በምንውየለት ሙሴ
በደርግ የግፍ አገዛዝ የተማረረው የኢትዮጵያ ሕዝብ መንገድ ከፍቶ ያስገባው የሕወሓት ቡድን፣ አራት ግቦችን ይዞ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. አዲስ አበባ ገባ፡፡ ግቦቹም፣ ዘረኝነትን እንደ መሀል ምሰሶ በመጠቀም አገርን በዘር ከፋፍሎ ሕዝብን ከሕዝብ በማባላት ኢትዮጵያን ማድከምና ከፋፍሎ መግዛት፣ ከልጅነታቸው ጀምሮ በከፍተኛ ጥላቻ የተተረከላቸው የውሸት ትርክት የአማራ ሕዝብን እንደ አንደኛ ጠላታቸው በመቁጠር አማራ ብለው የከለሉትን አካባቢና ሕዝብ በማንኛውም የደኅንነት መመዘኛ ማዳከምና በሌሎች ክልሎች የሚኖሩትን የአማራ ተወላጆች በማሳደድ፣ በማፈናቀልና በመግደል መበቀልና የተዋረደና የወረደ ዜጋ ማድረግ፣ ሕወሓት ሥልጣን እንደ ተቆናጠጠ መሀል አገር ይገኙ የነበሩትን ተንቀሳቃሽና ተንቀሳቃሽ ያልሆኑ ፋብሪካዎችንና ማሽነሪዎችን፣ ልዩ ልዩ የልማት መሣሪያዎችን በመንቀልና በመዝረፍ ትግራይ ወስዶ ኢትዮጵያን አድክሞ ትግራይን ለብቻ ማበልፀግ፣ ሥልጣን ላይ እስከ ቆዩበት ድረስ በሥውርና በግላጭ በተደራጀ መንገድ በቡድንም ሆነ በግለሰብ ኢትዮጵያን መዝረፍና ራቁቷን ማስቀረት ነበር፡፡
ከላይ የተጠቀሱትን ግቦች ለማስፈጸም ያለ ምንም ህሊናና ጥያቄ ሊያገለግሏቸው፣ ሊላላኩላቸውና ሊያስፈጽሙባቸው የሚችሏቸውን ነፃ ካደረጋቸው መንደሮች የለቀሟቸውን ሰዎች እየመለመሉና እያሠለጠኑ፣ ለዘረፋ በሚመቻቸው መንገድ እንደ አዲስ በአዋቀሩዋቸው የመንግሥት አመራሮች ውስጥ በማስቀመጥ ነበር፣ ከፌዴራል እስከ ወረዳ ባሉት የመንግሥት አስተዳደር መዋቅር በየአመራሩ የሕወሓት ሰው በማስቀመጥ አራቱንም ግቦች ለማስፈጸም የተቀናጀ ኔትወርክ ዘርግተዋል፡፡ ኃይልም ቢያስፈልግ በየከተማው የደኅንነት ኃላፊ ሆኖ ይመደብ የነበረው የሕወሓት ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው በክልልና በዞን አመራሮች በጣም የሚፈራ ስለነበር ማንኛውም የጥፋት ዕርምጃ ይወስዳል፣ ያስወስድም ነበር፡፡
ከክልሉ ፕሬዚዳንት የበለጠ ሥልጣንና ኃይል የነበራቸው እነዚህ በአማካሪና በደኅንነት ኃላፊነት ስም የተላኩት የሕወሓት ሰዎች ነበሩ፡፡ በሕግ ጉዳይም ቢሆን ይህ ቡድን ሕግን ራሱ በፈለገውና በሚመቸው መንገድ የሚያወጣ፣ የሚያስፈጽምና ራሱ ዳኛ ሆኖ የፈለገውን ያደረገና የማይገባ ጥቅም ያገኘበት አገዛዝ ነበር፡፡ የኢትዮጵያን ስም መጥራት የሚጠየፍ፣ አገሪቱንና ሕዝቧን የማይወድ በምንም ሁኔታ ኢትዮጵያዊነት የሌለበት የጥፋት ቡድን ነበር፡፡ ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያን በበቀል የገዛ ነበር፡፡ ስለሆነም አሁንም ሆነ ለወደፊት ሕወሓት ለኢትዮጵያ መልካም ያስባል ተብሎ አይገመትም፡፡
መሬቱንም፣ ሥልጣኑንም፣ ሕጉንና አጋሮችን (ተላላኪዎቹን) በእጁ ካስገባ በኋላ የጥፋት ቡድኑ ከሞላ ጎደል ግቦቹን አከናውኗል፡፡ ዘረኝነትና ሃይማኖትን በመጠቀም በጭካኔና በአረመኔ መንገድ ሕዝብ ገድሏል፣ ሕዝብን ከሕዝብ አባልቷል፣ ሕዝብ አፈናቅሏል፣ መሬት ነጥቋል፣ ንብረትና ሀብት ዘርፏል፣ አዘርፏል፡፡ አማራው፣ ኦሮሞው፣ ሶማሌው፣ ጋሞውና ወላይታው ወዘተ. መድረሻ እስኪያጣ ድረስ ተንገላቷል፣ ተሰቃይቷል፣ ሞቷል፡፡
