ጥላሁን ግዛው፣ ሐውዜንና ሃጫሉ ሁንዴሳ
በደረጀ ተክሌ ወልደ ማርያም
ሀ. የ29 ዓመቱ ወጣት ጥላሁን ግዛው
የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በ1961 ዓ.ም. ያካሄደው የተማሪዎች መማክርት ፕሬዚዳንትነት ምርጫ በብሔራዊ ኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበር ጥረት በመኮንን ቢሻው አሸናፊነት ሲደመደም፣ በግቢው የጀበሃን ዓላማ የሚያራምደው ቡድን መሸነፉ ተረጋገጠ፡፡ ይሁን እንጂ ጀበሃና አድናቂዎቹ የሚቀጥለውን ምርጫ በምንም መንገድ መሸነፍ አልፈለጉም፡፡ በዚህ ምርጫ እንዲመረጥ የሚፈልጉት ሰው በግቢው ውስጥ ለሚያከናውኑት የፕሮፓጋንዳ ሥራቸው አስፈጻሚ እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡ ዝግጅቱ በከፍተኛ ሁኔታ በጀበሃ አካላትና በረዳቶቻቸው በእነ ዋለልኝ ፊታውራሪነት እየተመራ የ1962 ዓ.ም. የፕሬዚዳንትነት ምርጫ ውጤት በምንም ዓይነት ከእጃቸው እንዳይወጣ፣ በሥውርም በግልጽም የዋሁን ተማሪ በማሳመንም ሆነ በማስፈራራት ሌት ከቀን ገፉበት፡፡
በኅዳር 1962 ዓ.ም. ምርጫው ተካሄደ፡፡ እንደተጠበቀው የጀበሃ አምላኪው ቡድን አሸነፈ፡፡ የ29 ዓመቱ ወጣት ጥላሁን ግዛው በፕሬዚዳንትነት ተመረጠ፡፡ የፕሬዚዳንትነት ዘመኑ ግን ከሁለት ወራት አልዘለለም፡፡ አሁን ሁኔታዎች ከጥላሁን ዕውቅና ውጪ እየተቀጣጠሉ መጡ፡፡ ኅዳር 1962 ዓ.ም. ሌላም ታሪክ ነበረው፡፡ ለሁኔታው ይበልጥ ማቀጣጠያ እንዲሆን የዋለልኝ የብሔር ብሔረሰብ ንባብ በልደት አዳራሽ እንዲነበብ የተደረገውም በዚሁ ወር ነበር፡፡ ልብ በሉ፡፡ ይህ የዋለልኝ ድርሰት የተደረሰው በኤርትራውያኑ በእነ ኃይሌ መንቆርዮስና በእነ ዮርዳኖስ ገብረ መድኅን ቡድን ሲሆን፣ ድርሰቱ ከሦስት ወራት በፊት አሜሪካ ፊላደልፊያ የተማሪዎች ስብሰባ ላይ ቀርቦ ውድቅ የተደረገ ነበር፡፡ በምን የንፋስ ፍጥነት አዲስ አበባ ገብቶ በዋለልኝ እንደተጻፈ ተደርጎ መቅረቡ፣ የጀበሃው ቡድን ለዓላማው እጅግ የተጋ መሆኑን ያሳያል፡፡ ስለሆነም በኅዳር 1962 ዓ.ም. በጥላሁን ግዛው የአሸናፊነት ምርጫና በዋለልኝ መኮንን ንባብ መንስዔነት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ሌሎች ለዚሁ ዓላማ የታደሙ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ ነገ ይህ ተንኮል በአገራቸውና በትውልዱ ላይ ሊያመጣ የሚችለውን መቅሰፍት ካለመገመት የተነሳ ጩኸቱንና ረብሻውን አፋፋሙት፡፡
ጥላሁን ነገሩ አላማረውም፡፡ ሁኔታው በዚህ ደረጃ እንደሚቀጣጠል ያልገመተው ጥላሁን አክራሪዎቹን የእነ ዋለልኝ ቡድንና ሌሎቹን የድራማ አቀናባሪዎች ሁኔታውን እንዲያለዝቡ መከራቸው፡፡ የዋሁ ጥላሁን በሠለጠነ መንገድ ንቅናቄውን ለመምራት ከረብሻ ይልቅ መወያየት እንደሚገባ አበክሮ ገለጸ፡፡ ይህ የጥላሁን ጥሪ ለጀበሃ ዓላማ የሚመች አልነበረም፡፡ ስለዚህም የጥላሁን ምክር መጠኑን ከማለፉ በፊትና የተመረጠበትን ይህን ስንኩል ዓላማ ባለመስማማት ከኃላፊነቱ ከመሰናበቱ በፊት፣ ራሱ ጥላሁን እንዲሰናበት ተወሰነ፡፡
ለጀበሃ ጥላሁንን ማስወገድ ሁለት ታላላቅ ዓላማዎችን ያሳካል፡፡ አንደኛው በድንገት ጥላሁን ጩኸታችሁ አላማረኝም ብሎ የፕሬዚዳንትነቱን ሥልጣን ቢለቅ ለኡስማን ሳላህ ሳቤ ቡድን ትልቅ ውርደት ይሆናል፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ የጥላሁን መወገድ ለኤርትራውያኑና ጉዳዩን በጥልቀት ሳያውቀው ለሚተራመሰው ወጣት የጩኸቱን ጥግ ለአገር ውስጥና ለውጭ ተመልካቾች ማሳየት እንዲችል ያደርገዋል፡፡ ለዚህም ቀን ተቆረጠለት፡፡ ታኅሳስ 19 ቀን 1962 ዓ.ም. አፍንጮ በር አስፋልት ዳር በተደረገው የምሽት ግድያ ላይ የተገኙት የቅርብ ዘመዱ መኮንን ሲሳይና የሴት ጓደኛው ዮዲት ታዬ የገዳዮቹን ማንነት ዓይተዋል፡፡ የጀበሃው ቡድን ጥላሁንን መግደሉ ብቻ አልበቃውም፡፡ ሕይወቱ ከማለፉ በፊት የቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የዛሬው የካቲት 12 ሆስፒታል ድረስ በመሄድ ፖሊስ ስለሚስጥሩ እንዳያውቅ በር ላይ ያልተለመደ ትንቅንቅ በመፍጠር፣ ከመርማሪ ፖሊሶች እንዳይገናኝ የሚያደርጉ ተማሪዎችን አደራጅቶ ሆስፒታሉ ውስጥ ከፍተኛ ረብሻ ፈጠረ፡፡ እኩለ ሌሊት አካባቢ ጥላሁን አረፈ፡፡
ከሕልፈቱም በኋላ ጀበሃ ለዓላማው እንዲያመቸው በር አሰብሮ አስከሬን አስነጥቆ ወደ ግቢው በረረ፡፡ ለዚሁ ተግባር ቀደም ሲል የተዘጋጁ ጽሑፎች ለሊቱን ሲበተኑ አደሩ፡፡ ንጋት ላይ ግቢው ተቀጣጠለ፡፡ ዋለልኝና ጓደኞቹ ቡድኑን መሩት፡፡ የአስከሬኑ ግብዓተ መሬት የሚፈጸመው ትውልድ ቦታው ማይጨው ሳይሆን አዲስ አበባ ነው ብሎ ቡድኑ ወሰነ፡፡ ይህ ደግሞ ሌላ አቧራ አስነሳ፣ ሌላ ሕይወት ቀጠፈ፣ ሌላ ደም ፈሰሰ፣ ተጨማሪ ንብረት ወደመ፡፡ የጀበሃ ዓላማ ጥላሁን ለምን ለምን ሞተ በሚል ዜማ ለረጅም ዘመን የተከለው ትርክት የማያባራ የእርስ በርስ ብጥብጥ በመፍጠር ኤርትራን አስገንጥሎ፣ ለኢትዮጵያ ደግሞ እስከ ዛሬ ድረስ የዘለቀ የረጅም ዘመናት ሰቆቃ አስጀመረ፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት በሪፎርም እንዲወገድ በማድረግ ኢትዮጵያን ወደ ዘመናዊ የሪፐብሊክ አስተዳደር ለማምጣት ይፈልጉ የነበሩ አካላት፣ በውጭ ኃይሎች በተነጠቁ አባላት በአመፃ ተበሉ፡፡ ይህ ለዛሬው ተረፈ፡፡
