Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበኢትዮጵያ እስከ ሐምሌ 17 ቀን በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 12,693 ሆኗል

በኢትዮጵያ እስከ ሐምሌ 17 ቀን በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 12,693 ሆኗል

ቀን:

“ከኮሮና ቫይረስ ተጠበቁ”

የ200 ሰዎች ሕይወት አልፏል

የጤና ሚኒስቴር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አስመልክቶ፣ ሐምሌ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫው እንዳስታወቀው፣ በኢትዮጵያ 24 ሰዓታት ውስጥ በተደረገ  7,264  የላቦራቶሪ ምርመራ 760 ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን፣ የሦስት ሰዎች ሕይወትም አልፏል፡፡

እስከ ተጠቀሰው ቀን ድረስ በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር 200 እንደሆነም ያስታወቀው ሚኒስቴሩ፣ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም 12,693 መድረሱ፣ ያገገሙትም 5,785 መሆናቸውን ተከትሎ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር 6,706 እንደሆኑና  68 ሰዎች በጽኑ መታመማቸውን ገልጿል፡፡ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ካለፈው መጋቢት ጀምሮ እስካሁን ለ364,322 ሰዎች ምርመራ መደረጉ ታውቋል፡፡

ኮቪድ-19 በወረርሽነት ዓለምን ካካለለ መንፈቅ አልፎታል፡፡ ባለፉት ስምንት ወራት ሕዝበ ዓለም ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠበቅ፣ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ እንዳይያዝ የጤና ባለሙያዎችና ዓለም አቀፋዊም ሆነ አገራዊ ተቋማት ማስገንዘቢያዎችን ከመስጠት ችላ ያሉበት ጊዜ አልነበረም፡፡

ኮቪድ-19 የሚተላለፍበት መንገድ አስመልክቶ እስካሁን ያለው አቋም፣ በሽታው ከሕመምተኛው አፍንጫ ወይም አፍ በሚወጣ ጥቂት ፈሳሽ አማካይነት የሚተላለፍ መሆኑ ነው፡፡ ኮቪድ-19 ያለበት ሰው ሲያስነጥስም ሆነ ሲተነፍስ ወደ ሌሎች ከማስተላለፍ ባለፈ፣ ከሕሙማን የሚወጣ ፈሳሽ ያረፈበትን ቦታ የነኩ ሰዎችም በበሽታው በቀላሉ ሊያዙ ይችላሉ፡፡ ሰዎች ከሰዎች ጋር ያላቸው ቅርርብ ከአንድ ሜትር በላይ መሆን አለበት የተባለውም በሽታው በትንፋሽ ስለሚተላለፍ ነው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች የሚያሳዩት ቫይረሱ በአየር ውስጥ ሳይሆን በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች የመተንፈሻ አካላት ከወጡ ፍሳሾች ጋር በሚኖር ንክኪ ብቻ የሚተላለፍ መሆኑን ነው፡፡

ይሁን እንጂ ሰሞኑን እየወጡ ያሉ መረጃዎች የኮሮና ቫይረስ በአየር ላይ የመተላለፍ ዕድሉ ሰፊ መሆኑ እየገለጹ ናቸው፡፡ ይህን ተከትሎ የዓለም ጤና ድርጅት በቫይረሱ የመጋለጥ ወይም ያለመጋለጥ ዙርያ የቀረቡ ጥናቶች ላይ እየመከረ መሆኑ ተዘግቧል፡፡ በአየር ላይ ቫይረሱ በመቆየት ወደ ሌላ ሰው ሊተላለፍ ስለሚችል ተገቢው ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡

ተተኳሪ ጉዳዮች

የኖቭል ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ከቀላል እስከ ከባድ የመተንፈሻ አካል ሕመም የሚያስከትል የቫይረስ ዝርያ ሲሆን በበሽታው የተያዙ ሰዎች ትኩሳት፣ ሳል፣ የትንፋሽ መቆራረጥና የመተንፈስ ችግር ምልክቶች ይታይባቸዋል፡፡

በዓለም ጤና ድርጅት አገላለጽ፣ ኮሮና ቫይረስ የተለያዩ የቫይረስ ዓይነቶችን የያዘ የቫይረስ ቤተሰብ ነው፡፡ ይህ ቫይረስ በሰዎችና በእንስሳት ላይ በሽታን ያስከትላል፡፡ በሰዎች ላይ የሚከሰተው ኮሮና ቫይረስ የመተንፈሻ አካላትን በመጉዳት ከተራ ጉንፋን እስከ ከፍተኛ የመተንፈሻ አካል ችግር የሚያደርስ ነው፡፡

