Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉሕዝባዊ ለውጡን ለመታደግ ምን መደረግ አለበት? (ክፍል አራት)

ሕዝባዊ ለውጡን ለመታደግ ምን መደረግ አለበት? (ክፍል አራት)

ቀን:

በያዳ ኡመታ

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች እስካሁን ያለው አካሄድ የፖለቲካ ውሳኔያቸው በተጨባጭ ሁኔታ ላይ የተመረኮዘ ሳይሆን፣ በምኞትና በግል ፍላጎት ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው፡፡ እነሱ የሚፈልጉትን እንጂ ይህን ብናደርግ ተቃራኒው ኃይል ይቀበላል ወይ? የሚቀርቡ ሐሳቦች ሁላችንን አሸናፊ ሊያደርጉን ይችላሉ? የሚለው ከግምት ውስጥ አይገባም፡፡ ሁሉም ለራሱ ብቻ የሚያሸንፍበትንና የሚጠቅመውን ይዞ ለማሸነፍ ብቻ ይኳትናል፡፡ ይህ የአንዱን ወገን ፍላጎት ብቻ የሚያስጠብቅ አካሄድ አያስማማም፡፡ ችግሮችንም በዘለቄታ እንዲፈቱ አያደርግም፡፡ የሚቀርበው የመፍትሔ ሐሳብ የተቃራኒውን ወገን ጥቅም ከግምት ውስጥ ካላስገባና መፈናፈኛ ካሳጣ፣ የታፈነ ነገር ፈንድቶ መውጣቱ ስለማይቀር ውጤቱ ጉዳት ያስከትላል፡፡

እነዚህ አብዛኞቹ የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሳደብና ከመዝለፍ ውጪ፣ ለአገር ዕርባና የሌለው ሥራ ላይ ተጠምደው ከሚውሉ ኃይሎች አገራችን ምንድነው የምታገኘው ጥቅም ሁላችንንም ያወያያል፡፡ በዚህ ዓይነት የፖለቲካ ባህላችን የብዙኃን ፓርቲ ሥርዓት ለአገራችን ይበጃል ወይስ ጥፋት ያስከትላል የሚለውም ሊጤን ይገባል፡፡ በታዳጊ አገሮች ለዴሞክራሲ ሥርዓት አለመጎልበት ዋነኛው ችግርም ይህንን ይመስላል፡፡ ምርጫው ባይተላለፍና በነሐሴ 2012 ዓ.ም. የሚካሄድ ቢሆን ኖሮ፣ እንዲሁም በኦሮሚያ ተፎካካሪዎቹ ባያሸንፉ ምርጫው ተጭበርብሯል ተብሎ እንደ ሰሞኑ ዓይነት ረብሻ ላለማንሳት፣ ሥልጣን በኃይል ለመያዝና አገሪቱን ብጥብጥ ውስጥ ላለማስገባት ምንም ዋስትና አልነበረም፡፡

በተፎካካሪ ፓርቲዎችና በገዥው ፓርቲ መካከል ያለው የግንኙነት ባህል ፈፅሞ መቀየር አለበት፡፡ እንደ ጠላት በመተያየት በማኅበራዊ ጉዳዮችም ያለ መገናኘት፣ ያለ መነጋገር፣ የመኮራረፍ፣ የአንዱን ሐሳብ ሌላው እንደ ጠላት የሚያይበት፣ የተለያየ አገር እንደሚኖሩ ጠላቶች የሚተያዩበት፣ አንዱ አንዱን ለማዋረድና አቶ ጀዋር እየሠሩ እንዳነበሩት ነጥብ ለማስቆጠር በሚያደርጉት ጥረትና ይህን በማድረጋቸው ጀብዱ እንደሠሩ የሚኩራሩበት ይህ የተዛባ ልማድ በፍፁም መቀየር አለበት፡፡ እነዚህ ኃይሎች ለአንድ አገርና ሕዝብ የሚሠሩ እስከሆኑ ድረስ ለአገርና ለሕዝብ ሊሠሩ የሚችሉት፣ በመደማመጥ በመግባባትና በመከባበር ነው መሆን ያለበት፡፡ ካልተደማመጡ ሥልጣን ላይ የማይኖረው ኃይል ሐሳብና ሥራ ከንቱ ይሆናል፡፡ በገዥው ፓርቲ ተቀባይነት ስለማይኖረው ይህ ትልቅ የአገር ሀብት ኪሳራ ነው፡፡ ይህ ነው በኢትዮጵያ እየሆነ የቆየው፡፡ ተቃዋሚው ኃይል ለመቃወም እንጂ በአገር ዕድገት ላይ የሚያመጣው ለውጥ ከሌለ ዝም ብሎ መቃወሙ፣ ሕዝቡን በመከፋፈል የአገር አንድነትንም ሆነ የልማት ሥራውን ከማዳከም ውጪ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ አይኖርም፡፡

አንዱ የሌላውን ሐሳብ በኃይል ለማስቀየር ከመሄድ በተለይ ገዥውን ፓርቲ በማግባባትና በማሳመን (Lobby) በማድረግ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ካልዳበረ፣ በመጯጯህና በጋጋታ ብዛት ውጤት ማምጣት አይቻልም፡፡ እስኪ ሁላችንም ከዚህ በፊት ከምንሠራው ተቃራኒውን እናስብ እንሥራ፡፡ በአንዱ እንቢ ካለህ ተቃራኒውን ሞክር እንደሚባለው ዓይነት፡፡ ተቃዋሚዎችና የገዥው ፓርቲ አባላት በፅሞና፣ በመከባበር ይነጋገሩ፣ ይቀራረቡ፡፡ ይህ የጥላቻና የቂም በቀል ባህል ይወገድ፡፡ በገዥው ፓርቲ ሥር የተደራጀው ኃይል የአገሪቱ ሀብት ነው፡፡ ብዙ የአገር ሀብት ወጥቶባቸው የተማሩና በርካታ የሥልጠና ወጪ ወጥቶባቸው የሠለጠኑ ኃይሎች እዚህ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ ተቃዋሚዎች ይህን ኃይል ጥቅም እንዳሌለው ለመወርወር የሚያሳዩት ፍላጎት አይሠራም፡፡ አሁን አገራችን ባለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ለዴሞክራሲ ቅድመ ሁኔታዎቹ እስኪሟሉ ድረስ በሕዝቡ ተቀባይነት፣ ቅቡልነት ያለውና ውሰጠ ፓርቲ ዴሞክራሲው የሰፋ ሆኖ፣ ሕዝቡ በሲቪክ ማኅበራቱ አማካይነት ተፅዕኖ ሊፈጥርበት የሚችል፣ በአንድ ፓርቲ ብንመራ ጠንካራና የተረጋጋች አገር ለመመሥረት የበለጠ ይጠቅማል የሚል እምነት አለው ይህ ጸሐፊ፡፡

ይህ ሲሆን ሁሉም ሰው የፖለቲካ ተንታኝና ፖለቲከኛ አይሆንም፡፡ በሥራው ላይ ብቻ ተጠምዶ ይውላል፡፡ መከፋፈልና መጋጨት ይቆማል፡፡ አገር ታድጋለች፡፡ ብዙዎቹ ይህን ሐሳብ ለመቀበል ይቸገሩ ይሆናል፡፡ ግን በእነዚህ ሐሳቦች ዙሪያ እንወያይ፣ እንከራከር፡፡ እንዲያውም የምርጫ ጊዜን በተመለከተም ለወደፊት ሕገ መንግሥቱ ሲሻሻል በየአምስት ዓመት መሆኑ ቀርቶ በየስምንት ዓመት ቢሆን፣ ሥልጣን የያዘው ኃይል ዕቅዱን ለማጠናቀቅ በአንፃራዊነት በቂ ጊዜ ይኖረዋል፡፡ የህንድና የቻይና ዕድገት ልዩነት አንዱ የተረጋጋና ረዘም ላለ ጊዜ ሥልጣን ላይ በመቆየት፣ የህንድ ዴሞክራሲ በየአምስት ዓመት ምርጫው ለማካሄድ የሚያስችልና ከቻይና በተቃራኒው መሆኑ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ስለዚህ ይህን በገዳ ሥርዓት ባህላችን ምርጫ በየስምንት ዓመት እንዲካሄድ ቢደረግ ሥልጣን ለሚይዘው ፓርቲና መንግሥት ረዘም ያለ የሥራ ዓመት መስጠት ብቻ ሳይሆን፣ በየአምስት ዓመቱ ለምርጫ የሚወጣውን ገንዘብና ጊዜ ከ50 በመቶ በላይ ለመቀነስም ያስችላል፡፡

ይሁን እንጂ ምዕራባዊያን የሚያቀርቡልንን መድኃኒት የግድ ለመውሰድ የምንገደድ ከሆነ፣ ከሁለቱ ነገሮች አንዱ ግን መደረግ አለበት፡፡ አንደኛው እነዚህ ተበታትነው የተደራጁ በርዕዮተ ዓለም አቋማቸው ላይ ተመሥርተው ተሰባስበው ከሁለትና ሦስት ያልበለጡ  ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሆነው ሥርዓት ጠብቀው እንዲሠሩ ማድረግ፡፡ መሰባሰብ ካልቻሉ በአሁኑ ጊዜ የእነሱ መኖር ለአገሪቱ የሚፈይደው ስለሌለ ተበትነው አባላቱ ባላቸው ሙያ፣ ወይም በሲቪክ አባልነት አማካይነት አገራቸውን ቢያገለግሉ ይመረጣል፡፡ ሁለተኛው አማራጭ የተፎካካሪ ፓርቲዎችንና ገዥ ፓርቲንም ጭምር የሚገዛ ጠበቅ ያለ ሕግ ኖሮ፣ እንደ አሁኑ ደጋፊና ወገንተኛ የብዙኃን መገናኛ ሳይኖራቸው የሚሠሩት የሕዝብን ጥቅም የማይጎዳ፣ ሕዝብንና አገርን የሚታደግ፣ ሥልጣን ላይ የሚኖርን ፓርቲ ወይም መንግሥት ለመገዳደር ብቻ ሳይሆን ስህተቶቹን የሚያስተካክል ዓይነት ሆኖ በአማራጭ የሐሳብ ምጥቁነት ብቻ ለማሸነፍ የሚሠራ፣ እንዲያውም በብሔርና በሃይማኖት ላይ የተመረኮዘ አደረጃጀትን በማገድ ነው ሊሠራ የሚገባው፡፡ እገሌ፣ የእገሌ ነፃ አውጭ ወይም የነፃነት ግንባር፣ ወዘተ. ለኢትዮጵያ አሁን አያስፈልጋትም፡፡ ህ ጊዜው አልፎበታል፡፡ ለመሆኑ በአሁኑ ጊዜ ማን ከማን ነው ነፃ የሚወጣው?