ለ. የ36 ዓመቱ ወጣት ሃጫሉ ሁንዴሳ
ሃጫሉ ከጥላሁን የሚጋራው ብዙ ነገር አለ፡፡ ሃጫሉ ወያኔን በመቃወም መንግሥትን እያስደነበረ መታሰር የጀመረው ገና በአፍላ ዕድሜው ነበር፡፡ የሕወሓት መንግሥት ፈጽሞ ለመንግሥትነት የማይመጥን የሕገወጦች ስብስብ መሆኑን በመድረክ ብቻ ሳይሆን፣ በተገኘው መንገድ ሁሉ ለሕዝብ ሲገልጽ የነበረው ሃጫሉ በተለይም ከፍተኛ የወያኔ ባለሥልጣናትና ወዳጆቻቸው በታደሙበት የሚሊኒየም አዳራሽ እጅና እግራቸውን የሚያንቀጠቅጥ ጥዑመ ዜማ ካሰማ በኋላ፣ ሃጫሉ የጠላትም የወዳጅም ከፍተኛ ትኩረት ስቦ ነበር፡፡ አማርኛንም ሆነ አፋን ኦሮሞን በጥራት የሚናገረው ሃጫሉ ሁንዴሳ ለቃለ መጠይቅ በሚቀርብበት ወቅት ከተጠቀመባቸው ጠንካራ ቃላት መካከል ኢትዮጵያን ከአንድ ትልቅ ሥዕል ጋር በማነፃፀር የተሳለችባቸው ቀለማት ደግሞ በብሔረሰቦች እንደሚመሰሉና ቀለማቱ ለየብቻቸው ዕውቅና እንዳላቸው ሁሉ፣ በጋራ ደግሞ አንድ ትልቅ ሥዕል እንደሚሠሩ በንፅፅር መግለጹ፣ በተጨማሪም በዘርና በዘረኝነት መካከል ያለውን ልዩነት በአንክሮ ማስረዳቱ በሳል ወጣት እንደነበር ያስገነዘበ አጋጣሚ ነበር፡፡ ከዚህም በላይ ግን መድረክ ላይ ሲወጣ ከሚያሰማቸው ስሜት አመንጪ ዘፈኖቹ ጋር ሕዝብ ዓይን ውስጥ መግባቱ የሚያስደስታቸውም እንደነበሩ ሁሉ፣ የሚያበሳጫቸውም ሊኖሩ እንደሚችሉ የታወቀ ነበር፡፡
ስለዚህም ይህንን ዝነኛ ከያኒ ከፍ ባለበት ወቅትና በተለይም በኦሮሞ ወጣቶች አዕምሮ ውስጥ በሰረፀበት ወቅት በድንገት ማስወገዱ፣ ድንገተኛ ሕዝባዊ አመፅ ሊፈጥር እንደሚችል ለአንድ ቡድን ግልጽ ከሆነ ቆይቷል፡፡ አመፁም በሕዝብና በመንግሥት መካከል ብቻ ሳይሆን፣ በሕዝብና በሕዝብ መካከል ሆኖ ማብቂያው ግን ቤተ መንግሥት እንዲሆን ቡድኑ አልሟል፡፡ ይህንን እሳት ለማቀጣጠል ግን አንድ መነሻ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ለማቀናበር ደግሞ ቀላል ጨዋታ ያስፈልጋል፡፡ ቀደም ሲል ከያኒው ስለአፄ ምኒልክ ሐውልት የሰጠውን ቃል በተለያዩ ሚዲያዎች እንዲሠራጭ በማድረግ፣ በያዘው አቋም ላይ ጠንካራ ተቃዋሚን ማደራጀትና ቅዋሜውን ማፋፋም ዋነኛው የቡድኑ ሥራ ሆነ፡፡ በዚህ ሁኔታ በሥርዓት በተጠና መሰሪ ተግባር ሃጫሉ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት ተገደለ፡፡ የታቀደው አመፅ ጎልቶ እንዲወጣ ምሽቱን በማኅበራዊ ሚዲያ ሲለቀቅ አደረ፡፡ ለዚሁ ጉዳይ ዝግጅታቸውን ያጠናቀቁ የተወሰኑ ቴሌቪዥኖችም እወጃቸውን ሳይነጋ ጀመሩት፡፡
