Friday, July 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ወጋገን ባንክ የ1.1 ቢሊዮን ብር ትርፍ አስመዘገበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለፈው ዓመት ባስመዘገበው ትርፍ ላይ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ቅናሽ ያሳየው ወጋገን ባንክ በ2012 ሒሳብ ዓመት ግን የ47 በመቶ ጭማሪ በማሳየት የ1.1 ቢሊዮን ብር ትርፍ እንዳስመዘገበ አስታወቀ፡፡ የተበላሸ የብድር መጠኑን ከ4.5 በመቶ ወደ 2.8 በመቶ ዝቅ አድርጓል፡፡

ባንኩ የ2012 ዓ.ም. አፈጻጸሙንና ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ድጋፍ መስጠቱን በማስመልከት፣ ሰኞ ሐምሌ 14 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በዓመቱ በርካታ ተግዳሮቶች ቢከሰቱም የተሻለ ትርፍ ያስመዘገበበት ዓመት እንደነበር አስታውቋል፡፡

የወጋገን ባንክ ፕሬዚዳት አቶ ዓባይ መሐሪ እንደገለጹት፣ ምንም እንኳ በሒሳብ ዓመቱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ኢኮኖሚያዊ እንቅቃሴዎች ላይ ባሳደረው መቀዛቀዝ ምክንያት በብድር አከፋፈልና በተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ቢያሳድርም፣ ባንኩን ትርፋማነት ከመሆን ግን አላገደውም፡፡ የብድር ወለድ ተመን ላይ ቅናሽ ቢያደርግም፣ ወጋገን ባንክ በ2012 ዓ.ም. በሁሉም የሥራ ዘርፎች ውጤት በማስመዝገቡ ከታክስ በፊት 1.1 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገብ መቻሉን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡ የተመዘገበው የትርፍ መጠን ካለፈው ዓመት አፈጻጸም ጋር ሲነፃፀር የ46.9 በመቶ ወይም 344.7 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው አቶ ዓባይ ገልጸዋል፡፡

የባንኩ የገቢ መጠንም ወደ 4.3 ቢሊዮን ብር ማደጉ ሲገለጽ፣ ከዓምናው አኳያ ሲታይ በ34.1 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ የባንኩን የተቀማጭ ገንዘብ መጠን በተመለከተ የፕሬዚዳንቱ ማብራሪያ፣ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 30.1 ቢሊዮን ብር መድረሱን ያመልክታል፡፡ ከዓምናው የ27.8 በመቶ ዕድገት ወይም 6.5 ቢሊዮን ብር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ የዓምናው ተቀማጭ ገንዘብ መጠን 23.5 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡

ከብድር አንፃርም ወጋገን ባንክ የ45 በመቶ ጭማሪ ያስመዘገበበትን ዓመት አሳልፏል፡፡ እንደ አቶ ዓባይ ገለጻ በአሁኑ ወቅት ለደንበኞች በተለያዩ የብድር ዘርፎች የተሰጠው አጠቃላይ የብድር መጠንም በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 23.9 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህ አፈጻጸም ካለፈው ዓመት የ16.5 ቢሊዮን ብር አኳያ፣ የ45 በመቶ ጭማሪ የተስተናገደበት ነው፡፡

የባንኩ የተበላሸ የብድር መጠን በቀዳሚው ዓመት 4.5 በመቶ ደርሶ ነበርና ይህ የተበላሸ የብድር መጠን በ2012 የሒሳብ ዓመት ምን ደረጃ ላይ ነው? ለሚለው ጥያቄ፣ አቶ ዓባይ ባንካቸው በቀዳሚው ዓመት የነበረውን የተበላሸ የብድር መጠን ዝቅ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ባንኩ ብድር ለማስመለስ ተግዳሮቶች እንደነበሩበት የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ የነበረውን የተበላሸ የብድር መጠን ለመቀነስ በተሠራው ሥራ በ2012 የሒሳብ ዓመት የባንኩ የተበላሸ የብድር መጠን ወደ 2.79 በመቶ ዝቅ ማለቱን አስታውሰዋል፡፡

