በግል፣ በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ጥምረት የሚተገበረውና 1.2 ሚሊዮን ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው ጤናችን በእጃችን ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ፡፡
ጤናችን በእጃችን ፕሮጀክት ለኮቪድ-19 ተጋላጭ ተብለው የተለዩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን፣ ጥቅጥቅ ባሉ የመኖሪያ አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎችን ለማገዝና ራሳቸውን ከወረርሽኙ እንዲጠብቁ ለማስቻል የሚሠራ መሆኑንም በጥምረቱ ዳልበርግ ግሩፕ ተወካይ አቶ ዳግማዊ ኃይለየሱስ ገልጸዋል፡፡
ሐምሌ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ፕሮጀክቱ ይፋ መሆኑን አስመልክተው አቶ ዳግማዊ እንደተናገሩት፣ የፕሮጀክቱ አባል አምራች ኩባንያዎች በፕሮጀክቱ የመጀመርያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ትርፍን መሠረት ያላደረገ ሥራ ለመሥራትና ሠራተኞቻቸውን በሥራ መደብ ላይ ለማቆየት የተስማሙ ሲሆን፣ ጥምረቱ ደግሞ ኩባንያዎቹ ጥሬ ዕቃዎችን ለማምረት ለክንውን የሚያወጡትን የሚሸፍን ይሆናል፡፡
ጥምረቱ የፊት ጭምብሎችንና ሳሙናዎችን የማምረትና የማሠራጨት፣ የውኃ ገንዳዎችን የመትከል፣ የባህሪ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ የግንዛቤ ለውጥ ፈጣሪ ትምህርቶችን ለኮቪድ-19 ወረርሽኝን ተጋላጭ ተብለው ለተለዩ 1.2 ሚሊዮን ያህል የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሚያደርስም ይሆናል፡፡
ዳልበርግ ግሩፕና ሮሃ ግሩፕ፣ ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የተጀመረው ብሔራዊ ምላሽ ላይ ዘላቂ ተፅዕኖ ለመፍጠር እንዲቻል የግልና የመንግሥት ተቋማትን በጋራ በማደራጀት ወደ ሥራ መግባቱን አቶ ዳግማዊ አስረድተው፣ ለአንድ ወር ለሚቆየው የፕሮጀክቱ የሙከራ ጊዜ የሚያስፈልገው 1,000,000 ዶላር በሮሃ ግሩፕ በኩል የተገኘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ቀሪው 5,000,000 ዶላር ከለጋሽ ድርጅቶች፣ ከግሉ ዘርፍና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የሚሰበሰብ መሆኑንም አክለዋል፡፡
ጥምረቱ የንፅህና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን ለማምረትና በጣም ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለማከፋፈል በዓይነቱ ለየት ያለ የንግድ ሥራ ሞዴሎችን ማስተዋወቅ መጀመሩም ተገልጿል፡፡
አቶ ዳግማዊ እንዳሉት፣ መንግሥት ለፕሮጀክቱ የሚመረቱ ዕቃዎች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስን ያነሳ ሲሆን፣ ዓላማውም የግል ተቋማት በኮቪድ-19 ላይ ለሚደረገው የመከላከል ሥራ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ነው፡፡
ፕሮጀክቱ 15 አገር በቀል አምራች ኩባንያዎችን በአንድ ላይ በማሰባሰብ ያወያየ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ሴቭ ዘ ችልድረን ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውንም አቶ ዳግማዊ አክለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ብሎክን መሠረት ያደረገ የማኅበረሰብ አደረጃጀት ኤጀንሲ በከተማው ውስጥ የሚገኙ 24,934 አካባቢዎችን በመለየት ባዘጋጀው መረጃ በመመሥረት በአሥር ክፍላተ ከተሞች በ121 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ 1,357 ማዕከላትን በመጠቀምም የፊት ጭንብሎችና ሳሙናዎችን ከፍተኛ ተጋላጭ ተብለው ለተለዩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንደሚያከፋፍልም ታውቋል፡፡
ሴቭ ዘ ችልድረን ለጥምረቱ የቴክኒክ ድጋፍ፣ መመርያና የኅብረተሰቡን ተሳትፎ በተመለከተ ድጋፍ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ የኮቪድ-19 ቅድመ መከላከያ ቁሳቁሶችም ደረጃቸውን የጠበቁ እንደሚሆኑ፣ የእጅ መታጠብ፣ የፊት ጭምብል ማድረግና አካላዊ ርቀት መጠበቅን የሚመለከቱ መልዕክቶችም በጤና ሚኒስቴር ወይም በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መርህ መሠረት እንደሚሠራጩ ተገልጿል፡፡ ሥራውን ለማከናወንም ከ260 በላይ የክፍለ ከተማና የወረዳ ቡድን አመራሮች ሠልጥነዋል፡፡
ሜሪ ጆይ ፕሮጀክቱ የሙከራ ጊዜውን ጨርሶ ሙሉ በሙሉ ከመጀመሩ በፊት፣ የፈንድ አስተዳደርንና የሥራ ሒደትን ለመቆጣጠር እንዲሁም የፕሮጀክቱን ውጤታማነት ለመገምገም ከጥምረቱ ጋር አብሮ የሚሠራ ይሆናል፡፡
የፕሮጀክቱን የሙከራ ጊዜ ጨምሮ ለስድስት ወራት የሚዘልቀው ጤናችን በእጃችን ፕሮጀክት፣ ለእያንዳንዱ ወር አንድ ሚሊዮን ዶላር በአጠቃላይም ስድስት ሚሊዮን ዶላር የሚፈጅ ነው፡፡
አቶ ዳግማዊ እንደሚሉት፣ የተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶችን ጭምር በመጠቀም ፕሮጀክቱን ቀጣይ ለማድረግ የሚሠራ ይሆናል፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትረስት ፈንድ ጋር በመሆንም ኮቪድ-19 ካለፈ በኋላ ጥሎ የሚሄደውን ተፅዕኖ ለመቀነስ እየተሠራ ነው፡፡