Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትሊግ ካምፓኒው 30 ሚሊዮን ብር በጀት እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል

ሊግ ካምፓኒው 30 ሚሊዮን ብር በጀት እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል

ቀን:

ፋሲል ከነማና መቐለ ሰብዓ እንደርታ በቀጣዩ ዓመት በአኅጉራዊ ውድድር ይሳተፉ ይሆን?

ዓምና የተቋቋመው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሊግ ካምፓኒ ለሚቀጥለው የውድድር ዓመት 30 ሚሊዮን ብር በጀት ለጠቅላላ ጉባዔ አቅርቦ ለማፀደቅ ውሳኔ ማሳለፉ ታወቀ፡፡ ሊግ ካምፓኒው በተጨማሪም የፋሲል ከተማ እግር ኳስ ክለብ  አኅጉራዊ ተሳትፎን በሚመለከት ለጻፈው ደብዳቤ ከውይይት ያለፈ ምንም ዓይነት ውሳኔ እንዳላሳለፈ እየተነገረ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ፋሲል ከተማና መቐለ ሰብዓ እንደርታ በአኅጉራዊ መድረክ የተሳትፎ ማረጋገጫ ማግኘታቸው የሚናገሩ አሉ፡፡

ፕሪሚየር ሊግ አሁን የሚጠራበትን ስያሜ ይዞ መካሄድ ከጀመረ ከሁለት አሥርታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ይሁንና ፕሪሚየር ሊጉ ስያሜውንና ዕድሜውን የሚመጥን ዕድገት እንደሌለው ይተቻል፡፡

ፕሪሚየር ሊጉ ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ዕድገት በሚል ብቻ ጥናት ሳይደረግ ውድድር መጀመሩ ለዕድገቱ መቀጨጭ የራሱን ድርሻ ማበርከቱ እንዳልቀረ የሚናገሩ አልጠፉም፡፡ ለዚህ በትልቁ የሚጠቀሰው ፕሪሚየር ሊጉን ጨምሮ 98 በመቶ የአገሪቱ ክለቦች በጀታቸው ሙሉ በሙሉ ከመንግሥት ቋት በመሆኑ እግር ኳሱ ገበያ ተኮር እንዳይሆን አድርጎታል፡፡

እግር ኳሱ በተለይም ፕሪሚየር ሊጉ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በብሔራዊ ፌዴሬሽንና ክለቦች የጋራ ጥረት ሊጉ ራሱን ችሎ መንቀሳቀስ ይችል ዘንድ በሊግ ካምፓኒ እንዲመራ ከስምምነት መድረሳቸው አይዘነጋም፡፡

ሊግ ካምፓኒው 30 ሚሊዮን ብር በጀት እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል

የሊግ ካምፓኒው አመራሮችን ውክልና በሚመለከት ለጊዜው በፕሪሚየር ሊጉ የሚሳተፉ ክለቦች ከሚገኙባቸው ክልሎች የተገኙ ናቸው፡፡ እነሱም ከአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ቡና የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ፣ ከኦሮሚያ አቶ አምበሴ መገርሳ፣ ከአማራ አቶ እሸቱ ቢያድጉ፣ ከደቡብ ክለቦቹ ብዙ በመሆናቸው ሁለት ተወካይ እንዲኖራቸው በተደረሰው ስምምነት መሠረት አቶ መንግሥቱ ቴሳቦና አቶ አሰፋ ኦሲሶ፣ ከትግራይ ከሳቴ (ዶ/ር) እና ከድሬዳዋ አቶ አምበሳው አውግቸው ናቸው፡፡

ጊዜው በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከአራት ሰው በላይ መሰብሰብ በአዋጅ የተከለከለበት ወቅት ቢሆንም፣ ግን ደግሞ የፕሪሚር ሊጉን ቀጣይ ዓመት በጀትና ሌሎች ከውድድርና ደንብ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን መመልከት የግድ በማለቱ የሊግ ካምፓኒው አመራሮች ባለፈው ሐሙስ ሐምሌ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ተገናኝተው ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡

አመራሮቹ ከተወያዩባቸው ጉዳዮች መካከል ሊግ ካምፓኒው በ2013 ውድድር ዓመት ለሚያከናውናቸው ዕቅዶች ማስፈጸሚያ የሚውለውን የ30 ሚሊዮን ብር በጀት በጠቅላላ ጉባዔ ለማፀደቅ መስማማታቸው ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያሳያል፡፡ በተጨማሪም የሊጉን የጥራት ደረጃ ከመጠበቅ ጀምሮ ክለቦቹን ለተለያዩ ችግሮችና አለመግባባቶች ሲዳርጉ ቆይተዋል በሚል ማሻሻያና ማስተካከያ የሚያስፈልጋቸው የውድድር ደንብና መመርያዎች ላይ ውይይት አድርገው የመፍትሔ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

 በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ተከትሎ እግር ኳሳዊ የሆኑ  ውድድሮችና እንቅስቃሴዎች የተከለከሉበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የሚቀጥለው ዓመት ውድድር እንዴት ይካሄድ የሚለውን አስመልክቶ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተለያዩ አስተያየቶች በመደመጥ ላይ ይገኛሉ፡፡

ከሚደመጡ አስተያየቶች የወረርሽኙ መተላለፊያ መንገድ ሰዎች ከቦታ ቦታ የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች ተከትሎ የሚፈጠሩ ግንኙነቶች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህን ግንኙነቶችና ንክኪዎች መቀነስ የሚቻለው ደግሞ የሰዎችን ጉዞና መሰል እንቅስቃሴዎች መግታት አንዱ የመከላከያ መንገድ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግና በተዋረድ የሚገኙ ቡድኖች የውድድሮቻቸው አካሄድ (ፎርማት) ለወረርሽኙ መስፋፋት የተመቻቸ በመሆኑ በተቻለ መጠን ችግሩን መከላከል በሚቻልበት አግባብ የውድድሩን ዓይነትና አካሄድ (ፎርማት) እንደገና ማደራጀትና ማዋቀር ያስፈልጋል የሚለው ደግሞ ሌላው ነው፡፡

የውድድሩን አካሄድ በሚመለከት የሊግ ካምፓኒው አመራሮች ያላቸው አቋም ምን እንደሆነ በነበረው ውይይት ማንሳት አለማንሳታቸውን ግልጽ ባያደርጉትም፣ ሊጉ ቀድሞ በነበረው የውድድር አካሄድ መቀጠል እንደሌለበት አቋም የያዙ እንዳሉ ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ አመራሮቹ በዚህ ጉዳይ ያላቸውን አቋም ሲናገሩ፣ ‹‹ሊጉ ቀድሞ በነበረው ተዟዙሮ ጨዋታ መቀጠል የለበትም ስንል በተዟዙሮ ጨዋታ ምክንያት ማለትም ለትራንስፖርት፣ ለሆቴልና ለአበል እየተባለ የሚባክነውን ገንዘብ ከብክነት ማዳን ብቻ ሳይሆን በዚሁ የውድድር አካሄድ ውድቀቱን እያፋጠነ ያለውን እግር ኳስ ማዳን ስላለብን ጭምር ነው፤›› በማለት አቋም የያዙ መኖራቸው ታውቋል፡፡

ከሊግ ካምፓኒው አመራሮች ውጭ የሚገኙ የእግር ኳስ ሙያተኞች በበኩላቸው፣ ቀድሞ የነበረው የአገሪቱ የሊግ አካሄድ መለወጥ እንዳለበት የሚያምኑ በርካታ ናቸው፡፡ ምክንያቱን አስመልክቶ ሙያተኞቹ ውድድሩ አካባቢያዊ ቢደረግ በተለይ እንደ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ሱማሌ በመሳሰሉት የሚኖሩ ታዳጊ ወጣቶች እግር ኳሱን ስለሚያዘወትሩ በቀጣይ አገርና ሕዝብን የሚወክል ጠንካራ እግር ኳስና ብሔራዊ ቡድን ማፍራት የሚያስችል ዕድል ይኖራል ብለው ያምናሉ፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ አሁን ላይ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት የክልል ወጣቶችም ተመሳሳይ ዕድል ይፈጥርላቸዋል ሲሉ ሙያተኞቹ ይከራከራሉ፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2012 ውድድር ዓመት በኮቪድ 19 ምክንያት መቋረጡን ተከትሎ፣ በ‹‹አሸናፊ፣ ወራጅና ወጪ በ2013 ውድድር ዓመት በአፍሪካ መድረክ የሚሳተፍ ቡድን የለም፤›› በማለት ሊግ ካምፓኒው ያሳለፈውን ውሳኔ፣ በተለይ የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር እስከሚቋረጥ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ላይ የነበሩት ፋሲል ከተማና መቐለ ሰብዓ እንደርታ በአኅጉራዊ መድረክ የመሳተፍ ዕድል ሊኖረን ይገባል በሚል ውሳኔውን መቃወማቸው አይዘነጋም፡፡

የፋሲል ከተማ እግር ኳስ ክለብ ለሊግ ካምፓኒው ውሳኔው ትክክለኛና ተገቢ እንዳልሆነ ጉዳዩን በደብዳቤ ሲገልጽ ቢቆይም፣ ምንም ዓይነት ምላሽ ሳያገኝ ቆይቷል፡፡ የሊግ ካምፓኒው ባደረገው ስብሰባ ላይ ፋሲል ከተማ ያስገባው ደብዳቤ ቢታይም ምንም ዓይነት መፍትሔ ሳይሰጠው ቀርቷል መባሉ ተሰምቷል፡፡

በሌላ በኩል ሁለቱ ክለቦች ፋሲል ከነማና መቐለ ሰብዓ እንደርታ በአኅጉራዊ መድረክ ለአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግና ለአፍሪካ ከለቦች ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመሳተፍ ዕድል ይኖራቸዋል መባሉ ተሰምቷል፡፡ የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ይህንኑ በድረ ገጹ አስፍሮታል፡፡ ክለቡ ያሰፈረውን መረጃ በሚመለከት ሊግ ካምፓኒው የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...