የተጎዳኸው፣ የደኸየው፣ ሥራ ያጣኸው፣ በዘርህና በሃይማኖትህ ወዘተ. ምክንያት ነው እየተባለ ሕወሓት የዘረኝነትን መርዝና የእምነት ጥላቻን በአገሪቱ በሙሉ አሠራጨ፡፡ ሆን ተብሎ አስተዳደጉም ሆነ ትምህርቱ በአገርና በወገን ፍቅር ሳይሆን በጥላቻ የተተበተበ ወጣት፣ ችግሩን ሁሉ በወገኑ ላይ ማወራረድ ጀመረ፡፡ ከወልቃይት እስከ ጌዴኦ፣ ከራያ እስከ ሐርጌሳ ወገን በወገኑ ላይ ተነሳ፡፡ ጠንሳሹም አቀጣጣዩም ከላይ ምሪት በተሰጠው መሠረት የሕወሓት ካድሬ ሆኖ ተገኘ፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ አሳፋሪ ነገር ተደረገ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንገቱን ደፋ፡፡ የኢትዮጲያ ሕዝብ ለዘመናት ያካበተውን የአኗኗር ዘይቤና ሥርዓት ሕወሓት በትንሽ ዓመታት ውስጥ ወደኋላ ጎተተው፡፡
ሁለተኛ ግቡን ለማስፈጸም ሕወሓት ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ የአማራን ሕዝብ የጀርባ አጥንቱን ሰብሮ በማያዳግም ሁኔታ፣ አካባቢውንም ሆነ ሕዝቡን ለማድከምና ለማደህየት ቆርጦ ተነሳ፡፡ የመጀመርያ ሥልቱ የትግራይ ክፍለ አገርን ከፍ አድርጎ ሌሎችን በመጨፍለቅ ኢትዮጵያን በዘር መከለል ነበር፡፡ ጎጃም፣ በጌምድርን፣ ወሎንና ሸዋን (ሰሜን ሽዋ) ጨፍልቆ አንድ ክልል ሲያደርግ፣ ትግራይን ከፍ አድርጎ ለብቻው ክልል አደረገው፡፡ አራቱም ግዛቶች መጨፍለቃቸው አልበቃ ብሎ እያንዳንዳቸው ለሦስትና ለአራት ከፋፍሎ በዞን አዋቀራቸው፡፡ በጣም የሚያስገርመው ግን ከአንዳንዳቸው ለም መሬት እየተመረጠ ብዙዎቹ ወደ ትግራይ ቀሪዎቹ፣ ወደ ሌሎች ክልሎች ካለ ኃፍረትና ይሉኝታ ታደሉ፡፡ ከበጌምድር ወልቃይትና ሁመራን፣ ከወሎ ራያንና ግማሽ ሰቆጣን ለትግራይ፡፡ ከጎጃም መተከልን ለቤንሻንጉል፡፡ ከሰሜን ሸዋ የተወሰነውን ለኦሮሚያ እንደ ዳቦ እየቆረሰ ለግሷል፡፡
እንግዲህ የአማራና የትግራይ፣ የአማራና የቤንሻንጉል፣ የአማራና የኦሮሞ ብጥብጥ ሥረ መሠረቱ ይህ የመሬት ነጠቃ ነው፡፡ ዋናው ዓላማ አማራ ከጎረቤቶቹ ሁሉ እየተናቆረ ኋላ ቀር ሆኖ እንዲኖር ነው፡፡ እንደ አንድ ክልል ስለተጨፈለቁና በዞን ደረጃ ስለተዋቀሩ ከፌዴራል መንግሥት የሚያገኙት የድጎማ በጀትና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች፣ ለእያንዳንዳቸው የሚደርሳቸው በጣም ያነሰና ፍትሐዊነትና እኩልነት የጎደለው አመዳደብ ነው፡፡ ለዘለቄታም በእኩልነት እንዳይጠቀም በሕዝብ ቆጠራው ሆነ ተብሎ የአማራ ሕዝብ ቁጥር በሦስት ሚሊዮን እንዲያንስ ሆኖ ተሠራ፡፡ ይህ ሁሉ ኢፍትሐዊ የጥቅም ክፍፍልና አድልኦ ተደምሮ አማራ ክልል ላይ የተሠራው ጠቅላላ የልማት፣ የመሠረተ ልማትና የማኅበራዊ ዕድገት ከሌሎች ጋር ሲወዳደር በጣም ያነሰ መሆኑ በጥናት ተመዝግቧል፡፡
አሁንም የሕወሓት ርዝራዥ ስላልጠፋ በአማራ ክልል ብዙ ከተሞች በውኃና በመብራት ዕጦትና እጥረት በሚሰቃዩበት ጊዜ፣ ለአንድ ትግራይ ክልል ከተማ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ለመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት እንደተመደበ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰማን፡፡ በተጨማሪም ክልሉ አራት አዳዲስ ኤርፖርቶች ሲሠሩለት በአማራ ክልል አንድ ከተማ የነበረ ኤርፖርት እንዲዘጋ ተደርጓል፡፡ ሌላ አዲስ ኤርፖርት እንዲሠራ ቢወሰንም ለአርሶ አደሮች የምንከፍለው ካሳ የለንም በሚል ቁንፅል ምክንያት እንዲቀር ሆኗል፡፡ የምፈራው እንደ ጨሞጋ የዳ ግድብ ፕሮጀክት ይህም የኤርፖርት ፕሮጀክት ደባ ተሠርቶበት እንዳይሰረዝ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው በክልል አወቃቀሩ ምክንያት ነው፡፡ ይህ የአማራ ክልል የተባለው ሕዝብን ባማከለ አዲስ መንገድ ካልተዋቀረ የወደፊቱ የአማራ ሕዝብ ሥቃይና እሮሮ ካለፉት 30 ዓመታት የባሰ እንዳይሆን እሠጋለሁ፡፡
የሚሻለውና የሚመረጠው የአሁኑ አማራ ክልል ከሦስት በማያንሱ፣ ከአምስት በማይበልጡ ክልሎች ቢዋቀር ነው፡፡ መጀመርያ አስተዳደሩ ለሕዝብ ቅርብ ይሆናል፡፡ ከደብረ ብርሃን ሆነ ወይም ከወልቃይት ባህር ዳር ምን ያህል ሩቅ እንደሆነች የሚያውቅ አቤቱታ ያለው ብቻ ነው፡፡ ሁለተኛ በጀቱም፣ መሠረተ ልማቱም፣ ፕሮጀክቶቹ ለሕዝቡ ቅርብ ይሆኑለታል፡፡ ሦስተኛ ለፖለቲካ ሥርዓትም ሆነ ለልማት ሕዝቡ በቅርበት ተሳታፊና ተዋናይ ይሆናል፡፡ አራተኛ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ቀጥታ ግንኙነት ይኖራቸዋል፡፡ በቅርቡ የተቋቋሙ የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባዔ ይህን ጽንሰ ሐሳብ የበለጠ ቢያየውና አማራጮችን ቢያቀርብ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ እንደ እኔ ዕይታ ዝም ብሎ የታለፈበት ጉዳይ አይደለም፡፡
ሕወሓት እንደ ሦስተኛ ግብ ያደረገው የሚቻለውን ያህል ከመሀል አገር በመዝረፍ የትግራይን ክልል ለማበልፀግ ነው በሚል የውሸት ትረካ፣ ራሳቸውንና ተላላኪ ካድሬዎችን ማበልፀግ ነው፡፡ ከባንኮች ዘረፋ ጀምሮ እስከ ሙሉ ፋብሪካ በመንቀልና ወደ መቀሌ በመውሰድ ኤፈርት (EFFORT) የሚባል ድርጅት አቋቁመው ትልቅ ዘረፋ በዚህ ድርጅት ስም አካሂደዋል፡፡ አርባ አምስት ከሚሆኑት የኤፈርት ድርጅቶች ብዙዎቹ አድልኦ በሞላበት ዘዴ ብድር ወስደው እንዳልከፈሉ ነጋዴዎች በግዳጅ እንዲገዙ፣ በኃይልና በሴራ ከኤፈርት ጋር ተወዳዳሪ የሆኑ ድርጅቶች በየምክንያቱ እንዲዘጉ ሆን ተብሎ እንዲከስር፣ የአንዳንዶችም ባለቤቶች እንዲታሰሩ ተደርጓል፡፡ በኢትዮጵያ ስምም ኤፈርት ከውጭ ድርጅቶች ተበድሯል፡፡ በፌዴራልና በክልል መንግሥት የሚሠሩ ግንባታዎች ፕሮጀክቶችና መሠረተ ልማቶች ለኤፈርት ድርጅቶች በቅድሚያ እንዲሰጡ ተደርገው፣ ሌሎች የግል ድርጀቶች እንዲንጫጩና በመጨረሻም ከጨዋታው ውጪ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡
ኤፈርት የተመደበ ሥራ አስኪያጅ ያልከበረና ገንዘብ ያላሸሸ ማንም የለም፡፡ ብዙዎችም ኑሯቸውን በአውሮፓና በአሜሪካ አድርገዋል፡፡ ኤፈርት አንዱ ትልቁ የገንዘብ ማሸሻ ዘዴ ነበር፡፡ ሜቴክና ኤፈርት የተቋቋሙት በመንግሥት ትዕዛዝ ያለ ምንም ቁጥጥር ገደብ ኢትዮጵያን ለመዝረፍና ለማደህየት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ አራተኛው ግብ ዘረፋው በኤፈርት ስም ብቻ ሳይሆን በጠቅላላ በኢትዮጵያ ምድር እንዲሆን ነው፡፡ ዘረፋው የተጀመረው አዲስ አበባ ነው፡፡ ትልቁ የዘረፋ ምንጭ መሬት ነበር፡፡ ከተማዋን በክፍለ ከተማ፣ በወረዳና በቀበሌ ከፋፍለው ቁልፍ የሆኑ የሥራ ምደባዎች በሕወሓት ሰዎች ሞልተው ቦታዎቹን እየመረጡ ይቀራመቷቸው ጀመር፡፡ በመጀመርያዎቹ የኢሕአዴግ 15 ዓመት ከ27 ወረዳዎች የ26 ሥራ አስፈጻሚዎችና ሥራ አስኪያጆች የሕወሓት ካድሬዎች ነበሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ግራና ቀኝ ቦታ እየታሰሰና እየተሸነሸነ ለራሳቸውና ለዘመዶቻቸው በገፍ የተሰጠው፡፡ ብድርም ያለ ገደብ ተፈቅዶላቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሕወሓቶች በአንድ ምሽት የሚከብሩበት ጊዜ ነበር፡፡
የአዲስ አበባ ፕሮጀክት እያለቀ በሄደበት ገዜ የጥፋት ቡድኑ ትኩረቱን ግዙፍና ዕምቅ ሀብት ባላቸው ጋምቤላና ቤንሻንጉል ክልሎች ላይ አደረገ፡፡ ሆን ብለው ባስቀመጧቸው አማካሪዎችና የደኅንነት ካድሬዎች የክልሎች መሪዎች በማስፈራራትም ሆነ በመደለል ሰፊ ለም መሬት በመውሰድና ካርታ በማስወጣት ለዘረፋ አመቻቹ፡፡ የራሳቸውን ሰው በፕሬዚዳንትነት በማስቀመጥ ልማት ባንክን እንደ ጥረት (ፈስሶ የማያልቅ የላም ወተት) ተጠቅመው የባዶ መሬት ካርታ በማስያዝ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ዘርፈዋል፡፡ ከንግድና ከሌሎች ባንኮች የተበደሩትና እስካሁን ያልመለሱት ገንዘብ ቢደመር ከአገሪቱ የዘረፏት ከ80 ቢሊዮን በር በላይ ይሆናል፡፡ እንግዲህ ይህ ገንዘብ ነው መልሶ ኢትዮጵያን የሚያጠቃው፣ ሕዝብ የሚያጋድለው፣ ኢኮኖሚውን የሚያዳክመውና ሕዝብን የሚከፋፍለው፡፡ እነዚህ ሰዎች አዲስ አበባ ላይ ብዙ ንብረት እንዳላቸው ስለሚታወቅ፣ በትንሹም ቢሆን የተዘረፈው ሀብት በእነዚህ ሰዎች ንብረቶች ቢወራረድ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ማለፍ አይቀርምና ያ ቀን ተቀየረ፡፡ ያ የጥፋት ቡድን ማሳደዱን ትቶ እሱ ተሳዳጅ ሆኖ የመጨረሻ የሆነችውን የጥፋት ጥይት ለመተኮስ እየተጣጣረ ነው፡፡ ብልህና ብልጡ መሪያችን ይህች ጥይት ሳትተኮስ ወይ ይቀልባታል ወይም ያኮላሻታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህም ሊሆን የሚችለው ማባበሉ ሲቆም፣ ትዕግሥቱ ገደብ ሲያልፍና ፍርኃቱ ሲያበቃ ነው፡፡ የማባበል የፍርኃትና የትዕግሥት ጠንቅ ብዙ ጎድቶናል፣ ብዙ ሕዝብ ሞቶብናል፣ ንብረትና ሀብት ወድሞብናል፣ አንዳንድ ጠላቶች ጊዜ አግኘተው ተጠናክረውብናል፣ ኢኮኖሚውን አቀዛቅዘውብናል፣ በመንግሥት ላይ ያለንን እምነት ሸርሽረውብናል፡፡ አሁን በቃ ማለት አለብን፡፡ ከሁሉም በላይ ወጣቱን ማባበል ስህተት ነው፡፡ ለወጣቱ እውነትና ድርጊት እንጂ በማይሟላ ተስፋ መደለል ወይም ጊዜያዊ ሽንገላ ማድረግ አያስፈልግም፡፡ በተለይ መንግሥት ይህን ዘዴ በመተውና ለፍትሕ በመቆም ተገቢውን ሕግና ሥርዓት ማስከበር አለበት፡፡ ጊዜ መስጠት ፍርኃትና ሥጋትን ያባዛል እንጂ አያስወግድም፡፡ አሁንም ሆነ ለወደፊት ጉዳቱ እንዳይቀጥል አድልኦ የሌለበት፣ ፍትሕ የሰፈነበትና እኩልነትን ያረጋገጠ ፈጣን ሕግና ሥርዓትን ማስከበር ይጠይቃል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትራችን ባላቸው ብልህነት ሰብዕና ላይ ጥበብንም በመጨመር የትልቅ አገር መሪ የመባልን ስም ማስመስከር ይገባቸዋል፡፡ ሁሉን ሕዝብ እኩል ማየትና ሁሉንም በፍትሐዊና በእኩልነት ከአገሪቱ ሀብት ተጠቃሚ እንዲሆን መሥራት፣ ማስፈጸምና ማረጋገጥ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የመጀመርያው የኢሕአዴግ ጠቅላይ ሚኒስትር ብልጥና ብልኃተኛ ቢሆኑም፣ ጥበብ ስላልነበራቸው አሁን ያለንበት አረንቋ ውስጥ ከተውናል፡፡ ዋናው ስህተታቸውም የሚመሩትን ሕዝብ በእኩልነት ስላልመሩት ነው፡፡ እናም ኢፍትሐዊና አድልኦ የበዛበት አመራር በመስጠታቸው ብቻ እንደ አገር መሪ ቆጥሬያቸው አላውቅም፡፡
የአሁኑ መሪያችን ክቡር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ካለፈው መሪ ስህተት እንደተማሩና ሕዝባቸውን በእኩልነት፣ አንዱ ወገን ሲጎዳ በዝምታ ባለማለፍ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ጥበብና ሥልጣን በአግባቡ እንደሚጠቀሙበት ሙሉ ተስፋና እምነት አለኝ፡፡ ስለሆነም እሳቸውን ደግፎ ይህንን ጥበብና ሥልጣን ያለ ምንም ሥጋትና ፍርኃት እንዲጠቀሙበት ከመምከርና ከመርዳት ውጪ ሌላ ምርጫ አይኖረንም፡፡ ምንም እንኳን መንፈሰ ጠንካራ ቢሆኑም ሥጋ አሸንፎ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ስህተት ቢሠሩ በትንሽ ጊዜ ውስጥ ያላሰብናቸውን መልካም ነገሮች ሁሉ ያደረጉልንን መሪ፣ በሆነ ባልሆነው ስህተታቸውን ማግዘፍና ጥሩ የሠሩትን ማጥላላት ተገቢ አይደለም፡፡ ይልቁንም አይዞን እያልን ስህተት ቢሠሩም እንዲያርሙ፣ ጥሩ ሲሠሩም ይበርቱበት እያልን የዜግነት ኃላፊነታችንን ብንወጣ ይሻላል ብዬ አምናለሁ፣ ጥረትም አደርጋለሁ፡፡ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ፈጣሪ ይጠብቅ! ጠላቶቿን ይደምስስ!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