Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉነገን ለማሳመር ከትናንት መማር ይኖርብናል!

ነገን ለማሳመር ከትናንት መማር ይኖርብናል!

ቀን:

በመርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ

ወቅታዊው የሀገራችን የፖለቲካ ትኩሳት ተባብሶ ከዕለት ወደ ዕለት እየተወሳሰበ የሄደ ይመስላል፡፡ ለአራዊት አስተዳደር እንኳ ይመጥናል ተብሎ የማይታመነው አስቀያሚ የብሔር ፖለቲካችን ጡዘት የመጨረሻው ጠርዝ ላይ ደርሶ፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ለማፈራረስ በጋራ ምለውና ተገዝተው በተነሳሱ እኩያን ሟርተኞች አስቀድሞ የተተነበየውን ያህል ባይሆንም፣ የአንዲት እናት አገር ውድና ብርቅዬ ልጆች ከዚህ በቀደመው ዘመናችን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በዘር፣ በቋንቋና በትውልድ ሐረግ እየተቧደንን እርስ በርሳችን ያላግባብ ወደ መንቆራቆሱ ናአንዳንዴም በቡጢ ወደ መቧቀሱ ማምራት ከጀመርን ትንሽ ሰነባብተናል፡፡

እነሆ የመላ ወገኖቻችንን ልብ ክፉኛ በሚያደማ ሁኔታ ‘ማነው ባለሳምንት?’ እየተባለ ሰዎች በማንነታቸውና በሚከተሉት እምነት እየተመረጡ፣ ሲጠቁና አረመኔያዊ የጭካኔ በትር በላያቸው ላይ እያረፈ ሕይወታቸው በከንቱ ሲያልፍና አካላቸው ሲጎዳ እንደ ዋዛ እያየንና እየታዘብን ነው፡፡

ዜጎች ዕድሜ ዘመናቸውን ሙሉ በላባቸው ጥረውና ግረው ያፈሩት አንጡራ ሀብትና ንብረት ሳይቀር በግፈኞች ዕርምጃ በጠራራ ፀሐይ እየወደመ ዶግ አመድ ሲሆን ማየትና መስማት እየተለመደ መጥቷል፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ ሥልጡን ሕዝብ ዘግይተን ከታጠቅነው ዘመናዊ ሕግና ሥርዓት ባሻገር በእጅጉ የበለፀገ፣ የዳበረና አንደኛው ማኅበረ-ሰብ ከሌላኛው ጋር በጥብቅ የሚተሳሰርበት አቃፊ ወግ፣ ባህልና እሴት ያልነበረን ይመስል ለምን በዚህ ደረጃ እስከ መጨካከን እንደደረስንና እርስ በርስ መጠፋፋት እንዳማረን በውል መጤን አለበት፡፡  ይልቁንም ቀስ በቀስ እየገባንበት ካለው አደገኛ የምስቅልቅል አዘቅት በአፋጣኝ ለመውጣት ቆም ብለን ማሰብና በየሠፈሩ ሸንጎ እየተቀመጥን፣ የምራችንን በመምከር እንደ ገና የምናንሰራራባቸውን ብልኃቶች ማፈላለግና ወደ ቀደሙ የተከበሩ እሴቶች ማማችን መመለስ ይኖርብናል፡፡

የሀጫሉ ግድያ አዲስ የሽብር ማቀጣጠያ ሰበብ ወይስ የተራዘመው መከራችን ማክተሚያ?

ኢትዮጵያና ወርኃ ሰኔ እንደተኳረፉ ቀጥለዋል፡፡ ለክረምቱ የእርሻ ሥራችን ዘወትር ተዘጋጅተን በተስፋ የምንጠብቀው እርጥቡ የሰኔ ወር ለምን ከተደጋጋሚ ረብሻ ጋር መላልሶ እንደሚጎበኘን ፈጽሞ ግልጽ አይደለም፡፡ ፈጣሪ ራሱ በዚሁ ‘በቃችሁ’ ይበለን እንጂ እንዳለፉት አቻዎቹ ሁሉ የዘንድሮውን ሰኔም ቢሆን የተቀበልነው በሌላ የመከራ አዙሪት መሆኑ ያበሳጫል፡፡ የአገራችንን መፃኢ ዕድል ለማጨለም ቆርጠው የተነሱና አዘውትረው የሚደክሙ ኃይሎች በወሰዱት ሌላ የተቀነባበረ ዕርምጃ ሰላማችን ተናግቷል፣ ህልውናችን ተፈትኗል፡፡

