Thursday, June 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አቢሲኒያ ባንክ እስከ 60 የሚደርሱ ወለሎችን የሚይዝ ሕንፃ ሊያስገነባ ነው 

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አቢሲኒያ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ በርዝመቱ ቀዳሚ እንደሚሆን የሚጠበቅ  ሕንፃ ለማስገንባት ዓለም አቀፍ ጨረታ አወጣ፡፡

ባንኩ በአዲስ አበባ ከተማ ለማስገንባት ያቀደው ከ50 እስከ 60 ወለሎች እንደሚኖሩት ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ሕንፃ የሚገነባውም ሜክሲኮ አደባባይ በሚገኙት ይዞታዎቹ ላይ ነው፡፡

እስካሁን በአዲስ አበባ ከተማ ትልቁን ርዝመት በመያዝ የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እያስገነባው የሚገኘው ሕንፃ ሲሆን፣ 46 ወለሎች ያሉት ይህ ሕንፃ ከመከላከለያ ሚኒስቴር ማዶ፣ ኢትዮጵያ ሆቴል አጠገብ ይገኛል፡፡ ይህ የንግድ ባንክ ሕንፃ በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡

አቢሲኒያ ባንክ ለሚያስገነባው ሕንፃ ተጫራቾችን በመጋበዝ ዝርዝር ፍላጎቱን ያስታወቀበት የጨረታ ሰነድ እንዳመለከተው፣ ለዋና መሥሪያ ቤትነት የታቀደውን ሕንፃ ለመገንባት የሚወዳደሩ ተቋራጮች ዲዛይኑንና የግንባታ ሥራውን በጥምረት መሥራት የሚችሉ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡

አቢሲኒያ ባንክ በአሁኑ ወቅት በዋና መሥሪያ ቤት የሚገለገልበት ሕንፃ ለገሃር አካባቢ የሚገኘውና ከአያት ሪል ስቴት በ400 ሚሊዮን ብር የገዛውን ሕንፃ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ውስጥ ከ24 ዓመታት በላይ የዘለቀው አቢሲኒያ ባንክ፣ ከአዋሽ ባንክ በመከተል የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን በመቀላቀል የሚጠቀስ ሁለተኛው የግል ባንክ ነው፡፡ ባንኩ በአሁኑ ወቅት በአትራፊነታቸው ቀዳሚ ከሚባሉ  ባንኮች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በ2012 ዓ.ም. ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት 1.34 ቢሊዮን ብር ማትረፉን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የብድር መጠኑን በ13 ቢሊዮን ብር ማሳደግ እንደቻለም ይጠቀሳል፡፡ ይህም ከፍተኛ የብድር ምጣኔ ያስመዘገበበት ዓመት እንዳሳለፈ ያመላክታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች