ሰሞኑን በ80 ዓመታቸው ዜና ዕረፍታቸው የተሰማው፣ ጥቁር አሜሪካዊው የመብት ተሟጋች ጆን ሉዊስ በአንድ ወቅት የተናገሩት፡፡ ለረዥም ጊዜ የአሜሪካ ምክር ቤት አባል የነበሩት ሉዊስ፣ የጥቁሮችን የመምረጥ መብት ለማስከበር እ.ኤ.አ. በ1965 ከሰልማ ወደ ሞንትጎሜሪ በተደረገ ትዕይንተ ሕዝብ ላይ ግንባር ቀደም የነበሩ ሲሆን፣ የመንግሥት ኃይሎች በፈጸሙት ጥቃት ክፉኛ ተጎድተው ነበር፡፡ ቀደም ሲል በ1963 ማርቲን ሉተር ኪንግ ‹‹ሕልም አለኝ›› የሚለውን ታዋቂ ዲስኩር ያሰሙበትን የዋሽንግተን ሠልፍ ካስተባበሩ መሪዎች የዚያኔው የ23 ዓመቱ ወጣት ሉዊስ አንዱ ነበሩ፡፡ በካንሰር ሕመም ሕልፈተ ሕይወታቸው የተሰማው ሉዊስ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በአገሪቱ ለሲቪሎች የሚሰጠውን ከፍተኛ የነፃነት ሜዳይ አበርክተውላቸዋል፡፡