በመሆኑም ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽቱ ላይ ከመዲናችን የተሠራጨው አስደንጋጭ ዜና ልብ ሰባሪና ተስፋ ቀባሪ ነበር፡፡ ገላን ኮንደሚኒየም በተባለው የከተማይቱ መንደር ወጣቱ የኪነ ጥበብ ባለሙያ ሀጫሉ ሁንዴሳ እስካሁን ድረስ ማንነታቸው በውል ካልታወቀ ወገኖች በተተኮሰ ጥይት ገና በለጋ እድሜው ውድ ሕይወቱን ለመነጠቅ ተረኛው ሰለባ ሆኗል፡፡

በእርግጥ ይህንን አሰቃቂ የወንጀል ድርጊት ማን እንደፈጸመው ከእነ ምክንያቱ  ፖሊስ ገና በማጣራት ላይ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ያም ሆኖ የእነ ኢንጂነር ስመኘው በቀለን አሟሟት ዛሬም ድረስ ቢሆን በቅጡ አናውቀውምና በዚህ ረገድ ያለብን ውስንነት ተቀርፎ ለተልዕኮው የተሰማሩት መርማሪ ፖሊሶቻችንና ሕግ አስከባሪዎቻችን የሀጫሉ ሁንዴሳን ደም አፍስሰውና አርቲስቱን ያላንዳች ርህራሔ በልተው የተሰወሩትን ነፍሰ ገዳዮች ማንነት፣ ለይተውና ከኋላቸው የዘረጉት መረብ ቢኖር ይህንኑ በረቀቀ የክትትልና የምርመራ ዘዴ በጣጥሰው ውጤቱን በተፋጠነ ሁኔታ ለፍርድ እንዲያቀርቡልን በጉጉት እንጠብቃለን፡፡

ታዲያ ይህንን የምንለው በስራው ለተጠመዱት አካላት የሁላችንም ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ሳንዘነጋ መሆን አለበት፡፡ ያለሕብረተ-ሰቡ ንቁ ተሳትፎና ተባባሪነት በፖሊስ የተናጠል እንቅስቃሴ ብቻ የሚጣራ ወንጀልም ሆነ በአደባባይ ተይዞና በጥፋተኝነት ተፈርዶበት የሚቀጣ ሰው አይኖርምና፡፡

እንዲያም ሆኖ ከወጣቱ የኪነ-ጥበብ ባለሙያ የግፍ ግድያ በስተጀርባ በአገሪቱ ህልውናም ሆነ በዜጎቿና በማኅበረሰቦቿ ዘመን ተሻጋሪ አብሮነት ላይ ምን ዓይነት ሴራ በህቡዕ ተሸርቦ፣ ወይም ተደግሶ እንደነበር ለመገመት በመካሄድ ላይ ያለውን የወንጀል ምርመራ ውጤት የግድ መጠበቅ የሚያስፈልገን አይመስልም፡፡

የቀብሩ ሥነ ሥርዓት እስከ ተፈጸመበት ዕለት ድረስ ባሉት ተከታዮቹ ቀናት ከሟች ቤተሰቦች ምርጫና ፍላጎት ባፈነገጠ አኳኋን ወደ ትውልድ ሥፍራው በመጓጓዝ ላይ ሳለ፣ የሰለባውን አስከሬን  በኃይል ነጥቆ በአስከፊ ሁኔታ ከማንገላታት አንስቶ ቡራዩ ላይ የኦሮሞ ወጣቶችን ስሜት በመኮርኮር ለአመፅ በማነሳሳትና በሚዲያ ጭምር ታግዞ በስፋት በመቀስቀስ በተጠቂነት ስሜት ወደ አደባባይ ወጥተው ጉዳዩ በማይመለከታቸው የሌሎች ብሔር፣ ብሔረሰቦች አባላት በሆኑ ንፁኃን ወገኖቻቸው ሕይወትና ንብረት ላይ ያልታሰበ የበቀል ዕርምጃ እንዲወስዱና አዲስ አበባን በሚያክል ግዙፍ ከተማ ውስጥ የለየለት ሁከትና የእርስ በርስ ብጥብጥ እንዲስፋፋ ተሞክሮ የነበረው አደገኛና ኃላፊነት የጎደለው የወሮበሎች ኦፐሬሽን የዚህ እኩይ ሴራ ዓይነተኛ ማሳያ ነው፡፡

