ኢትዮጵያ ውስጥ እየደረሱ ባሉ ግጭቶች ምክንያት በርካቶች ምሬታቸውን በተለያዩ መንገዶች እየገለጹ ነው፡፡ መንግሥት ሕግና ሥርዓት ማስከበር አለበት ከሚሉት ጀምሮ፣ ኢትዮጵያዊያንን በአንድነት ከእነ ልዩነቶቻቸው ሊያኖር የሚያስችል የጋራ የሆነ ሥርዓት ይኑር የሚሉት ድረስ በርካታ ጥያቄዎችም እየቀረቡ ነው፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ኢትዮጵያዊነትን ማዕከል አድርጎ መገንባት ሲገባው ለምን የልዩነት ምንጭ ሆኖ፣ ኢትዮጵያዊያንን እርስ በርስ ያጋድላል የሚሉ ድምፆችም ይሰማሉ፡፡ ‹‹ልዩነት ውበት ነው›› ተብሎ ለዓመታት በተሰበከበት አገር ውስጥ ለምን የጋራ የሆኑ ማኅበራዊ እሴቶች ይጨፈለቃሉ ሲሉም የሚሞግቱ አሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያዊነት ላይ ጥቃት እንደተነጣጠረ ስለሚመስላቸውና በቅርቡም በተለያዩ ሥፍራዎች የተፈጸሙ የጭካኔ ግድያዎችና ውድመቶች ይህንን አመላካች ናቸው የሚሉ ወገኖች፣ መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ የአገር ህልውና ጉዳይ ሊያሳስባቸው ይገባል ሲሉም ያሳስባሉ፡፡ ለዚህም ሲባል ጠቃሚ ምክረ ሐሳቦች ላይ ማተኮር ይገባሉ በማለትም ያስረዳሉ፡፡
ከእነዚህ መካከል አገራቸውን በምሥራቅና በሰሜን ጦር ግንባሮች ከ35 ዓመታት በላይ እንዳገለገሉ የሚናገሩት ሻለቃ መኮንን አለኸኝ፣ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የተሳናቸው ፖለቲከኞች አገር እንዳያፈርሱ ሥጋት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ ‹‹አገርን ከጠላት መጠበቅ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የተቀደሰ ተግባር ነበር፡፡ አሁን እንደማየው ግን ለአገራቸው ሽንጣቸውን ገትረው የሚሠሩ እንዳሉ ሁሉ፣ ኢትዮጵያን ለጠላት አሳልፈው የሚሰጡ እየታዩ ነው፡፡ እኔ እርጅና የተጫጫነኝ ቢሆንም፣ ለወጣቱ ትውልድ የማስተላልፈው መልዕክት አለኝ፡፡ በንጉሡ ዘመን አንድ ማስታወሻ ጥለው ያለፉትን የሌተና ጄኔራል ዓብይ አበበን መጽሐፍ ፈልገው ያንብቡ፡፡ ፖለቲከኞችም ቢያነቡት ያተርፉበታል ብዬ አስባለሁ፤›› በማለት ሁለት አንቀጾችን በማጣቀሻነት አቅርበዋል፡፡
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ከፍተኛ የጦር አዛዥ የነበሩት ሌተና ጄኔራል ዓብይ አበበ ‹‹አውቀን እንታረም›› በሚል ርዕስ በ1955 ዓ.ም. ባሳተሙት መጽሐፋቸው፣ ‹‹አገር ያለ ሰው ምድረ በዳ ሆና ትኖር ይሆናል፡፡ ሰው ግን ያለ አገር ሊኖር አይችልም፡፡ አገር ምን እንደሆነች ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ነገር ግን አገር የምትኖርበትን ዘዴ ገና አጥርተን ያወቅን አይመስልም፡፡ የአንድ አገር ሰዎች መሆናችንን እንድናውቅና ለአንድነታችን መጠጊያ እናታችንን ኢትዮጵያን ለማገልገል፣ ለማኖርና ለኑሯችንም ለመሥራት የምንችለው በአንድ መንፈስ ስንሠለፍና በንፁህ ህሊና ብቻ ስንተባበር ስለሆነ፣ ወደዚህም በቅንነት እንድንራመድ ስለሚያሻ የእያንዳንዳችን መንፈስ ከደካማነት ወደ ፅኑነት መለወጥ አለበት፡፡ መተዛዘንን፣ መተሳሰብን፣ ጠንካራ መንፈስን፣ ቅን ባህሪን፣ ፍቅርን፣ እርስ በርስ መተሳሰብንና አለመናናቅን ማወቅ ይገባናል፡፡ ይህ በመሀላችን ከሌለ ምንም አይኖርም፤›› ብለው ነበር፡፡
‹‹እርስ በርሳችን ባለመስማማትና በመቀናናት፣ አንዱ አንዱን ጥሎ የሚመኘውን ክብር ለመያዝና ለጊዜው ብቻ በጊዜው ለመታየት፣ ወንድምና ወንድም እየተጋጩ በውስጣችን በደረሰው መገዳደልና መዘራረፍ ከዘመን ወደ ዘመን እየተላለፈ የኢትዮጵያ ልጆች ደም በከንቱ እየፈሰሰ ሕዝቡም እየቀነሰ መሬቱ ተራቁቶ ይገኛል፡፡ ያለፈው አለፈ፡፡ ደግም ሆኑ ክፉ ሥራዎች ታሪክ ሆነው ስለሚገኙ ባለፈው ከመፀፀትና ባለፈው ነገር ላይ ከመተቸት፣ ያለፈውን ክፉ ነገር ሁሉ የታረመ ትምህርት አድርጎ የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያን መጪውን በማመዛዘን የዛሬው ተሻሽሎ ለነገ ሊተካ በሚገባው ላይ መድከም ግዴታችን ነው፤›› ማለታቸው በመጽሐፉ ላይ ሠፍሮ ይገኛል፡፡
ታዋቂው ጋዜጠኛ፣ ደራሲና የታሪክ ጸሐፊው ጄፍ ፒርስ በቅርቡ ባቀረቡት ጽሑፍ፣ ‹‹የኢትዮጵያዊያን ዋነኛ ጠላት ጥላቻ ነው፤›› ብለው ነበር፡፡ አሁንም ቤቶችን ቆላልፎ በገዛ ወገን ላይ እሳት መልቀቅ ከጥላቻ ስብከት የተገኘ ነው ብለው፣ ‹‹ኢትዮጵያዊያን አንድ ላይ ሆናችሁ ግን መጀመርያ በዓድዋ ቀጥሎም ከዓመታት በኋላ ዋነኛ ጠላታችሁን አሸንፋችሁ ነበር፡፡ እንደ አንድ ሕዝብ ሆናችሁ በማርክሲስቱ ደርግ ሞታችሁ ነበር፤›› በማለት ጥላቻን በማስወገድ አንድ ሁኑ ሲሉ ተማፅነዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ዓርብ ሐምሌ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ለሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ‹‹ሁላችንም እንደምናውቀው የፖለቲካ መዝገበ ቃላችን የተሞላው ‹ምታው፣ ደምስሰው፣ ቁረጠውና ፍለጠው› በሚሉ የሞት ቃላት ሲሆን፣ በመሳደድና በማሳደድ ዙሪያ መሽከርከር ከጀመረ ዘመናት ተቆጥረዋል። ‹ድርጊት ሲደጋገም ልማድ ይሆናል› እንዲሉ አሁን ያለው የፖለቲካ ባህላችን የተቀዳው በአንድ ወቅት እንደ ቀልድ በጀመርናቸው የሴራ፣ የመገዳደልና በጎራ ተከፋፍሎ ድንጋይ የመወራወር አጉል ልማዳችን ነው። በየአጋጣሚው ሲነገር፣ ሲጻፍና ሲዜም የኖረው ይኼ የተበላሸ ፖለቲካችን በትውልድ ጅረት ተንከባሎ እነሆ ዛሬ ላይ ደርሷል፤›› ብለው ነበር።
‹‹ይኼው እኛም እንደ መልካም ውርስ የመጠላለፍና የመገዳደል ባህልን ተቀብለን የየዕለት ኑሯችን በቆምንበት መርገጥ፣ ዛሬም ነገም አንድ ቦታ መሽከርከር ሆኗል። አገራችንን ወደፊት ለማራመድ የምንሻ ከሆነ ይኼንን ክፉ ውርስ አሽቀንጥረን መጣል ይኖርብናል፡፡ በመጥፎ ባህል ያደፈ ካባችንን አውልቀን በምትኩ በጋራ የምንበለፅግበትን ካባ ልንደርብ ይገባል። ለውጥ ሰዎችን በሰዎች፣ መሪዎችን በመሪዎች የመቀየር ሒደት ብቻ አይደለም። የተበላሸውን የፖለቲካ ሥነ ልቦና፣ የፖለቲካ ባህልና የፖለቲካ ሥርዓት ጭምር በአዲስ የመቀየር ጉዞ ነው። ተቋሞቻችንን፣ የእርስ በርስ ግንኙነታችንና የፖለቲካ ቋንቋችንን ጭምር መለወጥ ይገባናል። ይኼን ማድረግ ከቻልን እንደ አገርና እንደ ሕዝብ ወደ ምናስበው የብልፅግና ሠሰነት እንሻገራለን። ካልሆነም የኋላቀርነት አዘቅት ውስጥ ስንንደፋደፍ ዘለዓለም መኖራችን ነው፤›› ሲሉ አክለዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች በደረሰው ጉዳት ሰለባ የሆኑ ሰዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የፖለቲካው ተፅዕኖ እንደሚጎበኛቸው የታወቀ ነው የሚሉት፣ በሻሸመኔ ከተማ የደረሰውን ውድመት ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን የሚናገሩት የሕግ ባለሙያው አቶ ዘሪሁን ቅጣው፣ ‹‹ምንም እንኳ የአገሪቱ የፖለቲካ ባህል በጣም የተበላሸና ያልዘመነ ቢሆንም፣ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ እንዲህ ዓይነት ለአዕምሮ የሚሰቀጥጥ ድርጊት ሲፈጸም በቸልታ የተመለከቱ የአካባቢው አመራሮችም ሆኑ የበላይ አለቆቻቸው በሕግ ሊጠየቁ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ ተጠያቂነት ሲጠፋ ሥልጣን ላይ ያሉትም፣ ለሥልጣን የሚፎካከሩትም ለሕዝብ ደኅንነትና ለአገር ህልውና አደጋ ይፈጥራሉ ሲሉም አሳስበዋል፡፡ አቶ ዘሪሁን ሌላው ያነሱት ነጥብ ዴሞክራሲ ተግባራዊ መሆን የሚችለው ሕግ የሚያከብሩና የሚያስከብሩ ፖለቲከኞች ሲኖሩ ብቻ እንደሆነ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ እንደ እባብ ‹‹ካብ ለካብ የሚተያዩ›› ያሉዋቸው ፖለቲከኞች በሞሉበት አገር ልፋቱ ከንቱ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡ በሴራ በተሞላ ፖለቲካ አገር ከመከራ ውጪ ምንም እንደማታተርፍ አስጠንቅቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ ‹‹ሁላችንም ልብ ካልን ምንጊዜም ከመከራ የሚያተርፉ አካላት በዙሪያችን እንዳሉ እንረዳለን። የከብት ዕልቂት ለገበሬ መከራ ቢያመጣም ለጅብ ግን ሠርግና ምላሽ ነው። የዶሮ ዕልቂት ለባለቤቱ ኪሳራ ለሸለምጥማጥ ደግሞ ትርፍ ነው። የሁለት በጎች ጠብ ጥቅም ካስገኘ የሚጠቅመው ተኩላውን ነው። የሁለት እርግቦች ግብግብ አንጋጦ ለሚጠብቃቸው ድመት በረከት ነው፡፡ ምንም መልፋት ሳይጠበቅባቸው ድመቱና ተኩላው በእርግቦቹና በበጎቹ ጸብ ምክንያት በቀላሉ ሆዳቸውን ይሞላሉ፡፡ በተመሳሳይ በሰዎች ፀብም የሚያተርፉ ሞልተዋል። በእኛም አገር አሉ። አሁንም እርስ በእርሳችን እያጋጩን ከፍተኛ ጥቅም የሚያገኙት እነዚሁ ከቅርብም ከሩቅም ሆነው የሚጠብቁ የግጭት ነጋዴዎች ናቸው፤›› ነበር ያሉት።
‹‹ለለውጥ ስንታገል ዋነኛው ዱላ የሚሰነዘርብን ከመከራችን ሲያተርፉ ከነበሩ አካላት እንደሆነ ግልጽ ነው፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹በሁላችንም ቤት ለዘመናት የተዘራ የልዩነት መርዝ አለ፡፡ አሁን እዚህም እዚያም ሲፈነዳ የምናየው እሱን ነው። ፈንጂው ዛሬ ቢፈነዳም ከተቀበረ ግን ቆይቷል። የግጭት ፈንጂ ምን እንደሆነ፣ የት የት እንደ ተቀበረ፣ በማን እንደ ተቀበረ ማወቅ ለአንድ አካል የሚተው የቤት ሥራ ሳይሆን የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ነው። ማወቅም ብቻውን በቂ አይደለም፣ አንድ በአንድ እየተለቀመ መክሸፍ ይኖርበታል፤›› ብለዋል።
ሕዝብ እንዲበጣበጥ፣ አንዱ ብሔር በሌላው ላይ እንዲነሳ፣ አንዱ ሌላውን እንዲገድል፣ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያውያንን ንብረት እንዲያወድሙ፣ የጥላቻና የሞት ድግስ ቅስቀሳዎች በየሚዲያው እንዲካሄዱ የሚያደርጉት ፈንጂ ቀባሪዎቹ የግጭት ነጋዴዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል። አንዳንዶች ከእነሱ ጋር ተባብረው በሕዝብ ላይ ፈንጂዎቹን ያፈነዳሉ። ሳያውቁ ቆመውበት የሚፈነዳባቸውም ይኖራሉ። አንዳቸውም ጉዳትን እንጂ ጥቅም አያስገኙልም፡፡ ‹‹ከእንግዲህ ይበቃል፣ በጉያችን ይዘን ዘወትር መሰቃየት የለብንም፤›› ብለው ነበር፡፡
ጡረተኛው ሻለቃ መኮንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልዕክት በቴሌቪዥን መስማታቸውን ተናግረው፣ ‹‹እርግጥ ነው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት የተረዳሁት የመንግሥት ኃላፊነት ያለበትን ጫና ብቻ ሳይሆን፣ የተለያዩ ፍላጎቶችን አቻችሎ በመሄድ ሒደት ውስጥ ብዙ ፈተናዎች እንደነበሩ ነው፡፡ ነገር ግን ‹የነብር ጭራን አይዙም፣ ከያዙም አይለቁም› እንደሚባለው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ተጠርጣሪዎችን እስከ መጨረሻው ድረስ በሕግ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ አገር የምትኖረው ሕዝብ ሲኖር ነው፡፡ ሕዝብ በገዛ አገሩ እንደ ባዕድ እየታየ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አውሬ እየታደነ ሲገደል አጥፊዎችን ጉያ ውስጥ ይዞ መቀጠል አይቻልም፡፡ ትውልዱን በአገር ፍቅር እያነፁ አጥፊዎችን ግን ተገቢውን ቅጣት እንዲቀበሉ ማድረግ የመንግሥት ግዴታ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
‹‹አንገትን እንደ ሰጎን አሸዋ ውስጥ በመቅበር መፍትሔ የምናገኝበት ጊዜ ላይ አይደለንም። አጥፊዎቹን ፊት ለፊት እስካልተጋፈጥናቸው ድረስ የሚያደርሱትን ችግር በመሸሽ ብቻ አናመልጠውም። ላለማየት ጭንቅላትን ጎሬ ውስጥ በመቅበር ዘላቂ መፍትሔ ይገኛል ማለት ዘበት ነው። ዛሬ ጎረቤታችንን የጎበኘ እሳት ነገ ቤታችንን ማንኳኳቱ አይቀርም። ተነጣጥሎ አንድ በአንድ ማገዶ ከመሆን ይልቅ፣ ተባብሮ የተለኮሰውን እሳት እስከ ወዲያኛው ማሰናበት ይበጃል። ለዚያም ነገሮችን በጥንቃቄ መመልከት፣ ትዕግሥትና አርቆ አስተዋይነት በተሞላበት መንገድ መገምገምና ጥበብ ባለው ሁኔታ ተንቀሳቅሶ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው።
‹‹ማን ነው በየአካባቢያችን ሰላም እየነሳን ያለው? ከእነ ማን ጋር ሆኖ ነው የሚበጠብጠን? ለምንድነው የሚበጠብጠን? ጥቂት ነውጠኞች የጫሩት እሳት ብዙኃኑን ሲለበልብ ለምንድነው እኛስ ማስቆም ያልቻልነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል። እሳት ለኳሾቹ እነ ማን እንደሆኑ፣ ማገዶ እያቀበሉ እሳቱን የሚያባብሱት እነ ማን እንደሆኑ፣ ዳር ቆመው የሚያዩትና አብረው የሚሞቁት ጭምር እነ ማን እንደሆኑ ልናውቅ ይገባል። በመንግሥት በኩል እነዚህን ጥያቄዎች በየደረጃው ለመመርመርና አስፈላጊውን ሕግ የማስከበር ዕርምጃ ለመውሰድ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ቁርጠኞች ነን፤›› ብለዋል።
የሕግ ባለሙያው አቶ ዘሪሁን በዝዋይና በሻሸመኔ በነበረው ጉብኝታቸው የታዘቡትን ሲገልጹ፣ ‹‹የአካባቢው አስተዳዳሪዎችና የፀጥታ ኃላፊዎች ይህ ሁሉ ውድመት ሲደርስ የት ነበሩ ብዬ ስጠይቅ፣ የጉዳቱ ሰለባዎችም ሆኑ እነሱን ከጥቃት የተከላከሉ ሰዎች እንቆቅልሽ ነበር የሆነባቸው፤›› ብለው፣ ‹‹ይህ የሚያሳየው አንድም አገር ከሚያወድሙት ጋር በሚስጥር ስምምነት ነበራቸው፣ ካልሆነም የራሳቸውን ሕይወት ለማትረፍ ሲሉ ሕዝቡን ሜዳ ላይ በትነውና ለጥቃት አጋልጠው ሸሽተዋል፡፡ እኔ ግን ነጠብጣቦቹን አገናኝቼ ሁኔታውን የምረዳው አመራሮቹ የአውዳሚዎቹ ተባባሪ እንደሆኑ ነው፡፡ መንግሥት በእነዚህ ላይ የማያዳግም ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድ አለበት፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይም፣ ‹‹እሳቱን ማጥፋት ሲገባቸው በቸልታ የሚያልፉ ሰዎች በአንድም በሌላም መንገድ መከራችንን የሚያበዙብን መሆናቸው አያጠያይቅም። የሚወድመው የአገር ሀብት፣ የሚሞተው የሁላችንም ወገን ነውና ሕጋዊና ሞራላዊ ኃላፊነት እያለባቸው ዓይተው እንዳላዩ የሚያልፉ አካላት ፈፅሞ ከተጠያቂነት አያመልጡም፤›› ብለዋል። ‹‹የተጋረጠብን ችግር እስከ ወዲያኛው እንዲወገድ ወላጆች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የየአካባቢው የባህልና የሐሳብ መሪዎች አስተዋጽኦችሁ ከፍተኛ ከመሆኑ አኳያ ያለማመንታት ሚናችሁን እንድትወጡ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፤›› ብለው፣ ‹‹ከምንም በላይ ሕዝባችን አስፈላጊውን ሁሉ ከማድረግ መቆጠብ እንደሌለበት ሊታወቅ ይገባል፤›› ሲሉ አሳስበዋል።
እያንዳንዱ ዜጋ ጥፋተኞቹ በማስረጃ ለፍርድ እንዲቀርቡ የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበት፣ ከሕግ አስከባሪዎች ጋር ተባብሮ መሥራት፣ የመንደሩንና የከተማውን ሰላምና ልማት ተደራጅቶ መጠበቅ፣ በየአካባቢው የተለየ እንቅስቃሴ ሲታይ ለምን በማለት መጠየቅ፣ እነ ማን እንደሆኑ ማወቅ፣ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን አጥፊዎችን ለሕግ ማቅረብ ተገቢ መሆኑን አስገንዝበዋል። ‹‹ጎረቤቶቻችንን፣ የልማት ተቋማትን፣ የንግድ ድርጅቶችን፣ ሕዝባዊ ንብረቶችን፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን፣ የእምነት ተቋማትን፣ የትምህርትና የጤና ተቋማትን በጋራ እስካልጠበቅናቸው ድረስ ነገ የጉዳቱ የመጀመርያ ሰለባዎች እኛው ስለመሆናችን ነጋሪ አያሻንም፤›› በማለት ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
ጄፍ ፒርስም፣ ‹‹ኢትዮጵያዊያን እባካችሁ አገራችሁ ከአፍሪካ መሪዎች አንዷ ናት፡፡ አሁንም አፍሪካን መምራት ቀጥሉ፡፡ እንደ አንድ ሕዝብ ሆናችሁ እባካችሁ፤›› ሲሉ ተማፅኖ አቅርበዋል፡፡