‹‹በሕግም ቢሆን መቀጣት ያለብንን ተቀጥተን እንከፍላለን››
የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን
ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ጋር ሕጋዊ ውል በመፈጸም የኮንስትራክሽን መሣሪያዎችን ያከራዩ ባለሀብቶች፣ ኮርፖሬሽኑ በገባው ውል መሠረት ክፍያ ሊፈጽምላቸው ባለመቻሉ ከባንክ ለወሰዱት ብድር ማስያዣነት ያዋሏቸው ንብረቶቻቸው ለጨረታ እየቀረቡ መሆኑን ተናገሩ፡፡
የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በሰጠው ምላሽ፣ አከራዮቹ ያቀረቡት ቅሬታ ትክክል መሆኑንና ክፍያ ለመፈጸም መረጋገጥ ያለበት እውነታና ቅደም ተከተል ስላለ እንጂ፣ አከራዮቹ ትክክል መሆናቸውንና በሕግም ቢሆን መቀጣት ያለበትን ተቀጥቶ እንደሚከፍል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ዮናስ አያሌው (ኢንጂነር) ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ከ170 በላይ አባላት እንዳሉት የሚናገረው የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች አከራዮች ማኅበር (ኮማአማ) እንደገለጸው፣ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በመላው ኢትዮጵያ በሚሳተፍባቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች የኮንስትራከሽን ማሽነሪዎችን የሚጠቀመው ከባለሀብቶች በሚከራያቸው ማሽኖች ነው፡፡ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጀምሮ በመንገድ ግንባታ፣ በስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ፣ በግድቦችና በመስኖ ሥራዎች ላይ ባለሀብቶች የሚያቀርቧቸውን ግዙፍና መለስተኛ የኮንስትራክሽን ማሽኖች ኮርፖሬሽኑ በሕጋዊ ውል እየተከራየ ሲጠቀም ኖሯል ብሏል፡፡ አሁንም ውል እያደሰ በመጠቀም ላይ መሆኑን ገልጿል፡፡ ምንም እንኳን ባለሀብቶች ክፍያ እየተፈጸመላቸው ማሽነሪዎቹን የሚያቀርብ ቢሆንም፣ ለልማቱ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሚገኙም ማኅበሩ ጠቁሟል፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት ማለትም እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ በተመሳሳይ ሁኔታ መንግሥት ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን ክፍያ ሳይፈጽምላቸው ቆይቶ፣ አዲሱ አመራር በተሻለ ሁኔታ ተንቀሳቅሶ ውዝፍ ክፍያውን የፈጸመ ቢሆንም፣ የ2011 ዓ.ም. የካቲት ወርና የ2012 በጀት ዓመት ሙሉ ክፍያ ለአከራዮች እንዳልተፈጸመላቸው አስረድቷል፡፡
ክፍያው እንዲፈጸምላቸው በተደጋጋሚ ለኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች ያቀረቡት ጥያቄ በቂ ምላሽ ሊያገኝ እንዳልቻለ የገለጸው ማኅበሩ፣ ኮርፖሬሽኑ እስከ ሰኔ መጨረሻ ወር ድረስ መክፈል የነበረበት ከ287 ሚሊዮን ብር በላይ እንዳልከፈለ አስታውቋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በገባው ውል መሠረት ክፍያውን ባለመፈጸሙ ባለሀብቶች ከባንክ በከፍተኛ ወለድ ለማሽነሪዎች ላስያዙት የንብረት ዋስትና ጊዜውን ጠብቀው ክፍያ መፈጸም ባለመቻላቸው፣ ሐራጅ ወጥቶ እየተሸጠባቸው መሆኑን ማኅበሩ ለኮርፖሬሽኑ በጻፈው ደብዳቤ አሳውቋል፡፡ መንግሥት ባለሀብቱ ለአገሩ ያደረገውን አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ በማስገባትና በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችም ከመበተናቸውና ተጨማሪ የሥራ አጥነት ችግር ከመፈጠሩ በፊት፣ ክፍያው ተፈጽሞላቸው ሥራቸውን በገቡት ውል መሠረት በስምምነት እንዲቀጥሉና ለባንክ ያስያዙት ንብረታቸውም ከሐራጅ ሽያጭ እንዲታደግላቸው ጠይቀዋል፡፡ ምንም እንኳን በገቡት ውል መሠረት ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ መብታቸውን በሕግ ማስከበር እንደሚችሉ እምነታቸው ቢሆንም፣ ከኮርፖሬሽኑም ሆነ ከመንግሥት ጋር ያላቸው ግንኙነት መልካም የነበረ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት አዲሱ የኮርፖሬሽኑ አመራር ችግራቸው እውነተኛ መሆኑን ፈትሾና አረጋግጦ ክፍያቸውን እንዲፈጽምላቸው ማኅበሩ ጠይቋል፡፡
የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች አከራዮች ማኅበር ለመንግሥትና ለኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች ያቀረበውን የክፍያ ጥያቄ በሚመለከት፣ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ አያሌው (ኢንጂነር)ን ሪፖርተር አነጋግሯቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ አዲሱ አመራር መቀየሩንና አመራር ሲቀያየር ደግሞ መረጃ ማጣራት አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ተቋሙ ከኮንስትራክሽን ዕቃዎች ኪራይ ጋር በተያያዘ ያልተከፈለ የ2009 እና 2010 በጀት ዓመት ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ዕዳ መክፈሉን ገልጸዋል፡፡ ክፍያ መፈጸም ያለበት በቅደም ተከተል መሆን ስላለበት እንጂ፣ ኮርፖሬሽኑ ያለበት ዕዳ እየተጣራ እንዲከፈልና ከፕሮጀክት ወደ አመራሮች መጥቶና ተጣርቶ የሚከፈልበት ጊዜ እንዳይንዛዛ ተብሎ፣ የፕሮጀክቶች ኃላፊዎች ሥራውን አጣርተው ክፍያ እንዲፈጽሙ ሰርኩላር ማስተላለፋቸውን ዮናስ (ኢንጂነር) ተናግረዋል፡፡
ቀደም ባሉት አመራሮች ጊዜ በተፈጸመ የኮንስትራክሽን ዕቃዎች ኪራይ ጋር በተያያዘ፣ ‹‹አከራይና ተከራይ››ን ያካተተ ብዙ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸው ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ያንን ዓይነት ክስተት እንዳይደገም እያንዳንዱ ጉዳይ እየተጣራ እንዲከፈል እንጂ ተቋሙ ገንዘብ ስለሌለው እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
በአግባቡ በፕሮጀክት ኃላፊዎች ተጣርቶ የቀረበላቸውን እየከፈሉ መሆኑን ጠቁመው፣ በዚህ መንገድ አልፎ ክፍያ ያልተፈጸመለት ካለ እሳቸው ቢሮ ድረስ ቀርቦ ሊያነጋግራቸው እንደሚችልም አክለዋል፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት ከኢትዮጵያ መንገዶች ባሥልጣን ጋር በጋራ ያስተዳድሯቸው፣ የነበሩ ዲስትሪክቶች በአሁኑ ጊዜ መለያየታቸውን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው በሁለቱ ተቋማት መካከል የነበረ የመረጃ መለዋወጥ ሒደትም ጊዜ መውሰዱን ጠቁመው ያም ቢሆን ግን እየከፈሉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አንዳንድ አከራይ ባለሀብቶች ከባንክ ጋር ችግር እንደገጠማቸው ለተቋሙ በማሳወቃቸው፣ ኮሚቴ በማዋቀር የባንክ ዕዳ እንዲከፈልላቸውና ቀሪው ዕዳ ተጣርቶ እንዲከፈላቸው መወሰኑን ተናግረዋል፡፡ አሁንም በዚያ ደረጃ ላይ የደረሰና የተቸገረ አከራይ ካለ ተጣርቶ ገንዘቡ እስከሚከፈለው፣ አጣዳፊ ችግሩን በማስረዳት እንዲከፈልለት ማድረግ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
አንድ ማሽን ያከራየም ሆነ አሥር ማሽን ያራከየ ወይም መቶ ሺሕ ብር ያለውም ሆነ አሥር ሚሊዮን ብር ያለው አከራይ መብታቸው እኩል መሆኑን የተናገሩት ዮናስ (ኢንጂነር)፣ ሁሉም እንደ አመጣጡ እየተጣራ ክፍያ እንደሚፈጸምለት አረጋግጠው የ2012 በጀት ዓመት ክፍያን ግን ወደ ፕሮጀክቶቹ እየሄዱ መቀበል እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ተብሎ ሰርኩላር መተላለፉን አክለዋል፡፡ በየፕሮጀክቱ ያሉ ኃላፊዎች እዚያው አጣርተውና አረጋግጠው ወዲያውኑ እንዲከፍሏቸው በመደረጉ፣ ያለ ምንም መጉላላት መብታቸውን መጠየቅ እንደሚችሉና ተቋሙ በሕግም ቢሆን መቀጣት ያለበትን ተቀጥቶ ክፍያ ሊፈጽምላቸው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ‹‹እነሱ ከሌሉ እኛም የለንም፤›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ የ2012 በጀት ዓመትን እያጣሩ መሆኑንና ይህንንም የሚያደርጉት ደንበኞቻቸውን እንዳያጡ ተጠንቅቀው መሥራት ስላለባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