ወጋገንን ጨምሮ የአገሪቱ ባንኮች አሁን በአትራፊነታቸው መቀጠላቸው የተገለጸ ሲሆን፣ የኮሮና ወረርሽኝና ሌሎች ችግሮች ሊያስከትል የሚችለው ቀውስ በቀጣይ ዓመታት የሚታይ ሊሆን የሚችል ይሆናል እየተባለ ነውና አሁን እየተገኘ ያለው ትርፍ ሊቀጥል ይችላል ወይ? የሚል ይዘት ላለው ጥያቄ፣ አቶ ዓባይ ግልጽ መሆን ያለበት ለማንኛችንም ቀጣዩ ጊዜ የማይገመት መሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ምናልባት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለበሽታው ክትባት ሊገኝ ይችላል የሚል ተስፋ እንዳለ ገልጸው፣ መድኃኒቱ ተገኘም አልተገኘ ሥራዎች መቀጠል እንዳለባቸው፣ ከቫይረሱ መኖርና መለማመድ ግድ በመሆኑ፣ ይህን ታሳቢ ባደረገ መንገድ ሥራዎች ማስኬድ ተገቢ እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ ያምናሉ፡፡ ‹‹ምንም ይሁን፣ ምን ሳንሠራ መቀመጥ የለብንም፤›› ያሉት አቶ ዓባይ፣ ወደፊት የተሻለ ሁኔታ እንደሚፈጠርና በዚህ ሐሳብ መሠረት ለመጪው ዓመትም ዕቅድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ ሆኖም የባንኩ አትራፊነት ወደፊት ከሚኖረው ለውጥ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡

ባንኩ እግረ መንገዱን ይፋ ያደረገው፣ ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ሲሆን፣ የገንዘብ ድጋፉን አቶ ዓባይ ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ጸሐፊ መሸሻ ሸዋረገድ (ዶ/ር) አስረክበዋል፡፡

ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የተሰጠውን የገንዘብ ድጋፍና ተያያዥ ክንውኖችን በተመለከተ፣ ወጋገን ባንክ በተለያዩ ወቅቶች በጤናና ማኅበራዊ እንዲሁም በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት ከተለያዩ አካላት ጋር እየሠራ እንደሚገኝ አቶ ዓባይ ገልጸዋል፡፡ ባንኩ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ጋር በተለያዩ ዘርፎች አብሮ ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሱ በማስታወስ፣ ባንኩ የማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እንዲችል ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ተጠቅሷል፡፡ በየዓመቱም ለማኅበሩ አንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንዲሁም የ50 ሺሕ ብር ዓመታዊ የአባልነት መዋጮ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም ከ4,900 በላይ የሆኑትን የባንኩ ሠራተኞና የማኔጅመንት አባላትን በማስተባበር ለማኅበሩ በየወሩ ቋሚ ወርኃዊ መዋጮ እንዲያደርጉ ጥረት እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ ማኅበረሰቡም የአቅሙን በማዋጣት ማኅበሩን መርዳት እንዲችል የባንክ አካውንት በመክፈትና በባንኩ ቅርንጫፎች የሙዳይ ሳጥኖች በማስቀመጥ የማኅበሩን የገንዘብ አቅም ለማሳደግ ድጋፍ እንደሚደረግ የባንኩ ፕሬዚዳንት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ጸሐፊ መሸሻ (ዶ/ር) በበኩላቸው ባንኩ ባደረገው ድጋፍ አመስግነው፣ ይህንን ገንዘብ በአዲስ አበባ በቀን አንድ ጊዜ ምግብ ለሚቀርብላቸው 1,500 ዜጎች ድጋፍ የሚውል መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ገንዘብ ለ45 ቀናት አንድ ጊዜ ለመመገብ ያስችላል ብለዋል፡፡

ወጋገን ባንክ በ2012 ሒሳብ ዓመት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች 42 ተጨማሪ ቅርንጫፎችን የከፈተ ሲሆን፣ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻም የቅርንጫፎቹን ብዛት 382 ማድረስ መቻሉን ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡ በተመሳሳይ ባንኩ የኤሌክትሮኒክስ ባንኪንግ አገልግሎቱን በሰፊው ለማዳረስ እንዲችል በመላ አገሪቱ 297 የኤቲኤምና 273 ፖስ ማሽኖችን በመትከል እንዲሁም የሞባይልና የኢንተርኔት አገልግሎቶችን በስፋት በመስጠት በዘርፉ ቀዳሚ ባንክ ለመሆን እየሠራ መሆኑ በዕለቱ ባወጣው መግለጫው ላይ ጠቅሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች