Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከ660 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ያስከተለው እሳትና ድንገተኛ አደጋ

ከ660 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ያስከተለው እሳትና ድንገተኛ አደጋ

ቀን:

በተመስገን ተጋፋው

አዲስ አበባ ለእሳትና ለተለያዩ አደጋዎች ተጋላጭ ከሆኑ ከተሞች አንዷ ናት፡፡ በመሆኑም በከተማዋ የሚደርሱ አደጋዎችን ለመቀነስ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ ሆኖም ፍጹም ከአደጋ መፅዳት አይቻልምና እንደወትሮው በ2012 ዓ.ም. የተለያዩ አደጋዎችን አስተናግዳለች፡፡

በ2012 ዓ.ም. በ12 ወር ውስጥ የተከናወኑ ከአደጋ ጋር የተያያዙ ሥራዎችንና ተግዳሮቶችን በተመለከተ፣ የአዲስ አበባ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በሪፖርቱ አስቀምጧል፡፡ በሪፖርቱ መሠረት በአዲስ አበባ ከሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ 520 አደጋዎች ደርሰዋል፡፡ ከእነዚህም 335 የእሳት ቃጠሎ ሲሆኑ፣ 185 ደግሞ ከእሳት አደጋ ውጪና ድንገተኛ አደጋዎች ናቸው፡፡

በቃጠሎ አደጋ 102 የመኖሪያ ቤቶች፣ 55 ደግሞ የንግድ ቤቶች ሲቃጠሉ የወደመው ንብረት በገንዘብ ሲተመን 326,867,160 ብር፣ እንዲሁም በደረሱት 520 ድንገተኛ አደጋዎች ደግሞ የወደመው ንብረት 342,236,660 ብር መገመቱን በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

479 አደጋዎች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ክልል ውስጥ ሲከሰት በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ያጋጠመው 40 ነው፡፡ አደጋዎቹንም ለመቆጣጠር 953 ማሽነሪዎች፣ 440 አንቡላንሶች፣ 57 ፒክአፕ ተሽከርካሪዎች 6665 የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በድግግሞሽ ተሰማርተዋል፡፡ በአደጋው 105 ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን፣ 132 ሰዎች ቆስለዋል፡፡

ከድንገተኛ አደጋ 40ው የወንዝ፣ 27 ደግሞ የጎርፍ አደጋ ናቸው፡፡ የተከሰቱት አደጋዎች በሰው ላይ ያደረሱት ጉዳቶችን በተመለከተ፣ ዘንድሮ በእሳት ቃጠሎ ሕይወታቸው ያለፈ ሰባት ሲሆኑ፣ 49 ሰዎች ቆስለዋል፡፡ ከእሳት ውጪ በሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች 98 ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ 83 ደግሞ ቆስለዋል፡፡

በሌላ በኩል ኮሚሽኑ ከአደጋ ተኮር ዘገባው ባለፈ በተቋሙ ውስጥ ያሉትን ችግሮች በሪፖርቱ አቅርቧል፡፡

የውኃና የመብራት መቆራረጥ፣ በሥራ ክፍሉ አስፈላጊ የሆኑ የላፕቶፕና የፕሪንተር ግብዓቶች አለመሟላት፣ የአንቡላንስ እጥረት፣ የእጅ መገናኛ ሬዲዮ አለመሥራት፣ መኪናዎች ጋራዥ ገብተው በአግባቡ ተጠግነው አለማውጣት፣ የሃይድራንት መስመር ውኃ አለመኖር በአዲስ አበባ ከተማ በአሥር ክፍለ ከተሞች ላይ የሚገኝ ችግር መሆኑም ሪፖርቱ ሐምሌ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. በቀረበበት ወቅት ተነግሯል፡፡

የአቃቂ ቃሊቲ የእሳት አደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ሥራ አስኪያጅ ኮሎኔል ታደሰ ገመቹ የ2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸምን ሪፖርት ሲያቀርቡ እንደገለጹት፣ የእጅ መገናኛ ሬዲዮ ያለመሥራት፣ በግቢው ሕንፃ ላይ ውኃ አለመኖር፣ የመብራት መቆራረጥ፣ ለሥልጠና ድሪል ማካሄጃ በጀት ቶሎ ያለመለቀቅ፣ የመስመር ኢንተርኔት አለመኖርና ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር ተያይዞም የታቀዱ ሥራዎች በተፈለገው መጠን አለመፈጸማቸው ዘንድሮ ያጋጠሙ ችግሮች ናቸው፡፡

የቦሌ ሰሚት የእሳት አደጋና ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ፍቅሩ እንዳብራሩት፣ የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ውይይቶችና ግምገማዎች ቢደረጉም፣ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ግብዓቶችን ማግኘት ባለመቻሉ የተለያዩ ችግሮች ታይተዋል፡፡

የአደጋ ሥጋት ቅነሳና ውጤታማ የአደጋ ምላሽ በመስጠት ላይ ተቋሙ ትልቅ ሚና መጫወቱን አቶ ዓለማየሁ አስረድተው፣ ሁሉም አመራርና ሠራተኞች የሚፈጠሩ ችግሮችን በመገምገምና በመወያየት እንዲታረሙ ሲደረግ በተለይም ደግሞ የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸው ሠራተኞች የደመወዝ ቅጣትና የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንዲደርሳቸው መደረጉን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ በጋራና በቡድን የሚሠሩ ሥራዎችን ለማሳካትና ውጤታማ ለማድረግ ትልቅ ሥራ መሠራቱን፣ የአደጋ ክስተትን ለመቀነስና የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማዳበር የጥንቃቄ ባህልን ለማሳደግ የተለያዩ ሥልቶችን በመጠቀም የቅድመ መከላከል ግንዘቤ ማስጨበጥ ሥራ መሥራቱም ተገልጿል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ከተከሰተ ጀምሮ በኅብረተሰቡ ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ኅብረተሰቡ ራሱንና ቤተሰቡን በመጠበቅ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ በጎዳና ላይ ሰፊ ቅስቀሳዎችን ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡

በእሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ ሥጋት አመራር ሥልጠና ማዕከል ኃላፊ አማን አሰፋ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ለባለሙያዎች የሚያስፈልጉ ግብዓቶች እጥረት መኖሩንና እነዚህንም ችግሮች ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት ችግሮችን ለመፍታት ጥረቶች ቢደረጉም፣ መፍታት አልተቻለም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...