Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከስብራት መልስ

በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ከተሞች ተፈጠሮ በነበረው ሁከት የደረሰውን ውድመት የሚያመለክቱ ተከታታይ መረጃዎች እየተደመጡ ነው፡፡ ጥፋቱ ምን ያህል አስከፊ እንደነበር ከደረሰው የንብረት መውደም ባሻገር በንፁኃን ዜጎች ላይ የተፈጸሙት ግድያዎችና ድብደባዎች ያስገነዝባሉ፡፡

የጥፋት ዘመቻው በሚገባ የተቀናባበረ እንደነበር ማንም የሚገነዘበው ነው፡፡ አገር ለማተረማመስ፣ የአገር ሀብትና ንብረትን ለማጥፋት ብቻም ሳይሆን፣ የሌላ ክልል ተወላጆች ያፈሩትን ንብረትና ሕይወታቸውን መነጠቃቸውን ተከትሎ ሌሎችም ‹‹ምን ቀረኝና ዳግም ወደዚያ እሄዳለሁ›› እንዲሉ ጭምር የሚያስገድድ የሥነ ልቦና ጫና ለማሳደር ታስቦ ጭምር የተፈጸመ የሚመስለው ጥቃት ሕዝብን ዳር ከዳር አሳዝኗል፡፡ ጥቃቱ ኢትዮጵያዊ በገዛ ወገኑ ላይ ያደረሰው በማይመስል ደረጃ በርካቶችን ለሞትና ለጉዳት ከመዳረጉም ባሻገር፣ አውላላ ሜዳ ላይ የበተናቸውን ቤተሰቦች፣ የታረዙ ሕጻናትን ሰቆቃና ሰቀቀን ማየቱም ምን ያህል እንደሚያሳምም ከበርካቶች አንድነት የሚደመጠው ሲቃ ይገልጸዋል፡፡

የሁከቱ መነሻ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በተፈጠረ ግርግር ሰበሰብ ነው ቢባልም፣ ንፁኃን እየገደሉና እያቆሰሉ፣ ሀብትና ንብረታቸውን በአንድ ቅጽበት ለማውደም የተደረገው እንቅስቃሴ ግን ቀድሞውኑ የታሰበበት ጉዳይ እንደነበር ለመገመት አያዳግትም፡፡ የንግድና የመኖሪያ ቤቶች ተሰባብረዋል፡፡ ተቃጥለዋል፡፡ አንዳንዶቹ ማንነታቸው እየተመረጠ ጭምር ጥቃቱ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ተሽከርካሪዎች እሳት ተለቆባቸዋል፡፡ አንቡላንሶች ሳይቀሩ ተሰባብረዋል፡፡ ተቃጥለዋል፡፡

ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የፈሰሰባቸው ኢንቨስትመንቶች ለክፉዎች ተግባር ሰለባ ሆነዋል፡፡ በርካታ ምርቶች፣ ግብዓቶችና ልዩ ቁሳቁሶች ተዘርፈዋል፡፡ ለመዝረፍ ያልመተቹት ተንኮታኩተዋል፡፡ ይህ መጠነ ሰፊ ጥፋት ድንገተኛ ሐዘን የወለደው ነው ብሎ ለመቀበል ያዳግታል፡፡ ድርጊቱ አንዱን ከአንዱ ለማጋጨት የተጎነጎነ ሴራ ነው የሚለው የበርካቶች አመለካከት ለትክክለኛነት የቀረበ እንደሆነ ይጠቁመናል፡፡

የተፈጸመው ጥቃትና ጥፋት ሐዘን ከገባው፣ ቁጭት ካደረበት ዜጋ የማይጠበቅ ለመሆኑ፣ ጥቃቱን ያቀነባበሩትም ሆኑ አድራሾቹ አዕምሮ የጎደላቸው ለመሆናቸው ማሳያው የጤና ተቋማትና ትምህርት ቤቶችን ሳይቀሩ የጥቃት ሰለባ ማድረጋቸው ነው፡፡ የጤና ተቋም በማውደም የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍና ስሌቱ ምን እንደሆነ ወንጀለኞቹ ካልነገሩን በቀር ለእኛ ሳይከብደን ይቀራል? የፖለቲካ ቁማር ውጤቱና ማሸነፊያ መንገዱ ይህ ከሆነ ዝንተ ዓለም ጥንቅር ቢል ማንም አይጠላም፡፡

 ከዚህ በላይ ምቀኝነት፣ ከዚህ በላይ ጭካኔ ከየትም ሊመጣ አይችልም፡፡ ስለዚህም ይህ ጉዳይ የመንግሥትን መሠረታዊ ምላሽ ይፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያን ሶሪያ የማድረግ ያህል የተቃጣው ጥፋት፣ አንድ እንኳ የመንግሥት ቢሮና ሕንፃ ያልተረፈበት ወረዳ የግጭትና የጥቃት ሰለባ ሲሆን ማየቱ የጥፋቱ ጥግ ምን ያህል እንደሆነና ምን ያህል አስፈሪ አደጋ ውስጥ እንደነበርን በትክክል ያሳያል፡፡  

ነገን፣ የወደፊቱን አሻግረው በሚያዩ፣ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የኑሮ ምሰሶ ለመሆን የበቁ ወገኖች ላይ ካራ የመዘዙ ወገኖች፣ ከየት የተማሩት ሰይጣናዊ አድራጎት እንደሆነ ለማወቅ ይቸግራል፡፡   

ሁከቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ምስኪኖችን ተፈናቃይ ያደረገ ሲሆን፣ ንብረት በማውደም ላይ ያነጣጠረ በመሆኑም ጭምር ብዙዎችን ንብረት አልባ አድርጓል፡፡ የንብረቶች ባለቤቶች ግለሰቦችና መንግሥት ቢሆኑም፣ በተጨባጭ የአገር ሀብት ላይ  የተቃጣ የጥፋት ዘመቻ ተፈጽሟል፡፡ እንዲህ ያለ ውድመት በራስ ወገን ይፈጸማል ተብሎ በማይታሰብባት ኢትዮጵያ፣ በሃይማኖተኛነቷ በምትጠቀሰው አገር ውስጥ ይህ ሁሉ ለጆሮ የሚቀፍ ጥቃት መፈጸሙ በአገሪቱ ገጽታ ላይ ጥቁር ነጥብ ጥሎ መሄዱ የማይቀር ቢሆንም፣ ተገቢውን መቀጣጫ በአጥፊዎቹ ላይ በመስጠትና ጉዳዩን በጥልቀት በመመርመር እንዳይደገም የሚያስችል ሥራ ይጠይቃል፡፡

ድርጊቱ አገር በማጥፋት የፖለቲካ ፍላጎታቸውንና ጥቅማቸውን ለማሳካት የተፈጸሙት በመሆኑ፣ እንዲህ ባለ መንገድ አገር የማጥፋት ሴራ የተበተበበት አድራጎት እንዲገታ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ እንዲህ ያለው ፀያፍ ተግባር እስከወዲያኛው እንዳይፈጸም ሕግን ማስከበር ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡

እስካሁን የምንሰማው ሕንፃ፣ መኖሪያ ቤት፣ ድርጅት ተቃጠለ ወደመ የሚለውን አስከፊ ዜና ነው፡፡ ይሁን እንጂ በሁከትና ብጥብጡ የወደመው ሀብትና ንብረት ግምቱ ይኼን ያህል ነው ባይባልም በቢሊዮኖች የሚገመት የአገር አንጡራ ሀብት ግን በእብሪተኞች ጠፍቷል፡፡ የመንግሥትና የሕዝብ ተቋማት መረጃዎች አመድ ሆነዋል፡፡

የጥፋቱ መጠን በርካታ መገለጫዎች ያሉት ሲሆን፣ የአገሪቱን የወደፊት ዕርምጃ ወደኋላ የሳበ ጥፋት እንደሆነ በቀላሉ እየታየ ነው፡፡ ለሌላ ስንትና ስንት ሥራ ሊውል የሚችል ሀብት በክፉዎች ተግባር ለወደመና ለጠፋ ሀብት ማገገሚያ እንዲውል እያስገደደ ነው፡፡ ይህ የችግሩ ገጽታ ነው፡፡

ስለዚህ በአገር ላይ የተቃጣው ይህ ዘግናኝ ጥቃት በምንም መንገድ ይቅር የማይባል አጸያፊነት ነው፡፡ የተኬደበት አግባብም ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ መገለጫ የሌለው አዕምሮ አልባዎች የወጠኑት የጉስቁልና ውጤት ነው፡፡ ውንብድና ነው፡፡ ተግባሩን አለማውገዝም ተባባሪነት ነው፡፡ ተቃውሞ የሚገለጸው እንዲህ ባለው መንገድ እንደሆነ በማመን የተነሱ ድንገተኛ የፖለቲካ ሰዎችም ከዚህ በኋላ ስለአገርና ሕዝብ የሚናገሩት አንደበት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ የጥፋትና የክፋት መንገደኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለፍርድ ቀርበው፣ የእጃቸውን ማግኘታቸው ያለማወላወል ሁሉም ከመንግሥት የሚጠብቀው ዕርምጃ ነው፡፡

በተሳሳተ መንገድ ዜጎች በራሳቸው ወገንና ሀብት ላይ እንደዘምቱ ያነሳሱና ያቀናበሩ ሁሉ አገሪቱ ያላትን የመጨረሻ ቅጣት መቀበል ሲያንሳቸው ነው፡፡ የወደመውን ሀብት ለመመለስ ቢቻል እንኳ፣ የፈሰሰውን ደምና እንባ፣ የተሰበረውን ልብ በምንም መልኩ መመለስም መጠገንም ቀላል አይሆንም፡፡ ከባድ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ የጠፋውን ንብረት ለመመለስ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ እንዲህ ያለው ድርጊት እንዳይደገም ሊሠራ የሚገባው ሥራ ከሁሉም የላቀ ሊሆን ይገባዋል፡፡

ስለዚህ የሰሞኑን ተግባር ማውገዝ ብቻ ሳይሆን የዚህን ሴራ ጎንጓኞች በሕግ መፋረድ እስካልተቻለ ድረስ ነገም፣ ሌላ ለጥፋት እንዲዘጋጁ በር መክፈት ይሆናልና መንግሥት ሕግ የማስከበሩ ተግባር ላይ ቁርጠኛ መሆን ይኖርበታል፡፡

ሕግ ካልተከበረ፣ ንብረት የወደመባቸውን ዜጎች መታደግ ካልተቻለ ግን፣ በገዛ አገሩ ተስፋ የሌለው ባለሀብት እያበራከቱ፣ የባለሀብት ስደተኞችን ማበራከት እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

የጥፋቱ አስከፊ ገጽታ፣ ሀብትና ንብረት የወደመባቸው አካባቢዎች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ የሚፈልጉ ባለሀብቶችን ፍላጎት የሚጎዳ በመሆኑ፣ ይህንን ስሜት ለመለወጥና ያለ ሥጋት ገንዘባቸውን ለሥራ እንዲያውሉ ለማደፋፈር፣ የመንግሥት የሰላምና የፀጥታ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የድጋፍ ዕርምጃዎችም ወሳኝ ናቸው፡፡ የመንግሥት ታጋሽነት አገር እስኪጠፋ ድረስ መሆን የለበትም፡፡ ታጋሽነቱ መልካም የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር በማሰብ ነው ቢባልም፣ ከፖለቲካ በላይ ግን የሕዝብ ህልውና ይቀድማል፡፡ ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ያፈነገጡ አካላት እንዲህ ባለው ዕድል መጠቀም እንደማይፈልጉ የሰሞኑ ድርጊት አመላካች ነውና፣ መንግሥት ኃላፊቱን ይወጣ፡፡ ዜጎች በፈለጉበት የአገሪቱ ክፍል ሠርተው የመኖር መብታቸውንም በሚገባ የሚያረጋግጥና የሚያሰፍን ተጨባጭ ሥራ ይሥራ፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት