Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየታላቁ ህዳሴ ግድብ በኅብረተሰብ ጤና መሻሻል ላይ የሚኖረው በጎ ተፅዕኖ

የታላቁ ህዳሴ ግድብ በኅብረተሰብ ጤና መሻሻል ላይ የሚኖረው በጎ ተፅዕኖ

ቀን:

የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርበትና ተደራሽነት የኅብረተሰቡን ጤና ለማሻሻል ከሚኖረው ሚና አንዱ የቤት ውስጥ አየር ብክለትን፣ ተያያዥ የሰዎችን ሞትና ሕመም ማስቀረት ነው፡፡ እንደ ግብፅ ያሉ አገሮች የኤሌክትሪክ ኃይል ለሕዝባቸው መቶ በመቶ ተደራሽ ያደረጉ በቤት ውስጥ አየር ብክለት ተጋላጭነት የሚደርስ የሰዎች የጤና እክልና ሞት የለም ማለት ይቻላል፡፡ በአንፃሩ የኤሌክትሪክ ኃይል አነስተኛ በሆነባቸው ኢትዮጵያና የዓባይ ተፋሰስ አገሮች እንዲሁም የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ከፍተኛ የሆነ የጤና መታወክና ሞት እንደሚያስከትል ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

‹‹የዓባይ ግድብ ለኅብረተሰብ ጤና መሻሻል የሚኖረው ሚና›› በሚል ርዕስ ሐምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደው ውይይት ላይ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ብሔራዊ የጤና ምርምር መረጃ ማደራጃና ማጠናከሪያ ማዕከል አማካሪ አወቀ ምስጋናው (ዶ/ር) እንዳብራሩት፣ በቤት ውስጥ የአየር ብክለት አጋላጭነት የሚመጡ ዋና ዋና በሽታዎች የሳንባ ምች (ኒሞኒያ)፣ ስር የሰደደ የመተንፈሻ ቀዳዳ (ሲኦፒዲ) እና የልብ የደም ቧንቧ በሽታዎች፣ እንዲሁም የሳንባ፣ ካንሰርና ሌሎች የጤና ችግሮች ናቸው፡፡

ከጤና ችግሮቹም መካከል ከጭሱ በሚወጡ ጥቃቅን ንጥረ ነገሮችና የሚቀጣጠለው እሳት የመተንፈሻ ቀዳዳንና ሳንባን ወላፈኑ የመግረፍና የማቃጠል፣ የሰው ልጆች በሽታን የመቋቋም ኃይላቸውን ማዳከም፣ በደም ዝውውር ውስጥ የኦክስጅን እንቅስቃሴ በመግታት ከፍተኛ የጤና እክል ማስከተል፣ እንዲሁም በሚወለዱ ሕፃናት ክብደት መቀነስ ላይ እክል ማስከተሉ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

እንደ አማካሪው ገለጻ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከፎር ሔልዝ ማትሪክስ ኤንድ ኢቫሉዌሽን ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዋሽንግተን ጋር በመተባበር በ2011 ዓ.ም. የተለያዩ በሽታዎችን፣ በበሽታ ምክንያት በሰዎች ላይ የሚደርሰውን ሕመምና ሞት፣ እንዲሁም አጋላጭ መንስዔዎችን አጥንተው ሪፖርት አድርገዋል፡፡ ሪፖርቱ ኢትዮጵያንና የዓባይ ተፋሰስ እንዲሁም የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በአጠቃላይ 12 አገሮችን ያካተተ ነው፡፡

