Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላም ስምምነትን ያስታወሰው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ድንገተኛ ጉብኝት

የኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላም ስምምነትን ያስታወሰው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ድንገተኛ ጉብኝት

ቀን:

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ድንገት ሳይታሰብ ወደ ኤርትራ የልዑካን ቡድን ይዘው ጉብኝት አድርገው ተመልሰዋል፡፡ የሁለቱን አገሮች አዲስ ግንኙነትና የሰላም ስምምነት የሚያስታውሰው ጉብኝት፣ ከኢትዮጵያ በኩል ምንም ባይባልበትም በኤርትራ በኩል ፍንጭ ተሰምቶበታል፡፡

ልክ የዛሬ ሁለት ዓመት በዚህ ወር ነበር የዓለም መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት የሳበ ዜና ከአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የተሰማው። በኢትዮጵያ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ውስጥ የነበረውን ውስጣዊ የፖለቲካ ትግል አሸንፈው በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም. የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተመረጡት ዓብይ አህመድ (/)፣ ወደ ሥልጣን በመጡ በአራተኛው ወር ሐምሌ 2010 ዓ.ም. በድንገት ወደ ኤርትራ መጓዛቸው ነበር የዓለም ሚዲያዎችን ትኩረት የሳበው።

‹‹20 ዓመታት ወታደራዊ ፍጥጫ በኋላ ኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነታቸውን ለማደስ ድንገተኛና አስደናቂ የሆነ ስምምነት አደረጉ›› በማለት ነበር፣ በወቅቱ ታዋቂው  ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ሁነቱን የዘገበው።

ሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች በድንበር ይገባኛል ጥያቄ ባደረጉት አስከፊ ጦርነት ከተቋሰሉ በኋላየድንበር ውዝግባቸው በአልጀርሱ ስምምነት ዕልባት ማግኘቱ ይታወሳል። ይግባኝ የማይባልበት የአልጀርሱ ስምምነት የውዝግቡ ምንጭ የነበረውን የባድመ ከተማ ለኤርትራ የፈረደ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት አፈጻጸሙን አስመልክቶ ባነሳቸው የመርህ ጥያቄዎች የተነሳ መተግበር አልተቻለም።

በዚህም ምክንያት የሁለቱ አገሮች ሠራዊቶች በአወዛጋቢ የድንበር ወሰናቸው ላይ ሠፍረው እስከ 2010 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ተፋጠው የከረሙ ከመሆኑ ባሻገር፣ አልፎ አልፎም ጦር ሲማዘዙና በመሪዎች ደረጃም የቃላት ጦርነት ሲለዋወጡ ቆይተዋል።

በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተመረጡት ዓብይ (/) በፓርላማ በዓለ ሲመታቸው ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ያለውን የሰላም ዕጦት ፈተው ግንኙነቱን እንደሚያድሱ ቃል በገቡ በጥቂት ወራት ውስጥ፣ የአልጀርሱን ስምምነት ያለ ቅድመ ሁኔታ እንደሚቀበሉ አስታውቀዋል።

ይህንንም ተከትሎ 2010 ዓ.ም. ሐምሌ ወር መጀመርያ ላይ በቀጥታ ወደ አስመራ ማቅናታቸው የዓለም የፖለቲካ ማኅበረሰብን ትኩረት የሳበ ሲሆንኢትዮጵያውያን ደግሞ በመደነቅ የተከታተሉት ብቻ ሳይሆን፣ ተዋልደው የተቆራረጡ የሁለቱ አገሮች ቤተሰቦችንም እንባ በማፍሰስ ያገናኘ ክስተት ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይም በዋነኝነት በዚህ ስኬታማ የሰላም ጉዟቸው የዓለም የሰላም ኖቬል ተሸላሚ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

በሁለቱ አገሮች መሪዎች መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የሁለቱ አገሮች ድንበሮች የተከፈቱ ሲሆንየአየርና የየብስ ትራንስፖርት እንዲሁም የስልክ ግንኙነት ወዲያውኑ ተጀምሯል።

የድንበር አካባቢ ንግድ በሁለቱ አገሮች አዋሳኝ ከተሞች በመጀመሩም 20 ዓመታት ተፋዘው የቆዩትና በጦርነቱ ምክንያት የፈራረሱና የተጎዱ ከተሞችም ወዲያውኑ ሕይወት መዝራት ጀምረዋል።

ይሁን እንጂ ስምምነቱን ተከትሎ የገነፈሉት የንግድም ሆነ የእንቅስቃሴ ግንኙነቶች፣ በሁለት አገሮች መካከል የሚካሄዱ ሳይሆን በአንድ አገር ውስጥ እየተፈጸሙ ይመስል መልክ ባለመያዛቸው፣ ግንኙነቶቹን የሚገዛ የሕግ ማዕቀፍ እስኪበጅ ድረስ የድንበር አካባቢ ንግድና የየብስ ትራንስፖርት ግንኙነቶች እንዲገደቡ ማድረግን መንግሥታቱ መርጠዋል።

ነገር ግን ሁለቱ አገሮች ግንኙነታቸውን ለማሳለጥና ስምምነታቸውንም ወደ መሬት ለማውረድ የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎችን አበጅተው መልክ የማስያዙን ሒደት፣ ከሁለት ዓመት በኋላም ማጠናቀቅ አልቻሉም። በአልጀርሱ ስምምነት መሠረት አወዛጋቢውን ድንበርና የባድመ ከተማን የማካለል ተግባርም እስካሁን አልተጀመረም።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዞ ከሁለት ዓመት በኋላ

የኢትዮጵያና የኤርትራ የሰላም ስምምነት በተፈረመበት ወር ሁለተኛው ዓመት ማለትም ሐምሌ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (/) የሚመራ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ያካተተ ልዑክ ቡድን፣ ወደ ኤርትራ በመሄድ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቄና ከሌሎች አቻ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝቶና የሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አድርጎ ተመልሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኤርትራ በነበራቸው የሰሞኑ ጉብኝታቸው ወቅት ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር ከመከሩባቸው ጉዳዮች መካከል፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ትግበራን የተመለከተ ነበር። በውይይታቸውም የሰላም ስምምነቱ ትግበራ ሒደትንና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን እንደገመገሙ፣ የኤርትራ መንግሥት የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረ መስቀል ገልጸዋል።

አቶ የማነ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ ‹‹ሁለቱ አገሮች የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ ከሁለት ዓመት በኋላም ቢሆን፣ የኢትዮጵያ ጦር የኤርትራን ሉዓላዊ ግዛት አሁንም እንደተቆጣጠረ ይገኛል፤›› ብለዋል። አክለውም በሁለቱ አገሮች መካከል የተጀመረው የንግድና የኢኮኖሚ ግንኙነትም በሚፈለገው መጠንና ደረጃ ማደግ እንዳልቻለ ገልጸዋል።

የሁለቱ አገሮች የሰላም ስምምነት ትግበራ ሒደት በተወሳሰበው የኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ፣ እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ሰላምና ደኅንነት ሰንገው በያዙ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች ምክንያት በተፈለገው ደረጃ መተግበር አለመቻሉን አቶ የማነ ጠቁመዋል።

የሁለቱን አገሮች መሪዎች የሰሞኑ ውይይትና የሰላም ስምምነቱ ሁለተኛ ዓመትን በማስታወስ፣ የኤርትራ የኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር በዚሁ ሳምንት ባወጣው የአቋም መግለጫም የሰላም ስምምነቱ ለኤርትራ ሕዝብና መንግሥት ሁለትይነተኛ ፋይዳ ማበርከቱን አስታውቋል።

የመጀመርያው ፋይዳ በኢትዮጵያ ሥልጣን ላይ የነበረውን የሕወሓት የፖለቲካ ስብስብን በመጠቀም ላለፋት ሁለት አሥርት ዓመታት የኤርትራ መንግሥትና ሕዝብን ለማንበርከክ የተቃጣውን ሁሉን አቀፍ ጦርነት ማለትም ወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊና ዲፕሎማሲያዊ ጦርነት ድል የነሳ እንደሆነ አስታውቋል።
 

ሁለተኛው ፋይዳ ጎረቤትና ወንድም ከሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ጋር 80 ዓመታት ሲያቋስል የነበረውን የግጭት አዙሪት ፈውሶ፣ ዘላቂ ሰላምን የሚያፀና ስምምነት ነው ሲል ሚኒስቴሩ ገልጾታል።

በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ከሁለት ዓመት በፊት የተደረሰው የሰላም ስምምነት ዛሬም እንደ ፀና መሆኑን ያስታወሰው መግለጫውበዚህም ምክንያት አንዱ አንዱን ለማዳከም የማሴርና የመገዳደል ዓመታት ተሰብረው ዛሬ በጋራ እንዲመካከሩና እንዲተባበሩ አስችሏል ብሏል።

የሁለቱ ወንድም አገሮች የሰላም ስምምነት ከራሳቸው አልፎ ለአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላምና ደኅንነትም የራሱን ትሩፋት እንዳበረከተ የሚገልጸው መግለጫውትናንት በኤርትራ ጠላቶች ተስበውና ከእነዚሁ ጋር ወግነው የነበሩት ሱዳንና ሶማሊያም ከኤርትራ ጋር ወዳጅነት መሥርተው በጋራ ትብብር እንዲሠሩ ያስቻለ መሆኑንም አመልክቷል።

የመግለጫውን እውነታ ከሚያጠናክሩት ተግባራት መካከል ከአካባቢው ፖለቲካ ላለፋት ዓመታት ተገልለው የነበሩት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፣ በአካባቢው ያለውን የፖለቲካ ውጥረት ለማርገብ እያደረጉ የሚገኘው ዲፕሎማሳዊ ጥረት ይገኝበታል ብሏል።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ጋር ሰሞኑን ከመገናኘታቸው ጥቂት ቀናት አስቀድሞ በግብፅ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አካሂደው የነበሩ ሲሆን፣ በዚሁ ቆይታቸው ኤርትራን ከሚመለከተው ዲፕሎማሲያዊ ጉዳይ ባለፈ ኢትዮጵያና ግብፅ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ያላቸውን ልዩነት እንዲፈቱ በመምከር፣ ይኼንንም ለማሳካት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የማሸማገል ጥረት እንዲያደርጉ መስማማታቸው ይጠቀሳል።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ወደ ግብፅ ከማቅናታቸው ጥቂት ሳምንታት ቀደም ብሎ ለተመሳሳይ ዓላማ ወደ ሱዳን አቅንተው፣ በህዳሴ ግድቡ ላይ ያሉ ልዩነቶች እንዲፈቱ የበኩላቸውን ዲፕሎማሳዊ ጥረት ማድረጋቸው ተመልክቷል።

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ሁለቱ አገሮች ከማቀራረብ አልፎተዘንግታ የነበረችውን ኤርትራን ወደ ምሥራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ማዕከል መጥታ ጉልህ ተሳትፎ እንድታደርግ አስችሏል።

ይሁን እንጂ ጥቂት የማይባሉ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ፖለቲካ ልሂቃን በአንድ ነገር ይስማማሉ፡፡ ይኸውም በኢሳያስ አፈወርቂ ላይ ሙሉ እምነት መጣል አይቻልም የሚል ነው።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የአፍሪካ ፖለቲካ ሥሪትን ጠንቅቀው ያጠኑ በመሆናቸውአሁን ያገኙትን ዕድል ተጠቅመው በአካባቢው ብቸኛው ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመሆን ሊጠቀሙበት ይችላሉ የሚል ሥጋትም በልሂቃኑ ጎልቶ የሚደመጥ የሥጋት ድምፅ ነው።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...