ምንም እንኳን ግድያውና ውድመቱ በፈለጉት ደረጃ ባይዘልቅም ከ150 ሰዎች በላይ ሕይወት ቀጠፈ፡፡ ከፍተኛ ንብረትም አወደመ፡፡ የሥርዓተ ቀብሩ አፈጻጸም አዲስ ክስተት ፈጥሮ ባልተለመደ ሁኔታ አስከሬኑም የሚያርፈው ቤተሰቡ ባልፈቀደው ሁኔታ ትውልድ አካባቢው አምቦ ሳይሆን፣ አዲስ አበባ እንዲሆን ቡድኑ ንጥቂያ አከናወነ፡፡ ይህ ደግሞ ለተጨማሪ ሕይወት ማለፍ ለተጨማሪ ደም መፍሰስና ለተጨማሪ ንብረት መውደም ምክንያት ሆነ፡፡ ይህ አደጋ አገሪቱን ወዴት ሊወስዳት ይችል እንደነበር ለማየት ግን ፍትሕ አስፈጻሚው የሚለውን ለመስማት ትዕግሥት ይኑረን፡፡ ፍትሕ አስፈጻሚው ለፖለቲካ ቀመር ሲል እውነቱን ለመሰወር ቢሞክር እንኳን ታሪክ ሲቆይ ይጠራልና የሃጫሉ ግድያ ሚስጥር እንደ ጠዋት ፀሐይ ፍንትው ብሎ መውጣቱ አይቀሬ ነው፡፡
ሐ. ታሪካዊቷ ሐውዜን
ትግራይ ውስጥ የምትገኘው ትንሿ ሐውዜን በግብርና ወይም በኢንደስትሪ ልማቷ ሳይሆን፣ ዕድሜ ለሕወሓት የምትታወቀው በአሳዛኝ ዕልቂቷ ነው፡፡ ሕወሓት ኤርትራን በማስገንጠል ሻዕቢያን ለመርዳት ያደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል ዓመታትን ማስቆጠሩ፣ ከፈጣሪው ድርጅት ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ከከተተው ውሎ አድሯል፡፡ በመሆኑም ሕወሓት ወደ አዲስ አበባ የሚያደርገውን ጉዞ ፈጣን ማድረጉ ሁለት ዓላማ ነበረው፡፡
አንደኛው የፈጣሪውን የሻዕቢያን የረጅም ጊዜ ዓላማ ማለትም የኤርትራን መገንጠል ዕውን ማድረግ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ለግብፅ ሥጋት ምክንያት የሆነውንና ደርግ ከጣሊያን ኩባንያ ጋር በመሆን ለግብርና ልማት ማስፋፊያ እየገነባ ያለው ታላቁን የጣና በለስ ፕሮጀክት ሥራውን ከመጀመሩ በፊት ደርሶ ማውደምና ኢትዮጵያን ወደብ አልባ ማድረግ ነበር፡፡ ስለዚህም ይህንን የሻዕቢያና የግብፅ ተልዕኮ ይዞ ወደ አዲስ አበባ በመገስገስ ላይ ያለው ወያኔ ፍጥነቱን ይበልጥ የሚጨምርለት ተንኮል ሲያስብ፣ የሐውዜን ሕዝብና የሻምበል ለገሰ አስፋው ችኩል ባህሪ ተገጣጠሙለት፡፡ የሐውዜንን ሕዝብ ለዚህ አሰቃቂ ድርጊት ለማዘጋጀት በቅድሚያ ከዚህ በታች ያሉት ሦስት ዋና ዋና ተግባራት እንዲከናወኑ የወያኔ ባለሥልጣናት ወሰኑ፡፡
የመጀመርያው
በሬዲዮ የረጅም ጊዜ የፕሮፓጋንዳ ፕሮግራም በመቅረፅ የሐውዜን ሕዝብ ለወያኔ ትግል ስላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ በተደጋጋሚ በሬዲዮ በማስተላለፍ፣ የትግራይ የበላይ አስተዳዳሪ የነበረውን የሻምበል ለገሰ አስፋውን ትኩረት መሳብ ዋነኛው ተግባር ነበር፡፡ ይህም ሻምበል ለገሰ ሐውዜን ላይ እንዲዘምት የሚያስጨክነውን መልዕክት ማቀበል ማለት ነው፡፡
ሁለተኛው
በመቀጠልም በተካሄደው የቅስቀሳ ሥራ የሻምበል ለገሰን ብስጭት ጥግ ያደረሱት ወያኔዎች የሐውዜን ሕዝብ ለመሰል ተቃውሞ በብዛት አደባባይ እንዲወጣ ቀን ቆርጠው በማዘዝ ዕለቱን ደግሞ ለለገሰ በግልባጩ ማሳወቅ ሲሆን፣ እንዲሁም አውሮፕላኖቹ በሚደበድቡበት ወቅት በፊልም ለመቅረፅ እንዲቻል ቪዲዮ አንሺዎች በቦታው በቅድሚያ ተልከው ምሽግ እንዲያዘጋጁ ማድረግና ድብደባውን ከቅርብ እንዲቀርፁ ማድረግ ነበር፡፡
ሦስተኛው
ይህንን የሰቆቃ ፊልም አውሮፓ ሆነው ለሚጠባበቁት አባሎቻቸው በማከፋፈል ፊልሙን አባዝቶ በአውሮፓ፣ በተለይም በስካንዲኔቪያን ቸገሮችና አሜሪካ አካባቢ በማሠራጨት፣ በወገኖቻቸው ዕልቂት የፕሮጋንዳ ትርፍ የማጋበስ ሥራ ማከናወን ነበር፡፡ ሁሉም ነገር በዕቅዱ መሠረት ተከናወነ፡፡ ሐውዜንና ሕዝቧ የመሰሪ ፖለቲከኞች ጉዳይ ማስፈጸሚያ ሆኑ፡፡ በፊልሙ የተረበሹት አውሮፓውያን ለወያኔ ዕርዳታቸውንና ድጋፋቸውን አጎረፉት፡፡ ወያኔ አዲስ አበባ ሲገባ የሻዕቢያንና የግብፃውያኑን መመርያ አልረሳውም፡፡ ገና መቀመጫው ሳያርፍ ለኤርትራ መገንጠል ኤርትራውያን ለረፈረንደም እንዲዘጋጁ ማስተባበር ያዘ፡፡ የጣና በለስን ፕሮጀክት ማውደም ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ገና እንዳይሞከር ለማድረግ ጠቃሚ የሆኑ ንብረቶች ተፈታትተው ተጫኑ፡፡ ኢትዮጵያም ወደብ አልባ ሆነች፡፡ የሐውዜን ሕዝብ የሴራ ፖለቲካ ተፈጸመበት፡፡ በመሆኑም ታሪክ በደንብ ሚስጥራቸውን የሚያውቃቸው የጥላሁን ግዛው ግድያና የሐውዜን ሕዝብ ዕልቂት፣ ነገ እውነቱ ከሚረጋገጠው የሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ለጉዳይ ማስፈጸሚያ የተከናወኑ ነበሩ፡፡
ሰላም ሁኑ!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የአሜሪካን ኮሌጅ ኦፍ ቴክኖሎጂ ዲን ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