በጥናቱም መሠረት በሶማሊያ፣ ቡሩንዲና ኢትዮጵያ ከሁለት ሰው አንድ ሰው የቤት ውስጥ አየር ብክለት በሽታ በሚያስከትል ክብደትና መጠን ልክ ተጋላጭ መሆናቸውን፣ እ.ኤ.አ ከ1990 ጀምሮ በሱዳን ብክለቱ ከሁሉም አገሮች በተሻለ መጠን እየቀነሰ መምጣቱን፣ በግብፅ ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ ዜሮ መሆኑን፣ በ2019 በእነዚህ አገሮች በቤት ውስጥ አየር ብክለት ተጋላጭነት ምክንያት በአጠቃላይ የሞቱ ሰዎች ብዛት ከ278,288 በላይ መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ከሟቾቹም መካከል 85 ከመቶ ያህሉ ከኢትዮጵያ፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎ፣ ታንዛኒያ፣ ሶማሊያ፣ ኡጋንዳና ኬንያ ናቸው፡፡ በተመሳሳይ ዓመት በኢትዮጵያ 67,827 በግብፅ 73 ሰዎች በቤት ውስጥ የአየር ብክለት እንደሚሞቱ ከአወቀ ምስጋናው (ዶ/ር) ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በለጋ ዕድሜ መሞትና መታመምን በተመለከተ ሶማሊያ፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎ፣ ኢትዮጵያ ታንዛኒያ በከፍተኛ ደረጃ የተጎዱ ናቸው፡፡ በአንፃሩ ግብፅ ላይ ምንም ችግር የለም ማለት ይቻላል፡፡ ጥናቱን መሠረት በማድረግም የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የፖሊሲ አቅጣጫ ሐሳቦችን እንደሚከተለው ጠቁሟል፡፡

ኢትዮጵያና በጥናቱ ሪፖርት የተካተቱ አገሮች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቅመው የቤት ውስጥ አየር ብክለትን እንደ ግብፅ ቢቆጣጠሩ 300,000 የሚጠጋ ሕዝባቸውን ከሞት መታደግ ይችሉ እንደነበር አማካሪው ጠቁመው እነዚሁ የተጠቀሱት አገሮች በመተንፈሻ ቀዳዳና በቲቢ፣ በልብና በደም ቧንቧ፣ ስር በሰደደ የመተንፈሻ ቀዳዳ፣ እናቶችንና ሕፃናትን ከሚያጠቁ፣ እንዲሁም በስኳርና በኩላሊት በሽታዎች የሚሰቃዩ ወገኖቻቸውን መታደግና ለሕክምና የሚወጣውም ወጪ መቀነስ የሚችሉት እንደ ግብፅ መቶ በመቶ የኤሌክትሪክ ሽፋን ሲኖራቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በጥናት አቅራቢው አገላለጽ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዓላማ ለአገሪቱ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ማስተካከል ስለሆነ በተቻለ ፍጥነት በአጭር ዓመታት ውስጥ በማጠናቀቅ በዓመት የሚሞተውን ሰውና የሚታመመውን ኅብረተሰብ ሊታደጉ ይገባል፡፡  ግድቡ በጤናው ዘርፍ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚያስገኘውን ጥቅምና ተያያዥ የጤና ችግሮችን ማጥናት የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ ለዚህም አስፈላጊውን የሰው ኃይልና የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የማዕከሉ ከፍተኛ የጤና ምጣኔ ባለሙያ አቶ አማኑኤል ሉሉ ባቀረቡት ወረቀት ‹‹በጤናው ዘርፍ ዘላቂ የልማት ግብን (ኤሲዲጂ) ለማሳካት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች 100 እስከ 120 ዶላር ስለሚያስፈልጋቸው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለኢኮኖሚ ዕድገት ካለው አስተዋጽኦና የመንግሥት ቁርጠኝነት ታክሎበት በ2022 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ከፍተኛ የጤና አገልግሎት ሽፋን በመድረስ ዘላቂ የልማት ግብን (ኤሲዲጂ) ማሳካት ትችላለች›› ብለዋል፡፡

በአገሪቱ ከሁሉም የጤና ተቋማት ውስጥ በቂ የኃይል ምንጭ የነበራቸው 15 በመቶ ብቻ እንደነበሩ፣ ይህም ከጠቅላላው ጤና ኬላዎች አምስት በመቶና ከጤና ጣቢያዎች 28 በመቶ፣ ከመጀመርያ ደረጃ ሆስፒታሎች 60 በመቶ ብቻ በቂ የኃይል ምንጭ  እንደነበራቸው፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብም ለጤና ተቋማት የኃይል አቅርቦትን በማረጋገጥ የጤና አገልግሎትን እንደሚያጠናክር ነው ያመለከቱት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...