Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትሰላማዊና ሕጋዊ ባህሪና ምግባር የሌለው ትግል ዴሞክራሲን አያዋልድም!

ሰላማዊና ሕጋዊ ባህሪና ምግባር የሌለው ትግል ዴሞክራሲን አያዋልድም!

ቀን:

በገነት ዓለሙ

እየረሳነው ነው እንጂ፣ ኢትዮጵያ ከመጋቢት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለአምስት ወር ፀንቶ በሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ነች፡፡ አገር የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ በመግባቷም በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የጣለ በሽታ መከሰቱን ምክንያት በማድረግ፣ ለመንግሥት ልዩና የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሥልጣን ተሰጥቷል፡፡ በዚህ መሠረት ከአንድ ቤተሰብ አባላት ከሆኑ ውጪ ከሦስት በላይ ወይም ‹‹አራትና ከዚያ በላይ ሆኖ በአንድ ቦታ በአካል መገኘት››፣ ‹‹ለሰላምታና ለሌላ ማንኛውም ዓላማ በእጅ መጨባበጥ›› ተከልክሏል፡፡ አፍና አፍንጫ ላይ መሸፈኛ ማድረግ ግዴታ ሆኗል፣ ወዘተ፡፡

እነዚህን መንግሥት አዲስ ካወጣው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሥልጣን የመነጩ፣ የተለያዩና ያልተለመደዱ ክልከላዎችንና ትዕዛዝ በሕጎቹ የተፈጻሚነት የእስካሁኑ ሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ልዩ ልዩ አስተያየቶችን፣ ምላሾችን፣ ቅሬታዎችን ሲያስተናግዱ ዓይተናል፣ ሰምተናል፡፡ ፖሊስ ማስክ አላደረጋችሁም ያላቸውን ሰዎች በጅምላ አግዶ ቁጭ ብድግ አሠርቶ ወደ ሆነ ቦታ ወስዶና ትንሽ አቆይቶ፣ ገስፆም ይሁን ምክር ሰጥቶ ኮቪድን ሊከላከል፣ እንዲህ ያለውን አሠራር ጨምሮ ሌሎችንም የሕጎችን አፈጻጸም ብቻ ሳይሆን፣ ሕጎችን ራሳቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሰላ ሂስ በነፃነትና በዕውቀት ሲተች፣ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ደግሞ ከተለመደውና ከዱሮው የኮማንድ ፖስት (የ2009 እና 2010) ዘመን ጉድጓዱ አልወጣ ብሎ በጉብኝት፣ ተጨማሪ እሴት በሌለው መግለጫ ሲተረክ፣ እንዲያውም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ምክረ ሐሳብ ‹‹የጀርባ ተልዕኮ›› በአደባባይ ሊከስና ሲያጋልጥ ሰምተናል፣ ታዝበናል፡፡

- Advertisement -

የሕዝብ ጤንነትን አደጋ ላይ የጣለውና ለመንግሥትም የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሥልጣን ያስታጠቀው ኮቪድ 19 ሥርጭትን የመከላከል፣ የመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት የመቀነስ ሥልጣንና ተግባር የአገርም ፈተና ሆኖ ምርጫ አራዝሟል፡፡ የምርጫው መራዘም ራሱን የቻለ የ‹‹ተቃውሞ›› ርዕሰ ጉዳይ መሆኑ ባይቀርም፣ የኮቪድ 19 አደገኝነትም ሆነ በእሱ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ መግባታችንን የደነገገው የአገር ሕግ አስፈላጊነት ግን ሁሉንም በአንድነት ያስማማ ጉዳይ ነበር፡፡

