Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየዓባይ ውኃ የወደፊት አጠቃቀም ከህዳሴ ግድብ የድርድር አጀንዳ ጋር ተጣምሮ አስገዳጅ ስምምነት...

የዓባይ ውኃ የወደፊት አጠቃቀም ከህዳሴ ግድብ የድርድር አጀንዳ ጋር ተጣምሮ አስገዳጅ ስምምነት እንዲሆን መግባባት ላይ መደረሱ ተሰማ

ቀን:

የኢትዮጵያን የወደፊት በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብት የሚመለከት አጀንዳ ከህዳሴ ግድቡ የውኃ አሞላልና አስተዳደር ድርድር ጋር ተጣምሮ አስገዳጅ ስምምነት እንዲደረስበት፣ የሦስቱ አገሮች መሪዎች መግባባታቸውን የአፍሪካ ኅብረት አስታወቀ።

በአፍሪካ ኅብረት መሪነትና ታዛቢዎች በተገኙበት የኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን መሪዎች  ሐምሌ 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ባደረጉት ድርድር ወቅት ስምምነት እንደተደረሰ፣ ኅብረቱ ዓርብ ሐምሌ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

ሦስቱ አገሮች የህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና የግድቡ አስተዳደርን በተመለከተ ለበርካታ ዓመታት ሲያደርጉት የነበረው ድርድር በወሳኝ ጉዳዮች ለመግባባት ባለመቻላቸው ድርድሩ በተደጋጋሚ ሲቋረጥና ዳግም ሲጀመርእንዲሁም አንዴ ወደ አሜሪካ በኋላም ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት ተመርቶ እንደነበር ይታወሳል።

ለዓመታት ሲደረግ በነበረው በዚህ ድርድር መግባባት ላይ ለመድረስ ካላስቻሉት የልዩነት ነጥቦች መካከል ግብፅ የህዳሴ ግድቡን ድርድር መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያን የወደፊት በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብት የሚገድብ አንቀጽ በድርድሩ የስምምነት ሰነድ እንዲካተት በመፈለጓ እንደሆነ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ ሲገልጽና ይህንኑም ለተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በደብዳቤ ጭምር እንዳስታወቀ ይታወሳል።

ባለፈው ሳምንት በአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ መሪነት የሦስቱ አገሮች መሪዎች ባደረጉት ድርድር፣ የሱዳን መንግሥት ከላይ የተገለጸውን የልዩነት ነጥብ የሚያስታርቅ ሐሳብ ማቅረቡን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል።

የሱዳን መንግሥት ባቀረበው በዚህ አስታራቂ ሐሳብ ዓለም አቀፍ ሕግን መሠረት እስካደረገ ድረስ ኢትዮጵያ ወደፊት በዓባይ ውኃ ላይ የመጠቀም መብቷ ጥያቄ ሊነሳበት እንደማይገባ በመግለጽይኼንን የሚመለከት ጉዳይ የግድቡን ውኃ ሙሌትና አስተዳደር በተመለከተው ድርድር ውስጥ አጀንዳ መሆን የለበትም ማለቱ ተሰምቷል፡፡

የዓባይ ውኃ የወደፊት አጠቃቀምን የተመለከተ ነጥብ የህዳሴ ግድቡን በተመለከተው ድርድር ውስጥ በመሰንቀሩ ድርደሩን ከዳር ማድረስ እንዳልተቻለ የገለጸው የሱዳን መንግሥት፣ ሁለቱ ጉዳዮች ሊለያዩ ይገባል የሚል አቋም ማራመዱን ምንጮች ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በሱዳን በኩል የቀረበውን ይኼንን ነጥብ በመርህ ደረጃ መቀበሏን ለማወቅ የተቻለ ሲሆን፣ በግብፅ በኩል የሱዳንን አስታራቂ ሐሳብ ያለመቀበል ፍላጎት ቢስተዋልም በስተመጨረሻ እያወላዳች መቀበሏን ምንጮች አረጋግጠዋል።

የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (/) ድርድሩ የደረሰበትን ደረጃ በተመለከተ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴው ሐሙስ ሐምሌ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ሪፖርት ያደረጉ ሲሆንእሳቸውም የወደፊት የውኃ አጠቃቀምን የተመለከተ አጀንዳ ከግድቡ ሙሌትና አስተዳደር ድርድር ተነጥሎ ለብቻው እንዲካሄድ መግባባት መቻሉን ገልጸዋል።

በተደረሰው መግባባት መሠረትም የህዳሴ ግድቡ አጠቃላይ የውኃ ሙሌት ደረጃዎችን በተመለከተ ቅድሚያ ተሰጥቶት፣ በአጭር ጊዜ ስምምነት እንዲደረስ መግባባት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የወደፊት ውኃ አጠቃቀምን ጨምሮ ሁሉን አቀፍ አጠቃላይ ስምምነት፣ ከግድቡ ድርድር ተነጥሎ በቀጣይ በሚደረግ ድርድር ስምምነት እንዲደረስበት በመግባባት መወሰኑን አመልክተዋል።

ባለፈው ሳምንት በተደረገው ውይይት ግብፅ የህዳሴ ግድቡን በጋራ የማስተዳደር ጥያቄ አቅርባ እንደነበረ፣ በኢትዮጵያ በኩል ግን ተቀባይነት ባለማግኘቱ ውድቅ መደረጉን ገልጸዋል።

የወደፊት የውኃ አጠቃቀምን በተመለከተ ሁሉን አቀፍ ስምምነት እንዲደረስ፣ ኢትዮጵያ ስታራምደው የነበረ አቋም መሆኑን አክለዋል።

የዓባይን ውኃ የወደፊት የመጠቀም ጉዳይ በማንም መልካም ፈቃድ የሚወሰን አለመሆኑንና በኢትዮጵያ የመጠቀም መብት ላይ የሚመሠረት እንደሆነ የጠቆሙት ሚኒስትሩበዚህ ማዕቀፍ መሠረት በሚደረግ ድርድር ላይ ቅራኔዎች ከተፈጠሩ ሁሉን አቀፍ ወደሆነ የውኃ ክፍፍል ድርድር እንደሚገባ አስረድተዋል።

የአፍሪካ ኅብረት በበኩሉ በሦስቱ አገሮች መሪዎች የተደረገውን ድርድርና የተደረሰውን መግባባት አስመልክቶ ዓርብ ሐምሌ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ አገሮቹ የህዳሴ ግድቡን አጠቃላይ የሙሌት ደረጃዎችን በተመለከተ አስገዳጅ ስምምነት ላይ እንደደረሱ፣ ይህ ስምምነትም ከግደቡ በላይ ወደፊት የሚኖር በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብትን ያካተተ እንደሚሆን መግባባት መደረሱን አስታውቋል።

መግለጫው አክሎም ኅብረቱ የሚመራውን ይኼንን ድርድር ሊያስተጓጉል፣ ወይም ተፅዕኖ ሊያሳድር የሚችል መግለጫ ከመስጠት አገሮቹ እንዲቆጠቡም አሳስቧል።

ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የሪፖርተር ምንጮች በበኩላቸው የግድቡ አጠቃላይ የውኃ ሙሌት የኢትዮጵያን የወደፊት በዓባይ ውኃው ከመጠቀም መብት ጋር ተነጥሎ እንዲታይ ስምምነት መደረሱ መልካም ቢሆንምአሁን የተደረሰው ስምምነትም የኢትዮጵያን የወደፊት በውኃው የመጠቀም መብት እንደማይገድብ ማረጋገጥ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው አሳስበዋል።

ለዚህ የሚያነሱት ምክንያትም በህዳሴ ግድቡ ድርድር ላይ ሲነሱ የነበሩና አሁንም ያልተፈቱ እንደ የተራዘመ የድርቅ ወቅትና የግድቡ አስተዳደርን የተመለከቱ ነጥቦች የልዩነት ምንጭ የሆኑበት ምክንያት፣ የኢትዮጵያን የወደፊት የመጠቀም መብት የሚነኩ በመሆናቸው ነው።

የተራዘመ የድርቅ ወቅት ማለት የዓባይ ውኃ ዓመታዊ ተፈጥሯዊ ፍሰት ከረዥም ዓመታት አማካይ መጠኑ ለተከታታይ ዓመታት ከቀነሰየተራዘመ የድርቅ ወቅት ተደርጎ እንዲተረጎም በግብፅናሱዳን በኩል አቋም የተያዘበት እንደሆነ ምንጮች ይገልጻሉ።

የዓባይ ዓመታዊ የተፈጥሮ የፍሰት መጠን ከአማካይ መጠኑ ለተከታታይ ዓመታት የቀነሰው በዝናብ እጥረትም ሆነ ኢትዮጵያ በላይኛው የተፋሰሱ አካባቢ በምታካሂደው ልማትም ቢሆን፣ የተራዘመ የድርቅ ወቅት የሚል ትርጓሜ እንዲሰጠው ሁለቱ አገሮች ፍላጎት እንዳላቸውና ይህ ሁኔታ በሚከሰትበት ወቅት ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድቡ ከያዘችው ውኃ ላይ፣ ለታችኞቹ አገሮች የድርቅ ወቅት ማካካሻ እንድትለቅ ግዴታ ለማስገባት የሚደረግ ጥረት መሆኑን ምንጮች አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ይኼንን ትቀበላለች ማለት ከህዳሴ ግድቡ በላይ ባለው የተፋሰሱ አካል ላይ ተጨማሪ ልማት እንዳታካሂድእንዲሁም በላይኛው የተፋሰሱ አካል ላይ ልማት ካካሄደች የዓባይ ፍሰት ከአማካይ መጠኑ ለተከታታይ ዓመታት ስለሚቀንስ፣ የተራዘመ ድርቅ ነው ተብሎ በህዳሴ ግድቡ ከያዘችው ውኃ እንድትለቅና ግድቡ መቼም ቢሆን በሙሉ አቅሙ እንዳይሠራ ለማድረግ የተሸረበ ሴራ መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም ወደፊት በውኃው የመጠቀም መብት ከላይ በቀረበው መንገድ ቴክኒካዊ ሽፋን ይዞ በህዳሴ ግድቡ ድርድር ውስጥ ዳግም ሊገባ የሚችል በመሆኑየኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አሁንም ነገሩን በጥንቃቄ ማየትና መከታተል እንዳለበት አሳስበዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...