ከሰኔ 22 ሌሊት ጀምሮ ባሉት በእነዚሁ ቀናት እንደ ዝዋይ፣ ሻሸመኔ፣ አሳሳ፣ አርሲ ነገሌና በመሳሰሉት የኦሮሚያ ከተሞች ውስጥ በሚዲያ ጥሪ ተቀስቅሰው በጅምላ በወጡ ወራሪዎች ዕርምጃ በተከታታይ የተፈጸመውን ሰብዓዊ ዕልቂት፣ የእሳት ቃጠሎ፣ የንብረት ዘረፋና የተቋማት ውድመትማ ቤቱ ይቁጠረው ማለቱ ይሻላል፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ጽንፍ በረገጡትና ራሳቸውን አደባባይ ላይ አስጥተው በዕብሪት ሲደነፉም ሆነ በየደረሱበት ፈር የለቀቁና መርዘኛ የጥላቻ ዲስኩሮቻቸውን ያለ ገደብ ሲረጩ እንደ ከረሙ ጠንቅቀን በምናውቃቸው በእነዚያ አክራሪ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ይመራና ይዘወር እንደነበር በስፋት የሚታመነው ይህ ነውረኛና ሕገወጥ እንቅስቃሴ የመጨረሻ ግቡ፣ አገራዊ ትርምስ በመፍጠርና ኅብረ ብሔራዊነትን ወደ ጎን አሽቀንጥሮ በመጣል በሥልጣን ላይ ያለውን ፌደራላዊ መንግሥት ለአንድ ብሔር የቆመ በሚመስል ጠባብ ቡድን መዳፍ ሥር ጠቅሎ ማስገባት ነበር፡፡

እንግዲህ በሃጫሉ ላይ የደረሰው የሽብር ጥቃትና በህቡዕ የተፈጸመበት ዘግናኝ የነፍስ ግድያ ወንጀል ወደተባለው የመጨረሻ ግብ ለመሸጋገር በመረማመጃነት ከማገልገል ባለፈ፣ ያን ያህል ዋና ጉዳያቸው ነበር ለማለት ይቸግራል፡፡ ይልቁንም የሰለባውን አስከሬን “መቅበር ያለብን እዚሁ በመዲናችን አዲስ አበባ ነው” በሚል አጓጉል ሀኬት ጉዞው ተደናቅፎ ወደኋላ በመመለስ፣ አመፅ ባረገዙ ወጣቶች ታጅቦ ወደ ኦሮሚያ ባህል ማዕከል እንዲወሰድና የታጠቁ የጃዋር መሐመድ አጃቢዎች የማዕከሉን ጥበቃ በኃይል በመጣስ ወደ ውስጥ ዘልቀው ለመግባትም ሆነ ለጊዜው በስብሰባ ላይ ከነበሩ የኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ጋር ለመፋለም ያካሄዱት ግብግብ ፍንትው አድርጎ የሚያሳየን ቁምነገር ቢኖር፣ በሟች የመቀበሪያ ሥፍራ የት መሆን ላይ የመወሰን ሕጋዊ መብት የሌላቸው የእነዚህ ሁከት ፈጣሪ ወገኖች አምባጓሮ መላው የኦሮሞ ህዝብ ለታዋቂው የኪነጥበብ ፈርጥ የሚሰጠውን ክብርና የሚያሳየውን አድናቆት ለመበዝበዝና በከፍተኛ ደረጃ ላቀዱት የተደራጀ ወንጀል አፈጻጸም ቀላል ማሳለጫ አድርገው ያላግባብ ሊጠቀሙበት ከጅምሩ ማሴራቸውን ነው፡፡

እነሆ በርካታ ተዋናዮችን በማካተት የተቀነባበረ መስሎ ከሚታየው ከዚህ የለየለት አገር የማፍረስና እርስ በርስ የመጠፋፋት ተውኔት ጀርባ ጉራማይሌ ዜግነት እንዳለው የሚነገርለት ጃዋር መሐመድና ሸሪኩ የሆነው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር በቀለ ገርባ እጃቸው ሳይኖርበት አልቀረም ተብለው፣ በቁልፍ ተጠርጣሪነት ከእነ ግብረ አበሮቻቸው መያዛቸው እምብዛም የሚያስገርም አይደለም፡፡

