Friday, October 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ይድረስ ለሪፖርተርላለፈው ክረምት ቤት ይሠራ ይሆን?

  ላለፈው ክረምት ቤት ይሠራ ይሆን?

  ቀን:

  የሪፖርተር ጋዜጣ የሰኔ 28 የእሑድ ዕትም በአጋጣሚ ነበር ያነበብኩት፡፡ አንድ ወዳጄ ስልክ ደውሎ መሥሪያ ቤታችሁን የሚመለከት ጽሑፍ ወጥቶ አየሁት እንዴት ነው ነገሩ ችግር አለ እንዴ? ብሎ ስለጠየቀኝ፣ በጉዳዩ ላይ ሐሳብ ተለዋውጠን ስልኩን እንደዘጋሁ ጋዜጣውን መፈለግ ጀመርኩ፡፡ እናም አነበብኩት ከርዕሱ ጀምሮ የጸሐፊው ሐሳብ ግራ የሚያጋባ ነበር ‹‹አልለወጥም ወይስ ለውጡን አልደግፍም›› ይላል፡፡ ከዚያም ስለ ዓለማዊው ወቅታዊ ሁኔታ መነሻ ያደርግና ስለአገራችን ፖለቲካ፣ የለውጥ ሒደት ያወራል፡፡ በመጨረሻም ስለኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን እንቶፈንቶ ይደሰኩራል፡፡

  ጸሐፊው (በብዕር ስማቸው ሞቱማ) ምን ለመጻፍ እንደፈለጉ ግልጽ አይደለም፡፡ ከምናብ ይነሱና የፈለጉትን መልዕክት በወጉ ሳያስተላልፉ፣ አሉባልታ ውስጥ ገብተው ቁምነገር ሳይነግሩን ጽሑፉን ያጠቃልላሉ፡፡ ሲጀመር ጸሐፊው የመሥሪያ ቤቱ ባልደረባ ሆነው ሳለ ወሬ ነጋሪዎች ሹክ እንዳሏቸውና የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን አመራር፣ ማኔጅመንት ያለበትን ደረጃ በራሳቸው ውስን ዕውቀት ለመዳሰስ ይሞክራሉ፡፡ ጸሐፊው ቀና ቢሆኑና የተቋሙ ችግሮች እንዲፈቱ ፍላጎት ቢኖራቸው ኖሮ ራሳቸውን ባልደበቁ ነበር፡፡ የተነሱበት ሐሳብ ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን አምናም በዚሁ ወቅት በዚሁ ሪፖርተር ጋዜጣና በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ይህንኑ ሐሳብ ሲነግሩን ነበር፡፡ ምናልባት ክረምት ላይ ጸሐፊው የመጻፍ አባዜያቸው ይነሳ እንደሆነ አላውቅም፡፡ በእርግጥ ጸሐፊው ማን እንደሆኑ ባውቃቸውም ነፃነታቸውን ተጋፍቼ ስማቸውን በዚህ ጽሑፍ መግለጽ አልፈልግም፡፡

  የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከተመሠረተ አምስት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ወራት ቀርተውታል፡፡ የአመራርና ሠራተኞች ምደባ ከተደረገ ደግሞ እነሆ ሦስት ዓመት ሊደፍን ምንም አልቀረው፡፡ ጸሐፊውም እንዲሁ ማስተዋል ከተሳናቸው ሦስተኛ ዓመቱን ያዘ ማለት ነው፡፡

  አንድ ተቋም ውጤታማ የሚሆነው በማኔጅመንቱና በሠራተኛው ያላሰለሰ ጥረት ሊሆን ይገባዋል፡፡ ጸሐፊውም እንደሚሉት ደካማ አመራር ካለ ተቋሙንና ሠራተኛውን ወደ ውድቀት ይመራዋል፡፡ እዚህ ላይ የማኔጅመንቱ አባላት ደግሞ በግልም ይሁን በቡድን ተጠያቂ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ የአሁኑ ጸሐፊያችን (ሞቱማ) ደግሞ የማኔጅመንት አባል ሆነው የሚሠሩ እንደመሆናቸው መጠን አሉ ያሉትን ችግር ለማኔጅመንት አቅርበው የመፍትሔ አካል መሆን ሲገባቸው፣ እንጀራ የሚበሉበትን ተቋም ከአንዴም ሁለት ጊዜ በአደባባይ ሲተቹ መታየቱ ትዝብት ላይ የሚጥላቸው ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ጸሐፊው አሁን ያነሱት የአመራርና የሠራተኛ ምደባ ላይ የነበሩ ችግሮች በ2011 በጀት ዓመት ማጠቃለያ ግምገማ ላይ ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፣ በአጠቃላይ በሠራተኛና አመራር ግልጽ ግንዛቤ ተወስዶ መታረም የሚገባቸው ጉዳዮች እንዲታረሙ ተደርጓል፡፡ አመራሩና ሠራተኛው ኮርፖሬሽኑን ለማሳደግ በሚያስችሉ ተግባራት ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሠራ በመግባባት እልባት ያገኘ መሆኑን ላስታውሳቸው እወዳለሁ፡፡