የሃጫሉ ግድያ ያስከተለው ሐዘን፣ ቁጣና ተቃውሞ በዓይንም በሚዲያም እንዳየነው እንዲያ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጁን፣ አዋጁን ብቻ ሳይሆን ኮሮና ቫይረስ ራሱን በሽታውን ሆን ብሎ የዘነጋው፣ የተጋፈጠው፣ ይህም ራሱ ሆን ተብሎ የታቀደ፣ ይሁነኝ ተብሎ የተወሰደ የተቃውሞ ሥራ፣ የትግል ሥልት ሆኖ ነው? አዎ! ተብሎ በአዎንታ የሚመለስ ቢሆን የሚያሳስብ፣ የሚያስደነግጥና ጠንቀኛ አካሄድ በሆነ ነበር፡፡ የተገለጸውን የመሰለ እንዳየነው ዓይነት ያለ፣ ኃላፊነት የጎደለውና በሕዝብ ጤና ላይ የሚከተለውን የታወቀ አደጋ ማሰብ ያልቻለ የሕዝብን አደገኛ መሰባሰብና መከማቸት ያስከተለው ተቃውሞ ግን፣ በኮቪድ 19 የመከላከል የአገርና የሕዝብ ጤና ጥበቃ ሥራ ላይ ያስከተለው ኪሳራ ግን ከወዲሁ ገና ልክና መልኩ፣ ስፋቱና ክፋቱ ሳይታወቅ በፊት ሐዘን የሚያስቀምጠን ነው፡፡

የሕዝብ ጤናን አደጋ ላይ መጣል ራሱ የታቀደ የትግል መሣሪያ አልሆነም ማለት ግን፣ የሃጫሉ ግድያ የፈጠረው ቁጣና ተቃውሞ ከአደገኛ አጥፊና አውዳሚ የትግል ሥልት ነፃ ነው ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም ዋናው ጉዳይ ይኸው ነው፡፡ ተቃውሞ መብት ነው፡፡ የትግል መሣሪያም ነው፡፡ መብት ረገጣን፣ ግፍን፣ ጭቆናን መቃወም ሕገወጥነትን መቃወም ነው፡፡ በተለይም ከዴሞክራሲ ጎን ቆሞ የመታገል ጉዳይ ባለው ሕገ መንግሥት ውስጥ የተደነገጉት የሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብቶች ሕይወት እንዲያገኙ፣ መኗኗሪያ እንዲሆኑ መቆም ማለት ነው፡፡ ከሕገ መንግሥት በላይ የሆነ ገዥን ራሱን መቃወምና መታገልና አረማመድህና ባህርይ መቃኛ ያኑረው፣ በሕግ ይገዛ በሕግ ውስጥ ይወሰን ማለት፣ በአጠቃላይ በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ባገኙና በተረጋገጡ መብቶች አማካይነት ‹‹እንቢ›› ማለት ራሱ ከሕገ መንግሥቱ ጋር አይጋጭም፡፡ ተቃውሞም፣ እንቢታም ግን ሕጋዊና ሰላማዊ መሆን አለበት፡፡ የትኛውንም ዓይነት ሕገወጥነትንና መብት ረገጣን የሚቃወም የፖለቲካ ዕይታ ያጎለበተ ትግል፣ ትግልና ውመናን መለየት አለበት፡፡ በቀል፣ ጥቃት፣ ውድመት በሰዎችና በኑሯቸው ላይ ጥቃት መፈጸምና እልህ መወጫ ማድረግ መብት ማስከበሪያ በጭራሽ አይደለም፡፡

ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ውስጥ መወሰን ያለብን እንዲህ ባለው የዴሞክራሲና የነፃነት አየር በሚነፍስበት የአሁኑ የኢትዮጵያ ሁኔታ ብቻ አይደለም (ይህ ውሸት ነው የሚሉ ሰዎች መኖራቸውንም አልረሳም)፡፡ አምባገነናዊ መንግሥትንም እንኳ የምንታገልበት መሣሪያ ሕገ መንግሥታዊ፣ ሕጋዊና ሰላማዊ መሆን አለበት የሚባለው ዋናው የትግሉና የተቃውሞው መነሻ መንግሥት ከሕግ በላይ በመሆኑ ነው፡፡ ለሕግ መገዛት እንቢ በማለቱ ነው፡፡ በሕጉ ውስጥ ያሉ ብልሽቶችም መታረም የሚችሉት ሕግ የተከተለና ሰላማዊ አሠራር ሲኖር፣ ይህንንም ለማድረግ እሺ ያለና ተገድዶ የፈቀደ መንግሥት ሲኖር ነው፡፡

ለሰላማዊና ለሕጋዊ ትግል መታመንና መገዛት ፋይዳው ግን ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በቀድሞው (ቀድሞ መባል በጀመረው በኢሕአዴግ ኢትዮጵያ) ሁኔታ ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥትህን አክብር፣ ለአሠራርህ መቃኛ ይኑረው ብሎ በሰላማዊና በሕጋዊ ትግል መወጠር ቀስ እያለም ቢሆን፣ የሕዝብ ድምፅና ምርጫ አለመግባባታቸውን እያጋለጠ፣ ተመራጮች ወኪሎቻችን አለመሆናቸውን እያሳጣ፣ ሥራ አስፈጻሚው ‹‹ከወኪሎቻችን›› ከኢትዮጵያ ሕዝብ በላይ አድራጊ ፈጣሪ መሆናቸውን አደባባይ እያወጣ የሕዝብ ግንዛቤ ያደርጋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙ ገንዘብ የሚከሰክስበትን ፕሮፓጋንዳ ያቋቋመውን ውሸትና ወሬ እየነዳደለ መንግሥትን እርቃኑን ያስቀራል፡፡ የሕዝብን ትግልም ውጤታማ እያደረገ ይሄዳል፡፡ ሕጋዊና ሰላማዊ ያልሆነ የጥቃትና የውድመት እንቢታ ግን ሕግና ሰላም በማስከበር ስም ትርምስን፣ ፍጅትን፣ እርስ በርስ መተላለቅን በመከላከል ስም፣ ወይም በዚያው በትክክለኛ ምክንያት አምባገነንትንና ወታደራዊ ፈላጭ ቆራጭነትን በራስ ላይ ይጠራል፡፡ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጥቃት እያደረሱ መታገል በገዛ ራሱ ምክንያት ትክክል አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ አምባገነናዊነትን በኃይል ገርስሶ መጣል በራሱ ዴሞክራሲያዊ መንግሥትን የማረጋገጥ ዋስትና ስላልሆነ ነው፡፡

ቅድም ለመጥቀስ ወደ ሞከርኩት ወደ አዲሱ የኢትዮጵያ ሁኔታ እንመለስ፡፡ አሁን የምንገኝበት ወቅት የሽግግር ምዕራፍ ነው ሲባል ሕገ መንግሥቱን ካሰነካከለ አፈና ወደ ሕገ መንግሥታዊነትና ወደ ዴሞክራሲ የማለፍ ጉዞ ጀምረናል፡፡ እዚያ ጉዞ ውስጥም ነን ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ዋና አስኳል ፌዴራላዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሪፐብሊክ ናቸው፡፡ ተሰነካክሎ፣ ተጎሳቁሎ፣ ውሸት ሆኖ የኖረውም ፌዴራላዊነት፣ ዴሞክራሲያዊነትና ሪፐብሊክነት ነው፡፡ የሕዝብ ሥልጣን በነፃ ዴሞክራሲያዊ ሒደት አንዴም ዕውን ሆኖ አያውቅም፡፡ የኖርንበት የሩብ ምዕተ አገዛዝ ዓመት በፌዴራላዊነትና በዴሞክራሲያዊነት ቅርፅ የሚነግድ የሕወሓት/ኢሕአዴግ አምባገነንነት ነበር፡፡ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ሕዝብን ይወክላሉ ተብለው ሲመረጡ የኖሩ ሰዎች የዚሁ አምባገነንነት አገልጋዮች ነበሩ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ፓርቲና መንግሥት ይቀላቀሉ፣ ፓርቲ የመንግሥት ሥራዎችን ከላይ እስከ ታች ይዋጥ አይልም፡፡ ዛሬም በሽግግሩ ወቅት ገና ደህና አድርገን ያልደነገጥንበትና ያልተማርንበት ጉዳይ ቢሆንም፣ ሕገ መንግሥቱ ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት ገለልተኛ መሆን የሚገባቸውን ሁነኛ አውታራት ገዥው ፓርቲ ያቦተለካቸው አይደሉም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ገዥነታችሁ ሲደፈርና ተቃውሞ ሲነሳ ረሽኑ፣ 20 ሺሕ እና 30 ሺሕ ሰው እስር ቤት አጉሩ የሚል ሥልጣን ለገዥዎች አልሰጠም፡፡ ሕገ መንግሥቱ በተከሳሾች ላይ መንግሥት የሚዲያ ዘመቻ ያካሂድ፣ ግርፊያና ልዩ ልዩ ስቃይ ይፈጽም አይልም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ገዥው ፓርቲ በመንግሥት ሀብት እንዳሻው ይጠቀም፣ ታላቅ መሪ ለሚለው ሰው በሕዝብ ሀብት ላይ መዋጮ/ዕርዳታ ብጤ አከል አድርጎ ፋውንዴሽን ያቋቁም አይልም፡፡ በርካታ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው አሁንም በብዙ ትርምስ ውስጥ ቆም ብለንና ጊዜ ሰጥተንና ጎልጉለን ያልለየናቸውና ብይን ያልሰጠንባቸው፣ መዓት ኢሕገ መንግሥታዊ የሆነ ብዙ ጉዶች በኢትዮጵያ ምድር ሲሠሩ ኖረዋል፡፡

በ2008 ዓ.ም. የጀመረው የሕዝብ ትግል ምንም እንኳን በጠንቀኛና በመዘዘኛ ጥቃትና ውድመት የተነካካ ቢሆንም፣ አገር ሳይፈርስ መንግሥት ላይገረሰስ በገዥው ፓርቲ መዋቅር ውስጥ መገለባበጥ ፈጥሮ ለዓብይ አህመድ የኢሕአዴግ ሊቀመንበርነትና ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሹመት በር ከፍቷል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግሥት ከዴሞክራሲ አልባነት ወደ ዴሞክራሲ የመሸጋገር ዕቅድን መርጦ፣ የአገሪቱ የሥልጣን ዓምዶች ከፓርቲ ታማኝነትና መዳፍ የማላቀቅ ማሻሻያ የማካሄድ ሒደት ውስጥ መግባቱ፣ ከዚህ በፊት በአገሪቱ ታሪክ ያልነበረ አዲስ ውጤት ማለትም ሕዝብ በድምፁ ሿሚና ሻሪ የሚሆንበት ሥርዓተ መንግሥት ሊያመጣ የሚችል የሽግግር መንገድ ነው፡፡ በዚህ የአዲስ ምዕራፍ መንገድ የቀደደ ጅምር ጉዞ ውስጥ አገር ያስደነቀ ወሳኝ ዕርምጃዎች ተወሰዱ፡፡ አፈናን፣ በአስተሳሰብ መወነጃጀልና መታሰርን፣ መሳደድንና ብረት አንስቶ ጫካ መግባትን፣ ጎራ ፈጥሮ መኮራረፍን ያቃለሉ ዕርምጃዎች ተከታተሉ፡፡ የህሊና እስረኞች ተፈቱ፡፡ ተቀዋሚዎች ተጠሩ፡፡ ጎራ የፈጠሩ ከፖለቲካው ጋር ትስስርና ጉድኝት ያላቸው፣ በመኮራረፍ የፀኑ የጠላትነት ስሜቶችና ቡድድኖች (በሃይማኖት ዘርፍ) ተፈረካከሱ፡፡ መንግሥታዊ የግፍ ውንጀላና የጭቦ እስራትን፣ የሥቃይ ምርመራንና እስራትን ነውር ያደረጉ፣ አይደገመንም ያሉ ሥራዎች ተሠሩ፡፡ እነዚህ ሁሉ የዋናው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጥያቄ ማስጀመሪያዎች፣ ፈር መቅደጃ አስፈላጊ ምልክቶችና ትርጉም ያላቸው ዕርምጃዎች ነበሩ፡፡

ዋናውና መሠረታዊው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጥያቄ ደግሞ፣ ከፈላጭ ቆራጭነት ወደ ዴሞክራሲ የማለፍ የሽግግር ምዕራፍ የአገር ግዳጅ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ዋናው ተግባር ዴሞክራሲን ማደላደል ነው፡፡ ወደ ሕገ መንግሥት ማሻሻያም ሆነ ወደ ምርጫ ቀጥታ መግባት ሳይሆን፣ አስፈላጊ ከሆነ ሕገ መንግሥቱንም ጭምር ማሻሻል፣ ነፃና ፍትሐዊ ከሕዝብ ፈቃድ ጋር የተግባባ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ማደላደልና መፍጠር ነው፡፡

ይህን የሽግግር ዘመን ደግሞ ከሁሉም በላይ የተሻለ የሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች መነሻና መንድርደሪያ የሚያደርገው፣ ከዚህ የበለጠ ሁሉንም የሚያስማማና የሚያግባባ የሁሉም የጋራ አደራ የሆነ ምንም ነገር ስለሌለ ነው፡፡ ፓርቲዎችና የፖለቲካ ኃይሎች የትኛውንም ፍላጎቶቻቸውን ሆነ የሥልጣን ፍላጎቶቻቸውን ጭምር፣ በሕዝብ ድምፅ ማስወሰንና ማረጋገጥ የሚችሉት መጀመርያ እዚህ ላይ አንድ ሆነው ሲሠሩ ነው፡፡

አለመታደል ሆኖ ግን ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ሁሉ ይህ አልተገለጠላቸውም፡፡ የጋራና የወል አዳራቸው፣ የሥራና የፖለቲካ ጥበብ መጀመርያቸው ዋናው የአገር የፖለቲካ ጥያቄ ከፈላጭ ቆራጭነት ወደ ዴሞክራሲያዊ መሸጋገር፣ ሕገ መንግሥቱ በአጠቃላይ በዚህ ውስጥ የተደነገጉት መብቶችና ነፃነቶች በተለይ ነፍስ የሚዘሩበትን የአገር እስትንፋስ የእርስ በርስ መኗኗርያ የሚሆኑበትን መደላድል ማሰናዳት መሆኑን ዘንግተው ወይም እሱን አልፈው በግል፣ ለየብቻ ተልዕኳቸው ተጠመዱ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሲጎሳቆል ከነበረበት ምዕራፍ ወደ ሕገ መንግሥታዊነትና ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት ወደሚሆንበት ምዕራፍ መተላለፍን በዋስትና የሚያረጋግጡ የጋራ አደራዎቻቸውን መረባረቢያ ከማድረግ ይልቅ፣ ራሱን ዴሞክራሲን አስቀድሞ በማይጠይቁ በማያጣድፉና የጋራ ባልሆኑ ስንጥርጥር ጉዳዮች ላይ አገርን አንከወከው፡፡ የሽግግር ወቅት ዴሞክራሲን የማደላደል ትግሉ ለውጡን ከመክሸፍ ለማዳን ከመረባረብ መነሳት ቢኖርበትም፣ ለውጡን ሰላም የነሳው ከጋራ አደራቸው አፈንግጥው የእኔ ጉዳይ ይቅደም በመባባላቸው ነው፡፡

በዚህ ውስጥና በዚህ መካከል በአምባነንነትና በፈላጭ ቆራጭ የአገዛዝ ዘመን ታፍነውና ከእነ ስማቸውና ከእነ መኖራቸው ‹‹ክልክል›› ሆነው ተሰቅዘው የኖሩ አሮጌ ጥያቄዎች፣ ቅሬታዎችና ብሶቶች የለውጥ ብርሃን ሲፈነጥቅና የአገዛዙ ድቆሳ ሲረግብ ገና ሥር ባልያዘው የዴሞክራሲ አየር ውስጥ መዘርገፍ ጀመሩ፡፡ ዞንና ክልል ልሁን ማለት፣ በወሰን ጉዳይ መጠዛጠዝ፣ የአካባቢዬን መሬት ወይም ሲሳይ ተቀራመተኝ በሚሉት ላይ ጥቃት መሰንዘር ከፍ ያለ ጉዳትና ግዙፍ መፈናቀል፣ የለውጥ ኃይሎችም የለውጥ ተፀናዎቾችም ጭምር ይህንን የለውጡ ይዘት አድርገው አቀረቡት፡፡ የለውጡን መንግሥት በቀውስ አጣድፈውና አስምጠው ‹‹የአብዮታዊ ዴሞክራሲ›› አምባገነነትን እንመልሳለን ብለው የሚቃዡትም፣ የሚደንቅና የማይታሰብ ወዳጅነት ትናንት አሸባሪ ብለው ከፈረጇቸውና ከፈረዱባቸው ፓርቲዎችና የጥቃት ዓላማ አድርገው በገፍ ካሰሯቸው ወገኖች ጋር እንፈጥራለን እያሉ ነው፡፡

በዚህ ምክንያት የሁሉም ኃይሎች የለውጥ የመጀመርያው ደረጃ አብሮ የመሥራት ተልዕኮ፣ ሁሉም የጋራ አደራ ሊያደርጉት የሚገባው ዴሞክራሲ የሚፈልጋቸውን ሁኔታዎች የማመቻቸት ተግባር ተዘነጋና በኋላ ሊመጡ የሚገባቸው፣ ዴሞክራሲን ራሱን በቅድመ ሁኔታነት የሚጠይቁ ጉዳዮች እርስ በርስ መተናነቂያ ሆኑ፡፡ በአገራችን ዴሞክራሲን የማዳላደል የሽግግር ምዕራፍ ዋና ተግባርና ሥራ ሁሉም ከሕገ መግሥቱ እንነሳ የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎች፣ አይጥና ድመት የነበሩ ቡድኖች ሳይቀሩ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አገር መገንባትን ዋና ጉዳያችንና አደራችን አድርገን ብለው የተሰባሰቡበት፣ ነፃ የብዙኃን ማኅበራትና ነፃ የሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎዎች የተፍለቀለቁበት፣ መልካም የፖለቲካ አየር መፍጠር በዚህ አየር ውስጥም የፖለቲካ ወገንተኝነት የሌላቸው የዴሞክራሲ ተቋማትንና አውታራትን ማሰነዳዳት፣ ከቡድኖች የፖለቲካና የድምፅ ትርፍ ይልቅ ከሌሎች መካከል ለጤናማ የምርጫ እንቅስቃሴ ዘመቻና ላልተጭበረበረ የድምፅ አሰጣጥ ሥር መያዝ መጨነቅን የበለጠ የኅብረተሰብ ንቃተ ህሊናንና ግንዛቤን የማጎልበት ሥራ አንዱና ዋነኛው መረባረቢያቸው በሆነ ነበር፡፡ ይህ ሳይሆን በመቅረቱ በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይችል የሕዝብ ጤንነትን አደጋ ላይ የጣለ በሽታ (ኮቪድ 19) ያስተላለፈውን የምርጫ ጊዜ፣ እንኳን እሺ ብሎ መቀበል የጋራ መግባቢያ ሊሆን አልቻለም፡፡

ለምን እንዲህ ሆነ?  ለምን ለውጡን ማፋጠን አስቸጋሪ ሆነ? ለውጡን አፋጥኖ ጥያቄዎች የአመፅ መንገድ ሳይዙ የሚስተናገዱበት፣ ወንጀል የትግል ሽፋን ማግኘት የማይችልበት ሥርዓት ወይም አሠራር የመገንባት ጅምር ጥረታችን ሁሉም የማያወላውልበት ተግባር ለምን ሳይሆን ቀረ? የዚህም ጥያቄ መልስ የሚመስለኝ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ዋና ትኩረት፣ ቀዳሚ ተግባርና መሠረታዊ አደራ የጋራ አደራቸው መሆኑን ትተው ለየብቻ አጀንዳቸውን መራኮቻ ከማድረጋቸው የሚመነጭ ነው፡፡ ይበልጥ ስለሚያፍታታው ጉዳዩን ይህንን ጥያቄ ከመመለስ ማዕዘንም እንየው፡፡

የዓብይ መንግሥት ብሔረሰባዊ ማንነታችን ከኢትዮጵያ ማንነት ጋር አስማምቶ፣ ከዴሞክራሲ አልባነት ወደ ዴሞክራሲ የመሸጋገር ዕቅድ ይዞ፣ የአገሪቱን የሥልጣን አውታሮች ከፓርቲ ታማኝነትና ወገንተኝነት የማላቀቅ ማሻሻያ የማካሄድ ሒደት ውስጥ ሲገባ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የተሰባሰበው ድጋፍ አገርንም ዓለምንም ያስደመመ ቢሆንም፣ ባለብዙ አቅጣጫና የሚጠፋፋ ነበር፡፡ ያለው ሕገ መንግሥትና የፌዴራል አከፋፈል እንዳለ ሆኖ፣ ዴሞክራሲ ብቻ እንዲጨመር የሚሻውም እዚያ ድጋፍ ውስጥ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ቢቋቋምም የብሔር ብሔረሰብነት መነጽር ያለው ሕገ መንግሥትና የፌዴራል አባላት አከፋፈል ካልተቀየረ፣ የማኅበረሰቦች መንጓለልና መፈናቀል አይወገድም የሚለውም አለ፡፡ ያለው የፌዴራል አባላት አከፋፈል የአገረ ብሔር ድርሻ ሆኖ እንዲታወቅለት፣ የአገረ ብሔርን ሀብትና ምድር የብሔሩ ልጆች መጠቀሚያ እንዲሆን የሚሻውም አለ፡፡ ሁሉም ወገን ወደ ራሱ አቅጣጫ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ስቦ ለማሥጋትና የገዛ ራሱ ፖሊሲ አስፈጻሚ ለማድረግ በየፈርጁ የገመድ ጉተታ አካሄደ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩት የፖለቲካ ዝንባሌዎችም ሁለት ጫፍ የረገጡ፣ ወደ ኢትዮጵያ አንድነትና ወደ ብሔርተኛ መስመሮች የተሰባሰቡ ዋና ጎራዎች ሆኑ፡፡ ሁለቱም ከሞላ ጎደል እኩል ለውጡ ሽግግሩ ተቀልብሷል፣ ተቀጭቷል ብለው ለሽግግሩ ችግር ቢያዋጡም ዋናው ሽግግሩ ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ አገር ላይ ላንዣበበው አደጋ ዓይነተኛ ምክንያት ግን፣ ብሔር ላይ ባተኮሩና ኢትዮጰያ ላይ ባተኮሩ ቡድኖች መካከል የተፈጠረው በመናቆርና በጥላቻ የተማሰ ገደል ነው፡፡ እንኳንስ የለየላቸው የለውጡ ተፀናዋቾች፣ እንኳንስ መንግሥትን በቀውስና በጥያቄዎች ጋጋታ አዋክበው የቀድሞውንም ሆነ አዲስ ፈላጭ ቆራጭ ለመመለስ የሚመኙት ተቃዋሚዎች፣ ከአምባገነንነት መውጣትና ዴሞክራሲ ውስጥ መግባት እንሻለን በሚሉትም ውስጥ ጉዞው መጀመሩን ክደው፣ ወይም ጨንግፏል ብለው በመፀናወት ላይ ብቻ አልተወሰኑም፡፡ ከዚያም በላይ ጉዞውን ተፀናወተው የዓብይን መንግሥት በሕገ መንግሥቱ፣ በፌዴራልነትና በብሔረሰብ መብት ላይ የመጣ አውሬ አድርገው ይኮንናሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ፖሊሲና ሙያ ተብሎ የተያዘው አጥፊና አውዳሚ የትግል ሥልት ነው፡፡

ሽግግሩን መርቀው ከከፈቱት ታላላቅ ተግባራት መካከል አንዱ ተቃዋሚዎችን መጥራት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ሽግግር ለውጥ በ1983 ዓ.ም. አደጋ ላይ የወደቀውና ለ27 ዓመታት አምባገነንነትና አዳዲስ ችግሮች ወደ ተፈለፈለበት ሩብ ምርተ ዓመት ፍዳ የገባነው፣ ኢሕአዴግ ገዥው ቡድን ራሱ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪነት መለወጥ፣ ይህም የሚጠይቀውን አስተሳሰብና ምግባር መያዝ አለመቻሉ፣ እዚያው ጫካ ውስጥ ከለመደው የጦርነት ሥልት አለመውጣቱ ነው፡፡ ዛሬ እዚህ ችግር ውስጥ የገባውና አስቸጋሪ በሆነው ሥልጣን ላይ ባለው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን፣ ከውጭም ከውስጥም ለውጡ ወደ ሰላማዊና የሠለጠነ ትግል በጋበዛቸው ቡድኖች ጭምር ነው፡፡ በኦሮሚያ ደቡባዊና ምዕራባዊ ዳርቻዎች ውስጥ የሚካሄደውና ዓለም የሚያውቀው ነውጠኛነት የዓብይ አህመድ የሰላማዊና የሕጋዊ ትግል ጥሪ እንዴት አድርጎ ወደዚህ እንደተቀየረ ያሳያል፡፡ ከሃጫሉ ግድያ በኋላ በቅርቡ (July 3, 2020) ኢንተርናሽናል  ክራይሲስ ግሩፕ ያወጣው የዚህ ጉዳይ መግለጫ የሚጠቅሳቸውና (Armed Gangs Rampaging Through Mixed Ethnic Settlements) ያላቸው የተጠቁ ‹‹ጋንጎች›› ይህን ያህል አተራማሽ ኃይል የሆኑት፣ ከመንግሥት አቅም ማነስ ወይስ ከፖለቲካ ቡድኖች ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ውስጥ አልገባም ብሎ የመሸፈትና የማወጅ ስፋትና ክፍት ምሥል ነው?

በሰው ሕይወት ላይ ጥቃት መፈጸምና ንብረት ማውደም ከለውጡ በፊት በነበረው ትግል ውስጥ ተወስዶ ዝም ብሎ ተሸፋፍኖ ታልፏል፡፡ ምናልባትም በዝምታ አበጀህ ተብሎ ተመርቋል፡፡ ይህ ሰበብ አስባብ ባገኘ ቁጥር እያገረሸ ሕይወት በጅምላ የሚያረግፍና ንብረት የሚያወድም፣ ከዚያም በላይ በሰዎች መካከል መራራ ጥላቻንና ቂምን የሚተክል አታጋይነትና ትግል ከሁሉም በፊት ትግላችን ሰላማዊና ሕጋዊ ነው በሚሉ የፖለቲካ ኃይሎች በግልጽና በይፋ መወገዝ አለበት፡፡ ለውጡና ሽግግሩ በደቦ ጥቃትና ውድመት የሰውን ሕይወትና ንብረት ሲያጠፋ፣ የሕዝብን ሰላም ደኅንነትና ሠርቶ የማደር መስተጋብር ሲያናጋ፣ የአዲስ ሥራ ማቋቋም ዕድልን ከሩቅ እያባረረ ሥራ አጥነትን ሲያባብስ፣ ብሶትና ማንን ፈርቼ ባይነትና አፄ በጉልበቱ መሆን በሕግ አስከባሪነት መፍዘዝ ወይም ‹‹ሆደ ሰፊነት›› እየታገዘ በሰበብ አስባብ ሲደፋፈር፣ ተጠቃሁ ያለና መንግሥታዊ የደኅንነት ዋስትና ማጣት የተሰማው ሁሉ ራሱንና ቢጤዎቹን ሕግ አድርጎ መበቀልን ሙጢኝ ሲልና ዋስትናው ሲያደርግ፣ ይህ እርስ በርሱ እየተመጋገበ አገርን ያፈርሳል፡፡ የትኛው ፖለቲከኛ ነው የምፈልገው ይህንን ራሱን ነው የሚለን?

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...