መገናኛ ብዙኃን ሙያዊ ሥነ ምግባራቸውንና ባህሪያቸውን በመተው በግልጽ የጠራራ ፀሐይ ወገን ወገኑ ላይ ጦርነት የሚቀሰቅሱበትና የጦርነት ዓውድ የሚሆኑበት ደረጃ ላይ መደረሱን፣ የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል አስታወቁ፡፡
‹‹ሚዲያው ራሱን ካላከመ ሌላ የሚያክመው ፖለቲከኛ አያገኘም፡፡ ለራሱ ሲል ራሱን ማከም ያለበት ራሱ ነው፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ሚኒስትሯ ይህንን ማሳሰቢያ የሰጡት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣንና ጀስቲስ ፎር ኦል ፒ ኤፍ ኢትዮጵያ በጋራ ባዘጋጁት፣ የጥላቻ ንግግርን አስመልክቶ ዓርብ ሐምሌ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡
የመገናኛ ብዙኃን አራተኛ የመንግሥት አካል ናቸው የሚለውን ሐሳብ በኢትዮጵያ ያሉ መገናኛ ብዙኃን የተረዱት እንደማይመስላቸው የገለጹት ወ/ሮ ሙፈሪያት፣ ይህን ድርሻቸውን ለመወጣት ሁሉም የመገናኛ ብዙኃን ከወገንተኝነት ፀድተው የሙያቸውን ሥነ ምግባር በማክበር እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከዚህ አንፃር በቅጡ የተገራና የተቃኘ የመገናኛ ብዙኃን በእርግጥም አገር መገንቢያና ዴሞክራሲ ማምጫ መሣሪያ ሊሆን እንደሚል በመግለጽ፣ የታመመና የተቸገረ ዕለት ደግሞ የዚህ ተቃራኒ ተግባር ሊፈጽም እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ ‹‹ሚዲያው የመጀመርያው አማራጭን ተከትሎ መሄድ ከቻለ አገር በመገንባትና ትውልድ በማነፅ የማይተካ ሚና መጫወት ይችላል፡፡ ነገር ግን በግሌ ሚዲያው ተቃንቶ አልበቀለም የሚል አመለካከት አለኝ፤›› ሲሉ፣ የአገሪቱ ሚዲያ ተገርቶ አለመብቀሉን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም መሠረት በአሁኑ ጊዜ ሚዲያው ራሱ ሰክኖ ኅብረተሰቡን የማስከን ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት በማሳሰብ፣ መንግሥትም ዘርፉን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህ ለግማሽ ቀን በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ በርካታ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ፖለቲከኞችና ታዋቂ ግለሰቦች ታድመውበት የነበረ ሲሆን፣ በዕለቱም በምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) አማካይነት የመናገር ነፃነትና ኃላፊነት በኢትዮጵያ፣ እንዲሁም በአንጋፋው ጋዜጠኛ ንጉሴ ተፈራ (ዶ/ር) አማካይነት የኢትዮጵያ ሚዲያና የወቅቱ ችግሮች የሚሉ ለውይይት የሚሆኑ ሐሳቦች ቀርበዋል፡፡