  በእርግጥ ጸሐፊው በአመራር ምደባ ወቅት የአንድ ዘርፍ ኃላፊ ለመሆን ጓጉተው ብርቱ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም፣ ሳይሳካላቸው በመቅረቱ በወቅቱ ቅሬታ አቅርበው ቅሬታው ተቀባይነት አላገኘም፡፡ በወቅቱ የነበሩትን የኦፕሬሽን ኃላፊ ጠምደው መያዛቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡ እሳቸው (የኦፕሬሽን ኃላፊ) በድክመታቸው ከሥራ  ደረጃቸው ዝቅ ሲሉ ጸሐፊው ደግሞ ጮቤ መርገጣቸውን እናውቃለን፡፡ በእርግጥ ደካማ የሥራ መሪ ከድክመቱ ካልወጣ ወደጎን ማድረጉ ተገቢ ነው፡፡ የሥራ አመራር ቦርዱም እንደዚህ ደካማ ኃፊዎችን ገምግሞ ከኃላፊነት ሲያነሳ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ ደካማ አመራርን ገምግሞ ከኃላፊነት ያነሳ ቦርድ ደግሞ መልሶ ደካማ አመራር ይመድባል ማለት ግን ተገቢነት የለውም፡፡ ለማንኛውም የኮርፖሬሽኑን አመራር (ከፍተኛ አመራሮች) የሚመድበው ቦርድ በመሆኑ ጸሐፊው የቦርዱን ሥራ ተክተው ለመሥራት መዳዳታቸው፣ የተሿሚዎችን የጀርባ ታሪክ እያነፈነፉ (እውነትም ይሁን ሐሰት)  ለትችት መሽቀዳደም ተቋሙን ለመገንባት ሳይሆን ለማፍረስ ታልሞ እየተሠራ መሆኑን ነው የሚያሳየው፡፡ ጸሐፊው ይህን ያህል ለጋዜጣ የሚሆን የሐሰት ወሬ ከሚነዙ ቁጭ ብለው ተቋሙ የሚያድግበትን ስልት ቢነድፉ፣ በዘርፋቸው ያለውን ተልዕኮ ለማስፈጸም የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ደፋ ቀና ቢሉ፣ ለተቋሙም ለህሊናቸውም መልካም ባደረጉ ነበር፡፡ ግና ያለፈውን ክረምት እያስታወሱ ቤት በተሠራ ነበር ቢሉ ከነበር አያልፍም፣ ይልቁኑ አሁንም ክረምት ነውና ከርሞም ተመልሶ ይመጣልና ቁጭ ብሎ መቆዘሙን ትተው በእጃቸው ባለው ክረምት ቢጠቀሙ ስል ምክሬን እለግሳለሁ፡፡ አዲሱ የኮርፖሬሽኑ አመራሮችም እንደ (ሞቱማ) ያሉ በተቋሙ ተሰግስገው አሉባልታን እንደ ሥራ ቆጥረው በሚኖሩ ሥራ ፈቶች በሚጽፉት አሉባልታ ሳይረበሹ፣ አሁን ተቋሙን ለመለወጥ እያደረጉ ያለውን ጥረት ጠንክረው ሊገፉበት ይገባል እላለሁ፡፡ እነ ሞቱማ ድክመታቸውን ለመሸፈን ጠንካራ አመራር እንዲመጣ አይፈልጉም፡፡ ሠርቶ የሚያሠራ አመራር ሲያዩ ይደነግጣሉ ይሸበራሉ፡፡ ቀድመው አመራሩን ውዥንብር ውስጥ በመክተት የእነሱ ድክመት እንዳይፈተሽ ይከላከላሉ፡፡ ስለዚህ እነሱ አመላቸው ነውና ተዋቸው እላለሁ፡፡

  በመጨረሻም ለጸሐፊው አንድ ጥያቄ ላቅርብ፡፡ እርስዎ እንዳሉት መረጃውን ያገኙት ከተቋሙ ባልደረቦች ከሆነና እርስዎ የመሥሪያ ቤቱ ባልደረባ ካልሆኑ ምነው በአገሪቱ ስንት አዘቅት ውስጥ የገቡ ተቋማት እያሉ ይህን ለደሃው ሕዝብ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርትና አገልግሎት እያቀረበ ያለ ኮርፖሬሽን መልካም ገጽታ ጥላሸት ለመቀባት መሞከር ለምን ፈለጉ? የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ አንድ ነገር ሊያሳስብዎ ይወዳል፣ እርስዎ የተቋሙ ባልደረባና የማኔጅመንት አባል ሆነው ለአገርዎና ለተቋምዎ ምን አስተዋጽኦ አበረከቱ? እስኪ እርስዎ ዓይን ውስጥ ያለውን ምሰሶ ከዓይንዎ ያውጡና የኮርፖሬሽኑን ጉድፍ ይመልከቱ፡፡ ያን ጊዜ በእርግጠኝነት ንስሃ ይገባሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ መልካም የመለወጥ ዘመን ይሁንልዎ!

  (ሽንኩርት፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን)

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img