ጃዋርን ከመነሻው የተጠናወተው ክፉ መንፈስ

ራሱን በብዙኃኑ ቄሮዎች መሪነት የሰየመው ጃዋር መሐመድ እንደ ሌሎች አማፅያን ሁሉ ለውጡን ተንተርሶ ወደ አገር ቤት እንደገባ፣ በብርቱ ጉጉት ይጠብቁት ለነበሩ ወጣቶች ብሩህ ተስፋ የሰነቀ መስሎ ታይቷል፡፡ በማር የተሸፈኑት የጥላቻ ቅስቀሳዎቹ ብዙዎች በኃዋርያነት እንዲቀበሉትና እርሱ ያዘዛቸውን ሁሉ ያለ ማመንታት ለመፈጸም ሲሉ ሕይወታቸውን ሳይቀር እንዲገብሩ አነሳስቷቸዋል፡፡ ሆኖም በሰላማዊ ሰዎች ላይ ድንጋይ በመወርወር፣ የተሳለ ሜንጫና ገጀራ በመሰንዘር፣ ዘረፋ በመፈጸም፣ ቤት/ንብረት በማውደምም ሆነ አውራ ጎዳናዎችንና አደባባዮችን በመዝጋት በተጎጂዎች በኩል ከሚደርስባቸው የመልሶ ማጥቃት ምትና አልፎ አልፎም ከሚያጋጥማቸው የሞት አደጋ ውጭ ያተረፈላቸው አንዳች በረከት አልነበረም፡፡ ባልሆነ ፕሮፓጋንዳ እየተታለሉ በነፍጠኛ ስም በንፁኃን ወንድምና እህቶቻቸው ላይ በጅምላ የሚፈጽሙት የደመነፍስ ጥቃት በእነርሱም ላይ የማያልቅ የመከራ ውርጅብኝ ሲያወርድባቸው ታዝበናል፡፡

ለነገሩ ጃዋር መሐመድ የባለ ራዕይ ጀግና ያህል በሰፊው ሲመለክና ሲሰገድለት የምናየውና የምንሰማው ግንባር ቀደም ተከታዮቹ በሆኑት የኦሮሞ አማፅያን ብቻ ነው ለማለት ያዳግታል፡፡ ልደቱ አያሌው በዚያ ሰሞን ይህንን የአካይስት አለቃ አብዝቶ በአደባባይ ያንቆለጳጰሰ መስሎት፣ “ለእኔ እኮ ከኢሳይያስ አፈወርቂ ይልቅ ጃዋር መሐመድ ይሻለኛል” በማለት ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦኤምኤን) ላይ ቀርቦ ተረግርጎልን ነበር፡፡ ሰውየው የሚጥመውን የሚያውቀው ራሱ ባለቤቱ ነውና ምርጫውን ልናከብርለት ይገባ ይሆናል፡፡

‘ግራዝማች ግሪሳ’ (እኔ ሳልሆን ታየ ደንደኣ ያወጡለት መጠሪያ ነው) የዛሬውን አያድርገውና ለኦሮሚያ ክልል ቱባ ባለሥልጣናትና ከፍተኛ የፀጥታ አመራሮች ሳይቀር፣ ቢያንስ እስካለፈው ጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም. ሁለተኛ ሳምንት ድረስ አብዝተው የሚወዱትና ‘ሰበብ ፈልገው የሚያሞካሹት ወንድማቸው’፣ እንዲያውም በአንዳንዶቹ የቁልምጫ አጠራር ‘የአይን ብሌናቸው’ ጭምር ነበር፡፡ አገር ሁሉ ‘መፍቀሬ ጃዋር’ የሆነች በሚመስል አሳሳች አቀራረብ ይህ መናጢ ግለሰብ ከስደት ወደ አገር ቤት የገባ ሰሞን፣ ወደ አማራ ክልል ሳይቀር ጎራ በማለት አሸብራቂ ጃኖ እንዲጎናፀፍ ተፈቅዶለት በከፍተኛ አጀብ እየተጎማለለ አሹፎብንና አላግጦብን እንደተመለሰ የምንዘነጋው አይደለም፡፡

ውድ ወገኖቼ

መሳሳት በእርግጥ ለሰው ልጆች ያልተፈቀደ ዝንፈት አይደለም፡፡ የሆነ ጊዜ በሆነ ምክንያት ድንገት አዳልጦንም ቢሆን ተንሸራተን ልንወድቅና ልንጎዳ እንችል ይሆናል፡፡ ቁምነገሩ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ትናንት ከፈጸምነው ስህተት ዛሬ ላይ ወደ አዕምሯችን መለስ ብለን ለመማርና ከወደቅንበት በመነሳት ነገን ለማሳመር ያለን ዝግጁነት መሆን አለበት፡፡

“አገር ሲያረጅ ጃርት ያፈራል” እንዲሉ የጃዋር ወንጀል ማለቂያ የለውም፡፡ ለአገሪቱ የግዛት አንድነትና ዘላቂ ኅብረ ብሔራዊነት ግድ ሳይሰጠው “በጉልበትም ቢሆን ተገንጠሉ” ሲል ለተቃውሞ ሰልፍ የወጡትን ደመ ሞቃቶቹን የሲዳማ ኤጀቶዎች በአደባባይ ቀስቅሷል፣ ሃይል ለተቀላቀለበት አመፅ አነሳስቷል፡፡ ይኸው ሰበብ ሆኖም በሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም. በአዋሳና በሌሎች የቀድሞው የሲዳማ ዞን ከተሞችና የገጠር አካባቢዎች ይኖሩ በነበሩ በርካታ የሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ተወላጆች ሕይወትና ንብረት ላይ የደረሰውን ጥፋትና ውድመት የምናስታውሰው በከፍተኛ ሐዘንና ቁጭት ነው፡፡

ያ የጃዋር አደገኛ የአመፅ ጥሪ በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 241 መሠረት የአገሪቱን የፖለቲካና የግዛት አንድነት በመንካት የሚያስጠይቅና የሚያስቀጣ ከባድ የወንጀል አድራጎት እንደሆነ ገልጾ፣ ይህ ጸሐፊ አፋጣኝ እርምጃ ይወስድ ዘንድ መንግሥትን በወቅቱ እስከ ማሳሰብ ደርሶ እንደነበር አይዘነጋውም፡፡

ዛሬም ልድገመውና ተጠቃሹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 241 ድንጋጌ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡ “ማንም ሰው በኃይል ወይም በሌላ በማናቸውም ሕገ መንግሥቱን በሚፃረር መንገድ በቀጥታ ወይም በእጅ አዙር የአገሪቱ ሕዝቦች አንድነት እንዲፈርስ ወይም ፌደሬሽኑ እንዲከፋፈል ወይም ከፌደሬሽኑ ግዛት ወይም ሕዝብ ከፊሉ እንዲገነጠል የሚያደርግ ተግባር የፈጸመ እንደሆነ ከአሥር ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት ለመድረስ በሚችል ፅኑ እስራት ወይም ነገሩ ከባድ በሆነ ጊዜ በዕድሜ ልክ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል፡፡”

“የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም”ና እስከቅርብ ጊዜ ድረስ እንደ ልቡ ይሆን ዘንድ በመንግሥት አካላት ሳይቀር የተፈቀደለት መስሎ ይታይ የነበረው ይህ ጽንፈኛ ግለሰብ ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ሌሊት (ለ12 አጥቢያ) የሆነውንም እኮ ፈጽሞ ልንዘነጋው አይቻለንም፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ በግል መኖሪያ ቤቱ መሽጎ “ከእነ አጃቢዎቼ ተከብቤያለሁና ድረሱልኝ” ሲል ባስተላለፈው ሐሰተኛ የፌስቡክ ጥሪው ሳቢያ እንዳሻው የሚዘውራቸውን እነዚያኑ የኦሮሞ ወጣቶች እንደ ልማዱ ለአስከፊ አመፅ አነሳስቶ ባስከተለው ሁከትና ትርምስ፣ ከእኛ ከኢትዮጵያውያን አልፎ መላውን የአለም ኅብረተሰብ ክፉኛ ባሳዘነ ሁኔታ ከ85 ለማያንሱ ንፁኃን ወገኖቻችን ያልታሰበ ሕልፈተ ሕይወት ምክንያት ሆኗል፡፡

ይልቁንም ሰሞኑን ይህ አኃዝ የሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ወደ 97 እንዳሻቀበ ተሰምቷል፡፡ በእርግጥ ትክክለኛውን ቁጥር የሚያውቁት ለነገሩ ቅርበት ያላቸው አካላት ናቸውና ምናልባት ዘግይቶ የተነገረውን ቁጥር ማመኑ ሳይበጅ አይቀርም፡፡

ከጃዋር በስተጀርባ

የአገሪቱ ሕግ እንደማይፈቅድለት ቢያውቅም ቅሉ ጥንድ ዜግነቱን ያላግባብ እየተጠቀመ ከአንዱ ስርቻ ወደ ሌላው በመሽሎክሎክና የደለበ ሀብቱን መንጠላጠያ በማድረግ በተደራጀ መንገድ ከሚፈጸሙ ድንበር ዘለል ወንጀሎች ጋር ጥብቅ ትስስር እንዳለው የሚነገርለት ይህ የሚዲያ ታይኩን (ጃዋር መሐመድን ማለቴ ነው)፣ ፈርጀ-ብዙ በሆነው እንቅስቃሴው ብቻውን እንዳልሆነ ለመረዳት ያን ያህል ምስጢረ ሥላሴ ሊሆንብን አይችልም፡፡ ስለሆነም የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር እስካሁን አለቅጥ አብዝቶ ባሳየው መንግሥታዊ ዳተኝነት የተጎዱ ዜጎቹን በወጉ ሊክስና በአገሪቱ ውስጥ የሕግ የበላይነትን በአስተማማኝ ሁኔታ ሊያረጋግጥ የሚችለው በተለይ ጃዋር መሐመድንና የክፋት ሸሪኩን በቀለ ገርባን ማንም ተራ ሰው በቀላሉ ከሚመለከተው ከፊት ለፊታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ከጀርባቸው በኩል ዘልቆ በስፋት ከመረመረና እስከ መቀሌ ብቻ ሳይሆን እስከ ካይሮና እስከ ሚኖሶታ ድረስ በሥውር የተዘረጋውን ውስብስብ የወንጀል መረባቸውን በሚገባ አጣርቶ ከደረሰበትና ከበጣጠሰው ነው፡፡

ምላሰ ረዥሙ ግሪሳ ከሁሉም የበለጠ ከአራት ኪሎው የዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ከሁለት ዓመታት በፊት ሳያስበው በሕዝብ አመፅ ተባሮ ወደ መቀሌ ከኮበለለውና በዚያ መሽጎ ሱባዔ ከተቀመጠው፣ ወራዳው የደደቢት ጭፍራ ጋር ያልተቀደሰ ጉድኝት በመመሥረት እጅና ጓንት ሆኖ ሲንቀሳቀስ እንደቆየ ከማንም የተሰወረ ነገር አልነበረም፣ አይደለምም፡፡ ለኦሮሞ ነፃነት ‘ከእኔ በላይ ላሳር’ ሲል በየደረሰበት የጥላቻ መርዙን የሚረጨው ይህ ግብዝ ግለሰብ መሠረቴ ነው በሚለው በትግራይ ሕዝብ ስም እየማለና እየተገዘተ በአገሪቱ ውስጥ የማዕከላዊ መንግሥቱን በትረ ሥልጣን በኃይል ተቆጣጥሮ በቆየባቸው የሰላሳ ፈሪ ዓመታት እንደ ሌሎች ሰለባዎች ሁሉ፣ የኦሮሞ ጎልማሶችን የዘር ፍሬ በጭካኔ ሲያኮላሽ ከኖረው ጎጠኛ ቡድን ጋር በኃፍረተ ቢስነት ሲሞዳሞድ ዓላማው ሌላ ሳይሆን፣ በእሱና በጌቶቹ ፍረጃ የነፍጠኛውን አከርካሪ በተጣመረ ክንድ መስበርና ማንኮታኮት ነው፡፡

የአንድ ጀንበር መዘዝ ያለ ዘጠኝ ወር አይመዘዝ

በመሠረቱ ጃዋርና በቀለ፣ ህዝቅኤልና ፀጋዬ፣ አሉላና ብርሃነ መስቀል… እርስ በርስ እየተቀባበሉ በሐሰት እንደሚሰብኩት በኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያውያት መካከል የጠራ ዘር ፈልጎ ማግኘት ግመልን በመርፌ ቀዳዳ ለማሳለፍ የመሞከር ያህል ከባድ ነው፡፡ በጠላቶቻችን የተጣመመ ዕሳቤና የተንጋደደ ትርክት መሠረት ኢትዮጵያ እየተባለች በምትጠራው ሁሉን አቃፊ ምድር ንፁህ ኦሮሞ፣ ንፁህ አማራም ሆነ ንፁህ ትግሬ ወይም ወላይታ… ለራሱ ብቻ ተለይቶ ከተሰጠውና እርሱ ብቻ ተቆራኝቶ ከሚኖርበት የመሬት ክፍል ጋር ፈልገን ልናገኝ ከቶ አይቻለንም፡፡ እነርሱም ቢሆኑ ይህ ይጠፋቸዋል ተብሎ አይታመንም፡፡

በአንዲት ሉዓላዊት አገር ውስጥ ወጥነት ካለው ሕዝብ ይልቅ ተሰበጣጥሮ የሚታይ የተለያዩ ማኅበረሰቦች ዴሞግራፊያዊ አወቃቀር የሚኖረው ቀለም ለዕይታ እንኳ ይማርካል፡፡ ጠላቶቻችን ግን በቡድን ደረጃ ሊገለጹ የሚችሉ ተፈጥሯዊ ልዩነቶችን ጠብቆና እርስ በርስ ተከባብሮ በሚያስደምም ጥንካሬ እንደ አንድ ሕዝብ ተዋዶና ‘ጭቃና ጨፈቃ’ ሆኖ መኖር ወንጀል የሆነ ይመስል ጠዋት ማታ በአሀዳዊነት ሊከሱንና ሊያጠለሹን ሲደክሙ እንታዘባቸዋለን፡፡ እነርሱን ደስ አይበላቸውና እነሆ መላ ኢትዮጵያውያን ዳር እስከ ዳር ቅይጦችና በደም ሳይቀር የተሳሰርን የአንዲት እናት ልጆች ነን፡፡

ይሁን እንጂ “አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም” ነውና እነዚህ ወገኖች ቀድሞ ነገር በግንባር ቀደምትነት የቆሙለት ዓላማ ለሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ሕወሓት) በታማኝ አሽከርነት አድረው በዚህ ጠባብ ቡድን ፊታውራሪነት፣ ኅብረ ብሔራዊቷን ምድር በጎሳና በሃይማኖት ከፋፍሎ ለዘመናት ተሳስበንና ተደጋግፈን የኖርነውን ዜጎቿን እርስ በርስ በማባላትና አገሪቱን ጨርሶ በማፈራረስ እስከ ወዲያኛው ከዓለም ካርታ መሰረዝ በመሆኑ፣ አፋጣኝ እርማት የሚያስፈልገውን የብሔር ፌደራሊዝም በመንደርደሪያነት ተጠቅመው ከናካቴው ሊያጠፉን አለን በሚሉት አቅም ሁሉ መረባረባቸው የማይጠበቅ አልነበረም፡፡

እነሆ “አሀዳውያን በግድ ጨፍልቀው ኢትዮጵያ ሳይሉን በፊት ለየብቻችን የነበርን ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ነንና የየራሳችንን ትናንሽ ክልሎች ፈጥረን በየጎበዝ አለቆቻችን ምሪትና ዘዋሪነት የመተዳደር መብት አለን” ሲሉ፣ ማንነታቸውን በሐሰተኛ የዴሞክራሲ ጭንብል ሸፍነው ይነሳሱብን ዘንድ በማዕከላዊ ይዘቱ እምብዛም ከሕወሓት የፖለቲካ ፕሮግራም የማይለየው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ሳይቀር በተዘዋዋሪ መንገድ እንደፈቀደላቸው መዘንጋት የለብንም፡፡ በአሁኑ ወቅት እንደሚስተዋለው እርስ በርስ መጠቃቃትን በቀጥታ ባያበረታታ እንኳ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጠቢባን እስከ ጫፍ ድረስ ዘልቀው ያለቅጥ የተጠበቡበት አይነኬ መሳዩ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ገና ከጅምሩ የተሰናዳው፣ ከአንድነታችን ይልቅ በልዩነታችን ላይ አተኩረን ያለ እረፍት እንነታረክ ዘንድ እንዲገፋፋን ተደርጎ ነው፡፡

ስለሆነም እንደዚህ ጸሐፊ የፀና እምነት ከሆነ የዛሬዎቹ ባላንጣዎቻችን ሕወሓትና ኦነግ/ሸኔ ልብ ገዝተውና ወደ አዕምሯቸው ተመልሰው የበሉበትን ወጭት በመስበር፣ ያላግባብ የሰበቁትን ጦር ቢስቡ ወይም ይህንን ማድረጉ ተስኗቸው በመንግሥት ቁርጠኝነትና በብዙኃኑ የተባበረ ክንድ ተደቁሰው ከምድረ ገጽ ቢጠፉ ወይም ቢወገዱ እንኳ፣ በአገሪቱ የበላይ ሕግነት የሚያገለግለው ይህ ሕዝብ ከፋፋይና ብሔር ፈልፋይ አውራ ሰነድ በመላ ኢትዮጵያውያን የጋራ ፍላጎትና ውሳኔ በስፋትና በጥልቀት ተመክሮበት ካልተሻሻለ ወይም ካልተለወጠ በስተቀር፣ መፃኢው ዕድላችን ምንጊዜም ቢሆን እነርሱን ለመሳሰሉ ሌሎች አገር አፍራሽ ኃይሎች እንደተጋለጠ መቀጠሉ ከወዲሁ ተገማች ነው፡፡

ጭራሽ ቂልነት ካልሆነ በስተቀር በምድረ ኤርትራ ሰንኣፌ ላይ በበረኸኞቹ ሴራ ተጠንስሶ፣ በድብቅ ተረቆና አዲስ አበባ ላይ ለተጠራው የኢሕአዴግ ካድሬዎች ጉባዔ ቀርቦ እንደ ተመከረበትና እንደ ፀደቀ ተቆጥሮ ከፍላጎታችን ውጪ የተጫነብን ሕገ ማደሪያ መቀበሪያችን እስኪሆን ድረስ መፍቀድ ያለብን መስሎ አይሰማኝም፡፡

በተለይ የዚህችን አገር ለምለም ሳር ያላንዳች ተሻሚ እየጋጠና ትኩስ ወተቷን እየጨለጠ ለአካለ መጠን የደረሰው ከሀዲው የወያኔዎች ስብስብ መቀሌ ላይ ሆኖ ‘የፌደራሊስት ኃይሎች’ እያለ የሚያንቆለጳጵሳቸው አገልጋዮቹ፣ ማዕከላዊውን መንግሥት በጉልበት ፈንቅለው እንዲጥሉ ቀጭን ትእዛዝ አስተላልፏል፡፡ ይህንንም ሕገ መንግሥቱ ሳይቀር እንደሚፈቅድለት ኃፍረተ ቢሱ የደደቢት ቡድን ጨምሮ ሲቀባጥር በአንክሮ አድምጠነዋል፡፡

ሕወሓት በእርግጥ ከዚህም በላይ ገና ብዙ ሊለፍፍና የመጨረሻ እስትንፋሱ እስኪቋረጥ ድረስ ያዙኝ ልቀቁኝ በማለት የሞት ሞቱን ሊወራጭ ይችላል፡፡ ሆኖም ትናንት ዛሬ አይደለምና ለዚህ ቡድን አታካች ቱሪናፋም ሆነ ለውስጥና ለባህር ማዶ ተባባሪዎቹ ዱለታ በቀላሉ ሳንንበረከክ ልዩነቶቻችንን አሸንፈን እጅ ለእጅ በመያያዝ፣ የጋራ ቤታችን የሆነችውን ውድ አገራችን ኢትዮጵያን ከተደቀነባት መከራ የመታደግና ለልጆቻችን የማስተላለፍ ኀላፊነት አለብን፡፡ እኛስ ብንሆን ያገኘናት በዚህ መልክም አይደል? አበቃሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በሕግ ሙያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በ1981 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው የሕግ ፋኩልቲ ያገኙ ሲሆን፣ በሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተመድ የሰላም ዩኒቨርሲቲ ጣምራ ትብብር ይካሄድ ከነበረው የአፍሪካ ፕሮግራም በሰላምና በደኅንነት ጥናት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ ዋና የሕግ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...