ሚሊዮን የሕዝብ ብዛት ያላት አገር ስትሆን የባህር በርና ወደብ የላትም፡፡ ግብፅ 1,001,499 ካሬ ሜትር የቆዳ ስፋት፣ 100 ሚሊዮን የሕዝብ ብዛት ያላት ሲሆን፣ በሰሜን 2,450 ኪሎ ሜትር በሜዲትራኒያን የባህር በርና በምሥራቅ በቀይ ባህር በኩል 800 ኪሎ ሜትር ያላት አገር ነች፡፡ ኢትዮጵያ ከግዛቷ ተነስቶ 86 በመቶ ወደ ግብፅ የሚፈሰው የዓባይ ወንዝ ባለቤት ብትሆንም ከውኃው ምንም ተጠቃሚ ሳትሆን፣ ግብፅ ለናይል ወንዝ የ0% አቅርቦ ይዛ እስካሁን ድረስ የወንዙ ብቸኛ መቶ በመቶ ተጠቃሚ ሆና ቆይታለች፡፡ ከኢትዮጵያ ተነስተው የሚሄዱ ወንዞች 70 በመቶ ኢትዮጵያን ለቀው ወደ ጎረቤት አገሮች የሚፈሱ ናቸው፡፡ ግብፅ በከርሰ ምድሯ በግምት 50,000 ኪዩቢክ ኪሎ ሜትር የሆነው እጅግ ግዙፍ የውኃ ሀብት ያላት አገር ስትሆን፣ ኢትዮጵያ በከርሰ ምድሯ ያላት የውኃ ክምችት 10,000 ኪዩቢክ ኪሎ ሜትር ነው፡፡

ግብፅ ከኢትዮጵያ በተቃራኒ የዓባይ ወንዝ የምትጠቀመው ለግብርና ለም መሬት ለማጠጣት እንዲሁም ለምሳሌ ወደ አውሮፓ የሚላኩ ፍራፍሬዎችን ለማምረት ጭምር ነው፡፡ በግብፅ ውስጥ አንድ ሰው በዓመት በአማካይ 1,510 ኪሎ ዋት (ሰዓት) የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ ሲኖው በኢትዮጵያ ግን አንድ ሰው 69 ኪሎ ዋት (ሰዓት) ብቻ ነው ፍጆታ ያለው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የግብፅ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም 55,000 ሜጋ ዋት ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ወደ 4,300 ሜጋ ዋት የሚጠጋ ነው፡፡ ይህም የግድቡ ሙሌት ሲጠናቀቅ ይህ ወደ 10,000 ሜጋ ዋት ሊያድግ ይችላል፡፡

- Advertisement -

እነዚህ መረጃዎች ኢትዮጵያ ይህንን ግድብ ለመገንባት መነሳቷ ለምን በጣም አስፈላጊና ግዴታዊ እንደሆነ ለማስረዳት በአጭር ግንዛቤ የሚሰጡ ናቸው፡፡ 6,000 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው ይህ የአፍሪካ ትልቁ ግድብ በኢትዮጵያ በራሷ አቅም የተገነባ ነው፡፡ ይህም ከመንግሥት በጀትና ከማኅበረሰቡ እያንዳንዱ ዜጋ በነፍስ ወከፍ ባዋጡት ገንዘብ ነው፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተገነባው በኢትዮጵያ፣ በአሜሪካ፣ በጣሊያን እንዲሁም በጀርመን ኩባንያዎች በተቀናጀ ከፍተኛ ቴክኒካዊና ሙያቂ ብቃት ነው፡፡ ግድቡ ሁለት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውና ቁመቱም 145 ሜትር ነው፡፡ የደረጃ በደረጃ ሙሌቱ እ.ኤ.አ. በJuly 2020 የሚጀመርና እስከ 2027 ድረስ የሚቀጥል ነው፡፡