በሽታው በጠናባቸው ታማሚዎች ላይ ደግሞ እንደ ሳንባ ምች (ኒሞኒያ) ከባድ የመተንፈሻ አካላት ሕመም የሚያሳይ ሲሆን የኩላሊት ሥራ ማቆምና ሞትን ሊያስከትል የሚችል በሽታ ነው፡፡

ኅብረተሰቡ ከዚህ በፊት ማንኛውንም በሽታ ለመከላከል ሲጠቀምባቸው የነበረውን የበሽታ መከላከያ መንገዶች ችላ ሳይልና ሳይደናገጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን ያስተላለፈው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የበሽታውን ሥርጭት ለመቀነስ ቀጥለው የተዘረዘሩትን መልዕክቶች እንዲተገበሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡

        • ሳል ወይም ትኩሳት ካለው ግለሰብ ቢያንስ ሁለት የአዋቂ ዕርምጃ ርቀት ያህል መራቅ፣
        • እጅዎን በአግባቡ ሳይታጠቡ ዓይንና አፍንጫዎን አይንኩ
        • ከሰዎች ጋር አይጨባበጡ፣
        • እጅን በንፁህ ውኃና ሳሙና አዘውትረው ይታጠቡ፣
        • ሰዎች ወደ በሚበዙባቸው ቦታዎች በተለይም የሕመም ስሜት ካልዎት አይሂዱ፣
        • በሚያነጥሱበትና በሚያስሉበት ጊዜ አፍና አፍንጫዎን በሶፍት ወይም ክርንዎን አጥፈው በመጠቀም ወደ ሌሎች እንዳያስተላልፉ ይጠንቀቁ፣
        •  የተጠቀሙበትን ሶፍትና ተመሳሳይ ነገሮች በቆሻሻ ክዳን ባላቸው ማጠራቀሚያ ያስወግዱ፣
        • በሥራ ቦታ፣ በትራንስፖርትና መኖሪያ ወይም የመኝታ ክፍል መስኮት በመክፈት በቂ አየር እንዲኖር ያድርጉ፣
        • መረጃዎችን ከአስተማማኝ ምንጮች ብቻ በመቀበል፣ የተሳሳቱ መረጃዎች የሚያስከትሉትን መደናገርና ፍርኃት ይከላከሉ!
        • በሽታውን ሪፖርት ካደረጉ አገሮች የሚመጡ ሰዎች ወይም ንክኪ ያለው ማንኛውም ግለሰብ ራሱን 14 ቀን በመለየት በበሽታው አለመያዛቸውን ሲያረጋግጡ ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ እንመክራለን::

ከኮሮና ቫይረስ እንዴት እንጠበቅ?

  1. አንድ ሰው ከበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ አለው ሲባል በኮሮና ቫይረስ የታመመ ሰው ምልክቱን ማሳየት ከመጀመሩ ሁለት ቀናት በፊት በአንድ ሜትር ርቀት ውስጥ ሆኖ ከአሥራ አምስት ደቂቃ በላይ ቆይታ ሲኖራቸው ነው፡፡
  2. በተጨማሪም የግል የጤና መከላከያ መሣሪያዎችን ሳይጠቀሙ በበሽታው የተያዘን ሰው እንክብካቤ ሲያደርጉ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በበሽታው መታመማቸው ከተረጋገጡ ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸውን ሰዎች በመለየት በጤና ባለሙያዎች 14 ቀናት ክትትል ይደረግላቸዋል፡፡  
  3. በአገራችን ማኅበራዊ ግንኙነታችንየአኗኗር ባህላችን የጠነከረ በመሆኑ በአብዛኛው የምንጠቀማቸው ቁሳዊ ነገሮች በጋራ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ከዚህ አኳያ አንድ በቫይረሱ የታመመ ሰው ነገር ግን መታመሙ በሕክምና እስከሚረጋገጥ ድረስ ከሰዎች ጋር ከሚኖረው ንክኪ በተጨማሪ የሚጠቀምባቸው መገልገያዎች ሌሎችም ሊጠቀሙበት ስለሚችሉ ቫይረሱ በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው እንዲተላለፍ ያስችለዋል፡፡
  4. በሽታው በሳልና በማስነጠስ ወቅትና ከታማሚ ሰው ጋር በሚደረግ የቅርብ ንክኪ፣ ባልታጠበ እጅና በመሳሰሉት ይተላለፋል፡፡

በሽታውን ሪፖርት ወደ አደረጉ አገሮች የሚጓዙ መንገደኞች ሊያደርጓቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች

  • የትኩሳትና የሳል ምልክት ከሚያሳዩ ሰዎች ጋር ንክኪ አለማድረግ፣
  • እጅን በሳሙናና ውኃ መታጠብ በተለይ ደግሞ ከታመሙ ሰዎች ወይም ከአካባቢያቸው ጋር ንክኪ ካደረጉ፣
  • ያልበሰሉ የእንስሳት ተዋጽኦ የሆኑ ምግቦችን ከመመገብ መቆጠብ፣
  • ምክንያቱ ባልታወቀ በሽታ በታመሙም ሆነ ከሞቱ የቤትና የዱር እንስሳት ጋር ንክኪ አለማድረግ

በበሽታው መያዛቸውን የጠረጠሩ ሰዎች ማድረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎች

  • ወደ አገር በተመለሱ 14 ቀናት ጊዜ ውስጥ የመተንፈሻ አካል ሕመም፣ ትኩሳትና እንደ ሳል ያሉ የሕመም ምልክቶች ካሳዩ፣ በተጨማሪ የበሽታው ስሜት ከመፈጠሩ አሥራ አራት ቀናት በፊት በሽታውን ሪፖርት ወዳደረጉ አገሮች ሄደው ከነበረ፣ በሽታውን ሪፖርት ወዳደረጉ አገሮች ሄዶ የበሽታውን ምልከቶች ማሳየት የጀመረ ሰውን የሚያውቅ ማንኛውም ግለሰብ እንዲሁም የበሽታውን ምልክት ማሳየት የጀመረ ሰውን የሚያውቅ በአስቸኳይ 8335 ነፃ የስልክ መስመር በመደወል ሪፖርት ያድርጉ፡፡
  • በሚያስሉበትና በሚያስነጥሱበት ጊዜ በሽታው ወደ ጤነኛ ሰው እንዳይተላለፍ አፍና አፍንጫን በክንድ ወይም በሶፍት መሽፈን፣
  • አፍና አፍንጫን ለመሽፈን የተጠቀምንበትን ሶፍት በአግባቡ በቆሻሻ መጣያ ውስጥ ማስወገድና እጅን ሁል ጊዜ በውኃና በሳሙና መታጠብ ያስፈልጋል፡፡

ኅብረተሰቡ በሽታው በቀላሉ የሚተላለፍ በመሆኑ ሳይዘናጋ የሚተላለፉ መልዕክቶችንና መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ የበሽታውን ምልክት የሚያሳዩ ሰዎች በሚያገኝበትም ወቅት በተዘረጉ የነፃ የስልክ መስመሮች በመደወል እንዲያሳውቅና የበሽታውን ሥርጭት በመቆጣጠር በኩል የድርሻውን እንዲወጣ አሳስቧል፡፡

ለተጨማሪ መረጃ፣ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም በመደበኛ የስልክ ቁጥር 0118276796 ወይም በኢሜይል አድራሻ [email protected] በመጠቀም ማግኘት ይቻላል፡፡

 በተጨማሪም ለተለያዩ ጉዳዮች በአንድ ቦታ መሰባሰብን በማስወገድ፣ እጅን አዘውትሮ በመታጠብ፣ ሰዎች በሚሰበሰቡበት ቦታዎች ላይ የአፍንና የአፍንጫ መሸፈኛ (የፊት ማስክ) በማድረግ፣ በአካል ንክኪ የሚደረግ ሰላምታን በመተውና አካላዊ መራራቅን ተግባራዊ በማድረግ የበሽታውን ሥርጭት እንዲከላከል ኢንስቲትዩቱ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡

የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት መጨመርን ከግንዛቤ በማስገባት ኅብረተሰቡ ጥንቃቄዎችን አዘውትሮ እንዲተገብር አሳስበዋል፡፡ ሁለቱም ተቋማት ዕለት ዕለት በሚደረገው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በበሽታው መያዝን የሚወሰን መሆኑን በማስታወስ፣ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ አራቱን የ‹‹መ›› ሕጎች በመተግበር የበሽታውን ሥርጭት ሁሉም እንዲከላከል በጥብቅ አሳስበዋል፡፡

አራቱ የ‹‹መ›› ሕጎች

  • መራራቅ፡ አካላዊ ርቀት መጠበቅ፣
  • መታጠብ፡ እጅን በተደጋጋሚ በውኃና በሳሙና መታጠብ፣
  • መቆየት፡ አስገዳጅ ካልሆነ ቤት ውስጥ መቆየት፣
  • መሸፈን፡ ከቤታችን ወጥተን ስንቀሳቀስ የአፍንና የአፍንጫ መሸፈኛ (የፊት ማስክ) መጠቀም፡፡
spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...