 በእርግጥ በዚህ ረገድ በአገራችን አንድ የሚታይ በጎ ነገር የኢትዮጵያ የዜጎችና ማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) የተለያዩ ፓርቲዎች በማሰባሰብ የተደራጀ፣  የፓርቲው መሪዎችም አገራዊ ኃላፊነትን የተገነዘቡና የሚሰማቸው፣ የሰከኑ፣ የተከበሩ፣ ለሥልጣን ጉጉት ሲሉ አገርን የማያምሱና ሊመሠገኑ የሚገባቸው ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ነው፡፡ ሌሎች ፓርቲዎችም በዚህ ዓይነት ቢደራጁና ቢሠሩ በሌላ መንገድ የብዙኃን ፓርቲ መኖርን የሚያስጠላ ላያደርገው ይችላል፡፡

5.2. ከሕዝብ የሚጠበቁ ተግባራት

በአገራችን ኢትዮጵያ እየተካሄደው ባለው ፖለቲካዊ ትግል በፊት ለፊትነት ቀርበው ሲናቆሩ የሚታዩት ከኦሮሞ፣ ከአማራና ከትግራይ የተወጣጡ የፖለቲካ ልሂቃን ወይም ግለሰቦችና ቡድኖች ናቸው፡፡ በዚህ ለሥልጣንና ለክብር በሚደረግ ትግል ውስጥ እምብዛም የሌሉት የደቡብ፣ የሲዳማ፣ የሱማሌ፣ የሐረሪ፣ የአፋር፣ የቤንሻንጉል ጉምዝና የጋምቤላ ልሂቃንና ሕዝቦች በአብዛኛው እነዚያን ኃይሎች በዝምታ ወይም በትዝብትና በአግራሞት የሚመለከቱ የሚመስል ሁኔታ ይታያል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ምሁራኖቻቸው ስለአገራቸው ወቅታዊ ሁኔታ የሚጽፉና በተለያየ መንገድ ለአገራቸው ሰላምና ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ አሉ፡፡ በተለይ እንደ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ሙስጠፌና የጋምቤላው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አቶ ኦባንግ የመሳሰሉት እየተጫወቱት ያለው ሚናም ለሌሎች ትልቅ አርዓያ ነው፡፡ ግን በተባበረና በተቀናጀ ሁኔታ የእነዚህ ሕዝቦች ልሂቃን ችግሮቻችሁን በውይይት ፍቱ፣ ፋታ ስጡን፣ ወደ ልማት ገብተን ድህነትን እናሸንፍበት፣ ወዘተ. የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳትና ግፊት በመፍጠር ተወካዮቻቸውን መርጠው እስከ ማደራደር ድረስ በመሄድ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን አልነበረባቸውም ወይ? የሚለውን ጥያቄ ለማንሳት ነው፡፡

የቆየው የአገራችን የትግል ባህልና ሥልት በአጠቃላይ በሁለት ምክንያቶች ሊቀየር ይገባል፡፡ አንደኛው 21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ በመሆናችን የሠለጠነ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ሰላማዊ የሆነ የትግል ሥልት መከተል የግድ ይለናል፡፡ ስለዚህ የትጥቅ ትግል ማካሄድ፣ በሕዝባዊ አመፅ መንገድ በመዝጋትና ንብረትን በማቃጠል መንግሥትን ለመለወጥ የሚደረገው ትግል በአሁኑ ጊዜ ተገቢነት የለውም፡፡ የመጀመርያው መሆን ያለበት መንግሥት አካሄዱን እንዲያስተካክል፣ የአቋም ለውጥ በማድረግ በሠለጠነና በሰላማዊ መንገድ አገርና ሕዝብ ሳይጎዱ ጥያቄዎቻችንና ሐሳቦቻችን ተቀባይነት እንዲያገኙ ግፊት ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛ አሁን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በሕዝብ ትግል የመጣ በመሆኑ፣ ይህ መንግሥት በአግባቡ ሳይፈተሽ የአገሪቱን የተከማቸ ችግር በሙሉ አሁኑኑ እንዲፈታ መጠበቅ ተገቢ አይደለም፡፡  ያልተመለሱ ጥያቄዎች ካሉ በኃይል ሳይሆን በመግባባት፣ በመወትወትና በማሳመን ላይ የተመረኮዘ የትግል ሥልት መከተሉ ነው አዋጭ የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ሌሎችን ከዚህ ውጪ የሚንቀሳቀሱትን የድል አጥቢያ አርበኞችን በወጣቶች መስዋዕትነትና በሕዝብ ትግል የመጣውን ለውጥ በመጥለፍ እንዳይቀለብሱት ከዚህ ዕኩይ ድርጊታቸው እንዲታረሙ በማድረግ፣ የትግሉ ሒደት ትክክለኛውን መንገድ እንዲይዝ ነው መሥራት ያለበት፡፡

በዚህ ረገድ ከሕዝቡ የሚጠበቀው በአዎንታዊ አስተሳሰብ መጠመድ፣ ጥርጣሬን፣ ተቃርኖን አይሆንምና አይቻልም የሚሉትን አስተሳሰቦችና ቃላትን በማጥፋት ወይም በመቀነስ፣ ‹‹ይቻላል፣ ይሆናል፣ ይሳካል. . .›› በሚሉት አዎንታዊ አስተሳሰቦች ለመቀየር እንዲቻል መሥራት ነው፡፡ ሊሆን ወይም ሊመጣ ይችላል በሚል ጥርጣሬ ውስጥ በመነከር ለአሉታዊ አስተሳሰብ መጋለጥ ሳይሆን፣ ጥርጣሬን በማስወገድ በእምነት መሄዱ የተሻለ ጠቀሜታ አለው፡፡ የሚያጠራጥረው ጉዳይ ምናልባት ካጋጠመ በዚያን ጊዜ መፍትሔ መስጠቱ ነው የሚመረጠው፡፡  የአገሬ ጉዳይ እኔንም ያገባኛል፡፡ ማን ይህንን ሥልጣን ለፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ አክቲቪስቶችና የመንግሥት ኃላፊዎች ብቻ ሰጠ በማለት እያንዳንዱ ሰው ተነሳስቶ የራሱን አስተዋጽኦ ካደረገ አገራዊ ለውጥ ማምጣት ከባድ አይሆንም፡፡ በመንግሥት ቢሮ አገልግሎት ለማግኘት ችግር ለሚፈጥሩ ጉቦ መስጠት አይገባም፡፡ መብቴን በገንዘብ መግዛት የለብኝም የሚል አቋም አብዛኞቻችን ከያዝን ሙስናን በጣም መቀነስ እንችላለን፡፡ እንዲያ ሲደረግ ሙሰኞችም ጉቦ መጠበቅ ያቆማሉ፣ ሥራቸውን በአግባቡ ብቻ ይሠራሉ፡፡

እንዲህ የሚያስቸግሩ ግለሰቦችንም አጋልጠን ከሰጠንና ከሕዝቡ ማኅበራዊ ግንኙነቶች ሁሉ እንዲገለሉ የምናስደርግ ከሆነ፣ እውነትም ለውጥ ማምጣት እንችላለን፡፡ የበለፀጉ አገሮች ሕዝቦች ይህንን ስለሚያደርጉ ነው መብታቸውን ለማስከበርም ሆነ የዴሞክራሲ ሥርዓትን መገንባት የቻሉት፡፡ እኛ ምሁራን በዚህ ረገድ መሥራት የሚገባንን ያህል አልሠራንም፡፡ ይሉኝታን በመፍራት ወይም መዘለፍንና መሰደብን በመሸሽ በአድርባይነት ሳይማር ያስተማረንን ሕዝብ በበቂ ሁኔታ ሳንታደግ ቆይተናል፡፡ ሞጋች ሐሳቦችን በድፍረት በማቅረብ ተፎካካሪ የሚባሉ ፓርቲዎችንና አክቲቪስቶችንም ሆነ፣ በሥልጣን ላይ የሚገኝን ፓርቲና መንግሥት ስህተቶቻቸውን በማጋለጥ የተስተካከለ አቋም እንዳይዙ ወይም አርፈው እንዲቀመጡ በሚፈለገው ደረጃ አልሠራንም፡፡ ወላዋይነት አጥቅቶናል፡፡ ቁርጥ ያለ አቋም ወስደን ለአቋማችን ሽንጥ ገትረን መከራከር አልሆነልንም፡፡

አንዳንዶች በስህተትና በደመነፍስ በስሜት የሚነዳውን ወጣት ኃይል ለመማገድ ሲጥሩ፣ ትክክል አለመሆናቸውን እያስረዳን ልንታገላቸው ይገባል፡፡ በ1960ዎቹ በወጣቶቻችን ላይ የደረሰው ጉዳት በአሁኑ ጊዜ ሊደገም አይገባም፡፡ በተለይ በኦሮሚያ እየሸተተ ያለው የዚህ ዓይነት አዝማሚያን የኦሮሞ ምሁራን ሊታገሉትና ሊያከሽፉት ይገባል፡፡ ቤተሰቦችና አዋቂዎች በስሜት ብቻ የሚነጉዱ ወጣቶችን መክረው ወደ ተረጋጋና ትክክለኛ አቋም እንዲመጡ መሥራት አለባቸው፡፡ ጉዳዩ ለነገ የሚባልም አይደለም፡፡ ያገባኛል የሚል ሁሉ በእንጭጩ ሊገታው ይገባል፡፡ የሐሳብ ልዩነትን ወይም ጥያቄን በሰላማዊ መንገድ በማቅረብ ፋንታ ንብረትን ማለትም ፋብሪካን፣ ሆቴሎችን፣ መንግሥታዊና የግል ድርጅቶችንና ሌሎችን መሰባበር፣ ማቃጠል፣ ሱቆችንና ባንኮችን፣ የምግብ ሰብሎችን መዝረፍ፣ በተለይ ደግሞ ምንም የማያውቁ የንፁኃንን መተኪያ የሌላቸውን መኖሪያ ቤቶችንና ንብረቶች በማውደም፣ ከእነ ቤተሰባቸው በክረምት ወቅት ያለመጠለያ ማስቀረት ከሁሉም በላይ ያማል፡፡ በአጠቃላይ አገር አውዳሚ ወንጀሎችን በመሥራት የመንግሥትን አቋም ማስለወጥ ወይም የመንግሥት ሥርዓትን ማፍረስ፣ የተሄደበት ሁኔታ ምን ያህል አሳሳቢና ባለፉት ዓመታት የተፈጠሩ ወጣቶቻችን በምን ዓይነት የዘቀጠ ባህሪ የተቀረፁ መሆናቸውን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡

በክልል አካባቢ እነዚህ ወጣቶች በአብዛኛው የሚያቃጥሉትና የሚያጠፉት ንብረት ከብሔራቸው ውጪ የሆኑ የባለሀብቶች ንብረት እንደሆነም ይደመጣል፡፡ ይህ ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን የቆየንበት ነው፡፡ በ2008 ዓ.ም. አመፅ ጊዜ ነው ይህ ንብረት የማቃጠል የትግል ሥልት የተጀመረው፡፡ በቅርቡም በአማራ ክልል መርሐቤቴ አካባቢ ለመንገድ ሥራ እያገለገለ የሚገኘው ንብረትነታቸው የአቶ ገምሹ በየነ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዋጋ ያላቸው የኮንስትራክሽን ማሽኖች፣ በአካባቢው ኃይሎች ተቃጥሎም እንደነበረ የሚታወስ ነው፡፡ ምንድነው እየሆነ ያለው? እንደ ማኅበረሰብ ይህ ጉዳይ ሁላችንም የሚመለከተንና የፖለቲካ ባህላችንን ብልሹ ገጽታ የሚያሳይ ቢሆንም በልጆቻችን፣ በትውልድ የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ ላይ ብዙ መሥራት የሚጠይቀን መሆኑን ይጠቁማል፡፡ በሌላ በኩል ተስፋ የቆረጡ የሚመስሉ ሥራ አጥ ለሆኑ ወጣቶቻችን መጨነቅና የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ለመንግሥት ብቻ መተው የማይገባና የኅብረተሰቡን ዕገዛ የሚፈልግ መሆኑን ጭምር ነው ይህ የሚያረጋግጥልን፡፡

ለእነዚህ ወጣቶች በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዋጋ ያለውን መኪና ማቃጠል፣ እንደ ተራ ተግባርና ጨዋታ ወይም መደሰቻ ነው የሚያዩት፡፡ ይህ በውስጡ ሀብታም ጠልነትን፣ የድህነት እኩልነትንም ለማምጣት የሚሞከር ምቀኝነትን በውስጡ ያዘለ ተግባር ነው፡፡ ሀብታሞችን እየጠላ ሀብታም መሆን አይቻልም፡፡ ሀብታም ለመሆን መጣጣር ከሌለ ደግሞ አገር አታድግም፡፡ ተያይዞ በችጋር ማለቅ ወይም ለማኝና ተመፅዋች መሆን ነው፡፡ ሀብታሞች የሚጠሉ ከሆነ የሥራ ዕድል ማን ሊፈጥር ነው? አንድ አገር ሀብታም ናት የሚባለው እኮ የብዙ ሀብታሞች መኖር ድምር ነው፡፡ ንብረቶቹ በግለሰቦች ወይም በመንግሥት ባለይዞታነት ይመዝገቡ እንጂ፣ ሁሉም የአገር ሀብቶች ናቸው፡፡ ይህም በመሆኑ ግብር ለመንግሥት ይከፈላል፣ በኢንቨስትመንት የሥራ ዕድል ይፈጠራል፣ ጉዳት ሲያጋጥም እንደ የአሁኑ ኮሮና ወረርሽኝ መዋጮ በማድረግ ወይም በዕርዳታ መልክ አቅም ለሚያንሳቸው ወገኖች ይውላል፡፡

ስለዚህ የሚቃጠለውና የሚጠፋው ንብረት በግለሰቦቹ ስም ይመዝገብ እንጂ የአገር ሀብት ነው፡፡ የጠፋውን ንብረት ለመተካት ለመድኃኒት ግዥ፣ ለሆስፒታል ግንባታ፣ ለንፁህ የመጠጥ ውኃ ጉድጓድ ቁፋሮና ለክሊኒክ መሥሪያ፣ ወዘተ. ይውል የነበረ ገንዘብ ነው ለሚቃጠለው ንብረት መተኪያ ወጭ የሚደረገው፡፡ ለሌላ አስቸኳይ ተግባር መዋል ያለበት ውድ የአገር የውጭ ምንዛሪ ነው ለዚህ የሚባክነው፡፡ ይህ የአገሪቱን ገቢና ዕድገት ወደ ኋላ የሚመልስ፣ የባሰ ድህነትን የሚያመጣና እነዚያኑ ንብረቱን የሚያጠፉትን ወገኖች ጭምር የሚጎዳ መሆኑን እነዚህ ወጣቶችና ለዚህ እኩይ ተግባር የሚያሰማሯቸው ኃይሎች ይገነዘቡት ይሆን? ከመስመር የወጣውን ትውልድ እንደገና መቅረፅ፣ ለእነዚህ ወጣቶች የተመቻቸ ሁኔታ እንዲፈጠር በቅርበት መሥራት፣ ከመንግሥት፣ ከማኅበረሰቡና ከሕዝቡ ብዙ የሚጠበቅ ተግባር መኖሩን የሚጠቁም በመሆኑ ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡

እንዲህ ዓይነት ችግሮችን ለመፍታት መንግሥትና ሕዝብ በቅርበት አብረው መሥራታቸው ከምንም ጊዜ በላይ አሁን ያስፈልጋል፡፡ በገዥው ፓርቲ ካድሬዎች የሚመራ ብቻ ሳይሆን በምሁራንና በንግድ ማኅበረሰብ ተወካዮች የሚመሩ የውይይት መድረኮች  በየአካባቢዎች  ሊካሄዱና በሐሳብ ልዩነቶች ላይ በመመካከር፣ በመከራከር አሸናፊ ሐሳቦች ነጥረው እንዲወጡ ብርቱ ሥራ ሊሠራ ይገባል፡፡ በሐሳብ የተሸነፈው ወገን ሽንፈቱን አምኖ እንዲቀበል ለማድረግ ሕዝባዊ ግፊቶች እንዲኖሩ ሁኔታዎችም ሊመቻቹ ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነት መድረኮች ሰላምን ለማስፈን ብቻ ሳይሆን፣ የአገር አንድነትንም በማጠናከር የጋራ መግባባት ላይ ተደርሶ ለልማት ለመነሳሳትም ይጠቅማሉ፡፡ የሥራ ዕድል ፈጠራንም በማፋጠን በድህነት ላይ የሚደረገውን ትግል ውጤታማ ያደርጋል፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውንም ያጎለብታል፡፡ በታሪካችንም ላይ በመነጋገርና በመከራከር መግባባት አለብን፡፡ ባለመግባባታችን አገራችንን የታሪክ አልባ አድርገን የማንነት ቀውስ ውስጥ ወጣቱን ትውልድ እንዳናስገባ ተግባብተን መሥራት አለብን፡፡ ቀስ በቀስ የክልል አጥሩን መስበር ያሻል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ብሔርተኝነትን ነው ማጠናከር ያለብን፡፡ ስህተቶችን ፈጽመናል፡፡ ሕዝቦች እንዳይተሳሰሩ ባለፉት ዓመታት የተሠሩት ሥራዎች በስህተትነት ሊወሰዱ ይገባል፡፡

እኛም እንደ ሕዝብ ቁጭ ብለን ሁሉንም ከመንግሥት መጠበቅ ወይም ባለተራ፣ ወዘተ. እያልን ከበስተጀርባ ማማትና ማማረር ማቆም አለብን፡፡ የአገራችን ጉዳይ ይመለከተናል፡፡ ሁላችንም ኃላፊነት አለብን፡፡ የባዕድነት ስሜት ሳይሰማን ኃላፊነት ወስደን መሥራት፣ መጠየቅና ግፊት መፍጠር ይጠበቅብናል፡፡ በዚህ ዓይነት ነው መንግሥትን በመግራት ለልጆቻችን የምትስማማ አገርን መመሥረት የምንችለው፡፡ ይህች አገር የሁላችንም ናት፡፡ ስለዚህ የአገር ጉዳይ የሚያገባቸው ዜጎች የሚያቀርቡት ሐሳብ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በመቀበል፣ ጠቃሚዎቹንና ከጊዜው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚሄዱበትን መተግበር ይኖርበታል፡፡ የሕዝብ ተሳትፎ የሚባለው አንዱ ይኸው በመሆኑ ስለአገር ጉዳይ ዜጎች ሐሳቦችን እንዲያመነጩ መደገፍና ዕውቅና መስጠት አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ኅብረተሰቡ እነዚህን ኃላፊነቶች ለመወጣት በየግሉ፣ በየአካባቢውና በማኅበረሰቡ የሚያደርጋቸው ተግባራት እንደተጠበቀ ሆኖ ጠንካራና ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመሆን ግን ጠንካራ ከፖለቲካ ወገንተኝነት፣ የፀዳ ለእውነትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ብቻ የሚሠራ የሲቪክ ማኅበራት ያስፈልጋሉ፡፡

የሲቪል ማኅበራት ሚና ለዴሞክራሲ መጎልበት

የሲቪል ማኅበራት ለዴሞክራሲ ግንባታ አስፈላጊ ከሆኑ ተቋማት አንዱና መሠረታዊ ናቸው፡፡ የሲቪል ድርጅቶች ሚና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የመንግሥትን ሥልጣን መገደብና መቆጣጠር ነው፡፡ በእርግጥ ማንኛውም ዴሞክራሲ በአግባቡ የሚሠራና ሥልጣኑን የሚተገብር የመንግሥት ሥርዓት ሊኖረው ይገባል፡፡ የሲቪል ድርጅቶች የመንግሥት ኃላፊዎች በሕጉ ላይ ተመሥርተው ስለመሥራታቸው፣ አምባገነን ሆነው ኅብረተሰቡን እንዳይበድሉ፣ የፖለቲካ ሥልጣናቸው የተገደበ እንዲሆን የመከታተልና የመቆጣጠር ሚና የሚጫወቱ ናቸው፡፡

ሌላው የሲቪል ድርጅቶች ተግባር ሙስናን ማጋለጥና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች እንዲሻሻሉ የማሳመንና የማግባባት ሥራዎችን ማከናወን ነው፡፡ የወከሉትን ኅብረተሰብ ፍላጐትና ጥያቄዎች በማንሳት የሲቪል ማኅበራት ከመንግሥታዊ ድርጅቶችና ከሚመለከታቸው ጋር መሟገታቸውና መከራከራቸው አስፈላጊ ነው፡፡ የወከሉት ኅብረተሰብ በፖለቲካው ተሳትፎ እንዲኖረው፣ ባይተዋርና ግዴለሽ ከመሆን የአገሩን ጉዳይ እንዲከታተልና በምርጫ ወቅትም ተሳትፎ በማድረግ ተወካዮቹን እንዲመርጥ መገፋፋት የመሳሰሉት ተግባራት በማከናወን፣ ምክንያታዊና በዕውቀት የሚመራ ተጠያቂነትንና ግልጽነት የተላበሰ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲጎለብት በማድረግ፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማደግ የላቀ አስተዋጽኦ ማድረግ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሚጠበቅ ነው፡፡ የሚነሱ አሉባልታዎችን በማጥራት፣ በቂ መረጃ ለኅብረተሰቡ እንዲሰጥ በመግፋትና ኅብረተሰቡ የጥቂት ነውጠኛ ኃይሎች የተሳሰተ ወይም ጠቀሜታ የሌላቸው ሐሳቦች ተሸካሚና አራማጅ እንዳይሆን በማድረግ በኩል፣ የሲቪክ ድርጅቶች ሚና ቀላል አይሆንም፡፡

ስለሆነም የፖለቲካ ኃይሎች ከገደቡ እንዳይወጡ ሚዛኑን የሚቆጣጠሩና ንቁ ጥረት የሚያደርጉ፣ በሕዝቡ በገለልተኝነት የበለጠ እምነት የሚጣልባቸው  የሲቪክ ማኅበራት ለአገራችን ሰላምና ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እጅግ አስፈላጊ ናቸው፡፡ መንግሥትም ሐሳቡን ሊደግፈውና እነዚህ ተቋማት እንዲጠናከሩ ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ይህ ሐሳብ የቀረበበት ገለልተኛ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ተቋም ይበልጡን ከኦሮሞ የገዳ ሥርዓት ጋር ትስስር ያለውን የአስታራቂና የመካሪ የሽማግሌ ባህልን መሠረት በማድረግ፣ ዘመናዊ የሆኑ አራቱን የዴሞክራሲ ምሰሶዎችን ማለት ‹‹የመንግሥት በነፃና ትክክለኛ ምርጫ መለወጥ፣ የዜጎች ወሳኝ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮቻቸው የሚኖራቸው ሁለገብ ተሳትፎ፣ የሁሉም ዜጐች ሰብዓዊ መብት መከበርና የሕግ የበላይነት መረጋገጥ›› ተግባራት ይኖሩታል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ የሚቋቋም የሲቪል ድርጅት፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝቦች መብት ተንከባካቢ ድርጅት›› የሚል ስያሜ ሊኖረው ይችላል፡፡ በተቋሙ መመሥረት ላይ ስምምነት ከተደረሰ ስያሜው በውይይት ሊሻሻልና ሊለወጥም የሚችል ነው፡፡ ድርጅቱ በየመስተዳድሮቹ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች ኖሮት በሥሩ የተለያዩ ንዑስ ተቋማትን ሊመሠረት ይችላል፡፡ ተቋማቱም የጥናትና ምርምር፣ የገላጋይና የዕርቅ፣ የምርጫ፣ የሰብዓዊ መብት፣ የሥነ ጽሑፍ፣ የፕሬስ፣ ወዘተ. ቡድኖችን ሊያደራጅ ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ ይህ ሐሳብ ተንሸራሽሮ ተቀባይነት ካገኘ ዝርዝር ጥናቶች ሊካሄድበት ይችላል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች መብት ተንከባካቢ ድርጅት በሥሩ ባሉ የተለያዩ በርካታ ተቋማት አማካይነት ጠቅለል ባለ ሁኔታ የአገሪቱን አንድነትና ሰላም በማስጠበቅና ለልማት ሥራ ኅብረተሰቡን በማነሳሳት ድህነትንና ሥራ አጥነት በመቀነስ ረገድ፣ መንግሥትን በማገዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላል፡፡ በሒደቱም የአገሪቱ ገጽታ እንዲሻሻልና ሕዝቦች በሥርዓቱ ላይ ያላቸውን እምነት በመጨመር ለአገሪቱ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና ፖለቲካዊ ዕድገት የሚያበረክተው ድርሻ የላቀ ይሆናል፡፡

እንዲሁም የጥናትና የምርምር ሥራዎችን በማካሄድ በባህል ለውጥ ላይ በመሥራት ጭምር፣ ሕዝብንና መንግሥትን በስምምነት የማቀራረብ ሥራዎችን የሚያከናውን ከሆነ የሕዝብ በመንግሥት ላይ ዕርካታ ማጣት ዋነኛ ምክንያት የሆኑት የብልሹ አሠራር፣  የሙስና፣  የመልካም አስተዳደርና የመሳሰሉት ችግሮች ይቀርፋሉ፡፡ የሲቪክ ማኅበሩ ተቃዋሚ ኃይሎችም የአገሪቱን ሕገ መግሥትና ሌሎች ሕጎችን በመጣስ ጭምር በአገር ላይ ጉዳት የሚያደርሱና በኅብረሰቡ ላይ ያልተፈለገ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ከሆነ፣ እነሱን ጭምር ሕዝብ ታግሎ እንዲስተካከሉ ግፊት የሚፈጥር ይሆናል፡፡ የገለልተኝነት ሚና የሚኖረው በመሆኑ ተቋሙ በሕዝብ ተቀባይነት የሚኖረው ስለሚሆን በሁሉም ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ ይሆናል፡፡

በቀረበው ተቋም በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊና በፖለቲካው መስኮች የሚደረጉ ጥናቶች ገዥውን ፓርቲና መንግሥትንም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን የሚረዱ ስለሆነ፣ በአጠቃላይ ለአገሪቱ ሰላምና ዕድገት የሚኖረው ጠቀሜታ ጉልህ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ይህ አካሄድ የሕዝቡን በአገሩ ጉዳይ የተሳትፎ መድረክ ሆኖም የሚያገለግል ነው፡፡ በሌላ በኩል በቅርቡ እንደተነሳው የሕዝብ ቅሬታዎችን አንስተው ከገዥው ፓርቲና ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር የሸምጋይነት ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ ቅሬታ አቅራቢውንም ቅሬታዎችን ሊፈቱ አይችሉም በሚል የተፈረጁ ኃይሎችን ከሚያነጋግሩ፣ ይህ ተቋም ተነጋግሮ የማሳመንና የማረጋጋት ሚና ሊጫወት ይችላል፡፡ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የበለጠ እንዲህ ዓይነት ተቋማት ለአገራችን አይሻሉምን? በዚህ ረገድ በገለልተኝነት ሁለቱንም ቅሬታ አቅራቢ የሕዝብ አካል ከገዥው ፓርቲና ከመንግሥት ጋር በማቀራረብ እንዲደማመጡና እንዲነጋገሩ ሁኔታዎችን በማመቻቸት፣ ለሰላም መፈጠርና ለቀጣዩም ዕድገት ትልቅ ሚና ሊጫወት ይችላል፡፡ በሚቀጥለው የመጨረሻ ክፍል በመንግሥት መከናወን ያለባቸውን ጉዳዮች በተመለከተ የማጠቃለያ ጽሑፍ ይቀርባል፡፡ ቸር ይግጠመን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...