ይህ የናይል ውኃ ሀብቶች በፍትሐዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም በአሁኑ ወቅት ከ40 በመቶ በታች የኤሌክትሪክ ኃይል ላላት ኢትዮጵያ በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል እንድታገኝ ያስችላታል፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማፋጠን፣ መሠረተ ልማትን ለማሳደግ፣ ሥነ ምኅዳራዊ (የከባቢ አየር) እና ግብርናን ለማሻሻል እንዲሁም በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች የሥራ ዕድልን በመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ለአገሪቱ አጠቃላይ ልማትም ትልቅ መሠረት ይጥላል፡፡ ይህ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ቀንድም መረጋጋትንና ሰላምን ያጠናክራል፡፡ ግድቡ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገሮች የኤሌክትሪክ ኃይል በርካሽ አገልግሎት ማቅረብ ትችላለች፡፡ በዚህም ደግሞ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራና ጂቡቲ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

ግብፅ እ.ኤ.አ. በ1929 በታላቋ ብሪታንያና በግብፅ፣ በኋላም በሱዳንና በግብፅ መካከል የተደረገውን የቅኝ ግዛት የናይል ውኃ ውል ስምምነትን መሠረት በማድረግ ትከራከራለች፡፡ ይህም የውኃውን 86 በመቶ ድርሻ የምታመነጨውን ኢትዮጵያን የሚያገልና በውኃው ሁለቱ አገሮች ብቻ መጠቀም እንዲችሉ የሚፈቅድ ነው፡፡ ቅኝ ተግዛታ ለማታውቀው ኢትዮጵያ ይህ የቅኝ ግዛት የናይል ውኃ ስምምነት የሚሠራና የሚያስገድድ አይደለም፡፡ ፍትሐዊም አይደለም፡፡ ስለሆነም ግብፅና ሱዳን ይህንን እጅግ አስፈላጊ የተፈጥሮ ሀብት በፍትሐዊነት ለመጠቀም የ114 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንንና የጎረቤት አገሮችን የኑሮ ሁኔታ በእጅጉ ሊያሻሽል በሚቻልበት መልኩ ባካተተ የሦስትዮሽ ስምምነታቸውን ማጠናቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የጎረቤቶቿን የግብፅና የሱዳንን ፍላጎት ለማስተናገድና ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ፈቃደኛ ናት፡፡ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት የበኩሏን ሚና የተጫወተችና ከጎረቤት አገሮች ጋር በሰላማዊ የምጣኔ ሀብት ትብብር የረዥም ጊዜ ባህል እንዳላት ታሪክ ያሳያል፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት ዋና ከተማ፣ የተባበሩት መንግሥታትና የአውሮፓ ኅብረት መቀመጫና ቢሮዎች ያሉባት መሆኗም ያለ ምክንያት አይደለም፡፡

እስካሁን ድረስ በርካታ ቴክኒካዊና ፖለቲካዊ ድርድሮች የተከናወኑ ሲሆን፣ የተወሰዱት በግብፅ የአስተሳሰብና የአቋም ለውጥ ምክንያት የተጓተቱ ናቸው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት እ.ኤ.አ. በዚህ በሐምሌ ወር 2020 መጀመርያ ላይ ግብፅ ባቀረበችው ጥያቄ መሠረት ተሰብስቦ የነበረ ቢሆንም፣ አብዛኛዎቹ አባላት በኢትዮጵያ የቀረቡን የአፍሪካ መፍትሔ እንደሚደግፉ አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ የታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታና አጠቃቀምን ለዓለም ደኅንነት አደጋ አድርጋ አትወስደውም፡፡ ግድቡን የምትመለከተውም በአፍሪካ የውስጥ ጉዳይና የኢኮኖሚ ጉዳይ መሆኑን በሚመለከታቸው የአፍሪካ አገሮች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕዝቦች ኑሮ የሚያሻሽልና ለአገር ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ነው፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ጀርመንና በዓለም ውስጥ እንዳሉ ሌሎች አገሮች ሁሉ የራሷን ሀብቶች በራስ የመጠቀም መብቷ ተፈጥሯዊ ሕግ የሆነና ሉዓላዊነት ያላት አገር መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡

የግድቡ መሞላት ከኢትዮጵያ ግብፅን ሊጠቅም እንደሚችል ይታወቃል፡፡ ይህም የተጣራ ውኃን በመልቀቅ ጎፍን ለመቀነስና ከ80 በመቶ በላይ ደለልን ለማስወገድ ይረዳል፡፡ በአንዳንድ የሚዲያ ሪፖርቶች ላይ ስለ ውኃ እጥረት ከሚጠቀሰው በተቃራኒ መልኩም ግድቡ የሚገኝበት ቦታ ቀዝቃዛና ጥልቅ ሸለቆ በመሆኑ የውኃውን መትነን ይቀንሳል፡፡

በአብዛኛው ሚዲያ ወገንተኝነትን በመያዝ፣ ግድቡ መጥፎ ውጤቶች የሚያስከትል ነው፡፡ በማለት ለግብፅ የግድቡ ግንባታ እጅግ ጎጂና የአካባቢውን ነዋሪ ኑሮ እንደሚጎዳ ተደርጎ ይቀርባል፡፡ ይህም እውነታውን በማዛባት በሰዎች አስተያየት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር ነው፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት በፍጥነት የሚሠራጭና ሚዛናዊ ያልሆነ መረጃ ለግጭት አሉታዊ አቅም አለው፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ በዓለም ላይ እንደሚታየው የአንድ ወገን መረጃ ብዙውን ጊዜ ሰዎችን አላስፈላጊ ወደሆነ ቅፅበታዊ ድርጊት ውስጥ ያስገባል፡፡ ከወደ ጀርመን የሚመነጩ ዘገባዎች በአፍሪካ አገሮች ዘንድ ‹‹ትክክለኛ ባይሆኑም እንኳን እንደ እውነት ይወሰዳሉ›› እና ይህም ሰዎችን የአንድ ወገን ዕይታቸውን ይበልጥ የተረጋገጠ መስሎ እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡ የተሳሳቱ ወይም የተዛቡ መረጃዎች በተለይም በአገራችን በጣም ከባድ ችግር ሊፈጥሩ፣ ይህም በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ግጭቶች የበለጠ ሊያባብሱ ይችላሉ፡፡

‹‹የሳንቲሙን አንድ ጎን›› ብቻ የማየሳዩ፣ ሚዛናዊነትን የጠበቁ ሪፖርቶችና ጥንቃቄ የተሞላበት ምርምራን ማየት እንመኛለን፣ እንጠይቃለንም፡፡

እኛ በጀርመን አገር የምንኖር ኢትዮጵያውያንና ጀርመን-ኢትዮጵያውያን የማኅበረሰብ ተወካዮች በተለያዩ የአካዴሚክ መስኮች ላይ ተሰማርተን የምንገኝ ምሁራን፣ አርቲስቶችና በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የምንገኝ የግል ድርጅት ባለቤቶች፣ እርስዎን እንደ ፖለቲከኛ ብቻ ሳይሆን እንደ ሳይንቲስትና እንደ አንድ የኢትዮጵያ ወዳጅ ጉዳዩን በትኩረት እንዲከታተሉ፣ በተለይም በቻንስለርነት ዘመንዎ ሁሉ እንዳደረጉት – በሚልዎት መልኩ ፍትኃዊነት በተሞላ ሁኔታ እንዲመለከቱት፣ በአክብሮት እንጠይቅዎታለን፡፡ የእርስዎ አመለካከትና ሐሳብ በሁሉም ተሳታፊ አገሮች ዘንድ አድናቆትና ዕውቅና እንደሚያገኝ እርግጠኞች ነች፡፡

ከኢትዮጵያውያን ሙሁራንና ታዋቂ ግለሰቦች

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